ሶከር መጻሕፍት | ተጫዋችን-በ-ተጫዋች የመቆጣጠር ዘዴ

በዛሬው የሶከር መጻሕፍት መሰናዶአችን እ.ኤ.አ. በ2006 ለህትመት የበቃውን የጆን ፉት <ካልቺዮ> የተሰኘ መጽሃፍ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እያቀረብን እንገኛለን። ካልቺዮ በጣልያን እግርኳስ ታሪክ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም ለአንባቢዎቿ ይመጥናሉ ያለቻቸውን ምዕራፎች መራርጣ በትርጉም መልክ ማቅረቧን ቀጥላ ከመፅሐፉ ምዕራፍ አምስት ላይ የተቀነጨበውን ሁለተኛ ክፍል ይዛ ቀርባለች – መልካም ንባብ!

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የእግርኳስ ታክቲክ ዕድገት አዳዲስ ግኝቶችን አሳይቷል፡፡ ከእነዚህም አንዱ በመከላከል አጨዋወት ሥርዓተ-መዋቅር ሜዳ ላይ ተጫዋቾችን-በ-ተጫዋቾች ለመቆጣጠር (Man-Marking ለመተግበር) አሰልጣኞች ለተጫዋቾቻቸው የተናጠል ኃላፊነት ይሰጧቸው ጀመር፡፡ ይህንን ሚና የሚተገብሩት ተጫዋቾች “Man-Markers” በሚል ተሰየሙ፤ ከጊዜያት በኋላ ደግሞ ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ በሚያሳዩት የአጨዋወት ሥልት ሳቢያ ቀጥተኛ መጠሪያ ወጣላቸውና “Stoppers” ተባሉ፡፡ እነዚህ ተከላካዮች በዋናነት የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ኳስ እንዳያገኙ ካልሆነም ከኳስ ጋር ምቾት እንዳይሰማቸው ማድረግ መደበኛ ሥራቸው ሆነ፡፡ ይህን መተግበር ቢሳናቸው እንኳ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ኳሱን እግራቸው ሥር ይዘው ወደ ተጋጣሚ የላይኛው የሜዳ ክፍል ወይም የማጥቃት ሲሶ እንዳይሄዱ በቅርብ ርቀት ሆነው ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ተጠበባቸው፡፡ የጣልያን ተከላካዮች ብዙውን ጊዜ የተጋጣሚ ቡድን የፊት መስመር ተሰላፊዎችን እንቅስቃሴያዊ መዳረሻ ቀድመው ለመገመት ይጥራሉ፡፡ ከእንግሊዞቹ የመከላከል አጨዋወት ዘዴ በተለየም የባላንጣ ቡድን አጥቂዎች ላይ ዘለው ጉብ አይሉም፤ ይህን ከማድረግ ይልቅ እግር-በ-እግር ይከታተሏቸዋል፡፡ የቦታ ግምታቸው ካልተሳካ ተከላካዮቹ ለከፋ ቅጣት በማይዳርግና በተመረጠ የሜዳ ክልል አልያም በተገቢ ሰዓት “ያልተገባ ጨዋታ” ይፈጽማሉ፡፡ በጣልያን ይህን መሰሉ ድርጊት ቆየት ብሎ አማራጭ ሲጠፋ ሆን ተብሎ የሚደረግ “የመከላከል ታክቲክ እቅድ” አካል እየሆነ በመሄዱ በ1990ዎቹ “Tactical Foul” ሊሰኝ ቻለ፡፡ እንዲያውም ተጫዋቾች “Tactical Foul” የጨዋታው ቁልፍ ስትራቴጂ መሆኑንም መማር ጀመሩ፡፡ ሁሉም ተጫዋቾች መቼ ታክቲካል ፋውል መስራት እንዳለባቸው እና በየትኛው ጊዜ ደግሞ እንደማይኖርባቸው እንዲያውቁ ይደረጋል፡፡  የማስጠንቀቂያ ካርድ ሳይመዘዝባቸው ይህን ያልተገባ አጨዋወት መተግበር እንዲችሉም ይመከሩ ነበር፡፡ በጣልያን የእግርኳስ ቀጥታ ሥርጭት አስተላላፊዎች ይህን “ፋውል” ለሚሰራ ተከላካይ በተደጋጋሚ አድናቆት ሲቸሩ ይሰማሉ፡፡ በእርግጥ አልፎ አልፎም ቢሆን ሙገሳቸውን ሚዛናዊ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ ” ምናልባት ፍትሃዊ አጨዋወት ላይሆን ቢችልም…” የሚል አስተያየት እየሰጡም ለዘብ ያለ ትችት ሲያቀርቡ ይደመጣል፡፡ “ተገቢ የሆነ ፋውል” ወይም “ታክቲካል ፋውል” ከተሰኘው ያልተገባ አጨዋወት ጎን ለጎን ፋይዳ ቢስ ስለሆነው ፋውልም የተለያዩ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡ በወቅቱ ለሁለቱም ያልተገቡ አጨዋወቶች ይሰጥ የነበረው ሐሳብ ለየቅል ነበር፡፡ ፋይዳ ቢስ የሆነውን “ያልተገባ አጨዋወት” መፈጸም እጅጉን ያስወቅሳል፤ ለእግርኳስ ታክቲክ አተገባበር ብቁ ሆኖ ካለመገኘት ጋር የተያያዘ ግላዊ ችግር ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ጠቃሚ የሆነውን ያልተገባ አጨዋወት መተግበር ግን እንደ ጥሩ ልምድ ከመታየቱም በላይ ሙገሳ የሚያስቸር ተግባር ይሆናል፡፡ ይህ አይነቱን ያልተገባ አጨዋወት ሲተገብር የተያዘ ተጫዋች የማስጠንቀቂያ ካርድ ሲያይ ወይም ፋውሉ የከፋ ሆኖ ከሜዳ የመባረር ውሳኔ ሲወሰንበት ለቡድኑ እንደተከፈለ መስዋዕትነት ሁሉ ይቆጠራል፡፡

በ1960ዎቹ የነበረውን እግርኳስ በአብዛኛው የኢንተር ተከላካዮች ቢቆጣጠሩትም በጊዜው በጣልያን በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ታላላቅ ተከላካዮች ሲጫወቱ ታይቷል፡፡ በሚላን ይጫወት የነበረው የፓውሎ ማልዲኒ አባት ሴዛሬ ማልዲኒ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው ነው፡፡ የቀድሞው የቀኝ መስመር ተከላካይ ትልቁ ማልዲኒ ኋላ ላይ በመሐል ተከላካይነት አንቱታን ያተረፈ የሚላን ኮከብ መሆን ችሏል፡፡ ትልቁ ማልዲኒ በያዘው የቴክኒክ ክህሎት እና ከኳስ ጋር ባለው ችሎታ ከፍተኛ እርግጠኝነት ነበረው፡፡ ይህ መጠኑን ያለፈ የራስ መተማመን አልፎ አልፎ አሰቃቂ ስህተቶችን እንዲሰራ አድርጎታል፡፡ እንዲያውም እነዚህ አንዳንዴ የሚፈጠሩ ስህተቶች “ማልዲናቴ” እስከመባል ደርሰዋል፡፡ የማልዲኒ አምሳያ ልጁ ፓውሎ አባቱ ሲለማመድ እና ሲጫወት እየተመለከተ ቆይቶ በ1985-86 የውድድር ዘመን ለሚላን መጫወት ጀመረ፡፡ ፓውሎ ከህጻንነቱ ጀምሮ የሚላንን ቡድን ሲያይ አድጓል፡፡ ቁመተ-ሎጋ፣ መልከ መልካም እና ትጉሁ ማልዲኒ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የግራ መስመር ተከላካይነቱን ቦታ በቀዳሚነት ለመቆናጠጥ ችሏል፡፡ በቀጣዮቹ ሥስት አስርት ዓመታትም የሚላንና የጣልያን ብሄራዊ ቡድን የቦታው ተመራጭ ሆኖ ዘልቋል፡፡ 

ሰላማዊ ኑሮ ለመምረጡ ምስጋና ይግባና ማልዲኒ የእግርኳስ ህይወቱ ደርዝ ይዞለት ረዘም ላለ ጊዜ እንዲጫወት እና ለብሔራዊ ቡድኑ ከመቶ ጊዜያት በላይ መሰለፍ እንዲችል አብቅቶታል፡፡ (በ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ አብዛኞቹ ጣልያናውያን ኮከብ ተጫዋቾች ከሜዳ ውጪ በነበራቸው የግል ቅንጡ ህይወት ተገፋፍተው ከሚገቡበት አደገኛ የኑሮ ዘይቤ ማልዲኒ ራሱን አቅቦ መኖር መቻሉን ልብ ይሏል፡፡) ማልዲኒ ከተለያዩ ሱሶች ነጻ በመሆኑ የልጅነት ገጽታው ሳይቀየር፣ ተክለ ሰውነቱ ሳይጎዳ እና በአካል ብቃቱ ሳይዳከም የተጫዋችነት ዘመኑን በክብር አገባዷል፡፡ እርሱ በጭፈራ ቤቶች ጊዜውን ከማባከን ይልቅ በተጫዋችነት ዘመኑ የተለያዩ ክብረ ወሰኖችን ማስመዝገብ መርጧል፡፡ በእርግጥ አንዳንዴ ሃሊውድ በተሰኘው እና እርሱ በግማሽ ባለቤትነት በሚቆጣጠረው ሚላን ከተማ በሚገኘው ውዱና ማራኪው የምሽት ክበብ በሙዚቃ አጫዋችነት (ዲጄነት) ሲሳተፍ ታይቷል፡፡

የትንሹ ማልዲኒ የሜዳ ላይ እግርኳሳዊ ስኬት እጅግ የገዘፈ ነው፡፡ ከሃያ የውድድር ዘመናት በላይ በመጀመሪያ ተሰላፊነት የቦታው ምርጡ ተጫዋች ሆኖ አሳልፏል፤ አራት የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫን አሸንፏል፤ ሰባት የሊግ ድሎችን ተቀዳጅቷል፡፡ ከአርባ ዓመታት በፊት አባቱ በእንግሊዙ የዌምብሌይ ስታዲየም ያነሱትን ዋንጫ እርሱም በ2003 የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አምበል ሆኖ በተለየ ክብር አንስቷል፡፡ ተጫዋቹ የክለቡ የምንጊዜም ጀግና በመሆን ኗሪ ታሪኩን በሳንሲሮ አስቀምጧል፡፡ ከሌሎች ተከላካዮች በተለየ ከኳስ ጋር ምቾት ተሰምቶት ስለሚጫወት ቅብብሎችን ሲፈጽም፣ የተጋጣሚ ቡድንን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲመክት ወይም የማጥቃት ሒደቱን ለማገዝ ሲል መስመሩን ይዞ ወደ ተጋጣሚ ቡድን የሜዳ ክልል ሲከንፍ – እንደ እንቁ የሚያዩት፣ እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚሳሱለት እና በእጅጉ የሚንከባከቡት ደጋፊዎቹ ከመቀመጫቸው ተነስተው ያጨበጭቡለታል፤ የበለጠ እንዲተጋም ያበረታቱታል፡፡ ማልዲኒ እድሜው እየገፋ ሲሄድ ቀድሞ ሲጫወት ከነበረበት የመስመር ተከላካይነት ሚናው ወደ መሐል ተከላካይነት ተቀይሮ የተጫዋችነት ዘመኑን ማራዘም ችሏል፡፡ ሌሎቹ ተጫዋቾች ከጨዋታ በሚገለሉበት ዕድሜ እርሱ ግን ድንቅ ብቃቱን እያሳየ በእግርኳስ ስኬታማ ዓመታት ማሳለፍ መርጦ ተሳክቶለታል፡፡ ለምሉዕነት በቀረበው የማልዲኒ የተጫዋችነት ዘመን የብቃት መዋዠቅ ያሳየባቸው ጊዜያት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በጥቂት ጨዋታዎች በቀይ ካርድ ከሜዳ ተባሯል፤ በሌሎች አናሳ ጨዋታዎች ደግሞ የሚጠበቁ ስህተቶችን ሰርቷል፡፡ በጠንካራው እንዲሁም በፈላጭ-ቆራጩ የሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ ኃ/የተ/የግ/ማ ሥር በሚተዳደረው ታላቁ ክለብ የገዘፈ ስብዕና ተላብሶ-የማይነጥፍ ክብር እና ሙሉ እውቅና መጎናጸፍ ችሏል፡፡

ይቀጥላል…

የመጽሃፉ ደራሲ ጆን ማኪንቶሽ ፉት ይባላል፡፡ እንግሊዊው ጸሃፊ የጣልያንን ጓዳ-ጎድጓዳ አብጠርጥረው ከሚያውቁ የውጭ ምሁራን መካከል ይጠቀሳል፡፡ በበርካታ የጣልያን እና እንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎችም የጣልያንን ታሪክ አስተምሯል፡፡ በሃገሪቱ ፖለቲካ፣ ፍልስፍና እና ምጣኔ ኃብት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የታሪክ መጻሕፍትም አበርክቷል፡፡ በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎችም ጥልቀት ያላቸው ጥናቶቹን ያቀርባል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ