የሰማንያዎቹ… | የመሐል ሜዳው ጥበበኛ የጥላሁን መንገሻ ሕይወት

👉”.. ኢትዮጵያ ቡና በጣም መከባበር የነበረበት ዓላማ ያለው ደስ የሚል ቡድን ነበር።”

👉”..እኔ ኳስንም ቡናንም እወዳለው ነገር ግን እዛ ስሄድ የማልስማማበት ነገር ሀሳብ ይሆንብኛል። የእኔስ ጥፋት ምንድነው ? ብዬም ብዙ እስባለሁ።”

👉”.. በፍፁም ቅጣት ምት አመታት ውስጥ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች እንዳሉ ያስተማረኝ አሰልጣኝ ሥዩም አባተ ነው።”

👉”.. ለምድር ጦር ጨዋታ ላይ ልምምድ በእግር መረብ ኳስ ተጫውተን የምንመጣበት ጊዜ ነበር። ግራውንድ ቴኒስ ሜዳ ላይ በእግር ቅብብል ሁሉ ያሰራን ነበር።”

👉”.. በእርግጠኝነት አንድ ነገር መስራት እንደምችል ሁሉም የቡና አመራሮች ያውቃሉ። ነገር ግን የማይሆኑ ትዕዛዞች በፍፁም አልቀበልም። “

👉”.. በተጫዋችነት ዘመኔ የምቆጨው ብዙ ዓመታት አሳልፌ ትልልቅ ዋንጫዎችን አለማሳካቴ ነው። “

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ብዙ ያልተመሰከረለት ፣ ያልተተነተነለት ምጡቅ ችሎታ ያለው ነው። ጥበበኛ ፣ የተረጋጋው እና የፍፁም ቅጣት ምት ቀበኛ (Specialist) ነው። የሰማንያዎቹ ኮከብ ተጫዋች የነበረው አማካይ ጥላሁን መንገሻ ማነው?

ከጎረቤት ጓደኛው ጋር አሮጌው ፖስታ ቤት ለሚገኙት የጓደኛው አባት ምግብ ለማድረስ አልፎ አልፎ ይሄዱ ነበር። ጓደኛው አትሌቲክስ ስፖርት ይወድ ስለነበር በአንድ አጋጣሚ እግረ መንገዱ ወደ አዲሰ አበባ ስታድየም ጎራ በማለት የምዝገባ እና የሙከራውን ጊዜውን ያሳልፋል። ታዲያ እርሱ እስኪጨርስ ድረስ የዛሬው ባለ ታሪክ በስታድየሙ ግራ ጥላ ፎቅ ቁጭ ብሎ የጓደኛውን መምጣት እየተጠባበቀ ይገኛል። ድንገት ተቀምጦ ባለበት ሰዓት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ግብጠባቂ የነበረው ተስፋዬ ገብሩ በአጠገቡ ሲያልፍ “አንተ ልጅ እዚህ ቁጭ ብለህ ምን እየሰራህ ነው ?” ይለዋል “ጓደኛዬ ለአትሌቲክስ ምዝገባ መጥቶ እርሱ እስኪጨርስ እየጠበኩኝ ነው።” ብሎ ይመልስለታል። “አንተ አትመዘገብም እና ሙከራ አታደርግም ?” ሲለውም “አይ እኔ ቤተሰብ አላስፈቀድኩም ደግሞ እግርኳስን ብወድም የመጣሁት አጋጣሚ ነው” ይለዋል። “እግርኳስን የምትወድ ከሆነ በል ዝም ብለህ ግባና ተመዝገብ ሙከራውን አድርግ ካለፍክ በኃላ ቤተሰቦችህን ሄደህ ታስፈቅዳለህ ይለዋል።” ይህ ታዳጊ ብላቴናም ይመዘገባል ሙከራውንም ያልፋል። በዚህ ብላቴታ ውስጥ ያለውን የታመቀ አቅም ተስፋዬ ገብረወልድ በምን ታአምራዊ መለኮት እንዳወቀው ፈጣሪ እና እርሱ ናቸው የሚያውቁት። ይህ የጓደኛውን ሁኔታ ለመከታተል የመጣው ታዳጊ በመጨረሻም ለተለያዩ ትልልቅ ክለቦች፣ ለብሔራዊ ቡድን ድረስ ለመጫወት የበቃ ትልቅ ተጫዋች ከመሆኑም ባሻገር አሰልጣኝ በመሆንም ብዙ ትውልዶችን ለመፍጠር ችሏል።

ጥላሁን መንገሻ የትውልድ መገኛ ከተማ አዲስ አበባ በኮልፌ እና በጦር ኃይሎች መካከል የምትገኝ ጅማ ሠፈር የምትባል መንደር ናት። በሠፈር ውስጥ እግርኳስን ጅማሬው ሲያደርግ ሁሌም አዲስ አበባ ስታድየም በመሄድ ጨዋታዎችን እየተከታተለ ያየውን የጨዋታ ታክቲክ የሠፈሩን ልጆች እየሰበሰበ በፍላጎት የሚያሰለጥን ፣ መነሳሳትን እየፈጠረ በልጅነት አዕምሯቸው እግርኳስን እንዲወዱ ቀርፆ ያሳደገ ክብሩ ማሙሽ የሚባል ሰው ይህን ጥበበኛ እግርኳሰኛ የልጅነት ዕድሜውን እየተጫወተ እንዲያሳልፍ አድርጎታል።

በአዲስ አበባ ስታድየም ዙርያ አሁን ለዘበት ታሪክ ሆነው ባለፉ ያየኔ የብዙ ትውልድ መገኛ በሆኑ ሜዳዎች ፕሮጀክት ታቅፎ በጋሽ ታደሰ እየሰለጠነ ባለበት ወቅት ሙሉ ለሙሉ ቡድኑን ጭማድ ጠቅልሎ በሚያስተዳድርበት ወቅት በክለብ ደረጃ የእግርኳስ ህይወቱን አንድ ብሎ ጀምሯል። ሆኖም በ1980 ጭማድ እግርኳስ ክለብ የመፍረስ አደጋ ሲያጋጥመው ብዙ ዕውቅና ተወዳጅነት ወዳተረፈበት ኢትዮጵያ ቡና አምርቷል። በኢትዮጵያ ቡና ስምንት ዓመታትን በተጫወተባቸው ጊዜያት በደጋፊዎች ከሚወደዱ ምርጥ አማካዮችም ውስጥም መካተት ችሏል። በተለይ ፍፁም ቅጣት ምት ቡና ካገኘ ጥላሁን እንደሚያገባው ቀድመው እርግጠኛ የሚኮንለት ምርጥ ተጫዋች ነበር። ጥላሁን መንገሻ በሰማንያዎቹ በኢትዮጵያ ቡና መለያ ከታዩት ከካሳዬ አራጌ እና ከአብዱራዛቅ (ናይጄርያ) ጋር የነበራቸው ጥምረት ልዩ ነበር።

በኢትዮጵያ ቡና አብሮት ከተጫወቱ ተጫዋቾች መካከል ገብረኪዳን ነጋሽ(ጋምብሬ) ስለ ጥላሁን ሲናገር ” ጥላሁን ኦ… በዚህ ደረጃ መግለፅ በጣም ከባድ ነው። ጥልዬ እኔ ብቻ የምገልፀው ሰው አይደለም። የአጨዋወቱ እና የችሎታው ደረጃ ምንም የማታወጣለት ከእኔ በፊት የነበሩ ስለ እርሱ ሲነግሩኝ እሰማለው አብሬው በመጫወቴም በጣም ዕድለኛ ነኝ። እኔ እንዳውም ማጋነን አይሁንብኝ እንጂ እርሱ በዚህ ዘመን ቢሆን ኖሮ ከኢትዮጵያ ውጪ ወጥቶ መጫወት የሚያስችል አቅም የነበረው ሁሉን ያሟላ ተጫዋች ነው። ብዙ ሰዎች አጭር ቀጭን ሆኖ ሲያዩት ብዙ ነገር ይላሉ ግን ጥልዬ ብዙ ነገር ያለው ከርቀት የሚያስቆጥራቸው ጎሎች የማስታውስለት በጣም አስገራሚ ተጫዋች ነበር።”

1988 ላይ ከቡና ጋር በተለያዩ ምክንያቶች በተፈጠሩ በአለመግባባቶች ከክለቡ ጋር ተለያይቶ ለአንድ ዓመት ለአየር መንገድ ተጫውቶ ነበር። ለአየር መንገድ በነበረው አጭር ቆይታ ከተከተል ኡርጌቾ ጋር እስከ መጨረሻው ድረስ ለኮከብ ግብ አግቢነት እየተፎካከረ በመጨረሻ ጨዋታ ላይ ተከተል አግብቶ በለጠው እንጂ በወቅቱ የነበረው የሜዳላይ እንቅስቃሴው ጥሩ በመሆኑ አሰልጣኝ ሥዩም አባተ ቡናን ለማሰልጠን በድጋሚ ሲመለስ 1990 ለቡና ለመጫወት ችሏል። በቡና 1991 እና 92 ድርስ ቆይታ በማድረግ በታላቁ የእግርኳስ ሰው በአሰልጣኝ መንግስቱ ወርቁ አማካይነት ለሁለት ዓመት እግርኳስን በጉዳት እስካቆመበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ መድን በመጫወት አሳልፏል።

ሜዳ ውስጥ ጨዋታን የማንበብ አቅሙ እና በተረጋጋ ሁኔታ በብስለት እና በትኩረት እንደሚጫወት የሚነገርለት ጥላሁን በጉልበት ጉዳት ለወራት ከሜዳ በመራቁ ክለቡ ኢትዮጵያ መድን እንዳያሰናብተው እየሰጋ ባለበት አጋጣሚ ክለቡ በተለያዩ ቀውስ ውስጥ ቡድኑ ገብቶ አሰልጣኝ ያሰናብታል። የክለቡ አመራሮች በድንገት ስብሰባ አድረገው ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጥላሁን መንገሻን ጥሪ ያደርጉለታል። “ቡድኑን ካለበት ወቅታዊ ችግር እና የመውረድ አደጋ እንዲወጣ የማሰልጠን ኃላፊነት አንተ ተረክበህ ይልማ ከበደ(ጃሬ) በምክትል ኃላፊነት ያግዝሀል።” በሚል የተጫዋች አሰልጣኝ በመሆን የሥልጠና ህይወትን ጀምሯል። በውስጡ በነበረው የእግርኳስ ሀሳብ እና በሀገሪቱ አሉ በሚባሉ ታላላቅ አሰልጣኞች ስር ማለፉ ረድቶት መድንን ከመውረድ ለማትረፍ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ቡድኑን እንዳይወርድ ከማድረጉ ባሻገር እግርኳስን አቁሞ ወደ አሰልጣኝነቱ እንዲገባ መንደርደርያ ሆኖታል።

አብሮ በመጫወት እና በአሰልጣኝነትም አብረው መስራት የሚያቀው ይልማ ከበደ(ጃሬ) ስለ ጥላሁን መንገሻ እንዲህ በማለት ይናገራል። ” ጥላሁን በወቅቱ ከነበሩ የመሐል ሜዳ በጣም ጎበዝ፣ ብልጥ ተጫዋች አንዱ ነበር። በማጥቃቱ፣ በመከላከሉ በኩል የሚያግዝ በሁሉም መልኩ የሚሳተፍ ተጫዋች ነው። ስብዕናውም የዛኑ ያህል ከፍ ያለ ለሰው አሳቢ እና ተግባቢ ሰው ነው። በአሰልጣኝነቱም ዘመን አብረን ስንሰራ ጥሩ አስተሳሰብ ያለው ፣ ሰው እንዲያድግ የሚፈልግ ትልቅ አቅም ያለው ሰው ነው።”

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአንድ አጋጣሚ ከተጠራበት ውጭ እንደነበረው አቅም ብዙም ሀገሩን ማገልገል አልቻለም። በክለብ ደረጃ ለአስራ አምስት ዓመት ያለማቋረጥ በአራት ክለቦች በመጫወት ውጤታማ ጊዜ አሳልፏል። ጥላሁን በ1994 እግርኳስን በማቆም በዚሁ ዓመት ለመድን ጊዜዊ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ከሰራ በኃላ በተለያዩ ዓመታት የብርሀኔ ገብረእግዚአብሔር እና የካሳሁን ተካ ረዳት በመሆን ሲሰራ ቆይቷል። በ1996 ፣ 2000 እና 2007 ሦስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ቡና በመምጣት ቡድኑን የተሻለ ምዕራፍ በማድረስ ስኬታማ ቢሆንም በሦስቱም የማሰልጠን አጋጣሚዎች እርሱ ባልተረዳው ምክንያት ከክለቡ ጋር የተለያየበት መንገድ ሁሌም የሚቆጨው እና መልስ ያላገኘበት ጥያቄ ሆኖ አልፏል።

በመቀጠል ንግድ ባንክ ፣ ፋሲል ከነማ ፣ ድሬደዋ ከተማ እና ሀድያ ሆሳህና እስከ 2009 ድረስ አሰልጥኗል። በአሁኑ ሰዓት የራሱ የታዳጊዎች አካዳሚ ከፍቶ በመድኃኒያለም ትምህርት ቤት እያሰለጠነ ይገኛል። በሰማንያዎቹ ውስጥ ከተገኙ ድንቅ ጥበባኛ የመሐል ሜዳ ተጫዋች መካከል ጥላሁን መንገሻን በዛሬው የሰማንያዎቹ ኮከብ አምዳችን ፈልገን አግኝተን አውርአላውቅም።

” እኔ በግሌ እግር ኳስን በሚገባው መንገድ ተጫውቻለው ብዬ የማስበው በክለብ ደረጃ ሳይሆን ጋሽ ታዴ ጋር ትንሿ ሜዳ ነው። በምናብ የምንቀባበል አሁን ውጪ ያሉ ልጆች የነበሩበት ቡድን ነው። ከዛ በኋላ ደግሞ በታዳጊዎች እና ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተገነባ ቡድን በኢትዮጵያ ቡና ገጥሞኛል። እነካሳዬ ፣ ናይጄሪያ ፣ ተስፋዬ ድርግ ፣ አሸናፊ በጋሻው ነበሩበት። ትላልቆቹ ደግሞ እነ ሙሉጌታ ወልደየስ ፣ ሚሊዮን በጋሻው ፣ ዮናስ ፣ ጌቱ ገብረማርያም ፣ አስራት አዱኛ በደንብ እንድንጫወት ነፃነት ይሰጡን ነበር። አሰልጣኛችን ደግሞ ሥዩም አባተ ነበር። በጣም መከባበር የነበረበት ዓላማ ያለው ደስ የሚል ቡድን ነበር ፤ እንዴት እንደምናገርም አላውቅም።

“በተጫዋችነት ዘመኔ የምቆጨው ብዙ ዓመታት አሳልፌ ትልልቅ ዋንጫዎችን አለማሳካቴ ነው። እኔ ብቻ ሳልሆን ያ ስብስብ በብዙ ዋንጫ አለመታጀቡ ይቆጨኛል። ምክንያቱም ከእኔ በአቅም ያነሱ ተጫዋቾች አምስት ስድስት ዋንጫዎችን እንዳሳኩ ሲናገሩ የሚቆጭ ነገር ይኖረዋል። ከዛ ውጪ ግን ከሰፈር ከእነ አንዋር ትልቁ ጋር በክለብ ደረጃ ከነ ማንጎ ፣ ካሳዬ ፣ ጋንብሬ ጋር ከሁለት ትውልዶች ቴዎድሮስ ቦካንዴ ፣ ቴዲ ባርያው ፣ ዬሴፍ ተስፋዬ ጋር ከሌሎችም ከምፈልጋቸው እና ከምወዳቸው ተጫዋቾች ጋር የመጫወት ዕድሉን በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

“በኢትዮጵያ ቡና ምድር ጦር (መቻልን) ደጋግመው ማሸነፋችን ኳስን መሠረት አድርገን በጨዋወታችን ነው። አሰልጣኝ ሥዩም አባተም የሚያጫውተን አጨዋወት የሚታወቅ ነው። በዚህ አጋጣሚ ደስ ከሚለኝ ከአሰልጣኝ ሥዩም ነገር ውስጥ ለየክለቡ የተለያየ ዝግጅት ማድረጋችን ነው። ለየክለቡ የምንሰራቸው ነገሮች ይኖራሉ። የምድር ጦር ጨዋታ ላይ ልምምድ በእግር መረብ ኳስ ተጫውተን የምንመጣበት ጊዜ ነበር። ግራውንድ ቴኒስ ሜዳ ላይ በእግር ቅብብል ሁሉ ያሰራን ነበር። እንደሚመስለኝ እነሱ መቻል ጋር ስጋት የሚኖር ይመስለኛል። አንዳንድ ተጫዋቾችን በውጪም ስናገኛቸው ከትላልቆቹም ይልቅ መሀል ሜዳ የነበርነውን ተጫዋቾችን ለማቆም ይጨነቁ ነበር። ይህ ስጋታቸውም ይመስለኛል የምናሸንፋቸው። እኛም ግን እውነቱን ለመናገር ጥሩ አቅም ነበረን።

“የፍፁም ቅጣት ምት ችሎታውን ያገኘሁት ብዙ ጊዜ የፍፁም ቅጣት ምት ሲገኝ የሚሰጡት ለእኔ ነበር። በፍፁም ቅጣት ምት አመታት ውስጥ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች እንዳሉ ያስተማረኝ አሰልጣኝ ሥዩም አባተ ነው። ከዛ በፊትም በነበረው ሂደት ውስጥ ታደሰ ገብረመድህን የሚባል አሰልጣኝ ነበረን እሱም ተመሳሳይ ነገር ይነግረኝ ነበር። ትኩረት፣ ቦታ ማየት እና ኳስን አክርሮ መምታት መሰረታዊ ሀሳቦቹ ነበሩ። ውሳኔ ማሳለፍ እና ስመታ መወላወል እንደሌለብኝ ይነግሩኝ ነበር። እነዛን ነገሮች ተግባታዊ አደርግ ስለነበር መሰለኝ ጥሩ መቺ የሆንኩት።

“በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ካሳሁን ተካ ጊዜ ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ ዕድል አግኝቻለሁ። ለስድስት ወር ያህል ብቆይም በነበሩት ውድድሮች ግን መለያውን ለብሼ አልተጫወትኩም። በወቅቱ እኔ በነበርኩበት ጊዜ ከአልጄሪያ ጋር ይደረግ በነበረ ጨዋታ እስከ መጨረሻው ልምምድ ድረስ ባሚሰለፈው ቡድን ውስጥ ነበርኩኝ። ፓስፖርት እንዳመጣ ተነግሮኝ እሱን ይዤ ስመጣ ከ 18ቱ ውጪ ልሆን ችያለሁ። ለዛም ነው አሰልጣኝ ማንንም ሰው ቁጭ ብሎ የማናገር ልምድ ሊኖረው ይገባል። በእኛ ሀገር ሁኔታ ሁሌም አሰልጣኝ እና ተጫዋች አይጥ እና ድመት ሆኖ የሚኖርበት ጊዜ መጥፋት አለበት የሚል እምነት አለኝ። ያ ነገር እስኪሆን ድረስ ተጫዋቹ የውስጡን አውጥቶም አይናገርም ከልቡም አይጫወትም። ይህን እንዳስብ ያደረጉኝም እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ናቸው። ለምን እንደዛ እንደሆነ ለመጠየቅ ስሄድ እንኳን ጥሩ ምላሽ አላገኘሁም። የብሔራዊ ቡድን ሕይወቴም እንዲበላሽ ሆኗል።

“በኢትዮጵያ መድን ተጫዋች ሆኜ የአሰልጣኝነት ኃላፊነት ሊሰጡኝ የቻሉበት ምክንያት በወቅቱ እኔም ምክንያታቸውን አላወቅኩትም። ኮሚቴዎቹም ኃላፊነቱን ሊሰጡኝ እንዳሰቡ ነግረውኝ ነው የሄዱት። ይህን ጉዳይ እንደሰማው በወቅቱ የውጪ ጨዋታዎች ጥቂት ቦታዎች ላይ በሚታዩበት ጊዜ አብሬው አይ የነበረው ጋዜጠኛ ሁሴን አብዱልቀኒ ጋር ነበር የሄድኩት። ሁኔታውን ሳስረዳውም ‘አምነውብህ ዕድሉን ከሰጡህ አንተ ካሳለፍከው ልምድ እና ከምትወደውም አጨዋወት በመነሳት የራስህን ሙከራ አድርግ። ቡድኑ ቢወርድም ተጠያቂ አትሆንም። ከተረፈ ደግሞ ለወደፊት ህይወትህ ጠቃሚ ሊሆን ስለሚችል አትፍራ’ ብሎ ሞራል ሰጠኝ። ማታ ላይም ካሰለጠኑኝ አሰልጣኞች የምወዳቸውን ስራዎች በተለይ የአሰልጣኝ ስዩም ከኳስ ጋር የተገናኙ ልምምዶችን እንዲሁም ሁሴን ከሚሰጠኝ ቪዲዮች እና መፅዔቶች በመነሳት ዕቅዴን አዘጋጅቼ በማግስቱ ሄድኩኝ። ከልምምዱ በኋላም ‘ልምምዴን ጨርሻለው ስለተቀበላችሁኝ አመሰግናለሁ’ ስል ባልጠበቅኩት ሁኔታ አጨበጨቡልኝ። ይህም በጣም መነሳሳት ፈጠረልኝ እና በተጫወትኩባቸው ጊዜያቶች ደስ ብሎኝ የተጫወትኩባቸውን ወቅቶች ወደ ኋላ ሄጄ በማሰብ እነዛን ልምምዶች በማምጣት በግልም ከተጫዋቾቸ ጋር በማውራት የራሴን አሰለጣጠን ማሳደግ ጀመርኩ።

“በዋና አሰልጣኝነት 1996 መጀመሪያ ላይ በአቶ አብዱርሀማን አመራርነት ወደ ቡና የመጣሁት በምክትል አሰልጣኝነት ከካሳዬ ጋር ለመስራት ነበር። በመቀጠል ካሳዬ ባለመግባባት ሲለቅ ደግሞ ቡድኑን ይዤ እንድቀጥል ተነገረኝ። ውጤቱ ጥሩ እየሆነ ስሄድም ክለቡ እና በደጋፊ ማህበር አመራሮች ‘ምን ትፈልጋለህ ?’ ተብዬ ተጠየኩ። እኔም ቅጣት ላይ ይገኙ የነበሩ ስድስት ተጫዋቾች ስለነበሩ እነሱ ተመክረው እንዲመለሱ ጥያቄ አቀረብኩ። ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ተመለሱልኝ። በዛም ጥሩ ጊዜ አሳልፈን ውድድሩ ሊያልቅ ሦስት ጨዋታዎች ሲቀሩት በመሪነት ደረጃ ላይ እያለን ባልተረዳሁት ሁኔታ እንድነሳ ተደረገ። ቡናም ዋንጫውን ሳያገኝ እኔም ሳልቀጥል ቀረሁ። 2000 ላይ በድጋሚ ተጠራሁ። ያኔም ከአመራሩ ጋር ተመሳሳይ ችግር ነበር። ብዙ ሰዎች ታገስ ቢሉኝም ለውጥ የሚመጣ መስሎ ስላልተሰማኝ መልቀቂያ አስገብቼ ወጥቻለሁ። ከዛ በኋላ የቡናን ማንንም አመራር አግኝቼም አይቼም አላውቅም ነበር። 2006 ግን አቶ ይስማሸዋ ደውሎሎኝ አወራኝ። እኔም 1996 እና 2000 ላይ የተፈጠረው ነገር እንዳይደገም ብዬ በጉዳዩ ዙሪያ በደንብ አወራን። ከአንድ ወር ከ15 ቀን በላይ ተወያይተን ነበር የገባሁት። ነገር ግን 2006 ላይም ብዙም ባልተረዳሁት መንገድ ነው ቆይታዬ የተጠናቀቀው። በእርግጠኝነት አንድ ነገር መስራት እንደምችል ሁሉም የቡና አመራሮች ያውቃሉ። ነገር ግን የማይሆኑ ትዕዛዞች በፍፁም አልቀበልም። እንደኔ አመለካከት ምንም እንኳን ከ1980 ከልጅነቴ ጀምሮ የሚያውቁኝ ቢሆንም አሁን ላይ ግንኙነታችን የአባት እና የልጅ ሳይሆን የስራ ነበር መሆን የነበረበት።

“በቀጣይ የአሰልጣኝነት ጊዜ ወደ ፋሲል ሄጃለው። በጣም ጥሩ ቡድን ነበረን። አሁን ካለው ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ ጋር ጥሩ ሰራዎች በጥሩ አደረጃጀት አስተካከልኳቸው መስመር አስያዝኳቸው ከምላቸው ቡድኖች ውስጥ ነው። ፋሲል ከነማ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጊያለሁ። መጨረሻ ላይ ግን ውል ለማደስ በተቃረብንበት ወቅት የአመራር ለውጥ በመፈጠሩ አዲሱ አመራር የራሱን ሰው በአሰልጣኝነት ሾሟል። በድሬዳዋ ፣ በሀዲያ እና በንግድ ባንክም ሰርቻለው። በንግድ ባንክም የተፃፈ የሦስት ዓመት ዕቅድ ይዤ ሰርቻለው። ነገር ግን ከዕቅዱ በላይ ጥሩ ስራ ብሰራም የመጀመሪያው ዓመት ሲጠናቀቅ ሌላ አሰልጣኝ ነበር የፈለጉት። ይህም እንዴት እንደተፈጠረ አላውቅም። እኔ ትልቁ ችግሬ ኮንታክት የለኝም። ሥራ ከገባው ስራዬን ብቻ ነው የምወጣው። ከአመራር ጋርም ከስራ ውጪ ምንም ግንኙነት የለኝም። ከሀዲያ በኋላ ሌላ ክለብ አልሰራሁም ፤ ቤቴ ነኝ ያለሁት። እግርኳስ በጣም ይናፍቀኛል። ከልጅነቴም ጀምሮ ከእግርኳስ ሌላ ምንም ሀሳብ ኖሮኝ አያውቅም አሁንም የለኝም።

“አሁን እየሰራው የምገኘው እኔ በጋሽ ታዴ ስር በማለፌ ልጆች አንድ ላይ ተሰብሰበው በጥሩ ስብዕና ከተቀረፁ ጥሩ ነገር መስራት ይቻላል የሚል ዕምነት አለኝ። በመሆኑም ከአሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ ጋር ክሬስፖ የሚል ፕሮጀክት ከፍተን እንሰራ ነበር። እኔ ሰፈሬ አስኮ ነው። ስራው ደግሜ CMC ስለነበር ከዓመት በላይ ተመላልሼ ሰርቼ ነበር ከዛ ግን ድካሙን አልቻልኩትም። አሁን ግን በሠፈሬ መድኃኒያለም ትምህርት ቤት አስፈቅጄ እየሰራሁ ነው። እዛ ውስጥ ልጄም ተሳታፊ ነው። በሁለት ምድብ አርባ አምስት የሚሆኑ ልጆች አሉኝ። በሳምንት ሦስት ቀን እየሰራን ነበር። እንደ ዕቅዳችን በዚህ ዓመት ውድድር ውስጥ እንገባለን ብለን አስበን ነበር። ሆኖም በኮሮና ምክንያት አልተሳካም።

“የቤተሰብ ህይወት ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነኝ። አንድ ወንድ አንድ ሴት ልጆች አሉኝ። አማኑኤል እና ሔራን ይባላሉ። ትልቁ 12 ትንሿ ደግሞ አራት አመታቸው ነው።

“ገጠምኝን በተመለከተ እኔ በተጫዋችነት ዘመኔ ሜዳ ላይ ያለው ነገር ላይ ነበር ትኩረት የማደርገው። ግን ሁሌም ውስጤን የሚነካኝ እና የሚገርመኝ አንድ ነገር የቡና ነገር ነው። እኔ ኳስንም ቡናንም እወዳለው ነገር ግን እዛ ስሄድ የማልስማማበት ነገር ሀሳብ ይሆንብኛል። የእኔስ ጥፋት ምንድነው ? ብዬም ብዙ እስባለሁ። በእርግጥ ከአመራሮቹ ጋር እንጂ ከቡና ጋር አይደለም አለመግባባቱ። ሦስት ጊዜም በተመሳሳይ አጋጣሚ መሆኑ ግን ያናድዳል። ከዛ ውጪ ግን በተጫዋችነትም በአሰልጣኝነትም ለቡና አልሰራሁም አላደረኩለትም ብዬ የምቆጭበት ነገር ግን የለም።

“አሁን ላይ የ ‘A license’ አለኝ። በቀጣይ የሚፈልገኝ የሚያምንብኝ ክለብ ካገኘው እሰራለሁ። ነገር ግን እባካችሁ ብዬ የምለምንበት ምንም ዓይነት ሁኔታ የለም።

“ምስጋና ማቅረብ የምፈልገው በእኔ የእግርኳስ ህይወት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው ቅድም በሰፈር መነሳሳትን የፈጠረልኝ ያልኩት ክብሩ ማምሻ ነው ፤ እስካሁንም እንደታላቅ እና ታናሽ አብረን አለን። እሱን ላመሰግነው እወዳለሁ። ይስሀቅ በድሩ ከእነ ባለቤቱ ትልቅ አክብሮት አለኝ። እግርኳስን ሲናገርም፣ ሲያስረዳም ፣ ሲተነትንም በጣም ጎበዝ ነው። ሌላው የገጠመኝን ሚዲያ ሁሌም እከታተላለው። ሁሉም እግር ኳሱን ለማሳደግ ይጥራል። እኔም አንድ ቀን ኢትዮጵያ በእግርኳስ ትልቅ ስም እንዲኖራት እመኛለሁ የበኩሌንም እጥራለሁ።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ያጋሩ