“ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ላይ ያሉ ክለቦች በደሞዝ ጣርያው ላይ ጥያቄ አለኝ ካሉ መድረክ አመቻችተን ራሳቸው የወሰኑትን ሪቫይዝ ማድረግ ይችላሉ።” አቶ ባህሩ ጥላሁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ
በቅርቡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ለሁለት ቀናት ከክለቦች ጋር ጠቅላላ ጉባዔውን በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ለሁለት ቀናት ማከናወኑ ይታወሳል፡፡ በስብሰባው የሁለተኛ ቀን ውሎ በርካታ ውሳኔዎችን እና ካምፓኒው ሊሰራቸው ስላሰባቸው ጉዳዮች ተወያይቶ ውሳኔን ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡ ከእነኚህ ውሳኔዎች መካከል ክለቦች ለተጫዋቾች ከ50 ሺህ ብር በላይ መክፈል የለባቸውም የሚለው አስገዳጅ ህግን ዘንድሮ በተባለው የክፍያ ስርዓት ቀጥለው ከ2014 ጀምሮ ግን ሁሉም የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በሚችሉት አቅም መክፈል ይችላሉ የሚለው ውሳኔ የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ የፕሪምየር ሊግ ክለቦችን ብቻ የሚመለከት ቢሆንም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥር የሚተዳደሩ እና ከ20 ሺህ ብር በታች እንዲከፍሉ ገደብ የተጣለባቸው የከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ በተጨማሪም ለሌሎች የሊግ ዕርከን ያሉትን ይመለከታል ወይንስ የፌዴሬሽን አቋም ሌላ ነው ብለን የፌዴሬሽኑን የፅህፈት ቤት ኃላፊ ጠይቀን ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
“ባለፈውም የፕሪምየር ሊጉን ደመወዝ ጣሪያን ውሳኔ ያስቀመጡት ክለቦች ናቸው፡፡ አሁንም ክለቦች ናቸው ተወያይተው ይህን ያነሱት። ይህ ደግሞ የክለቦቹ ማንዴት ስለሆነ በዚህ ደረጃ ተነጋግረዋል። የፋይናንስ ስፖርታዊ ጨዋነትን የመከታተል የመቆጣጠር ሥራ ደግሞ የእኛ ይሆናል።
“ሊግ ካምፓኒው ፕሪምየር ሊግ ላይ ብቻ የሚሰራ ነው፡፡ ከፍተኛ ሊግ ላይ ያሉ ክለቦች ደግሞ መሰል ጥያቄ ካላቸው መድረኩን አመቻችተንላቸው እንዲወያዩ እናደርጋለን። አንደኛ ሊግም ላይ የሚኖረው ነገር ከከፍተኛ ሊጉ ጋር ተመሳሳይ ነው። ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ላይ ያሉ ክለቦች ጥያቄ አለኝ ካሉ መድረክ አመቻችተን ራሳቸው የወሰኑትን ሪቫይዝ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!