የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ሥያሜን በተመለከተ አቅጣጫ ተቀምጧል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በሊጉ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ሥያሜን በተመለከተ አዲስ አቅጣጫ ስለማስቀመጡ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል።

ዓምና የተቋቋመው ይህ የሊጉ ክለቦች ማኅበር አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለሁለት ቀናት አከናውኖ በዛሬው ዕለት አገባዷል። ጉባዔው ዛሬ ቀጥር ከተጠናቀቀ በኋላም 9 ሰዓት ላይ የማኅበሩ የቦርድ አመራሮች ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። የማኅበሩ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት በጉባኤው ላይ ስለ ክለቦች ሥያሜ የተነሳውን ጉዳይ እና የተቀመጠውን አቅጣጫ አብራርተዋል።

“ፊፋ የእግርኳስ ክለብ ሥያሜዎች ከዘር፣ ሃይማኖት እና ፖለቲካ ጋር እንዲገናኝ አይፈልግም። እግርኳስ ሦስቱን ነገሮች እንዲያንፀባርቅ ስለማይፈለግ ነው ሥያሜዎች ከእነሱ ውጪ ይሁኑ ያለው። እኛ ሃገር ግን አንዳንድ ክለቦች ከተጠቀሱት ጉዳዮች ጋር ግንኙነት አላቸው። እኛ አሁን ላይ ይሄኛው ክለብ ሥያሜውን ይቀይር አንልም። ግን በዚህ ዓመት ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የሚወጣጡ ግለሰቦችን አዋቅረን አንድ የአጥኚ ኮሚቴ ለማቋቋም አስበናል። ይህ ኮሚቴ የክለቦቹን ሥያሜ መርምሮ እንዲያቀርብን እናደርጋለን። ግን ክለቦቹም ይህንን ጉዳይ እያጤኑት እንዲቆዩ ምክረ ሃሳብ አስተላልፈናል።” ብለዋል።

መቶ አለቃ ጨምረውም ይህ ኮሚቴ የክለቦቹን ሥያሜ እየመረመረ ሌላ ግብረ ሃይል ደግሞ የክለቦቹን የፋይናንስ፣ የሰው ሃይል እና ተያያዥ ጉዳዮችን እንዲመረምር እናደርጋለን ብለዋል። ሰብሳቢው አያይዘውም ክለቦቹ ያሉበት ቁመና ተመርምሮ ከታወቀ በኋላ ማኅበሩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ እቅድ እንደሚያወጣ ተናግረዋል። በእቅዱ ውስጥም ክለቦች ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ወተው በሁለት እግራቸው ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ የሚገፋ አሰራር እንደሚዘጋጅ አመላክተዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!