ይህን ያውቁ ኖሯል? (፪) | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን…

በዛሬው ይህን ያውቁ ኖሯል? አምዳችን ባሳለፍነው ሳምንት የጀመርነውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተመለከቱ ዕውነታዎችን ተከታይ ክፍል ይዘን ቀርበናል።

– ኢትዮጵያ የመጀመርያውን ጨዋታ ካደረገች በኋላ ለቀጣይ ዘጠኝ ዓመታት ምንም አይነት የነጥብ ጨዋታ አላደረገችም (ኦሊምፒክን ሳያካትት) ። በ1949 የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታዋን ከግብፅ ጋር ከማድረጓ በፊትም 47 የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከተለያዩ ሀገራት፣ ክለቦች እና ስብስቦች ጋር አድርጋለች።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፊፋ በሚያወጣው ወርሃዊ የሀገራት ደረጃ ላይ ከፍተኛ ደረጃን ያገኘው 1999 መስከረም ወር ላይ ነው። በዚህ ወቅት በወጣው ደረጃ ላይ ብሔራዊ ቡድኑ 86ኛ ቦታን ይዞ ነበር። ይህም የቡድኑ ከፍተኛው ደረጃ ሆኖ ተመዝግቧል።

– በተቃራኒው ብሔራዊ ቡድኑ በዚሁ የፊፋ የሃገራት ወርሃዊ ደረጃ ላይ ዝቅተኛ ደረጃን ያገኘው 1994 ታህሳስ ወር ላይ ነው። በዚህ ወቅት ቡድኑ 155ኛ ደረጃን ይዞ ነበር። ደረጃውም የብሔራዊ ቡድኑ ዝቅተኛ ደረጃ ሆኖ የታሪክ መዝገብ ላይ ተፅፏል።

– እስካሁን 21 የዓለም ዋንጫ ውድድሮች የተከናወኑ ሲሆን ኢትዮጵያ በየትኛውም ውድድር ላይ ተሳትፋ አታቅም። ረዥም ርቀት ተጉዛ ለተሳትፎ ተቃርባ የነበረውም ለ2014 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የፕሌይ ኦፍ ዙር የደረሰችበት ነው።

– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ14 የተለያዩ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች። ከእነዚህ መካከል በ2010 ውድድር የምድብ ማጣርያ አራት ጨዋታዎች ካደረገ በኋላ በፊፋ በመታገዷ ከውድድር ተሰርዛለች።

– በቀደምት ጊዜያት የዓለም ዋንጫ ውድድር ዝቅተኛ የተሳታፊዎች ቁጥር ስለሚያስተናግድ የዓለም ሀገራት አህጉር ሳይለዩ የማጣርያ ጨዋታ ያደርጉ ነበር። ኢትዮጵያም ለ1962 ዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከእስራኤል ጋር ለመጫወት ተደልድላ ነበር። በወቅቱ የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታ በቶሎ ባለመጠናቀቁ ሁለቱንም ጨዋታዎች በእስራኤል ሜዳ ለመጫወት የተገደደችው ኢትዮጵያ 2-3 እና 0-1 ተሸንፋለች።

– በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ 54 ጨዋታዎችን ያከናወነች ሲሆን ከነዚህ መካከል አንድ ጨዋታ ያልተገባ ተጫዋች በማሰለፍ ምክንያት ፎርፌ፤ እንዲሁም አራት ጨዋታዎች ደግሞ ከተደረጉ በኋላ በፊፋ እገዳ በመጣሉ ምክንያት የተሰረዙ ናቸው።

– በ2009 ወደተጀመረው የቻን ውድድር ስናመራ ኢትዮጵያ ከስድስት ውድድሮች መካከል በአራቱ የማጣሪያ ውድድሮች ላይ ተሳትፋለች። በዚህም አስራ ሦስት ጨዋታዎችን አድርጋ ስድስት ስታሸንፍ፣ አራት ተሸንፋ ሦስት ጨዋታ ደግሞ ተሸንፋለች። 18 አስቆጥራ፣ 11 ተቆጥሮባት በሒደቱ ሁለት ጊዜ ወደ ውድድሩ አልፋለች።

– በቻን ውድድር ላይ ሁለት ጊዜ የተካፈለችው ኢትዮጵያ በውድድሩ ስድስት ጨዋታዎች አከናውና በአምስቱ ስትሸነፍ በአንዱ አቻ ተለያይታለች። አንድ ብቻ አስቆጥራ ዘጠኝ ጎሎችንም አስተናግዳለች።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!