የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከበረከት ሳሙኤል ጋር…

የድሬዳዋ ከተማው የመሐል ተከላካይ በረከት ሳሙኤል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ ይዘንላችሁ ቀርበናል።

በደቡብ ክልል በሚገኘው ዱራሜ ከተማ ተወልዶ ያደገው በረከት እስከ 15 ዓመቱ ድረስ በትውልድ ከተማው እድገቱን ካደረገ በኋላ ወደ መዲናችን አዲስ አበባ በመምጣት ህይወቱን ቀጥሏል። ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቱ በፊት የለከፈው የእግርኳስ ፍቅር ግን ገና በለጋ እድሜው ህይወቱን ከኳስ ውጪ እንዳያስብ እንዳደረገው ይናገረል። በተለይ ቤታቸው አጠገብ በሚገኘው የዱራሜ ስታዲየም ውሎውን እያደረገ ከኳስ ጋር ያለውን ቁርኝነት እንዳጠነከረ ያወሳል። በከተማው በነበረ ከ13 ዓመት በታች የፕሮጀክት ቡድን ውስጥም ታቅፎ ስልጠናዎችን እንደወሰደ ያስታውሳል። በረከት ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ግን በቀለም ትምህርቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ትምህርቱ ከኳስ ጋር ያለውን ቁርኝት አላላላበትም። ይልቁንም በትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ በሚያገኛቸው ጨዋታዎች ራሱን እያጎለበተ ቀጠለ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካገባደደ በኋላም ‘ወደ ክለብ መግባት አለብኝ’ በማለት የሙከራ ዕድል ሊያገኝባቸው የሚችልባቸው ቡድኖች ጋር ደጅ መጥናትን ተያያዘ። በዚህም ቦሌ ገርጂ የሚባለው ክለብ ውስጥ የመካተቱን ዕድል አግኝቶ የእግርኳክ ህይወቱን በክለብ ደረጃ መግፋት ጀመረ።

ተጫዋቹ 2003 ላይ ቦሌ ገርጂን ተቀላቅሎ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ 2005 ላይ ወደ ሱሉልታ ከተማ አቀና። ለሱሉልታም ሁለት ዓመት ከተጫወተ በኋላ ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማሳለፍ በነበረ የማጠቃለያ ውድድር ላይ ባሳየው ብቃት በሙገሮች ዕይታ ውስጥ ገብቶ 2007 ላይ ፊርማውን ለሙገር ሲሚንቶ አኖረ። እንደ ሱሉልታ ሁሉ በሙገርም ለሁለት ዓመታት የአቅሙን ከቸረ በኋላ 2009 ላይ ወደ ምስራቂቱ የሃገራችን ክፍል ድሬዳዋ በማቅናት ለድሬዳዋ ከተማ መጫወት ጀመረ። ላለፉት አራት ዓመታትም በድሬ ቤት ግልጋሎት እየሰጠ ቆይቷል።

በብሔራዊ ቡድን ደረጃ እስካሁን ምንም ግልጋሎት ያልሰጠው በረከት ሙገር እያለ ለመጀመሪያ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እንዲወክል ጥሪ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም በፓስፖርት ችግር ምክንያት የሃገሩን መለያ መልበስ ሳይችል ቀርቷል። በትላንትናው ዕለትም ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሉን ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቆ እንደነበረ መዘገባችን ይታወሳል።

በበርካታ የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች የሚወደደው ይህ ግዙፍ የመሐል ተከላካይ በዛሬው የ’ዘመናችን ከዋክብት ገፅ’ ላይ እንግዳ አድርገነው አዝናኝ ጥያቄዎችን አቅርበንለታል።

የእግርኳስ አርዓያህ ማነው?

ከሃገር ውስጥ ከሆነ አርዓያዬ ደጉ ደበበ ነው። ደጉን በጣም ነው የማደንቀው። አጨዋወቱም በጣም ነው የሚመቸኝ። እሱም የመሐል ተከላካይ ስለሆነ እንደ አርዓያ ነበር ስመለከተው የነበረው።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ በረከት ጊዜውን በምን እያሳለፈ ነው?

ውድድሩ ከተቋረጠ በኋላ በግሌ የልምምድ መርሐ-ግብሮችን አውጥቼ እየሰራሁ ነው። በሳምንት አምስት ቀን ሳላቋርጥ እሰራለሁ። በሊጉ ላይ የሚጫወቱ ጓደኞቼም እኔ የምኖርበት አካባቢ ስለሆነ የሚኖሩት አብረን ልምምዶችን እንሰራለን። ከዚህ ውጪ ስራዬ ብዬ ይሰራው ነገር የለኝም ነበር። ትዕዛዙንም ለማክበር እቤት ሆኜ ነበር ጊዜዬን የምገፋው።

ኮሮና ከመጣ በኋላ አዲስ እየለመድክ ያለህው ልማድ አለ?

በደንብ አለ። በተለይ ለቤተሰብ ጊዜ መስጠት የሚለውን ነገር አሁን ኮቪድ ከመጣ በኋላ ነው በደንብ እየተገበርኩት ያለሁት። እግርኳስ ተጫዋች ውድድር እያለ ለቤተሰቡ የሚሰጠው ጊዜ በጣም ትንሽ ነበር። አሁን ግን ጊዜ ስላገኘሁ ለቤተሰቤ ጥሩ ፍቅር እየሰጠሁ ነው።

ኮሮና ጠፋ ሲባል መጀመሪያ የምታረገው ነገር ምንድን ነው?

ሰው መጨበጥ እና ማቀፍ ነዋ (እየሳቀ)። እኔ መጨባበጥ በጣም ነው የናፈቀኝ።

ማንን ነው መጀመሪያ የምታቅፈው ወይም የምትጨብጠው?

ያገኘሁትን ሰው (እየሳቀ) ። ለነገሩ ጓደኞቼ አብረውኝ ስለማይጠፉ እነሱን ነው የምጨብጠው።

በግልህ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍክበት ዓመት መቼ ነው?

በአንፃራዊነት በግሌ ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፍኩ የሚሰማኝ 2007 ሙገር እንዲሁም 2010 ድሬዳዋ ቤት እያለሁ የተጫወትኩባቸው የውድድር ዘመናት ናቸው። በተለይ 2010 ላይ የነበረኝ ብቃት የሚገርም ነበር። ድሬዳዋ በሁለተኛ ዙር የሊጉ ውድድር ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች 5 ጎል ብቻ ነበር የገባበት። ያኔ ተከላካይ የነበርነው እኔ እና አንተነህ ተስፋዬ ነበርን። በጊዜው እኔም ምርጥ ነበርኩ፣ አንተነህም ድንቅ ነበር እንደገና ደግሞ ጥምረታችንም አስገራሚ ነበር።

በረከት እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን በምን ሙያ እናገኘው ነበር?

ሳስበው የታሪክ ተመራማሪ የምሆን ይመስለኝ ነበር። ምክንያቱም ከታሪክ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ስለምወድ በዚህ ሙያ እገኝ ነበር። እውነት ለመናገር ግን እግርኳስ ተጫዋች ባልሆን ሃገር ውስጥ የምቆይ አይመስለኝም። ቤተሰቦቼ ውጪ ስላሉ እነሱ ጋር የምሄድ የመስለኛል። ከታሪክ ጋር የተያያዘውንም ነገር እዛው ሆኜ እገፋበት ነበር።

አብሬው ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለሁ የምትለው ተጫዋች አለ?

በጣም ከማደንቀው ደጉ ደበበ ጋር ተጣምሬ ብጫወት ደስ ይለኛል። ለብዙ ጊዜ እንኳን ባይሆን ለተወሰነ ደቂቃ ከእርሱ ጋር ብጣመር ለእኔ ትልቅ ነገር ነው። በተጨማሪም ከአንተነህ ተስፋዬ ጋር ለረጅም ጊዜ አብሬ ብጫወት ደስ ይለኛል። ከአንተነህ ጋር ድሬዳዋ እያለ አብረን ተጫውተናል። ግን አሁንም ከማን ጋር ብትጣመር ደስ ይልካል ካልከኝ ከደጉ ቀጥሎ ከእርሱ ጋር ነው የምልህ።

አንተ የተከላካይ መስመር ተጫዋች ነህ። በተቃራኒ ስትገጥመው የሚከብድክ አጥቂ ይኖር ይሆን?

ያን ያህል የሚከብድን አጥቂ አጋጥሞኝ አያቅም። ግን ሳልሀዲን ሰዒድ በጣም ፈትኖኝ ነበር። ሳልዓዲን ምርጥ አጥቂ ነው። በጣም ነበር ያስቸገረኝ።

በዚህ ሰዓት በሃገራችን ከሚገኙ ተጫዋቾች ያንተ ምርጥ ተጫዋች ማነው?

ለእኔ ኤሊያስ ማሞ ምርጡ ተጫዋች ነው። እርግጥ ይህንን ምርጫ የምመርጠው አብሬያቸው ከተጫወትኳቸው እና በደንብ ካየኋቸው መካከል ነው። እኔ ደግሞ ከብዙ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ጋር ተጫውቻለሁ። ብዙ ጥሩ ተጫዋቾችን አይቻለሁ። ግን ኤሊያስ ለእኔ አንደኛው እና ምርጡ ነው።

ከአሰልጣኞችስ?

በዚህም ምርጫ ያሰለጠኑኝን አሠልጠኞች ነው ታሳቢ የማደርገው። ካሰለጠኑኝ በርካታ አሠልጣኞች መካከል ደግሞ በሙገር ሲሚንቶ ስጫወት ያሰለጠኑኝ ግርማ ለእኔ ምርጡ ናቸው።

በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበትን አጋጣሚ አጋራኝ?

በ2009 የመጨረሻ የሊጉ ጨዋታ ላይ የተፈጠረው ውጤት በጊዜው በጣም አስደስቶኛል። የዛኔ እኔ ስጫወትበት የነበረው ድሬዳዋ እና ጅማ አባቡና የወራጅነት እጣ ፈንታ አጋጥሞን ነበር። እንደውም በመጨረሻው ጨዋታ አባቡናዎች አቻ ቢወጣ መትረፍ ይችል ነበር። አባቡና ከተረፈ ደግሞ እኛ ወረድን ማለት ነው። ግን በመጨረሻው ጨዋታ እነሱ ተሸንፈው እና በሜዳችን ባለቀ ሰዓት አግብተን አሸንፈን ተረፍን። ይህ አጋጣሚ በጣም ነበር ያስፈነደቀኝ።

በተቃራኒው የተከፋህበትን እና ጥሩ ስሜት የማይሰጥህን አጋጣሚ አጫውተኝ?

ሙገር የወረደበት የውድድር ዘመን በጣም ያስከፋኝ ዓመት ነው። በተለይ የመጨረሻው ጨዋታ ላይ የተፈጠረው ነገር ደስ የማይል ነው። እኛ ከመከላከያ ጋር እየተጫወትን በሌላ ስታዲየም ደግሞ በሚደረገው የወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ ላይ የኤልፓን መሸነፍ እየተመኘን ነበር። አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የሚደረገው ጨዋታ ላይ እኔ በ85ኛው ደቂቃ ጎል አግብቼ ጨዋታውን አሸነፍን። ከዛ ሶዶ ላይ ደግሞ ኤልፓ ተሸነፈ የሚል መረጃ ደርሶን የሚገርም ደስታ ተሰምቶን ተረፍን ብለን ስታዲየሙን በጭፈራ ስንዞር ነበር። ግን የደረሰን መረጃ ስህተት ነበር። መልበሻ ክፍል ስንገባ እኛው ራሳችን እንደወረድን ስሰማ በጣም ነው ያዘንኩት። በጣምም ነው የተከፋሁት።

በእግርኳሱ ውስጥ ከሚገኙ ግለሰቦች የቅርብ ጓደኛህ ወይንም ሚስጥረኛህ ማነው?

በኳስም ሆነ ከኳስ ውጪ በርካታ ጓደኞች አሉኝ። ግን በጣም የምቀርባቸው እና እንደ ሚስጥረኛ የማማክራቸው ሳምሶን አሠፋ እና ሀብታሙ ወልዴ ናቸው።

እግርኳስ ካቆምክ በኋላ ምን ለመሆን ታስባለክ?

እግርኳስ መጫወት እንዳቆምኩ በቀጥታ ወደ አሠልጣኝነት ነው የምገባው። ከእግርኳስ መለየት ይከብደኛል። እንደውም በቅርቡ እየተጫወትኩ የአሠልጣኝነት ስልጠና ለመውሰድ አስቤያለሁ። ስለዚህ ጫማዬን ከሰቀልኩ በኋላ በስልጠናው ዓለም ታገኙኛላችሁ።

በረከት ብዙ ሰዎች የማያቁት ምን የተለየ ባህሪ አለው?

የተለየ ባህሪ እንኳን ብዙ የለኝም። ግን ብዙ ጊዜ ልምምድ ላይ በምከተለው ሃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት ከአሠልጣኞች ጋር እጣላለሁ። እኔ ጨዋታም ሆነ ልምምድ ላይ ያለኝን ነው አውጥጬ የምጫወተው። በዚህ ጊዜ ደግሞ ልምምድ ላይ ተጫዋቾችን እንዳልጎዳ አሠልጣኞች የጠይቁኛል። እኔ ግን ወይፍንክች። ይህ ባህሪዬ ለክፋት አደለም። ያለኝን አውጥቶ ከመስጠን ጋር በተያያዘ እንጂ። ከሜዳ ውጪ ደግሞ ከሁሉም ጋር ተግባቢ ነኝ።

የግል ህይወትህ ምን ይመስላል?

አሁን ላይ ባለትዳር ነኝ። እንደውም ከአንድ ወር በፊት የወንድ ልጅ አባት ሆኛለሁ። እዚሁ አዲስ አበባ ከባለቤቴ እና ከልጄ ጋር ነው እየኖርኩ የምገኘው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!