ስለ ዘላለም ምስክር (ማንዴላ) ሊያውቋቸው የሚገቡ ዕውነታዎች

የመሰለውን ያለምንም ፍራቻ በግልፅ በመናገር ይታወቃል። በኢትዮጵያ እግርኳስ በርካታ ክለቦች ተዟዙሮ በመጫወት ወደር አይገኝለትም። እርሱ ከተጫወተባቸው ክለብ ይልቅ ያልተጫወተበት ክለብ መጥቀስ ይቀላል ይባልለታል። የዘጠናዎቹ ድንቅ የመስመር አጥቂና አማካይ ዘላለም ምስክር (ማንዴላ) ማነው?

ከወታደር (ከአርበኞች) ቤተሰብ ነው የተወለደው። በወታደራዊ ሥነ-ስርዓት ተኮትኩቶ ማደጉ ረጅም ዓመታት ለመጫወቱ እና የተሰማውን ሥሜት ያለምንም ፍራቻ በግልፅ እንዲናገር የረዳው ይመስላል። በቀጥታ የተሰማውን እንደሚናገር ማሳያ አንድ ታሪክ እንንገራችሁ። በአንድ ወቅት አሰልጣኙ ተጫዋቾቹን ሰብስቦ ውይይት ያደርጋል። አሰልጣኙም መናገር የሚፈልገውን ተናግሮ ሊጨርስ ሲል አንድ መልዕክት ያስተላልፋል። ” ማንዴላ ሜዳ ላይ ከሚያሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ ወይም ከሜዳ ውጭ ከሚያሳየው መልካም ነገር ተነስቼ ወደፊት ትልቅ አሰልጣኝ ይሆናል ብዬ እናገራለው እናንተም…” እያለ ተናግሮ ሲጨርስ ይህ ያልተዋጠለት ወይም ያልገባው ማንዴላ እጁን አውጥቶ ” ኮች ልክ ነህ፤ እኔ ወደ ፊት ትልቅ አሰልጣኝ እሆናለው። ግን ምክትሌ የምትሆነው አንተ ነህ።” ስለማለቱ ይነገራል።

ዘላለም ምስክር ትውልዱ አዲስ አበባ ግቢ ገብርኤል አካባቢ ሲሆን በኋላም ወደ ልደታ ኮካ ሠፈር በመሄድ የዕድሜውን አብዛኛውን ክፍል ኖሯል። በልጅነቱ ወታደር አባቱን ቢያጣም እግርኳስን ተጫውተው ማለፋቸው እርሱንም ወደ እግርኳሱ እንዲያዘነብል አድርጎታል። ከሠፈር ልጆች ጋር በጨርቅ ኳስ በመጫወት የጀመረው የእግርኳስ ተጫዋችነት ፍላጎቱ አይሎ ከመንግሥት ለውጥ በኋላ ወደ ሰማንያዎቹ አጋማሽ አካባቢ መብራት ኃይል ሲ ቡድን መቀላቀል ችሏል። ወደ ዋናው ቡድን ለማደግ ብዙ ጊዜም አልፈጀበትም። ሆኖም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በማቅናት ቆይታ ካደረገ በኋላ በድጋሚ ወደ መብራት ኃይል ተመልሶ በ1990 መብራት ኃይል በጋሽ ሐጎስ ደስታ እየተመራ ታሪካዊውን የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ የቡድኑ አባል ነበር።

በመቀጠል ለቁጥር የሚታክቱ ክለቦች ተጫውቷል። ለአብነት ያህል መብራት ኃይል ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኒያላ፣ እርሻ ሰብል፣ መድን፣ ኢትዮጵያ ቡና (አዲስ አበባ ውስጥ ከባንክ ውጪ ያልተጫወተበት ክለብ እንደሌለ ይናገራል)። ወደ ክልል በመውጣትም መቐለ፣ ወንጂ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ሜታ ቢራ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ሰበታ ከተማን ጨምሮ በአጠቃላይ 19 ለሚደርሱ ክለቦች ተጫውቷል። ከመስመር እየተነሳ ጎሎች በማስቆጠር እና ለአጥቂዎች ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል እና ፈጣንነቱ የእርሱ መገለጫዋቹ እንደሆኑ ይነገርለታል።

አብረውት ከተጫወቱ ተጫዋቾች መካከል ቴዎድሮስ በቀለ (ቦካንዴ) ስለ ዘላለም ምስክር ይናገራል። ” ማንዴላ ማለት ሁሉም ቦታ የምታጫውተው በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነው። ከሜዳ ውጭም ከሰው ጋር ሲበዛ ተግባቢ እና ሳቅ ፈጣሪ ልጅ ነው። ረጅም ዓመት አቋሙን ጠብቆ መዝለቅ የቻለ አጥቂ፣ አማካይ እና የመስመር አጥቂ አድርገህ የምታጫውተው ጥሩ አቅም ያለው ተጫዋች ነበር”

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ የመጫወት እድል አግኝቷል። እጅግ አብዝቶ በተለያዩ ክለቦች መጫወቱ በእግርኳስ ሕይወቱ ላይ ወጥ የሆነ የስኬት ዓመታት እንዳያሳልፍ አድርጎታል የሚሉ እንዳለ ሆኖ በተለያዩ ክለቦች እየተዟዟሮ መጫወቱ እና በሁሉም ክለብ መፈለጉ በወቅቱ የነበረው አቋም ጥሩ እንደነበረ ማሳያ ነው የሚሉ አሉ። በእግርኳስ ቆይታውም በመብራት ኃይል የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ፣ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ወደ እግርኳስ ማብቂያው አካባቢ ደግሞ በብሔራዊ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ከሰበታ ከተማ ጋር የኮከብ ተጫዋችነት ክብርን አግኝቷል።

ሌላው አብሮት ከተጫወተው እና የቅርብ ጓደኛዎቹ መካከል አንዱ የሆነው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ስንታየሁ ጌታቸው (ቆጬ) ስለ ዘላለም ምስክር ሲናገር “ዘላለም አብሮኝ ተጫውቷል። በተጫዋችነት ዘመኑ በራሱ የሚተማመን ጎበዝ ተጫዋች ነበር። በተለይ ከመስመር ይዞ ወደ መሐል የሚገባበት መንገድ ከሌሎቹ ተጫዋቾች ልዩ ያደርገዋል። ከፍተኛ ፍጥነት አለው፣ ይሮጣል፣ ጠንካራ ምቶች ያሉት የማይፈራ ተጫዋች ነው። የግድ አሰልጣኝ በሚለው ብቻ አይደለም፤ ከመስመር ወደ መሐል መግባት ካለበት የሚገባ፣ ቀጥተኛ የመሰለውን የሚናገር የሚናገረውም እውነት የሆነውን ነው። በዛ ላይ በጣም ቀልደኛ እና ተረበኛ ነው። በዚህም ቀልደኛ ባህሪው ብዙ ሰው ይወደዋል። በርከት ያሉ ክለቦች ተዟዙሮ መጫወቱም ስለማይፈራ የትም ክለብ ሔዶ መጫወት እንደሚችል ሰለሚያውቅ ነው። አሰልጣኞች ሳይፈራ የሚናገር ለተጫዋቾች ጠበቃ ነው። በአጭሩ ዘላለም በጣም ብዙ አቅም ያለው ትልቅ ተጫዋች ነበር።”

ሃያ ዓመታት በዘለቀው የእግርኳስ ሕይወቱ የመጨረሻው ክለቡን ሰበታ ከተማ በማድረግ በ2006 በመላው አውሮፓ የኢትዮጵያውያን ውድድር በክብር አንግድነት ተጋብዞ በሄደበት ሳይመለስ ከሀገሩ ከወጣ ሰባት ዓመት ሆኖታል። አሁን ኑሮውን በለደን ከተማ በማድረግ እየኖረ የሚገኘው ይህ የዘጠናዎቹ ምርጥ ተጫዋች ከሚኖርበት ሀገር ከረጅም ዓመት በኃላ አግኝተነው በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ አናግረነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል። መልካም ቆይታ…

“የስኬት ጊዜዬ የምለው 1989 ላይ ከጊዮርጊስ ወደ መብራት ኃይል ተጉዤ ነብሳቸውን ይማረውና ከእነ ጋሽ ሐጎስ ጋር ዋንጫ ያነሳንበትን ዓመት ነው። ከዚህ በመቀጠል ቡና ገብቼ ጊዮርጊስን አሸንፈን የአሸናፊዎች አሸናፊን ዋንጫ ስናነሳ ደስ ብሎኛል። በተጨማሪም ወደ መጨረሻው የእግርኳስ ሕይወቴ ሜታ አቦ ገብቼ ቡድኑን ወደ ብሔራዊ ሊግ ለማሳደግ መቐለ ላይ የማጠቃለያ ውድድር በነበረ ጨዋታ ላይ ተጫውቼ ኮከብ ተብዬ የተመረጥኩበት ጊዜ ልዩ ስሜት ይሰጠኛል። ብቻ በአጠቃላይ የእግርኳስ ህይወቴን የጀመርኩበት እና ብዙ ነገር ያየሁበት ክለብ መብራት ኃይል ነው። ከዛም በኃላ የተጫወተኩባቸው ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኒያላ፣ እርሻ ሰብል፣ መድን፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አዲስ አበባ ውስጥ ከባንክ ውጪ ያልተጫወትኩበት ክለብ የለም። ወደ ክልል መቐለ፣ ወንጂ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ሜታ… እነዚህ የማስታውሳቸው ነው። ሁሉም ጋር ደስተኛ ሆኜ አሳልፌያለሁ።

“ረጅም ዓመት የመጫወት ሚስጢሩ የፈጣሪ ሥራ ነው። በህይወቴ የምበላውን ምግብ እና የምኖርበትን መንገድ መርጬ አላቅም፤ አስቤበትም አላውቅም። እንዳልኩት የፈጣሪ ሥራ ነው። ከዚህ በተረፈ ግን የሚገባውን እረፍት አርፋለሁ። በተጨማሪም ከልጅነቴ ጀምሮ ስፖርት በጣም እሰራ ነበር። ነብሱን ይማረው እና ቢረጋ ይሰጠን የነበረው ልምምድ በጣም ጥሩ ነበር። የተመጣጠነ እና ለሰውነት ተስማሚ የሆነ ልምምድ ነበር መብራት ኃይል እያለ ሲያሰራን የነበረው። ለዚህም ነው አሁን ያለኝ አካላዊ ቁመና ጥሩ የሆነው። ብዙ ሰዎችም በዚህ ይገረማሉ። ግን ምንም ሚስጥር የለውም።

“የአርበኛ ቤተሰብ ውስጥ ከአያቶቼ ጋር ነው ያደግኩት። ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ እና ሥነ-ምግባር ባላቸው ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግኩት። በመብራት ኃይልም አሰልጣኞቹ እና ኮሚቴዎቹን ጨምሮ እንደአባት ሆነው በጣም ሥነ- ስርዓት ያለበት ቤት ውስጥ አድጌያለው። በዚህ ሁኔታ ካደግኩ በኋላ ለማንም የማልሽማቀቅ ሰው ሆኛለሁ። በኳስ ላይም የሚመስለኝን እናገራለው። የማይመስለኝን እተዋለው። ራሴ ጥዬ ወጣለው እንጂ ተገፍቼ የወጣሁበት ጊዜ የለም። ‘ጎበዝ ነው ይጫወታል፤ ንግግሩ ግን ከባድ ነው’ ይሉኛል። ልክ ነው ኢትዮጽያ ውስጥ ብዙ የሚያስቸግር ነገር አለ። ያልተለመደ ቢሆንም በመሥራቴ እና በችሎታዬ ስለሚፈልጉኝ በቃኝ ብዬ እስክወጣ ድረስ በጥሩ ሁኔታ ተጫውቻለው። አሁንም ቢሆን እስከ ህይወቴ ፍፃሜ ለፕሬዘዳንትም ቢሆን ያልመሰለኝን ነገር እናገራለሁ።

“ምንም የሚቆጨኝ እና የማዝንበት ነገር የለም። ፈጣሪ የሰጠኝን ጥበብ ተጠቅሜ ነው 20 ዓመት የተጫወትኩት። በቆይታዬም በጣም ደስተኛ ነኝ። አሁን ራሱ ኳስ አቁሜያለው ማለት አልችልም። በክለብ እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ መጫወት የምችልበትን እድል ባገኝ መጫወት እችላለሁ። ግን በትልቅ ደረጃ ኳስ መጫወት ያቆምኩት 2006 ላይ በሰበታ ከተማ ክለብ ነው። ኳስ እንዳቆምኩም ወደ እንግሊዝ ተጓዝኩ። አሁንም እንግሊዝ ነኝ። እንደውም ስድስት ዓመት ሆኖ በአብዛኛው ጊዜ እየተጫወትኩ ነው። በሀገር ውስጥ ክለብ ካገኘው አሁንም መጥቼ መጫወት እችላለሁ (…እየሳቀ)

“ብዙ ገጠመኞች አሉ። ግን በሴካፋ ውድድር ያጋጠመኝን ነገር ላጫውትህ። ለዚህ የሴካፋ ውድድር ዩጋንዳ ሄደን ነበር። በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ነብሱን ይማረውና አሰግድ ተስፋዬ፣ ብሩክ እስጢፋኖስ እና አሸናፊ በጋሻው ነበሩ። እና ሆቴላችን በር ላይ የሆኑ ፈረንጆች በመኪና ውስጥ ፍራፍሬ ጭነው ቆመው አየን። ከዛ ሄደን እንደ ራሳችን ንብረት አንስተን መመገብ ጀመርን። ፈረንጆቹ ሲመጡ ፍራፍሬያቸው መቀነሱን አይተው በጣም ይቆጡ ጀመሩ። በዚህ ሰዓት ብሩክ እኛ እንደበላነው ነግሯቸው ሮጠን ያመለጥንበት እና የተደበቅንበትን ጊዜ አልረሳውም።

“የኢትዮጵያን እግርኳስ እከታተላለው ፤ ስመጣም ገብቼ አያለው። በአብዛኛው ደርሼባቸዋለው። አሁን ብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱ ጓደኞችም አሉኝ። እናወራለን፣ እናጫወታለን፤ እከታተላለው።

“ማንዴላ የሚለው ቅፅል ስም የወጣልኝ ይመስለኛል መብራት ኃይል B እና C እያለን እየተመራን በመጨረሻ ደቂቃ ጎል አስቆጥር ነበር። እንደውም አንድ አብሮ አደጌ ነበር፤ እሱን አልፌ ሁለት ግብ ያገባውበትና ያሸነፍንበት ወቅት ነበር። በዛ ምክንያት እንደቀልድ ነበር ስሙ የወጣልኝ። በመጨረሻ ደቂቃ ጎል እያስቆጠረ ከመሸነፍ ‘ነፃ አወጣን’ በማለት ከነፃ አውጪው የደቡብ አፍሪካው ታጋይ ማንዴላ ጋር አያይዘው ስም አወጡ እንጂ ከታላቁ መሪ ጋር በመልክም አንመሳሰልም።

“ክለብ የምቀያይረው ምክንያቱ እኔ ያደግኩት መብራት ኃይል ቤት ነው። እዚያ ደግሞ ከሁሉም የተሻለ እግርኳስን የሚያውቁ ሰዎች ነበሩ የሚያሰለጥኑን። ለምሳሌ C ላይ ነፍሱን የማረውን እና ዘሩ ቢረጋ ፣ B ላይ እነጋሽ ታዴ ፣ ወንድምአገኝ ፣ ተስፋዬ(ቱታ) በመንግሥቱ ወርቁ ውስጥ ያለፉ የእርሱን አሰለጣጠን የያዙ በጣም በሚገርም ሁኔታ የሚያሰለጥኑ ናቸው። ገና C እያለን ነው dribbling , accuracy , cross , free kick ሁሉን ነገር የጨረስነው። እኔ መብራት ኃይል C ያየሁትን ሌላ ክለብ ዋናው ቡድናቸው ላይ እንኳን አይሰሩትም። እዛ ደረጃ ላይ እያለን ነበር በቀኝም በግራም ከ30 ሜትር የተሳካ ኳስ እናቀብል የነበረው። ብሔራዊ ቡድን ላይ ተጠርተህ ይህን ማድረግ ካልቻልክ ምኑን ተጫዋች ሆንከው ? በዚህ መንገድ እላይ ወጥቼ ይህን ከማያውቁ አሰልጣኞች ጋር ስጓተት ወይ ሽልማት ላይ ካሳነሱኝ ወይም ሌላ ጓደኛዬን ከበደሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ድረስ ገብቼ ሁሉን ነገር የማስተካክል ሰው ነኝ። አይሆንም ብለው ከእኔ ጋር የሚበጣበጡ ከሆነ ግን ክለቡን ጥዬ ሄዳለው እንጂ ተጨቁኜ ፣ ወደዛ ወደዚህ ሁን ተብዬ ፣ ደመወዝ እየተቀጣው የምቀመጥ ሰው አይደለሁም። ሌላ ጋር እሄዳለው መድኃኒያለም ካለ እሰራለው እገባለው እጫወታለው ፤ የኖርኩት እንደዚህ ነው። እሺ የምል ሰው አይደለሁም ፤ የማልቆይበት ምክንያት ከአሰልጣኞች ጋር ስለማልግባባ ነው። ምክንያቱም አስተምሮ ፣አንፆ ፣ ከጥፋት መልሶ ፣ መክሮ እንድትስተካከል የሚያደርግህ አሰልጣኝ የለም። ከአሰልጣኝ የማደንቃቸው ነፍሳቸውን ይማር ጋሽ ሀጎስ ደስታን ነው። ብታጠፋ፣ ብታድር ፣ ብትጠጣ ከቤትህ መጥተው ጠርተው አስተምረው አሳውቀው ጥሩ ሰው እንድትሆን ያደጉሀል። ሰውነት ቢሻውም ልክ እንደዚህ ዓይነት ባህሪ ነው ያለው። በጣም በብዙ ነገር እንድትቀረፅ ፣ ትዳር እንድትይዝ ፣ ብታጠፋም እንድትስተካከል እንጂ ይጥፋ ፣ ይባረር አይልም። አሥራት ኃይሌም ቆንጆ ባህሪ አለው። ተጨዋች እንዲከፋ ፣ እንዲጎዳ ፣ እንዲባረር አይፈልግም። ከዛ በተረፈ በጣም ብዙ አሰልጣኞች አይቻለው። እግርኳሱን እና ፖለቲካውን አንድ ነው የሚያደርጉት። እናጥፋው ፣ እናባረው ማለትን እንጂ አስተምሮ የሚያንፅ ማንም የለም።

“የአሰልጣኝ ኮርስ እየተከታተልኩ ነው። ወደ ፊት ወደ አሰልጣኝነቱ እገባለው የሚል ተስፋ አለኝ። በእግርኳሱ ላይ ያሳለፉ ሰዎች ጥሩ ሥነምግባር ካላቸው መልካም ነገር ይሰራሉ ብዬ አስባለው። አሁን ላይ ኳሱ እየወረደ እንዳለ ነው የሚሰማኝ። ወይ ወጣቶቹ አሰልጣኞች ሥራውን ቢሰሩ መልካም ነገር ይመጣል ብዬ አስባለው ፤ እኔ ግን ኮርሱን እየተከታተልኩ ነው። ወደ አሰልጣኝነቱም እመጣለሁ ብዬ ነው የማስበው።

“የቤተሰብ ህይወቴ አባት የለኝም እንጂ እናቴ ፣ ወንድሞቼ እና እህት አለቺኝ። ከዛ ባለፈ ግን እንደቤተሰብ የምወዳቸው እና የሚወዱኝ በየዓለማቱ ብዙ ሰዎች አሉኝ። ጓደኛም አለቺኝ አብረን ነው የምንኖረው።

“መጨረሻ ሳልናገር የማላልፈው የእኛ ሀገር አሰልጣኞች ብዙ ሊማሩ እና ሊያውቁ ይገባል። እኛ በነበርንበት ጊዜም እንደ አባት ገስፆ የመመለስ ነገር የነበራቸው እነ ሰውነት ቢሻው፣ አሥራት ኃይሌ ነፍሳቸውን ይማር ጋሽ ሐጎስ ጋር ቢሆኑም ሌሎቹ ልክ እንደ ፖለቲካ ድርጅት በለው፣ ቁረጠው፣ ፍለጠው፣ 20% ደመወዝ ይቆረጥ፣ ከክለብ ይባረር ነው። እንጂ ማንም አስተምሮ አሳውቆ የሚያሳልፍ አሰልጣኝ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ብዙ ተጫዋቾች ያለጊዜያቸው እንዲያቆሙ ሆኗል። እና ብዙ ስህተት አለ አሰልጣኞችም ጋር ይህ መታረም አለበት መልዕክቴ ነው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!