👉”የህክምና ባለሙያን በድምፅ ብልጫ ቀዶ ጥገና እንዲሰራ አትመርጠውም”
👉”የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማለት ከተለያዩ ኮሚቴዎች (ሙያተኞች) የመጡትን ምክረ ሀሳቦች እና ውሳኔዎችን የሚያፀድቅ፣ ለአሰራር ምቹ የሚያደርግ እንጂ በቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚሰጥ አይደለም።”
👉”ቴክኒክ ኮሚቴ ያቀረበለትን የምክረ ሀሳብ ሰነድ አልቀበልም ካለ ሥራ አስፈፃሚው አልመከርም ብሏል ማለት ነው።”
👉”በረጅም ክትትል እንጂ በሁለት፣ ሦስት ስብሰባ አሰልጣኝ መሾም ከባድ ነው።”
ሰሞነኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኝ ቅጥር ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል። የዚህ ፁሑፍ ዋና አላማ እከሌ ለምን ተሻረ እከሌ ለምን ተመረጠ የሚለው ጉዳይ አሳስቦት አይደለም። ከምርጫው ቀደም ባሉ ጊዜያትም በተለያዩ ዘገባዎች ፌዴሬሽኑ በድምፅ ብልጫ አዲስ አሰልጣኝ ለመሾም ስለማሰቡ አስነብበን በርካቶች ሲወያዩበት ቆይቷል። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ከዚህ ቀደም የተካሄዱ የአሰልጣኝ ቅጥር ምርጫዎች በብዙ ሴራዎች የተተበተቡ ቢሆንም አሰልጣኝ በድምፅ ብልጫ ሲቀጠርም ሆነ ሲሻር ብዙ አልተመለከትንም። ምን አልባትም ይህ አካሄድ በዘመናዊ እግርኳስ ራሳቸውን እያሳደጉ ሀገራት ያላደረጉትን ኢትዮጵያ አሰልጣኝ በድምፅ ብልጫ የሻረች የሾመች ብቸኛ ሀገር ሳያደርገን አይቀርም። ይህ አካሄድ ምን እንድምታ አለው? ሌሎች ሀገሮችስ ይህ ተሞክሮ አላቸው ወይ? ስንል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ ሳሙኤል ስለሺን አናግረን ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።
“የአሰልጣኝ ቅጥር ቴክኒካል ነገር ነው። በቴክኒካል ጉዳይ ላይ ተወያይቶ አሰልጣኝ ሊሾም የሚገባው ቴክኒክ ኮሚቴው ነው። ነገር ግን የዲሲፒሊን እና ሌሎች አስተዳደራዊ ችግሮች ከተፈጠሩ አስተዳደር ክፍሉ (ሥራ አስፈፃሚው) ገብቶ ውሳኔ ይሰጣል። ከዚህ ቀደም የተመረጠው አሰልጣኝ የተሾመው ቴክኒካል በሆኑ ጉዳዮች ለምሳሌ በአቅሙ፣ በውጤት ከሆነ የሚሻረው ቴክኒካል ሰነድ ቀርቦ ያንን ሰነድ ተከትሎ ነው ውሳኔ የሚወሰነው። የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማለት ከተለያዩ ኮሚቴዎች (በፕሮፌሽናል ሙያተኞች) የመጡትን ውሳኔዎችን የሚያፀድቅ፣ ለአሰራር ምቹ የሚያደርግ እንጂ በቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚሰጥ አይደለም። ስለዚህ የአሰልጣኙ ስንበት ጉዳይ የዲሲፒሊን ወይም አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሌሎችም ከሆነ በድምፅ ብልጫ መወሰኑት ችግር የለውም። ሆኖም ግን ከቦታው የተነሳው እና አዲስ አሰልጣኝ የተሾመው በቴክኒካል ግምገማ ከሆነ ግን በድምፅ ብልጫ መሻርና መወሰን ብዙም የሚያስኬድ አይደለም።
“በየትኛውም የሥራ መስክ ለምሳሌ የህክምና ባለሙያን በድምፅ ብልጫ ቀዶ ጥገና እንዲሰራ አትመርጠውም። የባንክ ባለሙያን በድምፅ ብልጫ መርጠህ ገንዘብ እንዲያስተዳደር አታደርገውም። ሰዎች ይወዳደራሉ ቴክኒካሊ ይመረመራሉ፣ ይመዘናሉ፣ ይፈተናሉ። ከዛ በደሞዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ጉዳይ አስተዳደራዊ ድርድር ያደርጋሉ እንጂ በድምፅ ብልጫ አትቀጥርም። ይህ እንግዲህ ፖለቲካ ያመጣው የዲሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ እኛ ሌላ ፅንፍ ይዟል። ይህ ችግር በየትኛውም ሴክተር ያለ ነው። ዲሞክራሲ ሊደር ሺፕ በድምፅ ብልጫ ሲሆን ገለልተኝነትን ወይም ዲሞክራቲክ መሆንን ለማሳየት ይመስላል። በእግርኳሱ ግን ይህ አይሰራም። አንድ የህክምና ባለሙያ ዘጠናዘጠኝ ሰዎች እጅ ስላወጡለት ጎበዝ ነው ማለት አይደለም። እጅም ስላላወጡለት ሰነፍ ነው ማለት አይደለም። ቴክኒካል ነገሮች የሚፈቱት በቴክኒካል ነገሮች ብቻ ነው። በነገራችን ላይ ሥራ አስፈፃሚው ቴክኒክ ኮሚቴን ያዋቀረው አንዱና ዋና ምክንያት በቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ሀሳብ እንዲሰጠው ነው። ምክንያቱም የሥራ አስፈፃሚ አባላት የእግርኳስ ባለሙያ እንዳልሆኑ ስለሚታሰብ ነው። ሥራ አስፈፃሚው የእግርኳስ ባለሙያ ካልሆነ በእግርኳስ ጉዳይ የሚረዳው አንድ የቴክኒክ አካል አቋቁሟል። ስለዚህ ቴክኒክ ኮሚቴ ያቀረበለትን የምክረ ሀሳብ ሰነድ አልቀበልም ካለ ሥራ አስፈፃሚው አልመከርም ብሏል ማለት ነው። አንተ አንድ ተቋም እንዲያማክርህ ቀጥረኸው እርሱ ያመጣልህን ምክረ ሀሳብ አልቀበልም ካለ መጀመርያ ለምን ያዋቅረዋል?
“በውጭ ሀገራት ባሉ የአሰልጣኝ ቅጥሮች እንዲህ ያለ የድምፅ ብልጫ ቅጥር እኔ እስከማቀው የለም። እንደሚታወቀው እኔም እስኪገባኝ ድረሰ በእግርኳሱ የዳበሩ ሀገራት አሰልጣኝ ለመቅጠር ረጅም ጊዜ ነው የሚከታተሉት እንጂ በስብሰባ አይደለም የሚመለምሉት። ለብሔራዊ ቡድን እና ለክለብም ቢሆን ረጅም ጊዜ ነው ክትትል የሚያደርጉት ለምሳሌ እንግሊዝ ሳውዝጌትን ፣ ጀርመን ክሊንስማን እና ዩአኪም ሎው ሲያመጡ ያ ፌዴሬሽን በደንብ ረጅም ጊዜ ነው የሚከታተለው። ያለው የጨዋታ ፍልስፍና፣ ሊሰራው ስላሰበው ቡድን፣ የወደፊት እቅዱ ዙርያ፣ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመሆን የሚቀመጥ መስፈርት (ደረጃ) አለ። በአጋጣሚ ሆኖ የእሳት ፋጥፊያ (ለምሳሌ የውጤት ከቀውስ ሲፈጠር ወድያውኑ ሰዎችን የመቀያየር) ካልሆነ ድንገት ተነስተው አሰልጣኝ አይሾሙም። አሁን እኛ ሀገር ስድስት ወር በኮሮና ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለማሰብ ረጅም ጊዜ ነበረን። በዚህ ረጅም ጊዜ ውስጥ የምንፈልገውን ደረጃ በስብሰባ ወይም በድምፅ ብልጫ ሳይሆን በትልቅ ሰነድ ዳብሮ የሚቀርብ መሆን ነበረበት። በረጅም ክትትል አሰልጣኞች ይሾማሉ እንጂ በሁለት፣ ሦስት ስብሰባ አሰልጣኝ መሾም ከባድ ነው።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!