የታማኙ ደጋፊ የቀብር ሥነ-ስርዓት ተፈፀመ

ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የኢትዮ ኤሌክትሪክ አንጋፋ ደጋፊ በቀለ ሄኒ የቀብር ሥነ- ስርዓት ዛሬ በሳሪስ አቦ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለይም በአዲስ አበባ ስታድየም በረጅም ዓመታት የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ደጋፊነታቸው የሚታወቁት አቶ በቀለ ሄኒ በቀድሞው ሸዋ ክፍለሀገር በመናገሻ አውራጃ ቀርሳ እና ማሊማ በሚባል ቦታ 1944 ላይ ነበር የተወለዱት። ከመንፈሳዊ ትምህርት በኋላ በአዲስ አበባ ጉለሌ መድኃኒያለም እና በንፋስ ስልክ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን በአዋሽ ኮንስትራክሽን በጀመረው የስራ ህይወታቸው ከ1967 ጀምሮ በሰፊው በሚታወቁበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሲሰሩ ቆይተዋል። ከስፖርት ክለቡ ጋር ተቆራኝተው በኖሩበት በዚህ መስሪያ ቤትም በሙያቸው ጡረታ እስከወጡበት 2001 ድረስ በመቀጠልም በኮንትራት እስከ 2011 ድረስ አገልግለዋል።

ከ1968 ጀምሮ የያኔውን መብራት ኃይል ያሁኑን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብን በታማኝነት ሲደግፉ የኖሩት አቶ በቀለ ‘በቀለ ኮረንቲ’ በሚል ቅፅል እስከመጠራት ደርሰዋል። የሚወዱት ክለባቸው እስከዘጠናዎቹ አጋማሽ በነበረው የከፍታ ዘመን ዘወትር ከማይጠፉበት የአዲስ አበባ ስታድየም ምስማር ተራ የቀኝ ወገን ሆነው የክለባቸውን ደስታ ሲጋሩ ኖረዋል። በቀጣይ ዓመታት ክለቡ እየተዳከመ ሲሄድ እና በርካታ ደጋፊዎቹን ሲያጣም ቀይ ለባሹ ታላቅ ሰው ግን ከቦታቸው አልተንቀሳቀሱም። የሚወዱት ክለባቸው ከዋናው ሊግ ወርዶ በከፍተኛ ሊጉ ለመወዳደር ሲገደድም እንደቀድሞው ወደ ክፍለ ሀገር ለመሄድ የጤናቸው ሁኔታ ባይፈቅድም በአዲስ አበባ በተጫወተ ቁጥር ግን ድጋፋቸውን አላቋረጡም።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ የከፍታ እና የዝቅታ ዘመን በድጋፍ የኖሩት በቀለ ኮረንቲ ክለቡን በተለያየ ኮሚቴዎች ውስጥ ሆነው የበኩላቸውን በማድረግም ያገለገሉ ሲሆን ለእግርኳስ እና ለሀገራቸው ባላቸውም ፍቅር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመሄድ ጭምር ደግፈዋል። ከስፖርት ፍቃራቸው ባልተናነሰ በማህበራዊ እና በመንፈሳዊ ህይወታቸው እጅግ የተመሰገኑ የነበሩት አቶ በቀለ ሄኒ ካደረባቸው ህመም ጋር በብርታት ሲታገሉ ቆይተው መስከረም 17 ቀን 2013 በተወለዱ በ71 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። አቶ በቀለ የአራት ወንዶች እና የአራት ሴት ልጄች አባት የነበሩ ሲሆን በስምንት የልጅ ልጆችም ተባርከዋል።

ዛሬ ረፋድ 09፡00 ላይ ወደጃ ዘመዶቻቸው እንዲሁም የኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እና በርካታ የስፖርት ቤተሰብ በተገኘበት በሳሪስ አቦ ቤተክርስቲያን የቀብር ሥነ- ስርዓታቸው ተፈፅሟል።

የሶከር ኢትዮጵያ ድረ ገፅ ባልደረቦች በአንጋፋው ደጋፊ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን በመግለፅ ለቤተሰቦቻቸው ፣ ለወዳጆቻቸው እና ለዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛሉ።

ነፍስ ይማር ኮረንቲ!

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!