የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከዳዊት እስጢፋኖስ ጋር…

👉“በጣም ብቻ ሳይሆን ከሚገባው በላይ አይናፋር ነኝ”

👉”በዚህ ሰዓት ከሚገኙ የሃገራችን ተጫዋቾች ምርጡ ተጫዋች…”

👉”ከዚህ በፊትም ኳስ አቆማለሁ ብዬ የወሰንኩባቸው ጊዜያት ነበሩ”

👉”የግል ህይወት የሚባል ነገር የለኝም”

ባሌ የተወለደው የዛሬው እንግዳችን ዳዊት እስጢፋኖስ ሁለት ዓመት ሲሞላው ወደ መዲናችን አዲስ አበባ ተጉዞ ኑሮውን እንደጀመረ ይናገራል። እስጢፋኖስ አካባቢም እድገቱን አድርጎ ከቤተሰቦቹ ጋር ኑሮውን ቀጥሏል። እንደማንኛውም ታዳጊ በሰፈር ውስጥ ጨዋታዎች ላይ ኳስን ሲጫወት የነበረው ተጫዋቹ በተለይ እድገቱን ባደረገበት መስቀል አደባባይ ውሎውን በማድረግ እጅጉን ወደ እግርኳሱ እንደቀረበ ያወሳል። በዚህ የአስፋልት መጫወቻ ሥፍራ ላይ እየተጫወተ ባለበት ሰዓት በአሠልጣኝ ፀጋዬ በሚመራው የ4 ኪሎ ፕሮጀክት ቡድን ውስጥ በወላጅ አባቱ አማካኝነት እንዲታቀፍ ተደረገ። በዚህ ፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ራሱን እያጎለበተ በሚገኝበት ሰዓትም 1993 ላይ አዲስ አበባን ወክሎ በአዲስ አበባ ምርጥ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ተካቶ አዳማ ላይ በተደረገው ውድድር ላይ ተሳተፈ። በዚህ ውድድር ላይ የክለብ አሠልጣኞች እና መልማዮች ስለነበሩ ተጫዋቹን ለማስፈረም ጥያቄዎች ማጉረፍ ጀመሩ። ከመጡት በርካታ የእናስፈርምህ ጥያቄዎች መካከል ተጫዋቹ የባንኮች ቡድን አሠልጣኝ ይሁኔ ታዬን ጥያቄ ተቀብሎ በ1994 ለባንኮች ሦስተኛ ቡድን (C) ለመጫወት ተስማምቶ የእግርኳክ ህይወቱን ወደ ተሻለ ደረጃ አሸጋገረ። በዚህ የባንኮች የሲ (C) ቡድን ለአንድ ዓመት ከተጫወተ በኋላ በ1995 ወደ ተስፋ ቡድን አደገ። በሁለተኛ ቡድኑም ለሁለት ዓመታት ግልጋሎት ሰጥቶ 1997 ላይ ዋናውን የባንኮች ማሊያ ለብሶ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጫወት ጀመረ።

ለሦስት ዓመታት በባንኮች ቤት ከቆየ በኋላ ሚሌኒየሙ ላይ ቀጣይ ጉዞውን ወደ መከላከያ አደረገ። በጦሩ ቤት ለሁለት ዓመት ከግማሽ ከተጫወተ በኋላ ለግማሽ ዓመት በደደቢት አሳልፎ 2003 ላይ ብዙ ታሪኮችን ወደሰራበት ኢትዮጵያ ቡና አመራ። በመጀመሪያ ዓመት የክለቡ ቆይታም የሊጉን ዋንጫ አንስቶ በክለቡ ደጋፊዎች ልብ ውስጥ በቀላሉ መግባት ቻለ። በቡናማዎቹ ለአምስት ዓመታት የአቅሙን ሰጥቶ 2008 ላይ ወደ ምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል ድሬዳዋ መጫወት ያዘ። ለአንድ ዓመት በድሬዳዋ ቆይታውን ካደረገ በኋላም ዳግም ወደ መዲው ክለብ መብራት ሃይል በመምጣት በተመሳሳይ ለአንድ ተጫወተ። በቀጣዩ ዓመትም ወደ ጎንደር በማቅናት ለስድስት ወራት ዐፄዎቹን ከወከለ በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ መከላከያ በድጋሜ ተጓዘ። በመከላከያም ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ተጫውቶ አምና አዲሱን የሊጉን ክለብ ሰበታ ከተማን ተቀላቅሎ መጫወት ቀጠለ።

ዓምናን ጨምሮ ለ15 ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተጫወተው ዳዊት በክለብ እንዳለው ረጅም የእግርኳስ ህይወት በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የለውም። የሆነው ሆኖ ግን 1997 ላይ በባንኮች ዋና ቡድን ውስጥ መጫወት ሲጀምር ለመጀሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ወጣቶች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ እንዲካተት ተደርጎ ሃገሩን ማገልገል ጀመረ። በወጣት ብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ከቀረበለት ከሁለት ዓመታት በኋላም (2000) ለመጀመሪያ ጊዜ ዋናውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲያገለግል ጥሪ ቀረበለት። ከዛም በኋላ አልፎ አልፎ ብሔራዊ ቡድኑን ለማሰልጠን በሚመጡት አሠልጣኞች ጥሪ እየቀረበለት በስብስቡ መካተት ቀጠለ። 2013 ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው የቡድን ስብስብ ውስጥ የነበረው ተጫዋቹ 2006 ላይ በአሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ አማካኝነት ከተጠራ በኋላ ግን ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ዳግም መምጣት ሳይችል ቀርቷል።

በሚያሳያቸው የሜዳ ላይ ጥበቦች መነሻነት በታዋቂው እና ጥበበኛው ሰዓሊ ዳቪንቼ ስም ሲጠራ የሚሰማው ይህ ተጫዋች በዛሬው የዘመናችን ከዋክብት ገፅ ላይ እንግዳ አድርገነው አዝናኝ ጥያቄዎችን አቅርበንለታል።

የእግርኳስ አርዓያህ ማነው?

ያደኩበት ሰፈር ለአዲስ አበባ ስታዲየም ቅርብ ስለነበረ ብዙ ተጫዋቾችን የማየት እድሉን ሰጥቶኛል። በታዳጊነቴ በጣም በርካታ ጨዋታዎችን ስታዲየም እየተገኘሁ ተመልክቻለሁ። በጊዜው ደግሞ ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾች ነበሩ። አንዱን ወስደህ አንዱን አትተውም። ግን በወቅቱ አምስት ተጫዋቾች በግሌ ትልቅ ቦታ እሰጣቸው ነበር። ነብሱን ይማረው እና የአሠግድ ተስፋዬ፣ የኤሊያስ ጁዋር፣ የካሳዬ አራጌ፣ የትልቁ አንዋር እና የተክሌ ብርሃኔ አድናቂ ነበርኩ።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ ዳዊት ጊዜውን በምን እያሳለፈ ነው?

በህይወት ዘመኔ እንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ጊዜ አላጋጠመኝም። ስፖርተኛ እንደ ሌላው ማኅበረሰብ ቤት ቁጭ ብሎ መክረም አይችልም። ምክንያቱም ከእንቅስቃሴ መራቅ ስለሌለበት። እኔ በዚህ ጊዜ በጣም ጨንቆኝ ነበር። ወጥቼ ልምምድ ሰርቼ እንዳልመጣ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት ነኝ። መውጣት መግባት ካበዛሁ የእነሱ ነገር አደጋ ላይ ሊሆን ይችላል። ከዚህ መነሻነት እንደ ሌላው ጊዜ ስፖርት በደንብ ስሰራ አልነበረም። ይህንን ስል ግን ሙሉ ለሙሉ አርፌ ነበር ማለት አደለም። በአጠቃላይ ግን ሊጉ ከተቋረጠ በኋላ ቤት ውስጥ ነው ጊዜዬን ያሳለፍኩት። ቤት ውስጥም ከዚህ በፊት በደንብ ስሰጠው ያልነበረውን የቤተሰብ ፍቅር ለባለቤቴ እና ለልጆቼ እየሰጠሁ እንዲሁም የማላቃቸውን ነገሮች እያነበብኩ ራሴን በማብቃት ጊዜዬን አሳልፌያለሁ።

ኮሮና ከመጣ በኋላ አዲስ እየለመድክ ያለህው ልማድ አለ?

ብዙም አዲስ ነገር የለም። ግን በፊት አንባቢ ነገር ነበርኩ። ለምን እንደሆነ አላውቅም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይህንን ልማዴን አቁሜው ነበር። ኮቪድ-19 ከመጣ በኋላ ግን ይህንን የበፊት ልማዴን እንደ አዲስ ጀምሬያለሁ። በተለይ ከእግርኳሱ ጋር የተገናኙ መጽሐፍቶችን እና ትንታኔዎችን አነባለሁ።

ኮሮና አሁን ጠፍቷል ቢባል መጀመሪያ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው?

ከባድ ጥያቄ ነው። ብዙ ማድረግ የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ። ግን እኔ ዘመኔ በሙሉ ከኳስ ጋር ስለሆነ ያለፈው በመጀመሪያም ኳስ የምጫወት ይመስለኛል።

በግልህ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍክበት ዓመት መቼ ነው?

በግል ብዙ ጥሩ ዓመታቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን በዋንጫ የሚጠናቀቁ ሲኖሩ ደግሞ እነሱን ታስቀድማለህ። ከዚህ መነሻነት 2003 ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ዋንጫ ያነሳሁበት ጊዜ ጥሩ ስሜት ይሰጠኛል። ዓመቱ በግሌም ሆነ እንደ ቡድን ስኬታማ የሆንኩበት ነበር። ለእኔም ሆነ ለኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያውን እና ብቸኛውን የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ያገኘንበት ስለነበሬ ዓመቱ ጥሩ ነበር።

ዳዊት እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን በምን ሙያ እናገኘው ነበር?

እግርኳስ ተጫዋች ባልሆን እግርኳስ ተጫዋች ነበር የምሆነው (እየሳቀ)። የተፈጠርኩት ለኳስ ነው። ግን ምናልባት ኳስ ተጫዋች ባልሆን ዶክተር የምሆን ይመስለኛል። ሰውን መርዳት ትልቅ እርካታ ስለሚሰጠኝ ምናልባት ዶክተር ሆኜ በነጭ ጋውን እገኝ ነበር።

አብሬው ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለሁ የምትለው ተጫዋች አለ?

እኛ ሃገር ባለው ነገር ይህንን ጥያቄ መመለስ ከባድ ነው። ምክንያቱም ጨዋታዎችን በቴሌቪዥን ስለማትመለከት። በሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን አብዛኞቹን ተጫዋቾች የምታያቸው ስትገጥማቸው ነው። ያለበለዚያ ይህንን ለመመለስ አብረውህ የተጫወቱትን ብቻ ታሳቢ ታደርጋለህ። ከዚህ መነሻነት በኢትዮጵያ ቡና አምስት ዓመታት አምናም በሰበታ አብሮኝ የተጫወተውን መሱዑድ መሐመድ እመርጣለሁ። ከመሱዑድ ጋር መጫወት በጣም ድንቅ ነው።

እሺ በተቃራኒ ስትገጥመውስ የሚከብድህ ተጫዋች ይኖር ይሆን?

በተናጥል አንድ ተጫዋች የለም። ምናልባት እንደ ቡድን ግን ሊኖር ይችላል። አለበለዚያ ደግሞ ከሜዳዎች አለመመቸት ጋር ተያይዞ ከባድ ፈተናዎች ሊገጥሙህ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ በተናጥል የከበደኝ ተጫዋች እስላሁን አላገኘሁም።

በዚህ ሰዓት በሃገራችን ከሚገኙ ተጫዋቾች ያንተ ምርጡ ተጫዋች ማነው?

በዚህ ሰዓት ከሚገኙ የሃገራችን ተጫዋቾች ምርጡ ሱራፌል ዳኛቸው ነው።

ይህንኑ ጥያቄ ወደ አሠልጣኞች እንውሰደው። ከአሠልጣኞችስ?

አሠልጣኞችን ለማወዳደር ይከብዳል። አብረባቸው የሰራሃቸውን ብቻ ነው ታሳቢ የምታደርገው። መናገርም የምትችለው ስለእነሱ ነው። እና አብሬያቸው ከሰራኋቸው ውስጥ ደግሞ አሠልጣኝ ውበቱ አባተን አስበልጣለሁ። ከውበቱ ጋር ለረጅም ዓመታት አብረን ሰርተናል። ብቸኛውንም ዋንጫ በኢትዮጵያ ቡና ያገኘነው ከእርሱ ጋር ነው። አምናም በሰበታ አብረን እየሰራን ነው። ስለዚህ ለእኔ ምርጡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነው።

ቅፅል ስም አለህ?

በርከት ያሉ ቅፅል ስሞች ናቸው ያሉኝ። ብዙ የሚያውቁኝ ሰዎች ግን ዳቪንቼ ነው የሚሉኝ።

ለምንድን ነው ዳቪንቼ የተባልከው?

ይህንን ቅፅል ስም ያወጣልኝ ስንታየሁ ተፈሪ የሚባል ኳስ ወዳድ ነው። አሁን እንደውም ካናዳ ነው የሚገኘው። ኳስ ጥበብ ነው ብሎ ስለሚያስብ ከሰዓሊው ዳቪንቼ ጋር አገናኘኝ። በተጨማሪም ዳዊት ስለሆነ ስሜ ዳቪንቼ ወደሚለው ቀረበለት።

ከየትኛው የሊጉ ክለብ ጋር ስትጋጠም ነው ደስታ የሚሰማህ?

እንደማንኛውም ተጫዋች የደርቢ ጨዋታዎችን በጉጉት እጠብቃለሁ። በክለብ ህይወቴ ረጅሙን ጊዜ ያሳለፍኩት በኢትዮጵያ ቡና ቤት በመሆኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚደረገውን የደርቢ ጨዋታ በጉጉት እጠብቃለሁ።

እግርኳስ ካቆምክ በኋላ ምን ለመሆን ታስባለክ?

የእኔ ህይወት ከእግርኳስ ጋር የተገናኘ ነው። ወደፊትም ከዚህ ሙያ ይወጣል ብዬ አላስብም። በእስካሁኑ ህይወቴ ግን ብዙ የምቆጭባቸው ነገሮቸ አሉ። በዋናነት በሃገራችን ለቴክኒካል ተጫዋቾች የሚሰጠው ትኩረት ያበሳጨኛል። ስለዚህ እንደ እኔ አይነት ተጫዋቾችን ለማዳን ወደ ስልጠናው እገባለሁ።

ከዚህ በኋላ ዳዊት ለስንት ዓመታት እግርኳስ ይጫወታል?

ይህ ከባድ ጥያቄ ነው። ከዚህ በፊትም ኳስ አቆማለሁ ብዬ የወሰንኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። በተለይ ሃገሬን ማገልገል እየቻልኩ ባልተመረጥኩበት ጊዜ። ይህ ደግሞ ያበሳጨኝ እና ኳስ ለማቆም እንድወስን ያደርገኛል። ግን ውስጤ ያለው የኳስ ፍቅር ውሳኔዬን እየቀለበሰ ቆይቷል። አሁንም ከዚህ ዓመት በኋላ አቆማለሁ ማለት አልችልም። አሁንም ግን በውስጤ ጥሩ አቅም ስላለ በቶሎ ኳስ አላቆምም።

የግል ህይወትህ ምን ይመስላል?

የግል ህይወት የሚባል ነገር የለኝም (እየሳቀ)። ባለትዳር ነኝ። ስለዚህ የጋራ ሆኗል። የአንድ ወንድ እና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነኝ። አሁንም ከእነርሱ ጋር ነው እየኖርኩ የምገኘው።

ከባለቤትህ ጋር የተገናኛችሁበት አጋጣሚ አጫውተኝ እስኪ?

2008 ላይ ድሬዳዋን ስቀላቀል ነው ባለቤቴን ያገኘኋት። እሷ በወቅቱ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበረች። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ካፌ ውስጥ ነው የተገናኘነው። እየተራመደች እንቅፋት ሲመታት ተወርውሬ በማዳኔ ነው ግንኙነቱ የተጀመረው። እንደውም እሷን ካዳንኩ በኋላ ግብ ጠባቂ ሆኜ መጫወት ልጀምር እንዴ? ብዬ አስቤ ነበር (እየሳቀ)።

ዳዊት ምን የተለየ ባህሪ አለው?

ብዙ ሰዎች የማይቀበሉትን እና የማያምኑትን ነገር ልንገርህ። በጣም አይናፋር ነኝ። በጣም ብቻ ሳይሆን ከሚገባው በላይ አይናፋር ነኝ። ግን ይሄ ባህሪ ከሜዳ ውጪ ነው። ሜዳ ላይ ፍፁም የተለየሁ ሰው ነኝ። በዚህ አጋጣሚ እንደውም ሰዎች ይህንን ባህሪዬን ቢረዱኝ ደስ ይለኛል። ብዙዎች ከጉራ ጋር ያይይዙታል። ግን ጉራ ሳይሆን ማፈር ነው ያለብኝ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!