አስተያየት | ወጣት አሰልጣኞች እና መዳረሻችን

የአስኮ እግርኳስ ፕሮጀክት አምና-በ2012 ከተመሰረተ ሃያኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡ መቼም ለአሰልጣኞቹ የሥልጠናው ጉዞ አታካችነት አያጠያይቅም፡፡ የባለሙያው አካልና አዕምሮ ይዝላል፤ አድካሚነቱ ስለሚበዛ ትዕግስትን ይፈታተናል፡፡ የታዳጊዎቹን ያልተገራና አስቸጋሪ ባሕርይ ማረቅ በራሱ ከባድ ኃላፊነት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የፕሮጀክቱ አሰልጣኞች ቡድን አባል መሆን ከሚሰጠው ሙያዊ እርካታ ይልቅ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ይበልጣል፡፡ በእንዲህ አይነቱ ሥራ መሰማራት ከፍተኛ ጽናት ይጠይቃል፡፡ በሜዳ ችግር፣ በገንዘብ  እጦት፣ በልምምድ መሥሪያ ቁሳቁሶች እጥረት እና በሌሎች ቁጥር-ሥፍር የሌላቸው ተግዳሮቶች ሳቢያ ረዘም ላለ ጊዜ የሥልጠናው አካል መሆን ይከብዳል፡፡ ታዳጊዎችን አሰልጥኖ ትልቅ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ዘመናዊ፣ አበረታችና ተስፋ የሚጣልበት የዝውውር ሥርዓት ባለመኖሩ የተለፋቸባው ሰልጣኞች በሚፈለገው ልክና ደረጃ ሲያድጉ አይታይም፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ሃያ ዓመታት ከላይ የጠቃቀስኳቸው ችግሮች ሳይበግሩን-ፍላጎታችንም ሳይወርድ ይኸው አሁንም እየሰራን እንገኛለን፡፡ በእርግጥ ይህ ፕሮጀክት በስራ በቆባቸው ጊዜያት በሁለቱም ጾታዎች በርካታ ታዳጊዎችን ማሰልጠን ችሏል፡፡ ከአንድ መቶ ሰላሳ በላይ ታዳጊዎችንም ለተለያዩ ክለቦች አበርክቷል፡፡ዘካሪያስ ቱጂ፣ በኋይሉ ተሻገር፣ ባህሩ ነጋሽ፣ ዮናታን ብርሃነ፣ አዲስ ፍስሃ፣ ፍቃዱ ደነቀ፣ ሚካኤል በየነ፣ ተዘራ ጌታቸው፣ መሰሉ አበራ እና ሙሴ ከበላ የመሳሰሉት ተጫዋቾች ከአስኮው ፕሮጀክት ከወጡትና በሃገሪቱ የእግርኳስ የሊግ ውድድሮች  በተለያዩ እርከኖች በሚገኙ ክለቦች ውስጥ መጫወት ከቻሉት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በዚሁ ፕሮጀክት የታዳጊዎች ስልጠና ለበርካታ ዓመታት የቀየን አሰልጣኞች ከእኛ አቅም በላይ በሆነ ምክንያት ለሃገራችን እግርኳስ ጎልቶ የሚጠቀስ አስተዋፅኦ ማበርከት ባንችልም ጥቂት ለማይባሉ ወጣቶች ኳስ ተጫዋች የመሆን እድል በመፍጠራችን እና በህይወታቸው ላይ በበጎ መልኩ የሚታይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳደራችን ያስደስተናል፡፡

ታዳጊዎችን በእግርኳስ ማሳተፍ ቀዳሚ ዓላማው ተተኪ ተጫዋቾችን ማፍራት ቢሆንም ፋይዳው ከዚህም ላቅ ያለ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በስልጠናው የሚሳተፉ ታዳጊዎች ጤናማ ይሆናሉ፤ አካላዊ እና አዕምሯዊ ጥንካሬ ይኖራቸዋል፤ ከተለያዩ ሱሶች ይጠበቃሉ፤ ብቁና አምራች የሆኑ ዜጎች ይወጣቸዋል፡፡ ከዚህም ላቅ ካለ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርሱ እግርኳሰኞች ሆነው  ህልማቸውን ለመኖር ይታደላሉ፡፡ በሃገራችን የተለያዩ ክለቦች የመጫወት እድልም ያገኛሉ፡፡  እነዚህ ታዳጊዎች በአግባቡ በተወጠነ መርኃግብር እንዲሁም ደረጃውን በጠበቀ ጥራት ያለው ሥልጠና ቢሰለጥኑ የተሻለ ቦታ ይደርሳሉ፡፡ በእኛ አቅም በሚፈለገው ስነ-ምግባር ታንጸው በእግርኳሱ ባይሳካላቸው እንኳ በሌላኛው የህይወት መስመራቸው የተሻለ ዜጋ እንዲሆኑ ለመርዳት በመጣር ግለሰባዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ማህበረሰባዊ ከፍ ሲልም ሃገራዊ ስሜታቸው እንዲጎለብት እንጥራለን፡፡

ልፋታችን ፍሬ አፍርቶ-ሰልጣኞቹም ተሳክቶላቸው አልያም እድል ቀንቷቸው በትልቅ ደረጃ እግርኳስን ከሚጫወቱት ባሻገር በትምህርታቸው እና በተለያዩ ሞያዎች ውጤታማ የሆኑትን ስናይ እንደሰታለን፡፡ ጊዜያችን እና ጉልበታችን መክኖ እንዳልቀረ እንረዳለን፤ የበለጠ ለመሥራትም እንነሳሳለን፡፡ ይሁን እንጂ ከመንግስትም ይሁን ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የእግርኳሱ አካላት የሚደረግ የተለየ አበረታች ድጋፍ አናገኝም፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ በየሰፈሩ እና በየፕሮጀክቱ ያለው የወጣት አሰልጣኞች አበርክቶት ተመልካች የለውም፡፡ እኛም የዚሁ ችግር ሰለባ ነን፡፡ እግርኳሱን የሚመለከተው የመንግስት መሥሪያ ቤት በግላቸው ለሚንቀሳቀሱ የታዳጊ ማሰልጠኛዎች ተገቢውን ክትትልና አስፈላጊውን ድጋፍ አያደርግም ብሎ መናገር ድፍረት ነው ብዬ አላምንም፡፡ ለብዙሃን መገናኛዎች የዜና ፍጆታ የሚውሉ ጊዜያዊ ጉብኝቶች ካልሆኑ በስተቀር ለስልጠና አካዳሚዎቹም ሆነ ለፕሮጀክቱ ትኩረት አይቸርም፡፡ ያለመታደል ሆኖ እነዚህን ማሰልጠኛ ማዕከላት የሚያስተባብርና የላቀ ሚና እንዲጫወቱ የሚያግዝ እግርኳሳዊ የአመራር መዋቅር ባለመዘርጋቱ አብሮ የመሥራት ባህል ሳናዳብር የፕሮጀክቶቹ ዘላቂ ህልውና አጠያያቂ እየሆነ ሄዷል፡፡ የእግርኳሳችን አስተዳደራዊ ከባቢ በብልሹ እና ኋላ-ቀር አሰራር ተተብትቦ ጥልቅ ፍላጎት፣ የተሻለ እውቀትና በቂ ተመክሮ ያለን በየሰፈሩ የምንገኝ ወጣት አሰልጣኞች ሃገራዊ እገዛ እንደናፈቀን አለን፡፡ የአስኮ እግርኳስ ፕሮጀክትም ይሁን ሌሎች በግል የሚንቀሳቀሱ የታዳጊ ተጫዋቾች ማሰልጠኛ ማዕከላት ዞር ብሎ የሚያየን አጥተናል፡፡

እኔ የምሰራበትን የአስኮ ፕሮጀክት የስፓርት ኮሚሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው የሚሾሙ ባለስልጣናት በየጊዜው ይጎበኙታል፡፡ ትልልቅ አሰልጣኞች እና የስፖርት ጋዜጠኞችም በተደጋጋሚ መጥተው የምንሰራውን አይተዋል፡፡ የአስኮ እግርኳስ ፕሮጀክት ባለፉት ሃያ ዓመታት ያለመታከት ታዳጊዎች ላይ ሲሰራ በእግርኳሱ ባለስልጣናት የተገባለት “ቃል” እጅግ ብዙ ነው፡፡ በእግርኳስ አመራሩ አካላት የሚገቡት የድጋፍ “ቃሎች” ተስፋ ከመሆን የዘለሉ አልነበሩም፡፡ አሁን ደግሞ ተስፋ መሆናቸውም ደብዝዟል፡፡ ቀድሞ ቃሎቹ ተፈጻሚ የሚሆኑ እየመሰለን እንተጋ ነበር፡፡ እግርኳሳችንን ለማሳደግ የተቻለንን ያህል ጥረን፣ ምንያህል ትጉህ እንደሆንን ያለንን አቅም አሳይተን፣ ሰልጣኞቻችን አድገውና ለሃገሪቱ የእግርኳስ ደረጃ ብቁ ተጫዋቾች ማፍራት ችለን ለዘለቄታው
“አይዟችሁ! ከጎናችሁ ነን!” የሚለን ማጣታችን እንቆቅልሽ ሆኖብናል፡፡ ነገሩን ስናሰላስለው ግርም ይለናል፡፡ በእርግጥ ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱን ጨምሮ ሌሎች አሰልጣኞችም የፕሮጀክቱ ተጫዋቾች ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያሳዩ ተመለክተው ያውቃሉ፡፡  እነዚያን የያዩአቸውንና የተደነቁባቸውን ታዳጊዎች “የት ደረሱ?” ብለው አለመጠየቃቸው ግን አሳዝኖናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ክለቦች እየተጫወቱ ካሉ ተጫዋቾች ያልተናነሰ ችሎታ ይዘው በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በተንሰራፋው ብልሹ አሰራር፣ ሙስና፣ ደካማ የስልጠና “ሲስተም” እና ወጥ ያልሆነ የተጫዋቾች አያያዝ ምክንያት በእኛው “እግርኳስ” ስኬታማ ሳይሆኑ ተስፋ ቆርጠው ጨዋታውን የሙሉ ጊዜ ሥራ ለማድረግ መትጋት ያቆሙ ወጣቶች ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ እግርኳሱን እርግፍ አድርገው ትተው በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተው ህይወታቸውን ከሚመሩት ውጪ  ትልቅ ተስፋ በጣሉበትና ድንቅ ተስጥኦ በታደሉበት ስፖርት “ውጤታማ” መሆን ሲሳናቸው በሕይወታቸው ጭምር ተስፋ አጥተው የተለያዩ ሱሶች ተገዢ ሆነው ኑሯቸውን እየገፉ የሚገኙም አሉ፡፡

ታዳጊና ወጣት ተጫዋቾች ላይ ለረጅም ጊዜ ለሰራ አሰልጣኝ ልዩ ተስጥኦ የነበራቸው፣ “የት ይደርሳሉ!” የተባሉ፣ እምቅ አቅም የታደሉና በተስፋ የሞላናቸው ተጫዋቾች በእግርኳሳችን በተለይም በክለቦቻችን ተገቢው ትኩረት ሲነፈጋቸው፣ በደካማ ስልጠና እና በወረደ የተጫዋቾች አያያዝ የተነሳ በሰፈር ቀርተው ከማየት በላይ የሚያሳምም ነገር የለም፡፡ ይህንን ስል በራሳቸው ስንፍና እግርኳስ ያቆሙ የሉም እያልኩኝ አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ ብዙ ሰዎች ያገኙትን ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው በኢትዮጵያ ቡና እየተጫወቱ ስላሉት አቡበከር ናስርና ሚኪያስ መኮንን ወይም ሌሎች መሰል ተጫዋቾች ያወራል፡፡ ከእነርሱ ያልተናነሰ አቅም ኖሯቸውና በታዳጊ ፕሮጀክቶች ሰልጥነው ሰፈር የቀሩ ተጫዋቾች እንዳሉ ማንም አያስብም፡፡ ምንም እንኳ የክለቦቻችን መጠን አናሳ መሆን ችግሮቹን ለማባባስ ቁልፍ ሚና ቢኖራቸውም ባሉን ክለቦች የዘረጋነው የምልመላ መስፈርት ጤናማ ባለመሆኑ ታዳጊ ተጫዋቾች በቂ እድል እንዳያገኙ አስገድዷል፡፡

መንግሥት ግን ወደ እግርኳሳችን ዞር የሚለው መቼ ይሆን? በስፖርት ኮሚሽን፣ በፌዴሬሽን እና በክለቦች የመሪነት ኃላፊነት ከተጣለባችሁ ሰዎች አንዳንዶቻችሁ ለእግርኳሱ ምንም ራዕይ ያልሰነቃችሁ፣ ለቦታው የሚመጥን እውቀት የሌላችሁ፣ ሥራውን በትጋት ለመሥራት ያልተዘጋጃችሁ፣….. በእናንተ የአመራር ድክመት ትውልድ እየተጎዳ እንደሆነ የምትረዱት መቼ ነው? አሁን-አሁን ደግሞ ለመኖር ብላችሁ ጽዩፍ በሆኑ ተግባራት የምትሳተፉ አንዳንድ አሰልጣኞችስ ነገ ላይ “…አሰልጥነው ነበር።”  ከሚል የዘለለ ኗሪ ታሪክ እንደማይኖራችሁ የምትረዱት መቼ ነው?

ታዳጊ ፕሮጀክቶች ላይ ለምንሰራ አሰልጣኞችም ችግሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ ብዙ መስዋዕትነት በከፈልንበት ሙያ ራሳችንን በትምህርትና በልምድ እያሳደግን የሃገራችን እግርኳስ ላይ በትልቅ ደረጃ የመሳተፍ ፍላጎትና እምቅ አቅም ቢኖረንም መንገዱ በተለያየ ምክንያት እየተዘጋ አሁን እየታየን ያለው ጭላንችል ተስፋ ብቻ ሆኗል፡፡ እርግጥ ነው ታዳጊ ላይ የሰራ አሰልጣኝ ሁሉ በትልቅ ደረጃ ያሰለጥናል ማለት አይደለም፡፡ አንዳንዶቻችን ግን ታዳጊዎችን ከማሰልጠን ባሻገር ትልልቆቹ ተጫዋቾች ላይም የመስራት እውቀትና ብቃት እንዳለን ሊታወቅ ይገባል፡፡

ያሰለጠንናቸው ታዳጊ ተጫዋቾች የሚፈለገው ቦታ አለመድረሳቸው እና ፕሮጀክቱም አንድ እርምጃ ወደፊት ፈቅ አለማለቱ እጅጉን ያሳስበናል፡፡  በአጠቃላይ የሃገራችን እግርኳስ እንዲያድግ ጠንካራ ስራ አለመሰራቱ እንዳለ ሆኖ ታዳጊ ላይ ለምንሰራ አሰልጣኞች በተለያዩ እርከኖች በሚወዳደሩ ክለቦች የማሰልጠን እድሉን አለማግኘታችን በስልጠናው መስክ እንድናድግ የሚያደርግ አሰራር አለመዘርጋቱን ያሳየናል፡፡ ይህን ሁሉ ዓመት ሰርተንና በሚቻለን አቅም በግል ጥረት እውቀታችንን ለማሳደግ ለፍተን ገና የማንወጣው የሚመስል ሌላ ተራራ ከፊታችን አስቀምጦልናል፡፡

ለ”Merit” ቦታ የሌለው የሃገራችን የእግርኳስ አሰልጣኝነት መመዘኛ ሌሎች መስፈርቶችን በማስቀደም ብዙዎችን የሚገፋ ጥቂቶችን ደግሞ የሚጠቅም አሰራር ዘርግቷል፡፡ ለዚህ ወቀሳዬ እኔ በግሌ ከገጠሙኝ ችግሮች አንዱን ላንሳ፡፡ ለሁለት ጊዜያት ያህል በክለቦች የታዳጊ ቡድን የማሰልጠን ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ ሁለተኛውን እድል የሰጠኝ በምሰራበት ፕሮጀክት ለአምስት ዓመታት ያህል ካሰለጥንኳቸው ታዳጊዎች ዘጠኙን የወሰደው ክለብ ነው፡፡ ተጫዋቾቹን ካስመረጥኩኝ በኋላ ክለቡን እኔ እንድረከበው ተፈለገና ተመረጥኩኝ፡፡ ከተጫዋቾቹ ምርጫ በኋላ በወቅቱ ከነበረው የክለቡ ቴክኒክ ዳይሬክተር ጋር ቅጥር ለመፈፀም ከተስማማን በኋላ “በክለባችን ተጫውተው ስራ የሌላቸው ሰዎች እያሉ ሌላ አሰልጣኝ አይቀጠርም፡፡” የሚል ሐሳብ ተቀባይነት አገኘ፡፡ የእኔም ቅጥር ሳይሳካ ቀረ፡፡ ገጠመኙ በጣም የሚያሳዝንና በታዳጊዎች ላይ ውጤታማ ስራ እየሰራ ላለ ወጣት አሰልጣኝ ቅስም ሰባሪ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የአሰልጣኞች የቅጥር ሁኔታዎችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክለቦቻችን ደጋግመን እያየን ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ ተጫውተው ያለፉ ዕድሉ ሊሰጣቸው የተገቡ ቢሆኑም አንዳንዶቹ ግን ከእግርኳስ ከራቁ ሰንበትብት ያሉና የዘመናዊ እግርኳስ ስልጠና ምን ደረጃ እንደደረሰ የማያውቁ ነበሩ፡፡ በዚህም ሳቢያ በእነርሱ ምክንያት የብዙ ታዳጊ ተጫዋቾች ህይወት ችግር ውስጥ ሲወድቅና እምቅ አቅማቸውን መጠቀም ሲያቅታቸው ተመልክተናል፡፡ ምንም እንኳ ለአንዳንድ ተጫዋቾች በመጫወት ያገለገሉት ክለብ ውስጥ የማሰልጠን እድል መፍጠሩ ተገቢ ቢሆንም ቅጥሩ ግን የማሰልጠን ችሎታ እና ብቃትን መሰረት ያደረገ መሆን ይገባዋል፡፡ የተጫወተ ሁሉ ደግሞ አሰልጣኝ መሆን ስለማይችል ለሌሎች የስራ ዕድል ለማመቻቸት መሞከርም ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ለበሽተኛው እግርኳሳችን ባለመድሃኒት ሊሆኑ የሚችሉ ባለሞያዎችም ስላሉ በቀላሉ ተስፋ እንዳናስቆርጣቸው ማሰብም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

አሰልጣኝ ከመሆን በፊት በክለብ ተጫውቶ ማለፍን እንደ ትልቅ ቅድመ-መስፈርት የሚቆጥሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በስልጠናው ዓለም ያለን አንዳንዶቻችን ክለብ ያልተጫወትነው በተለያዩ ምክንያቶች እንጂ ኳስ ስለማንችል ብቻ እንዳልነበረም እነዚህ ወገኖች መረዳት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ለእግርኳስ ያለን ጥልቅ ፍቅር ማሰልጠንን ጥለን እንዳንወጣ ይዞን እንጂ ማሰልጠንን ሙጥኝ  ያልነው ስላልተማርን ወይም ሌላ የሥራ ዕድል ስለሌለን እንዳልሆነም መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ የሥልጠናው ዘርፍ ጥሩ የአሰራር መዋቅር (structure) መዘርጋት እስካልተቻለ ድረስ አሰልጣኞችም ሆነ ተጫዋቾች የሚመዘኑበት መንገድ አይታወቅም፡፡ ይህ የሚዘረጋው ዘመናዊ የአሰራር ሲስተም የሁሉንም ችሎታና ብቃት ባለሙያዎች ፍንትው አድርጎ እንዲያሳይ ማድረግ አለብን፡፡

ይህንን ማድረግ ካልቻልን እንደ እኔ ላለ ወጣት አሰልጣኝ የሃገሬን እግርኳስ አድጎ ማየት፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ተሳታፊ መሆን፣ ዛሬ ላይ እንደጉድ በምንጮህላቸው የአውሮፓ ክለቦች ውስጥ የሃገሬ ልጅ ሲጫወት መመልከት፣ እኔም በትልቅ መድረክ ማሰልጠን የምችልበት ዕድል ማግኘት የምመኘው እንጂ እውን ሳይሆን የሚያልፍ ሃሳብ ሆኖ ይቀራል፡፡    

በመግቢያዬ ያነሳሁት አስኮ እግርኳስ ፕሮጀክት በሃያ ዓመት ውስጥ በርካታ ታዳጊዎችን በማሰልጠን ሃገራዊ ግዴታውን ተወጥቷል፡፡ፕሮጀክቱ በስራ በቆየባቸው ዓመታት ውስጥ ማደግ ሲገባው በተለይም ከሚመለከታቸው እና በየደረጃው ካሉ የመንግስት አካላት ተገቢውን ድጋፍ ማግኘት ሳይችል የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት ችግር ውስጥ ይገኛል፡፡ ዛሬም ፕሮጀክቱ በማይመች ሜዳ ስልጠናውን ይሰጣል፡፡ በኳስና በአንዳንድ የመገልገያ ቁሶች እጥረት ይቸገራል፤ አሁንም ድረስ የሚሰራው በበጎ ፍቃድ አሰልጣኞችነው፡፡ የሚገርመው ለፍቶ ያሳደጋቸውን ባለክህሎት ታዳጊዎች ለክለቦች ለምኖ ይሰጣል፡፡ አጠቃላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ያለማደግ ችግር የብዙዎቻችንን ህልም “ህልም ብቻ!” አድርጎብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያላችሁ የስፓርት አመራሮችና የፌዴሬሽን መሪዎች ተጠያቂ ከመሆን አትድኑም፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


ስለ ፀሐፊው

የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!