ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ከዚህ ቀደም ውል የሚፈርሙበት ቅፅ ተቀየረ

ክለቦች ከዚህ ቀደም ተጫዋቾችን እና አሰልጣኞችን ውል የሚያስፈርሙበት ቅፅ እና አሰራር መቀየሩን ለማወቅ ችለናል።

ለበርካታ ዓመታት ክለቦች በፌዴሬሽኑ የተዘጋጀና በየጊዜው ኮፒ እና ፕሪንት እያደረጉ ተጫዋቾችን እና አሰልጣኞችን ሲያስፈርሙበት የነበረው የውል መፈራረሚያ ቅፅ ለውጥ ተደርጎበት ፌዴሬሽኑ በተለየ መንገድ ለክለቦች በሽያጭ መልክ አቅርቦ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ አገልግሎት ላይ ውሏል።

የፌዴሬሽኑ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ይህ ቅፅ የራሱ መለያ ኮድ እና ማህተም ያለው በመሆኑ ክለቦች እስከ አሁን ሲያስፈርሙበት የነበረውን ውል ቀደው በአዲስ መልክ ብቻ ማስፈረም ይኖርባቸዋል። አዲሱ ውል አንዱ ገፅ በ50 ብር የሚሸጥ ሲሆን በድምሩ ለአንድ ተጫዋች የሚያስፈልገው የመፈራረሚያ ቅፅ ብዛት አራት በመሆኑ እስከ 200 ድረስ እያወጡ በመግዛት በአዲሱ ውል ተጫዋቾችን ማስፈረም ጀምረዋል፡፡

ከዓርብ መስከረም 15 ዓርብ ጀምሮ በርካታ ተጫዋቾች ፌዴሬሽን በመገኘት በአዲሱ ውል መሠረት እየተገለገሉ ሲሆን ማንኛውም ክለብ ወደ ፌዴሬሽን ሲመጣ አገልግሎት ለማግኘት ለተጫዋቾቹ የ2012 ደሞዛቸውን ሙሉ በሙሉ ደመወዝ ከፍሎ ማጠናቀቁን የሚያሳይ የማረጋገጫ ደብዳቤ አብሮ ይዞ መምጣት እንዳለበት አቶ ባህሩ አሳስበዋል፡፡

በአዲሱ ውል ክለቦች ተጫዋቾችን ካስፈረሙ በኃላ የፈረሙበት የውል ዝርዝር ወደ ኦንላይን በመቀየር (TMS) በተባለው የዝውውር ሲስተም ውስጥ እንዲገባ የሚደረግ ሲሆን የተጫዋቾቹ መታወቂያ ተያይዞ በኮምፒውተር ሲስተሙ እንደሚገባም ነግረውናል፡፡ በተለይ ለውጪ ሀገር ተጫዋቾች ደመወዝ ያልፈፀሙ ክለቦች ይህ ሲስተም በቀጥታ ከፊፋ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ እንደማይስተናገዱም ለድረ-ገፃችን ተናግረዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!