የዳኞች ገፅ | በደጋፊ ተፅዕኖ የማይወድቀው የቀድሞ ፌደራል ዳኛ ሰለሞን ዓለምሰገድ

በሰማንያዎቹ ውስጥ ከታዩ አይረሴ ዳኞች መካከል አንዱ ነው። በተክለ ቁመናው ቀጭን እና ረዘም ያለ ነው። ድፍረት የተሞላበቸው ውሳኔዎቹ፣ በደጋፊ ተፅዕኖ ስር ሳይገባ ህጉ የሚፈቅደውን፣ ያመነበትን በመወሰን የሚታወቅ ጎበዝ ዳኛ እንደነበረ ብዙዎች ይመሰክሩለታል። በተለይ በ1982 በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደረጉትን ጨዋታ የነበረው ብቃቱ እርሱን ከህዝብ ጋር አስተዋውቆታል። ከዚህ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ትልቅ ጨዋታዎችን በዳኝነት መርቷል። 

ኢንተርናሽናል ዳኛ የመሆን አቅሙ ቢኖረውም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካለት እንደቀረ ይነገርለታል። ከአስራ ሰባት ዓመት የዳኝነት አገልግሎት በኃላ ራሱን ካገለለ በኃላ ለኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት ካለው ከፍተኛ ፍላጎት በሙያው፣ ባካበተው ከፍተኛ ልምድ እና ባለው የገንዘብ አቅም ለማገልገል በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት እና በዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢነት በተለያዩ ጊዜያት ሠርቷል። ሆኖም በኃላ እንዳሰበው እና እንደፈለገው ባለመሆኑ ምክንያት በገዛ ፍቃዱ ለመልቀቅ ተገዷል። በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ ከትንሽ የንግድ ህይወት ጅማሮ አንስቶ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎቹ ከመሳተፉ በተጓዳኝ የአሴር ሪልስቴት ባለቤት እና ሥራ አስከያጅ በመሆን እየሰራ ይገኛል። ከቀድሞ አንጋፋ ዳኞች አንዱ የሆነው ፌደራል ዳኛ ሰለሞን ዓለምሰገድ የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳች ነው። በዳኝነት ሕይወቱ ዙርያ እና አሁን ስለሚገኝበት ደረጃ ያደረግነውን ቃለ መጠይቅ እንዲህ አቅርበነዋል መልካም ቆይታ።

በመጀመርያ ካለህ የሥራ ኃላፊነት የተነሳ ለቃለ መጠይቅ ስንፈልግህ ጊዜህን አጣበ ለቃለ መጠይቁ ፍቃደኛ ስለሆንክ አመሰግናለሁ።

እኔም በጣም አመሰግናለው አስታውሳቹ ፈልጋቹ በዳኝነት ህይወቴ ዙርያ ቃለመጠይቅ ልታደርጉኝ ስለፈለጋችሁ አመሰግናለው።

ወደ ጥያቄዬ ልግባ ጋሽ ሰለሞን ትውልድ እና እድገትህ የት እንደሆነ አጫውተኝ ?

የተወለድኩት አክሱም ከተማ ነው። እስከ አስር ዓመቴ ድረስ ያደጉት በዚሁ ከተማ ነው። በኃላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሠንጋ ተራ አካባቢ ነው ያደኩት። እንደማንኛውም ወጣት እግርኳስን እወድ ስለነበር በዛን ጊዜ ከፍተኛ ሦስት ቀበሌ አርባ ሰባት ይባላል። እዛ ኳስ እየተጫወትኩ አድጌያለው።

የዳኝነት አጀማመርህ እንዴት ነው? በምን ምክንያት ተነሳስተህ ነው ወደ ዳኝነቱ ልትገባ የቻልከው ?

ቅድም እንዳልኩህ እግርኳስን መጫወት እወድ ስለነበር እንዲሁም በጣም ቀጭን ስለሆንኩ እኛን ሰብስቦ ያሰለጥነን የነበረው አሰልጣኝ ጎሣዬ መስፍን የሚባል ሰው የተለያዩ የወዳጅነት ጨዋታዎች ሲኖሩ አጫውት ይለኝ ነበር። ምን አልባት እርሱ ከእኔ በላይ በውስጤ ያለውን አቅም ቀድሞ ተረድቶ ይሆናል። ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አካባቢ አንድ ሜዳ ነበር፤ እዛ ማጫወት ጀመርኩ። በኋላ በአስራ ስምንት ዓመቴ ዓመቴ በ1971 የመጀመርያውን የመምርያ ኮርስ መውሰድ ችያለው። በመቀጠል የከፍተኛ ቀበሌዎች ውድድር እያጫወትኩ ዳኝነቱን ቀጥዬ ከፍ ወዳለ ደረጃ መድረስ ችያለው። ለካ እኔ የማላቀው ውስጤ የነበረ ዝንባሌ እና ችሎታ ነበር። በዚህም እየታወቅኩ መጣው። እንግዲህ ከመጫወት ወደ ማጫወት ዞርኩ ማለት ነው።

በወቅቱ በመምርያ ደረጃ በነበረህ ተሳትፎ የምታጫውታቸው ጨዋታዎች ምን ይመስሉ ነበር ?

የከፍተኛ፣ የቀበሌ ውድድሮችን አጫወት ነበር። በኋላም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ውድድር፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄዱ የውስጥ ውድድሮች ነበሩ የማጫውታቸው። ብቻ በየመንደሩ እየዞርኩ አጫውት ነበር። ያኔ ክፍያው ያስቃል፤ ዋና ዳኛ ስንሆን አምስት ብር፣ ረዳት ዳኛ ስንሆን ሦስት ብር ነበር። በዚህ ሒደት ውስጥ በዳኝነቱ ከፍተኛ ብስለት እያገኘሁ መጣው። ሳላስበው ፈጥኜ ከመጀመርያው መምርያ ሁለት ወደ አንድ ከዛም ወደ ፌደራል ዳኛ መሻገር ችያለው።

መቼም በእናተ ጊዜ ፌደራል ዳኛ ለመሆን ረዘም ያለ ዓመት ይወስዳል። በደንብ ልምዱን እና አቅሙን እያገኛችሁ እንትሄዱ… ለመሆኑ ጋሽ ሰለሞን ፌደራል ዳኛ ለመሆን ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?

ልክ ነህ ረጅም ዓመት ይፈጃል። ፌደራል ዳኝነት እንዲህ በቀላሉ የሚሰጥ መዓረግ አይደለም። በደንብ በተለያዩ ውድድሮች ተፈትነህ እንጂ በቀጥታ ተነስተህ አዲስ አበባ ስታዲየም አትገባም። ብዙ ልምድ አግኝተህ፣ የሚሰጥ ማዕረግ ነው። በቀን ሦስት ጨዋታዎችን አንድ በመሐል፣ አንድ በረዳት ዳኝነት በየሜዳው፣ በየጫካው እየተዟዟርን እያጫወትን ቆይተን ፌዴራል ለመሆን ወደ ስምንት ዓመት ወስዶብኛል። በ1979 (80) የሆንኩ ይመስለኛል።

የእግርኳስ ዳኛ መሆንህ ጠቅሞህ በወቅቱ ከነበሩ የመንግስት ግዳጆች (ውሳኔዎችን) አልፈሀል ይባላል። እስቲ ምን ነበር ?

ዳኛ በመሆኔ ምክንያት ከብሔራዊ ውትድርና ቀርቻለው። በከፍተኛ ቀበሌ ውድድሮች ሳጫውት ያዩኝ አመራሮች በዳኝነት የምሰጠውን አገልግሎት አይተው እርሱ እዚህ ማገልገል አለበት ብለው አስቀርተውኛል። መሠረተ ትምህርት ዘመቻ ጅማ ደርሶኝ ነበር። በእግርኳስ ምክንያት ከዛ ቀርቻለው። ፈጣሪ ረድቶኝ እግርኳስ ከእነዚህ ነገሮች አሳልፎ እየጠቀመኝ እዚህ አድርሶኛል። አሁን በግል የንግድ ሥራ ላይ ነው ያለሁት። እውነት ለመናገር እዚህ የንግድ ስራ ላይ ለመድረሴ እግርኳስ የተወሰነ ተፅእኖ የለውም ልልህ አልችልም።

ብዙዎቹ ዳኞች በእናተም ዘመን ፌደራል ዳኛ ሆነው በአዲስ አበባ ስታዲየም በተመልካች መሐል ማጫወት ይመኛሉ። አንተ በአዲስ አበባ ስታዲየም ለመጀመርያ ጊዜ ያጫወትከውን ታስታውሰዋለህ ?

ወቅቱ መቼ እንደሆነ ባላስታውሰውም በመምርያ ደረጃ የመጀመርያ ጨዋታዬ እርሻ ሰብል ከ ፖሊስ (ኦሜድላ) አጫውቻለው። ፌደራል ዳኛ ሆኜ በረዳት ዳኝነት ነው። ደግሞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ለመጀመርያ ጊዜ ያጫወትኩት አስታውሳለው ፖሊስ እና መብራት ኃይል ያደረጉትን ጨዋታ ነው። ጋሽ ተስፋዬ ገብረኢየሱስ በመሐል ዳኝነት፣ ጋሽ ሽፈራው እሸቱ ከኔ ጋር ረዳት ዳኛ በመሆን በ1979 ልጅ ሆኜ አጫውቻለው። ይሄን የሚያሳይ ፎቶም አለኝ። ከ1980 አጋማሽ ወዲህ ጀምሮ ደግሞ ወደ ዋና ዳኝነት ተሻግሬ አጫውቻለሁ።


በፌደራል ዳኝነትህ ለአጭር ዓመታት ነው አጫውተህ ያቆምከው። እስቲ በእነዚህ ዓመታት ካጫወትካቸው ጨዋታዎች የማትረሳው የምታስታውሰው (ፈተነኝ) የምትለው ጨዋታ የቱ ነው?

በጣም የማልረሳቸው ብዙ ጨዋታዎች አሉ። ከእነርሱ ውስጥ በጣም አነጋጋሪ የሆነው እና እኔም የታወቅኩበት የቡና እና የጊዮርጊስ ጨዋታ ነው። በ1982 የተደረገው ይህ ጨዋታ እኔም በዳኝነቴ የተፈተንኩበት ከፈጣሪ ጋር ጥንካሬዬን ያሳየሁበት የማልረሳው ጨዋታ ነበር። ምን መሰለህ በቅዱስ ጊዮርጊስ የጎል ክልል ውስጥ የድሬዳዋ ልጅ የሆነው አብዱልከሪም ኳስ በእጅ ይነካል። ፍፁም ቅጣት ምት መስጠት ነበረብኝ። ሆኖም ረዳት ዳኘውን አላሳመነውም። ከኔ የተለየ ሀሳብ ነበረው። ወሳኙ እኔ ስለነበርኩ ወሰንኩና ፍፁም ቅጣት ምቱ ተመታ። ገባ ፣ ጨዋታው በሁለት አቻ ተጠናቀቀ። በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር። ከሠላሳ እስከ አርባ ሺህ ተመልካች የነበረበት ለኔ የተሳካ ጥሩ ጊዜ ያለፍኩበት ነበር። ከጨዋታው በኋላ ጋዜጠኛ ፀጋ ቁምላቸው በቴሌቭዥን አሳይቶት ለቃለ መጠይቅ ጠርቶኝ ጠይቆኛል። በወቅቱ በደጋፊዎች በውሳኔዬ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር። ለጊዜው ውጤት ስለሚፈልጉ ሊቃወሙ ሁልጊዜ ደግሞ ክለቦች የዳኝነትህ አቋም ውለው አድረው ሲያውቁ ያከብሩሀል። ከዛም በኋላ ባጫውት ጊዮርጊሶች ደስ ይላቸዋል። እንዲያውም ሙሉጌታ ከበደ በአንዳንድ ቃለ መጠይቆቹ ላይ ‘ለምን ዳኝነትን ያቆማል? ለምን አይጀምርም?’ እያለ ሲናገር እንደነበረ አውቃለሁ። ሁሉም ለኢትዮጵያ እግርኳስ ትክክለኛ ፍትህ እንዳገኘ ሲያውቅ ለጊዜው ማሸነፉን ቢፈልገውም ያልሆነ ውሳኔ ብትሰጠው ነገ ይታዘብሀል። ስለዚህ በትክክለኛ ውሳኔህ ሁልጊዜ ትከበራለህ። ሌላው መቻል እና ኦሜድላ የምሽት ጨዋታ ዘጠና ደቂቃ ኳስ ያልቆመበት ጨዋታ እንደነበረ አስታውሳለው። እነ ንጉሴ ገብሬ፣ ሙሉዓለም እጅጉ፣ ተስፋዬ ፈጠነ የነበሩበት ጊዜ ነው። ጨዋታውም አንድ ለአንድ ያለቀ ጨዋታ ነበር። የዳኝነት የመጨረሻ ጨዋታዬ በ1987 የሆነው የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከ ሙገር ሲሚንቶ ያደረጉት ሙሉጌታ ከበደ የነበረበት እርሱ የመጨረሻ ጨዋታዬ ሆኖ አስታውሰዋለው።

የአተን የዳኝነት ዘመንን እንዴት ታስታውሰዋለህ ?

የዳኝነት ዘመኔ ሲቆጠር ወደ አስራ ሰባት ዓመት ይሆነዋል። በ1987 ነው ዳኝነትን ያቆምኩት ዳኝነት ለኔ በጣም ወድጄው፣ ደስ ብሎኝ ያገለገልኩበት የሙያ ዘመን ነው። በኔ ትውልድ የነበረው ኳስ ሀገራችን በአፍሪካ የጎላ ታሪክ አይኑራት እንጂ ስድስት፣ ስምንት እና አስር ሰዓት ይደረጉ የነበሩ ሦስቱም ጨዋታዎች በጣም አርኪ፣ ውበት ያላቸው፣ ብዙ የጎል ሙከራዎች የነበሩበት ለዳኝነት ፈተና የነበረ፤ ይህ ሰው ዳኛ ነው አይደለም ተብሎ የሚፈተንባቸው ጨዋታዎች እንደነበሩ አስታውሳለው።

ዳኛ በነበርክባቸው ቆይታ ያገኘኃቸው የኮከብነት ሽልማት አሉ ?

በኛ ዘመን አሁን እንዳለው የኮከብ ዳኝነት የሚባል ሽልማት ነገር አልነበረም። የፍፃሜ ጨዋታዎችን መርተህ የምታገኘው ሜዳልያ ነበር። ከዚህ በተረፈ በሀገር ውስጥ ኮርሶችን ወስደን የምስክር ወረቀት ተጨማሪ የፊፋ የካፍ ኮርሶች ሲመጡ በመውሰድ የምናገኛቸው የምስጋና ሰርቲፊኬቶች አሉ።

የዚህ ዘመን ትውልድ ሰለሞን ዓለምሰገድን አያቀውም። እና እስቲ እኔ እንዲህ ያለ ዳኛ ነበርኩ ብለህ ራስህን ግለፅልኝ ?

የኔ ነገር ለመግለፅ በመጀመርያ ደካማ ጎኔ ሯጭ አይደለሁም። ሰለሞን አይሮጥም በሚለው እታወቃለው። ጠንካራ ነገሬ ግን ዕይታዬ ጥሩ ነው፤ ውሳኔ ላይ ግራና ቀኝ አልልም፤ ጨዋታ አይስበኝም። ለኔ ጨዋታዬ ዳኝነቱ ነው። ምንም ዓይነት ጨዋታ ቢኖር ምንም አልሳብም፣ ጨዋታው አይመስጠኝም። በጨዋታ ውስጥ የኔ ዳኝነት አቅም በህጉ መሠረት እየተፈፀመ ነው ወይ ብዬ ነው የማስበው። ውሳኔ ላይ ባላንስ ለማድረግ የሚባል ነገር የለኝም። ልክም ይሁን አይሁን በዛው ነው የምቀጥለው። ለኔ የክለብ ትንሽ ፣ ትልቅ የለኝም። ሁሉም እኩል ነው። የበለጠ ደግሞ ተመልካቹ የሚፈርደው ይሆናል።

ጋሽ ሰለሞን ለምድነው ኢንተርናሽናል ዳኛ ያልሆንከው ?

ምንድነው መሰለህ… ንግድ የጀመርኩት በ1977 ነው። ከ78 ጀምሮ ለዳኝነት የነበረኝ ፍላጎት ሳላስበው እየተቀዛቀዘ መምጣቱን አስባለሁ። ይህም ተፅዕኖ እያሳደረብኝ መምጣቱን ተገነዘብኩ። መጨረሻ አካባቢ የሆነ ነገር ተፈጠረ እንጂ ኢንተርናሽናል ለመሆን አልፌ ስሜ ሄዶ ነበር። ግን በኃላ ባጁ አልመጣም። ዓለም አሰፋ ከዚህ በፊት ካንተ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሮታል። ከዚህ ውጭ በርግጥ የሩጫ ችግር አለብኝ። ይሄም ቢሆን ፈተናውን እንድወድቅ አላደረገኝም። በዳኝነት ሕይወቴ ባለመሮጥ ምክንያት የተፈጠረብኝ ምንም ዓይነት ስህተት እንዳልተፈጠረ አስታውሳለው።

ልምድ እያገኘህ፣ የበለጠ የማጫወት አቅምህ እያደገ ባለበት ሰዓት ድንገት ሳይታሰብ ነው ዳኝነትን ያቆምከው። ምንድነው ምክንያትህ ለማቆምህ ?

1985 ላይ ትዳር መሠረትኩ። ከዛ በኃላ የሥራ መደራረብ ጫናዎች ተፈጠሩ፣ ንግድ ውስጥ ገባሁ፣ ኃላፊነቶች እየበዙብኝ መጡ። በዚህም በዳኝነት ለመቀጠል በፍፁም አልቻልኩም። ዳኝነትን ብወደውም ሁኔታዎች የሚመቹ አልሆኑም። ሌላ ይሄ ነው ያራቀኝ የምለው ብዙ ምክንያት የለም። አንዳንድ ሰዎች በቡና እና በጊዮርጊስ ጨዋታ መካከል የተፈጠረው ነገር ይመስላቸዋል። ግን እርሱ የተፈጠረው 1982 ነው። ከዛ በኃላ እስከ 87 ድረስ አጫውቻለው። ግን ፈጣሪ ረድቶኝ ትላልቅ ኢንቨስትመንት ውስጥ ገባሁ። ከእርሱ ጋር አብሮኝ ሊሄድ ባለመቻሉም ዳኝነትን ለማቆም ተገድጃለው።

ዳኝነት ካቆምክ በኃላ በፌደሬሽን ውስጥ በሥራ አስፈፃሚነት መጥተህ እየሰራህ ብዙ ሳትቆይ ለመልቀቅ ያበቃህ ምክንያት ምድነው?

እንግዲህ ምንድነው… የኢትዮጵያ እግርኳስ ትልቁ ችግሩ አደረጃጀቱ ከባለሙያ ጋር የተያያዘ አልነበረም። ያኔ የእግርኳስ ቤተሰቡ በኔ ላይ ከነበረው ዕምነት የተነሳ ጫና አሳድሮ ከድሬዳዋ ተወክዬ ነው የገባሁት። በሥራ አስፈፃሚነት ሦስት ጊዜ ገብቻለው። የመጀመርያው እዛ አካባቢ እንደ ባለሙያ የሚያሰራ ባለመሆኑ ትቼ ወጥቻለው። ለሁለተኛ ጊዜ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቤ ሆኜ ገብቼ የተወሰነ አገልግሎት ሰጥቼ ትቼ ወጥቻለው። መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የተወሰነ የአመራር ችግር በነበረበት ጊዜ በሙያ ያለፉ ሰዎች እንዲገቡ ብለው የስፖርት ቤተሰቡ ጫና ሲያሳድር በሚሌንየሙ ጊዜ ገብቼ ምክትል ፕሬዝደንት በመሆን አገልግያለው። ጥሩ የስራ አፈፃፀም ነበረን፣ የሥራ አስፈፃሚው ስብጥር፣ በእግርኳሱ ያለፉ፣ ገንዘብ የማይፈልጉ ያላቸውን አቅም እና እውቀት ለመስጠት የሚፈልግ ነበሩ። አንድ ተርም እንደሰራው ቅድም እንዳልኩህ አደረጃጀቱ የተስተካከለ ስላልሆነ የመሥራት ፍላጎት ቢኖረኝም ለመውጣት ችያለው። የኢትዮጵያ እግርኳስን ስታዲየም በሚደረግ ጨዋታ ብቻ ልትለውጠው አትችልም። ከሥር መሠረቱ የአደረጃጀት ሥራ ካልሰራህበት መሠረታዊ ለውጥ ልታመጣበት አትችልም። የሆኑ ጥሩ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ተገጣጥመው የሆነ ዋንጫ ለአንድ ጊዜ ሊያመጡልህ ይችላሉ። ሆኖም ተከታታይነት እና ቀጣይነት ያለው የእግርኳስ እድገት ለመስራት ግን ከታች ያለውን ችግር ማየት ያስፈልጋል።

ከእግርኳሱ አካባቢ ከራቅክ ረዘም ያለ ዓመት እያስቆጠርክ ነው። የኢትዮጵያ እግርኳስን በተለያዩ አጋጣሚዎች ትከታተላለህ ? አሁን ያለው የዳኝነት ሁኔታስ እንዴት ነው ?

እግርኳሱን በጣም በቅርበት አልከታተልም። በሚያጋጥሙኝ አጋጣሚዎች በመገናኛ ብዙኃን አያለው እንጂ እውነት ለመናገር በቅርበት አልከታተልም። ዳኝነትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ዳኝነት ክራይስስ ላይ እንዳለ ከርቀት እሰማለው። ግን ደግሞ በግል ጥረታቸው የሚገርሙ ዳኞች አሉ። በኛም ዘመን ጠንካራ ዳኞች ነበሩ በሚባልበት ጊዜ ያልተደረሰበትን ማሳካት ያልቻሉ እንደነ በዓምላክ ተሰማ እና ሊዲያ ታፈሰ ዓይነት ወጣቶች ስታይ ደግሞ ሙያውን እንደሚውያቅ እና እንደሚወድ ሰው ትደሰታለህ። አጠቃላይ ዳኝነቱ ከሚባለው፣ ከሚሰማው፣ ራሱ ዳኛው ካልሰጠው ክብር ተነስተህ፣ ፌዴሬሽኑ ካጎደለው ክብር ተነስተህ ያለው ታዓማኒነት፣ በክለቦች ምን ያህል ዳኞች ይከበራሉ፣ ዳኞችስ ምን ያህል ራሳቸውን ያስከብራሉ የሚለውን ስታይ የሆነ ውድቀት እንዳለ ታያለህ።

አንድ ዳኛ የሆነ ግለሰብ ወይም ወደፊት ዳኛ ለመሆን የሚያስብ ሰው ካለህ ከፍተኛ ልምድ ምን መሆን አለበት ብለህ ትመክረዋለህ ?

ዳኛ የሆነም ዳኛ ለመሆን የሚያስብ “ሀ” ብሎ ሲጀምር ነፃነት ያለው ሰው፣ ስብዕናው ንፁሕ የሆነ መሆን ይኖርበታል። ደሀ ወይም ሀብታም መሆን አይጠበቅበትም። ግን ንፁሕ ሰው መሆን አለበት። ማንም ጋር ምንም ግኑኝነት የሌለው መሆች አለበት። የታመንክ ለመሆን መጀመርያ ንፁሕ መሆን ያስፈልጋል። ክለቦች እንዲያምኑህ ከማንም ክለብ እና ሰው ጋር በምንም ዓይነት መንገድ ግኑኝነት የሌለህ ሰው መሆን መቻል አለብህ። ዳኝነት ይሄን ይፈልጋል። አንድ ሜዳ ውስጥ ቢሳሳት እንኳን ሌላ ነገር ሊያደርግ ፈልጎ አይደለም ተብሎ እንዲታመን መጀመርያ ከሜዳ ውጭ ያለው ህይወቱ ንፁሕ መሆን አለበት። ንፁሕ በሆነ ቁጥር የመወሰን ነፃነት ያገኛል። ከፍተኛ ደረጃ ይደርሳል። ይህ ነው መጀመርያ ምክሬ። ከዚህ በኋላ ያሉ ነገሮች ቴክኒካል እና የህግ እውቀትህን ማዳበር፣ የአካል ብቃትህን ዝግጁ ማድረግ እና ያለመፍራት በቀጣይ የሚመጡ ናቸው። እነዚህን ነገሮች ካሟላህ ንፁሕ እና ጠንካራ ዳኛ መሆን ትችላለህ። የፈለገ ችሎታ ቢኖርህ ስብዕና ከሌለህ ግን ሜዳ ውስጥ ጎልተህ መታየት አትችልም።

በአሁኑ ወቅት በንግዱ ዓለም የተለያዩ ከፍተኛ ኃለፊነቶች አሉብህ። እስቲ ከመነሻህ ጀምሮ አሁን እስከ ደረስክበት ያለውን አጫውተኝ?

የንግድን ሥራ ስጀምር ምንም የሀብት መሠረት አልነበረኝም። በትንሽ ካፒታል መርካቶ አካባቢ ስለነበርኩና የንግድ ሀሳቡ ስለነበረኝ 1978 አካባቢ ንግዱን ጀምሬ አሁን የትሬዲንግ ሥራ አለ ፣ በሪልስቴቱም አሴር የተሰኘ የኮንስራክሽን ድርጅት አለኝ። ባለቤቴም በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የራሷን አስተዋፆኦ እያደረገች ትገኛለች።

ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ተመልሰህ በኃላፊነቱ የማገልገል እቅዱ አለህ ለወደፊት?

አላውቅም እንዲህ ነው ብዬ ያቀድኩት ነገር የለም። አሁን መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ ነኝ። ፈጣሪን ማገልገል የምፈልግ ሰው ነኝ። እንደ ዜጋ ኢትዮጵያ ሀገሬ ነች በሁሉም ልማት በእግርኳሰም ጭምር እንድታድግ እፈልጋለው። ፈጣሪ ከፈቀደ የትኛውንም አስተዋፆኦ ላደርግ የምችለው ነገር ካለ አደርጋለው። እግርኳስ እንድታወቅ ያደረገኝ ስለሆነ የኢትዮጵያ እግርኳስ ውለታ አለብኝ። የማገልገል ዕድሉን ካገኘሁ ብዙ ወደ ኃላ የምል ሰው አይደለሁም።

የቤተሰብ ህይወትህ ምን ይመስላል?

ሦስት ልጆች አሉኝ። የሀያ ስድስት፣ የሀያ አምስት እና የአስራ ሁለት ዓመት ልጆች አሉኝ። የመጨረሻው ልጄ በጣም እግርኳስ ይወዳል። እንዳውም በኳስ ትንተና መንሱርን እበልጠዋለው ይላል። የመጀመርያዋ ልጄ ራሷን ችላ እንግሊዝ ሀገር ነው የምትኖረው። ሁለቱ ወንድ ልጆቼ ከባለቤቴ ጋር እዚህ ነው የሚኖሩት።

በመጨረሻ…

በዳኝነት ዘመኔ በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ በጣም ደስታኛ ነኝ። በወቅቱ የነበሩ ድንቅ ተጫዋቾች ሙሉዓለም እጅጉ፣ ንጉሴ ገብሬ፣ ሙሉጌታ ከበደ፣ ሙሉጌታ ወልደየስ፣ ገብረመድኅን ኃይሌ፣ ፀጋየ ፋንታሁን፣ ሚሊዮን በጋሻው፣ ዳኛቸው ደምሴ፣ አብርሀም ብስራት፣ አብዲ ሰዒድ፣ ካሳዬ አራጌ፣ ኃይሌ ካሴ፣ አፈወርቅ ጠና ጋሻውና ሌሎችም ድንቅ ተጫዋቾች በነበሩበት ዘመን ማጫወት እድለኝነት ነው። በጣም ነው የማመሰግናቸው። በዳኝነት በኩል በቀለ ኪዳኔ ፣ ተስፋዬ ገብረየሱስና፣ ዓለም አሰፋ ወዳጆቼ ኃይሉ ተሰማ፣ ኃይለመላክ ተሰማ፣ ኪነ ጥቡና እና ሌሎችንም ዳኞች ጋር አብሬ በመስራቴ ደስተኛ ነኝ። በጣም አመሰግናቸዋለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!