ናይጄርያዊው አጥቂ ከምዓም አናብስት ጋር ለመቆየት ተስማማ

ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ውሉን ያጠናቀቀው ኦኪኪ ኦፎላቢ ከክለቡ ጋር ለተጨማሪ ዓመት ለመቀጠል ተስማማ።

ባለፈው የውድድር ዓመት መቐለን ተቀላቅሎ ለቡድኑ ሰባት ግቦች ያስቆጠረው አጥቂው ውሉን አራዝሞ ከክለቡ ጋር ስለመቀጠሉ አጠራጣሪ ሆኖ ቢቆይም በመጨረሻ ግን ከምዓም አናብስት ጋር ለመቀጠል ወስኗል። በሃገሩ የኮቪድ 19 ምርመራ ካደረገ በኃላ ቅዳሜ ማታ ቦሌ አየርማረፍያ የሚደርሰው አጥቂው በቀናት ውስጥ ውሉን አራዝሞ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል።

በ2010 የወራት ቆይታ ካደረገበት ማሌዥያው ከላንታን ለቆ ጅማ አባጅፋርን የተቀላቀለው ግዙፉ አጥቂ ዓመቱን በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እና ከቡድኑ ጋር በሊግ ቻምፒዮንነት አገባዶ በ2011 ለጥቂት ወራት ወደ ግብፁ ኢስማኢሊያ አቅንቶ ጥቂት ጨዋታዎች ቢያደርግም ከክለቡ ጋር ያለውን ውል በስምምነት ቀዶ በድጋሚ ወደ ጅማ አባጅፋር ተመልሶ የስድስት ወራት ቆይታ አድርጓል። ባለፈው የውድድር ዓመት ደግሞ የቀድሞ አሰልጣኙን ተከትሎ ወደ መቐለ 70 እንደርታ በማምራት የውድድር ዓመቱን አሳልፏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!