የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ለሀገራችን አሰልጣኞች በቅድመ ውድድር ዝግጅት እና ተያያዥነት ባላቸው እግርኳሳዊ ሀሳቦች ዙርያ ስልጠና የሰጡ ሲሆን ሰፊ ውይይትም ተደርጎበታል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ከገባ ጊዜ ጀምሮ ሀገራዊ የእግር ኳስ ውድድሮች በመቋረጣቸው እና ሁሉም አሰልጣኞች በየቤታቸው በመሆናቸው የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር እና የፊፋ የፊትነስ ኤክስፐርት አብርሀም መብራቱ አሜሪካ ከሚገኘው አሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታሁን ጋር በማዘጋጀት እንዲሰጥ ማድረግ ከጀመሩ ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡ በዛሬው ዕለትም በቅድመ ዝግጅት ወቅት የክለብ አሰልጣኞች ሊከተሉት ስለሚገባ የዝግጅት እቅድ ትግበራ እና የስልጠና ሒደት ላይ ያተኮረ ስልጠና እንግዳ በመጋበዝ እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
ዛሬ 12፡30 የጀመረው እና ከሁለት ሰዓታት በላይ የፈጀውን ስልጠና የሰጡት የ63 ዓመቱ ፓርቹጋላዊ አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ የመግቢያ ንግግርን አድርገዋል፡፡ በንግግራቸው “ኢትዮጵያ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ጥሩ ቆይታን ያደረኩ ያህል ይሰማኛል። በጣም ደስ የሚሉ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ያሉበትን ሀገር አሰልጥኜ በማለፌ እጅጉን ደስ ብሎኛል። አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የጀመረውን ሥራ ሳይጨርስ በመነሳቱ ቅር ቢለኝም አሁን ለተሾመው አሰልጣኝ ውበቱ መልካም ምኞቴን መግለፅ እፈልጋለሁ።” በማለት ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ አሰልጣኙ በመቀጠል በያዙባቸው ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ እንዲሁም ክለቦች በቅድመ ውድድር ዝግጅት ወቅት ሲሰሩ የነበሩትን የልምምድ መርሀ ግብር እና መሰል ጉዳዮች ለሀገራችን አሰልጣኞች በቅድሚያ በተሞክሮ መልክ ገለፃን ካደረጉ በኃላ ወደ ዛሬው የውይይት ርዕስ በስፋት በመግባት አብራርተዋል፡፡
አሰልጣኙ በተለይ በቅድመ ውድድር ወቅት አፍሪካ ውስጥ ያሉ ክለቦች ከዝግጅት አንፃር ደካማ በመሆናቸው ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች በንቃት በዚህ ረገድ መሥራት እኖዳለባቸው ገልፀው በጊዜ ተከፋፍለው ሊሰሩ ስለሚገባቸው መርሀ ግብሮችም አስረድተዋል፡፡ ዝግጅት የውድድር መጀመሪያም መጨረሻም ስለሆነ በተለይ በዚህ የኮሮና ወቅት በትጋት መሥራት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኙ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን ካነሱ በኃላ ተካፋይ የነበሩ አሰልጣኞች ጥያቄ በማቅረብ በስፋት ማብራሪያን ከመልስ ጋር ከተጋባዡ እንግዳ አግኝተዋል፡፡
የዚህ ውይይት አዘጋጅ ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ አዲስ ለተሾሙት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በዙም ቪዲዮ ውይይቱ ላይ “እንኳን ደስ አለህ፤ መልካም የውጤት ጊዜ እንዲኖርህ እመኛለሁ፤ በርታ ለማለት እፈልጋለሁ። እኔም ከጎንህ ነኝ። ሁላችሁም ኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች ልታግዙት ይገባል።” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው ምስጋና አቅርበው ከሁሉም አሰልጣኞች እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!