የሴቶች ገፅ | ቆይታ ከረድኤት አስረሳኸኝ ጋር…

በሴቶች እግርኳስ በጥሩ አጥቂነታቸው ከሚጠቀሱ ወጣቶች መካከል አንዷ የሆነችው ረድኤት አስረሳኸኝ የዛሬው የሴቶች ገፅ እንግዳ ነች፡፡

ትውልድ እና ዕድገቷ በዱራሜ ከተማ የሆነው ተጫዋቿ የመጫወት ህልሟ የጀመረው ከ2003 ጀምሮ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተጫዋች በሰፈር ውስጥ በመጫወት ሲሆን ከነበራት ፈጣን እድገት አኳያ በቶሎ በትውልድ ቀዬዋ በሚገኝ ፕሮጀክት ታቅፋ የታዳጊነት የስልጠና ዓለምን ተቀላቅላ መጫወት ጀመረች። ለዱራሜ ከተማ፣ ለከምባታ ጠምባሮ ዞን አልፎም ደግሞ ለደቡብ ክልል በተለያየ የዕድሜ ዕርከኖቾ ተሰልፋ ተጫውታለች፡፡

ደቡብ ክልልን ወክላ በመጫወት ላይ እያለች 2008 ደደቢትን ተቀላቅላ በፕሪምየር ሊጉ ላይ ብቅ ያለች ቢሆንም ልምድ አልባ ስለነበረች ብዙም ጎልታ መውጣት ባለመቻሏ 2009 ወደ ሲዳማ ቡና አምርታ የሁለት አመት ቆይታን ካደረገች በኃላ ግን መልካም እንቅስቃሴን ማሳየቷ በብዙ ክለቦች ዓይን ውስጥ መግባት ቻለች። በ2011 ጌዲኦ ዲላን ከተቀላቀለች በኃላ በሊጉ ግቦችን በማስቆጠር ለቡድኗ የፊት መስመር መጠናከር የነበራት አስተዋጽኦ እጅጉን ላቅ ያለ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ተጫዋቿ በአሰልጣኝ ፍሬው ሀይለገብርኤል ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጠርታ ኢትዮጵያ ብሩንዲን 5ለ1 በሆነ ውጤት ስትረታ ሁለት ግሩም ግቦችን አስቆጥራ የነበረችው አጥቂዋ ረድኤት አስረሳኸኝ አዝናኝ ጥያቄዎችን ባቀፈው የሴቶች ገፅ የዛሬ መሰናዶ እንግዳ ናት፡፡

እግር ኳስ ተጫዋች ለመሆንሽ አርዓያ ያደረግሻት ማናት/ች?

ሎዛ አበራ ነች። ያው የአንድ አካባቢ ልጆች ስለነበርን በደንብ ማያት የነበረው እሷን ነው፡፡አብረንም ሰርተናል፤ ደደቢት ብዙም ተጫወትኩ ብዬ ባለምንም አንድ ላይ ተጫውተናል። በሷ ላይ በማየው ነገር ነገር ነው አርዓያዬ ያደረኳት፡፡

የእግር ኳስ ውድድሮች በኮቪድ 19 ምክንያት ተቋርጠዋል። ከተቋረጠ በኃላ ወቅቱን እንዴት ነበር ስታሳልፊው የነበረው ?

ጊዜዬን እያሳለፍኩ የነበረው ቤተሰቦቼን በመርዳት፣ አንዳንድ ሥራዎችን በማገዝ እና በተወሰነ መልኩ ባለኝ ትርፍ ሰዓት ልምምዶችን እሰራለሁ። በተጨማሪ ቤተክርስቲያን በመሄድ ነበር ጊዜዬን ሳሳልፍ የነበረው፡፡

ረድኤት እግር ኳስ ተጫዋች ባትሆን ኖሮ በምን ሞያ ላይ እናገኛት ነበር ?

በትምህርት በርትቼ የሆነ ሥራ ላይ እገኝ ነበር፡፡ከዚህ ውጪ የተለየ ነገር አይኖረኝም። ምክንያቱም ለትምህርት ያለኝ ነገር በጣም ጥሩ ነው፡፡ አሁን ላይ ባልማርም ያኔ ብቀጥል ጥሩ ቦታ እደርስ ነበር፡፡ አሁንም አይቀርም፤ ጎን ለጎን አድርጌ ማሳካት እችላለሁ፡፡

ጥሩ ዓመትን በግሌ አሳልፌበታለሁ የምትይው መቼ ነው ?

ባለፈው ዓመት 2012 ኮሮና እስኪገባ ድረስ ጥሩ ዓመትን እያሳለፍኩ ነበር፡፡ ባለሁበት ቡድን ውስጥ በብዙ ነገር ስኬታማ ነበርኩ። ጎልም በማስቆጠር ለቡድኑም ውጤት በማስገኝት በብሔራዊ ቡድንም በነበረኝ አቋም የተነሳ የኔ ጥሩ ዓመት እና ጊዜን ነበር እያሳለፍኩ የነበረው፡፡

አብሬያት ብጣመር እና ብጫወት ደስ ይለኛል ብለሽ የምታስቢያት ተጫዋች ማን ትሆን ?

አብሪያት ብጫወት ደስ የሚለኝ፤ አሁንም አብሪያት እየተጫወትኩኝ ነው፡፡ ሁለት ዓመት አብረን ተጫውተናል አብረን ስንጫወት ከእኔ ጋር ባላት ነገር ነው ጥሩ ነገር ነው የምመርጣት። እፀገት ግርማ ትባላለች፤ ጌዲኦ ዲላ ውስጥ ስትጫወት አራት ዓመቷ ነው። በክለብ በብሔራዊ ቡድንም አብረን ነበርን። ይሄን ይሄን ከማየት የምመርጣት እሷን ብቻ ናት፡፡

በተቃራኒው ስትገጥሚያት የምትከብድሽ ተጫዋች አለች ?

የምትከብደኝ ተጫዋች የለችም !

በእግር ኳሱ ደስተኛ የሆንሽበት መቼ ነው ?

ወደ ክለብ ህይወት ከተቀላቀልኩ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ፈጣሪ ይመስገን፡፡ባለው ነገርም አሁንም ደስተኛ ነኝ። ብዙም የተከፋሁበትም ሆነ ያሳዘነኝ ነገር ስለሌለ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

በእግርኳስ ውስጥ ካሉ ሰዎች መካከል የቅርብ ጓደኛሽ ወይንም የሚስጥርሽ ተካፋይ ማነው/ማናት ?

በጣም የምቀርበው ጓደኛ የለኝም። ከሁሉም ጋር እግባባለሁ። ቅርብ ጊዜ ላይ ያገኘዋት ሚስጥሬን ማካፍላት ግን አብራኝ የምትጫወተው ፋሲካ በቀለ ናት፡፡

ረድኤት ሰዎች የማያውቁት የተደበቀ ሊታወቅልኝ ይገባል የምትይው ባህሪ አለሽ? እስቲ አጫውቺኝ ?

የተለየ ድብቅ ባህሪ የለኝም። ብዙዎች እንደሚያውቁት ከሜዳ ውጪ ዝምተኛ ነኝ። ብዙ መናገር አልወድም። ሜዳ ውስጥ ደግሞ ግዴታ መናደድ መበሳጨት አለ። ይሄ ሁሉ ነገር አለ። እኔ ለምሳሌ ሜዳ ውስጥ በጣም እናደዳለሁ፡፡

ከእግር ኳስ ውጪ በምን ጊዜሽን ታሳልፊያለሽ? ምንስ ያዝናናሻል ?

በትርፍ ጊዜዬ የሚያዝናናኝ ማንበብ እና ረጅም ጉዞን ማለትም ወክ ማድረግ እና እግርኳሶችን ማየት ያዝናኑኛል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!