ይህን ያውቁ ኖሯል? | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን…

ላለፉት 12 ተከታታይ ሳምንታት ስለ ፕሪምየር ሊጉ ዕውነታዎች ስናቀርብ መቆየታችንሚታወስ ሲሆን በዛሬው “ይህን ያውቁ ኖሯል?” አምዳችን በአዲስ ርዕሰ ጉዳይ የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድንን የተመለከቱ ዕውነታዎችን አጠናክረን ቀርበናል።

*ማስታወሻ : የተጠቀሱት ዘመናት በሙሉ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ናቸው።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጨዋታ ያደረገው ታኅሣሥ 22 ቀን 1940 ላይ ነው። ብሔራዊ ቡድኑ በጊዜው ከፍሬንች ሶማሌ ላንድ (አሁን ጅቡቲ) ጋር በመጫወት ነው የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጨዋታውን ያደረገው። በጨዋታውም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 5-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

2- ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ የነጥብ ጨዋታውን ያደረገው የካቲት 8 ቀን 1949 ላይ ነው። በዚህ ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ የግብፅ ብሔራዊ ቡድንን ገጥሞ 4-0 ተረቷል። ነገርግን በቅድሚያ ቡድኑ ከደቡብ አፍሪካ ጋር እንዲጫወት ነበር መርሐ-ግብር የወጣለት። ሆኖም ተጋጣሚው ደቡብ አፍሪካ ግን በወቅቱ በአፓርታይድ ምክንያት በመታገዷ ጨዋታውን ማድረግ ሳይትችል ቀርቶ ብሔራዊ ቡድን ከግብፅ ጋር የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታውን አከናውኗል። ከዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ቀድሞ ደግሞ በኦሊምፒክ ማጣሪያ ሚያዚያ 20 ቀን1948 ላይ በተመሳሳይ ከግብፅ ጋር ተጫውቶ 4-1 ተሸንፎ ነበር።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሰፊ ውጤት ያሸነፈው ቡድን ጅቡቲን ነው። በ1946 ግንቦት ወር ላይ በተደረገው የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አስር ግቦችን አስቆትሮ በተቃራኒው ሁለት ግቦችን ብቻ በማስተናገድ በሥምንት የግብ ልዩነት ጨዋታውን አሸንፏል።

– ብሔራዊ ቡድኑ በሰፊ ጎል ያሸነፈበት የነጥብ ጨዋታ ደግሞ የተመዘገበው 1962 ላይ ነው። በዚህ ዓመት ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ታንዛኒያን ገጥሞ ሰባት ግቦችን አስቆጥሮ አሸንፏል። ከዚህ መነሻነት 7-0 ያጠናቀቀው ግጥሚያ በነጥብ ጨዋታ በሰፊ ጎል ያሸነፈው ሆኖ ታሪክ ላይ ተፅፏል።

– በተቃራኒው ብሔራዊ ቡድኑ በሰፊ የግብ ልዩነት የተረታው በኢራቅ (0-13) አቻው ነው። እርግጥ ይህንን ጨዋታ ያደረገው ስብስብ ብሔራዊ ቡድንን የወከለ ስለመሆኑ እርግጠኛ መረጃ የለም። ከዚህ ሽንፈት ውጪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ1951 በሶቪየት ኅብረት 13-3 የተሸነፈበት ውጤት ሌላው በብዙ ጎል የተረታበት ሆኖ ተመዝግቧል።

– ብሔራዊ ቡድኑ በሰፊ ጎል የተሸነፈበት የነጥብ ጨዋታ በዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያ ላይ ነው። በ1989 ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አሌክሳንድሪያ ላይ ከግብፅ ጋር የተጫወተው ቡድኑ 8-1 ተሸንፏል። ይህ ውጤትም በነጥብ ጨዋታ ብዙ ጎል አስተናግደን በሰፊ የግብ ልዩነት የተረታንበት ሆኖ ተመዝግቧል።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ጨዋታውን ያደረገው ኅዳር 9 ቀን 2012 ላይ ነው። በዚህ ቀን ቡድኑ አይቮሪኮስትን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል።

– ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ዓለማቀፍ የነጥብ ጨዋታ ማድረግ ከጀመረበት 1948 ጀምሮ እስካሁን በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳትፎ አያውቅም።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ መስራች እና የመጀመርያ ተሳታፊ ከሆኑ ሦስት ሀገራት አንዱ ሲሆን በአጠቃላይ አስር ጊዜ ተሳትፎ አንድ ጊዜ (1954) የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።

– በቅርቡ የተጀመረው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ላይ ዋልያዎቹ ሁለት ጊዜ የተሳተፉ ሲሆን ሁለቱንም ከምድብ ተሰናብተዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!