መንግሥቱ ወርቁ ሲታወሱ (፰) | የአራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ትውስታ

በህይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምን ጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን እያሰብን እንገኛለን። የታላቁን የእግርኳስ ሰው ዕድገት ፣ የእግር ኳስ አጀማመር ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ትውስታዎች እና የብሔራዊ ቡድን አስተዋፅኦን እያነሳንም ሰንብተናል። ዛሬ ደግሞ ታላቁ በአራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ክስተቶች ላይ እናተኩራለን።

ማስታወሻ ፡ በገነነ ሊብሮ በመፅሀፍ መልክ የተዘጋጀው ከመንግሥቱ ወርቁ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እና የልሣነ-ጊዮርጊስ ጋዜጣ የታላቁን ሰው ህልፈት ተከትሎ በተከታታይ ያወጣቸው ፅሀፎች ዋነኛ ግብዓት እንደሆኑ እንገልፃለን።

1956 የአራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ በሆነችው ጋና ተዘጋጀ። ነባር ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያ ፣ ግብፅ ፣ ሱዳን እና ቱኒዚያ እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈሉት ናይጄሪያ እና ጋና በሁለት ምድቦች የተከፈሉ ስድስቱ በውድድሩ ላይ የተገኙ ቡድኖች ናቸው። በወቅቱ ህግ መሰረት የምድቦቹ አንደኞች ለዋንጫ ሁለተኞች ደግሞ ለደረጃ እርስ በእርስ የሚጫወቱ ሲሆን ኢትዮጵያ ከጋና እና ቱኒዚያ ጋር ነበር የተደለደለችው ፤ የመጀመሪያ ጨዋታዋን የምታደርገው ደግሞ ከአዘጋጇ ከጋና ጋር ነበር። ኢትዮጵያ የሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለድል ከሆነች በኋላ በቀጣዩ በዚህ ውድድር አሸናፊ ለመሆን ግምቱን አግኝታለች። ከዚህም በላይ ቻምፒዮን የሆነው ስብስብ ወደ አውሮፓ አምርቶ ግሪክ ላይ የዝግጅት ጨዋታዎችን ማድረጉ እና ተጫዋቾቹም ተጨማሪ ልምድንም አካብተው ለውድድሩ መቅረባቸው ክብራቸውን ያስጠብቃሉ ተብለው እንዲታሰቡ ምክንያቶች ነበሩ። እነርሱም ቢሆኑ ዋንጫውን ደግመው እንደሚመለሱ ዕምነቱ ነበራቸው። ነገር ግን ጋና ከደረሱ በኋላ የገጠማቸው ነገር ሌላ ነበር። መንግሥቱ የያኔውን ትውስታ ከሊብሮ ጋር በነበረው ቆይታ እንዲህ አስታውሶታል።

“ጋና አፍሪካን ዋንጫ ተካፍሎ ስለማያውቅ ግብፅም የበፊቱ ተጫዋቾች ወጥተው አዲስ ተጫዋች ስለሆኑ ስለማያሰጉ ኢትዮጵያን ብቻ ከረታን ዋንጫ እንወስዳለን ብለው ስላሰቡ ገና ስንገባ ሌላ ቦታ ይዘውን ሄዱ፡፡ ሀገሩ መቀት ስለሆነ ከአንድ ወር በፊት የያዝነውን ዘመናዊ ሆቴል አንሰጥም ብለው ወስደው ባንጋሎ ውስጥ ከተቱን፡፡ እዚያ ያለው ሙቀት በጣም የሚያስመርር ነው፡፡ አያስተኛህም ምግብ ደግሞ አይሰጡንም፡፡ ውሀ እንኳን እንደልብ እንዳንጠጣ ከለከሉን ፤ እነርሱ ቅኝ ገዥዎቻቸው የሚሰሯቸውን  ተንኮል በእኛ ላይ መፈፀም ጀመሩ፡፡ በጣም የሚገርመው የእነርሱ ተጋጣሚ የቱኒዚያን ቡድን እንኳን እንደዚህ አላደረጉትም፡፡ እኛ የ3ኛ አፍሪካ ዋንጫን ስለረታን ከአውሮፓ ቡድኖች ጋርም ገጥመን ስለምንቋቋም እኛን በረሀብና ውሃ ጥም አዳክመው ሞራላችን ሲነካ ነው ለመግጠም የፈለጉት፡፡ በኋላ ረሀብ ሲበዛብን ለእኛ ኤንባሲ አቤት አልን፡፡ እዚያ ያሉት አምባሳደር አቶ ፍሬው ሁኔታው በጣም ስላናደዳቸው እሳቸውም ቢከራከሩም መፍትሄ ስላጡ ከኤንባሲው በጀት ላይ አቀናንሰው ፍየል እየገዙ (ሙቀት ስለሆነ ፍየል ብቻ ነው ያለው) እየጠበሱ ያበሉን ነበር፡፡ ይሄን ደግሞ እስከ መቼ ትዘልቅበታለህ ? የእሳቸውን በጀት ጨረስንባቸው፡፡ ረሀቡን መቋቋም አልቻልንም፡፡”

በምድቡ የመጀመሪያው ጨዋታ ጋና እና ቱኒዚያ 1-1 ተለያይተዋል። ይህም ኢትዮጵያ በተለይ ጋናን ካሸነፈች አዘጋጇን ከውድድሩ ከማስወጣቷ በተጨማሪ የማለፍ ዕድሏ በእጅጉ እንዲሰፋ ይሆናል። ነገር ግን ቡድኑ በአካል እና አዕምሮ ደክሞ ነበር ወደ ጨዋታው የገባው። ከዚህ በተጨማሪም ጨዋታው ላይ በተፈጠረው ረብሻ የቡድኑ ተሰላፊዎች ከፖሊስ ጋር ጭምር እስከመደባደብ ደረሱ። ይህን ክስተት መንግሥቱ እንዲህ ባለ ሁኔታ ተርኮታል። ” በደረሰብን ግፍ ምክንያት አቅም የለንም ግን እልህ ብቻ ነው የተረፈን፡፡ አጠገቤ ብዙ ጊዜ ሲጫወት የነበረው ኢታሎ ቫሳሎ ከዚህ በፊት ኬንያ ላይ ስለተሰበረ ነፍሱን ይማረውና ጌታቸው አብዶ ነው ከእኔ ጋር የተሰለፈው፡፡ ጌታቸው ደግሞ ያኔ ልጅ ነው 16 ዓመት አይሞላውም፡፡ ኢታሎ ከእኔ ጋር በጣም ነው የምንግባባው ከእርሱ ጋር በኳስን ብቻ ሳይሆን ተከላካዮቹ ሊማቱ ሲፈልጉ እንዲሁ ተጠቃቅሰን እንመታቸዋለን፡፡ በቴስታ ጠብ ነው የምናደርጋቸው። በተለይ ኢታሎ ጋር ያለ ድፍረት እኔ አይቼ አላውቅም፡፡ በቃ ወንድ ነው ማለት ትችላለህ ምንም ነገር አይፈራም፡፡ ተከላካዩ አንበሳ ወይም ነብርም ቢሆን ምንም ደንታ አይሰጠውም፡፡ ውጭ ሀገር እርሱና ጌታቸው ዱላ ያስነሱት ፀብ መብረጃ የለውም፡፡ በዚያ ላይ ያባብሱታል፡፡ ለጋና ጨዋታ ኢታሎ ተሰብሮ ስለነበር ለመጫወት ሳይሆን ዝም ብሎ ነበር የመጣው ፤ አይጫወትም ጄሶ ገብቶለት በክራንች ቤንች ላይ ቁጭ ብሏል፡፡ እኛ ሜዳ ስንገባ ህዝቡ ጥቅጥቅ ብሏል፡፡ የክብር እንግዳው የመከላከያ ሚኒስትራቸው ነው፡፡ ማዕረጉ ደግሞ ጄኔራል ነው፡፡ እየተጫወትን እያለ ዳኛው ከኮንጎ የመጣ ነው፡፡ ከመጀመሪያውም አላማረንም። ተስፋዬ ወዲ ቀጭን ፔናሊቲ ኤርያ ውስጥ ያገኘውን ኳስ አክሮ ሲመታ የውስጥ ብረቱን መቶ ኳሱ ወደ ውስጥ ገብቶ ሁለቴ ከነጠረ በኋላ ወደ ውጭ ወጣ፡፡ ጎል ስለሆነ እነርሱም ዝም ቢሉም ዳኛው ግን ሳያጸድቀው ቀረ፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ አንድ ኳስ እኛ ላይ ተመታና ጊላ ተወርውሮ ያዘ፡፡ በወደቀበት የእነርሱ ተጫዋች አገጩን በጫማ ሲለው ጊላ ኳሱን ትቶ መንከባለል ጀመረ ፤ ያችንም አገቧት፡፡ ዳኛው ፊሽካ ይነፋል ብለን ስንጠብቅ አሁንም ዝም አለ፡፡ ከእንግዲህ ከመጣንበት ጀምሮ የነበረው ረሀብ፣ የደረሰብን በደል በሜዳ ላይ ዳኛ የሚፈጽመው አሳፋሪ ነገር ተደማምሮ ንዴት ውስጥ ከተተን፡፡ ግን መጀመሪያ በቀለብ ስለጎዱን አቅም አልነበረንም፡፡ የጋና ቡድን ያን ያህል ስለሆነ ሁለት ጎል ቢያገባም እናሸንፈዋለን ብለን መጫወት ጀመርን፡፡ ለካ ያ ጎል ሲገባ ሕዝቡ እንደዚያ ሲጨፍር የክብር እንግዳ የሆነው ጄኔራል ከትሪቡን ይወርድና በስሜት የኢትዮጵያን ባንዲራ ከተሰቀለበት ማውረድ ይጀምራል፡፡ ይሄ ደግሞ በጣም የሚያሳፍር ነው፡፡ አሁን ማን ይሙት የእኛ መከላከያ ሚኒስቴር የሰው ባንዲራ ያወርዳል? (መንግሥቱ በጣም ገርሞት ሁኔታውን አስታውሶ እራሱን ነቀነቀ) እሱ ባንዲራ ሲያወርድ በዚያን ሰዓት እኛ ኳሱን ይዘን እየተቀባበልን በማጥቃት ላይ ነን፡፡ ተስፋዬ ለእኔ ሰጥቶኝ እኔ ነበርኩ ወደ ፊት የምነዳው መሀል ሜዳውን አልፈናል፡፡ ከዚያ ሉቻኖ ተቀበለና ለጌታቸው ሰጠው ኢታሎ በዳኛው ሁኔታ ተናዶ ዳኛው በእረፍት ሲወጣ ለመፈንከት በክራንች መሬቱን እየመታ ውጪ ቆሞ ይጠብቃል፡፡ እርግጠኛ ነኝ በዚያ ጨዋታ እርሱ ወይም ጌታቸው ዱላ ሜዳ ውስጥ ቢኖሩ ረብሻ ተነስቶ ነበር፡፡ ሌሎችን ግን ምግብም ስለጎዳን አቅማችንን ለመጫወት ብቻ ነው ያደረግነው፡፡ ኢታሎ ውጭ ቆሞ ሳለ የእነርሱ ጄኔራል ባንዲራችንን ሲያወርድ አይቶ እግሩ ጀሶ እንደገባለት በክራንች እያነከሰ ተንደርድሮ በመሄድ ጄኔራሉን አናቱን ከኋላ ሲለው ባንዲራው ግማሹ ላይ እያለ ሰውዬው ከነማዕረጉ መሬት ላይ ተዘረረ፡፡”

ከዚህ በኋላ ጨዋታው ወደ አስቂኝ ፊልምነት የተቀየረ ይመስላል። የኢታሎን ተግባር የተመለከቱ ፖሊሶች እሱን ለመደብደብ ሲሮጡ ሜዳ ውስጥ የነበሩት እነመንግሥቱም ከሜዳ ወጥተው ወደ ግርግሩ ሮጡ። ውስጣቸው የነበረውን እልህ በፀቡ ለማብረድ እግሩ በጀሶ የታሰረው ኢታሎን ከፖሊሶች ለማዳን ገሰገሱ። መንግሥቱ ‘በቃ ወንድ ነው !’ ያለው ኢታሎም ፖሊሶችን ጭምር በክራንቹ እየመታ መጣል ጀምሯል። ከሜዳ ግር ብለው የወጡት ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችም ደርሰው ከፖሊሶቹ ጋር የለየለት ድብድብ ውስጥ ገቡ። በፀቡ መጀመሪያ ጋናዎች ያስቆጠሩትንም ግብ ዳኛው አፅድቆታል። “ነገሩ ቲያትር ነው የሚመስለው እንደዚያን ቀን ፖሊስ እስኪበቃን ደብድበን አናውቅም፡፡ የዚያንም ያህል ተደብድበናል፡፡ ከዚያ የእነርሱ ተጫዋቾችና የፌዴሬሽኑ ሠራተኞች መጥተው እኛን ይገላግሉን ጀመር፡፡ ፖሊሶቹም ተረጋጉ ከዚያ አንድ አምስታችንን ወደዚያ ወስደው አረጋግተው ጨዋታ እንዲጀመር ሊያደርጉ ሲሉ ኢታሎ እንደገና አንዱን ወታደር አናቱን ብሎ መታው፡፡ ከዚያ እንደገና ድብድብ ተጀመረ፡፡ ኢታሎ እንኳን ጄሶ ታስሮለት እግሩ ቢቆረጥም ይጣላል፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን ትንሽ ሲበደል ሟች ነው፡፡ እንደዚያ ሆኖ ባንዲራውን ያወረደውን ጄኔራል እንደገና ከመታው በኋላ ካልተደባደብኩ እያለ ይፎክር ነበር በኋላ ፎርፌ እንዳይሆን ይድነቃቸውም ለምኖን ወደ ሜዳ ገባን።” በማለት መንግሥቱ ከሊብሮ ጋር በነበረው ቆይታ ሁኔታውን አስታውሶታል።

ጨዋታው በጋና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ። በመሆኑም ኢትዮጵያ ቱኒዚያን ብታሸንፍ እንኳን ወደ ፍፃሜ የማለፍ ዕድሏ መክኗል። እንደመንግሥቱ ገለፃም በወቅቱ በተደረገባቸው ነገር እጅግ በመበሳጨታቸው ለቱኒዚያ ለቀው ጋናን ለመጣል ይፎክሩ ጀመር። እንደዛቱት ካደረጉ እና ቱኒዚያ ኢትዮጵያን 3-0 ካሸነፈች ከጋና በልጣ ወደ ፍፃሜው ማለፏ ነው። ጋናዎች ግን ይህ እንዳይሆን ወዲያው እንክብካቤ እንደጀመሩ መንግሥቱ ይናገራል። “ይገርምሀል በምግብና በመኝታ እንደበደሉን ስላወቁ ገና ሆቴል ልንሄድ ስንል ሾፌሩ ወደ ሌላ ቦታ ይዞን ሄደ። ለካ እነርሱ ገና ከሜዳ ሳንወጣ በፊት ከነበርንበት ከአሰቃቂው ሆቴል እቃችንን በሙሉ አውጥተው ከተማ ውስጥ ትልቁ ዘመናዊ ሆቴል አስገብተውታል፡፡ ቱኒዚያን እንድናሸንፍላቸው። እኛ ደግሞ 7 ነው የምንለቀው ብለን ዛትን፡፡ ያኔ ጋናዎች ፈሩን፡፡ ሆቴል እንደደረስን መድኃኒቱ ፣ ሐኪሙ ፣ ኦራንጁ በቃ ቤተመንግስት የገባን መሰለ። እንደደረስን ይሄንን ስናውቅ የእነርሱን ሐኪሞችና ሠራተኞች መደባደብ ጀመርን፡፡ ያን ያህል ጊዜ በድላችሁን እንዴት አሁን ትመጣላችሁ ብለን ተጣላን፡፡ እኛ ተመካክረን 7 እንለቃለን ብለን ወስነናል፡፡ በኋላ ጋሽ ይድነቃቸው ሁኔታችንን  አይቶ ጠረጠረና ሰብስቦ ‘ስሙ ልጆች እንደዚህ ልታደርጉ እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ በእርግጥ ችግር ደርሶባችኋል ግን ይሄ እየተለመደ መጥቷል፡፡ አንደኛ ነገር አሁን ብትለቁ ጋናና ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ ገና ብዙ የአፍሪካ ዋንጫ አለ፡፡ ለቱኒዚያ ብትለቁ ይሄ ቲም ሁሌም እንደዚህ ነው ተብሎ ታሪካችንን ታበላሻላችሁ፡፡ ሁለተኛ ነገር ደግሞ እናንተ አብዳችኋል ወይስ ጤነኛ ናችሁ ? አሁን አራት እና አምስት ብትለቁ በየት በኩል ልትወጡ ነው ?’ አለን፡፡ ትዝ ሲለን ለካ ሰው ሀገር ነው ያለነው ሁኔታው አስፈራን፡፡ ግን ጨዋታው እስኪደርስ ድረስ እያስፈራራን ብዙ ተጠቀምን፡፡”

የተጠበቀው ጨዋታ ተደረገ እና ኢትዮጵያ ቱኒዚያን 4-2 አሸነፈች። መንግሥቱ ወርቁም በጨዋታው ሁለት ግቦች አስቆጠረ። የብሔራዊ ቡድኑ በሙሉ አቅም መጫወት ጋናን በአንደኝነት እንድታልፍ ሲያደርግ ኢትዮጵያም ለሦስተኝነት ከግብፅ ጋር የመጫወትን ዕድል አስገኘላት። ከቱኒዚያው ጨዋታ በኋላ የነበረውን ድባብ መንግሥቱ እንዲህ ገልፆታል። “ጨዋታው ከአላቀ በኋላ ሀገር ሜዳውን አጥለቀለቀው እያንዳንዳችን ለ40 እና ለ50 እየሆኑ እየተሸከመን ይጨፍሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም ጋና ለዋንጫ አለፈ፡፡ በየጋዜጣው ናሽናል ሄሮ እየተባልን ፎቷችን ወጣ፡፡ እኔም ተሸክመውኝ ሲጨፍሩ ይሄኔ ለቀን ቢሆን ኖሮ ለ40 እና ለ50 ሆነው እንደዚሁ ይቦጫጭቁን ነበር ብዬ አሰብኩ፡፡ ከዛ ማታ ቤተመንግሥት ተጠርተን ፕሬዝዳንቱ ባለበት ተጋበዝን፡፡ በጣም አመሰገኑን ስለደረሰውም በደል ይቅርታ ጠየቁን፡፡”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!