የሴቶች ገፅ | የመጀመሪያዋ የብሔራዊ ቡድን አምበል እየሩሳሌም ነጋሽ

ስኬታማዋ ተከላካይ እና የመጀመሪያዋ የብሔራዊ ቡድን አምበል እየሩሳሌም ነጋሽ የዛሬዋ የሴቶች ገፅ እንግዳችን ናት፡፡

አዲስ አበባ ለሀገር ከባቡር ጣቢያው ጀርባ በሚገኘው ሠፈር ውስጥ ነው ትውልድ እና ዕድገቷ። አካባቢው በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ እግርኳስ የሚዘወተርበት ስፍራ ስለነበረ የዛሬዋ እንግዳችንም ከመኖሪያ ቤታቸው ፊት ለፊት ወንዶች ሲጫወቱ ትመለከት ስለነበር እሷም መመልከትን ብቻ ሳይሆን ‘ለምን ጠጋ ብዬ ኳስን አላቀብልም ?’ ብላ ትነሳና ሌሎች ሲጫወቱ እሷ ደግሞ ኳስ እያመላለሰች ማቀበል ጀመረች። የቀድሞዋ ታዳጊ እየሩሳሌም ከማቀበል ባለፈ ለምን አልጫወትም በማለት ትመኝና የአስራ አምስት አመት ዕድሜ ላይ ሆና እግርኳስን ከወንዶች ጋር ተጣምራ መጫወት ጀመረች፡፡ ዕድሜዋ እየበሰለ ሲመጣ አቶ ዓለማየሁ የሚባል አንድ ግለሰብ የአካባቢውን ታዳጊዎች እየሰበሰበ በማዘጋጀት ውድድሮች ሲያደርግ ያኔ እየሩሳሌም ዕድሉን አገኘች።

በዚህ ውድድር ላይ እየተጫወተች እያለ አንዲት በአካባቢው ትኖር የነበረች ሰው ወደ እየሩሳሌም ጠጋ ትልና ወደ ተሻለ ፕሮጀክት እንድትገባ ሹክ ትላታለች። እሷም ሳታመነታ ጠንካራ ተጫዋቾችን በማፍራት ወደሚታወቀው የጋሽ ኢተፋ ፕሮጀክት ገብታ አራት ዓመታትን በሚገባ ስለ እግርኳስ የተሻለ ዕውቀትን ከቀሰመች በኃላ በአሁኑ ሰዓት በወንዶች እግርኳስ ላይ እየሰራ ወደሚገኘው እና በ1990ቹ አጋማሽ በሴቶች እግር ኳስ አሰልጣኝነት ይታወቅ ወደነበረው አሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ (ድሬ) ቡድን ወደ ሆነው አዲስ ኮከብ ተቀላቅላ በደንብ ራሷን እያበቃች አቅሟንም እያጠናከረች መጣች፡፡ እየሩሳሌም ወደ አዲስ ኮከብ ካመራች በኃላ ብዙ አመርቂ ስኬቶችን አስመዝግባ አልፋለች፡፡ ቡድኑ በአዲስ አበባ ዲቪዚዮን ተሳታፊ ሲሆን ዕድሉን አግኝታ የተጫወተች ሲሆን በቡድኑ ቆይታዋም ለአዲስ አበባ ምርጥ እንዲሁም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲቋቋም ለብሔራዊ ቡድን ተጠርቶ ከመጫወትም ባለፈ የመጀመሪያዋ አምበልም መሆን መቻሏን ወደ ኃላ መለስ ብላ አውግታናለች፡፡

ለብሔራዊ ቡድን የተከላካይ መስመር ጥንካሬን የፈጠረችው የያኔዋ ተጫዋች ዩጋንዳን ከገጠመው ስብስብ በኃላ ኩዊንስ ኮሌጅ የተባለ የእግርኳስ ክለብ ይፈልጋት ስለነበር ያለማቅማማት ጥያቄውን ተቀብላ የክለብ ህይወቷን ጀመረች፡፡ “ከብሔራዊ ቡድን ስንመለስ አብዛኛዎቻችን ተጫዋቾች የትምህርት ስኮላርሺፕ ተሰጥቶን ኩዊንስ ኮሌጅ ነው የገባነው። በርካታ አብረን የነበርን ተጫዋቾች አንድ ላይ በአንድ ቡድን ውስጥ ሆነን መጫወት ጀመርን። በደመወዝ ለአንድ ዓመት በዚህ ቡድን ውስጥ ከተጫወትኩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ቡና አመራሁ።” ስትል ከብሔራዊ ቡድን ተሳትፎዋ መልስ ስለነበራት ቆይታ ትናገራለች፡፡

በ1990ዎቹ በአዲስ አበባ ጥቂት ክለቦች ግን ደግሞ በርካታ ጥሩ አቅም ያላቸው ሴት እግርኳስ ተጫዋቾች በስፋት የታዩበት ወቅት ነበር። ከእነዚህም መካከል ደግሞ የአሁኗ አሰልጣኝ እየሩሳሌም ነጋሽ አንዷ ነች፡፡ በተለይ ለሴቶች እግር ትኩረት እንዲኖረው የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን እነ ጋሽ ሰዒድ ፣ ብርሀኑ ከበደ እና አቶ አፈወርቅን የመሳሰሉ ጠንካራ መሪዎች በሰዓቱ በመኖራቸው የሴት ተጫዋቾች ቁጥር ከፍ እንዲል የዲቪዚዮን ውድድርን ያሰናዱ ስለነበር እየሩሳሌም በዚህ ውድድር ላይ በስፋት ተጫውታ አሳልፋለች፡፡ በኩዊንስ ኮሌጅ በመጫወት ላይ እያለች ከደመወዝ ክፍያ መብለጥ እና ማነስ የተነሳ ቡድኑን ለመልቀቅ እንደተገደደች እና ባስገራሚ መልኩ ኢትዮጵያ ቡናን ስለተቀላቀለችቀት ወቅት ስትናገር “ከኩዊንስ ኮሌጅ ጋር በገንዘብ ነው የተጣላነው ፤ ለሁላችንም እኩል አልከፍል ስላለን። ክለቡ በወቅቱ ትክክል ነበር። የተሻለ አቅም ያላቸው የተሻለ ክፍያ ያስፈልጋቸዋል የቤንቾች ደመወዝ ደግሞ ማነስ አለበት ነበር የተባለው። በወቅቱ የነበረን ፍቅር የሚገርም በመሆኑ ‘አንፈልግም !’ ብለን ለእኛ የታሰበው ብር እኩል ይካፈለን አልን። ይሄ ሁኔታ ደግሞ አላግባባንም። እኔም ለቅቄ ወደ ኢትዮጵያ ቡና መጣሁ።” ትላለች።

አዳማ ላይ በነበረው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የአዲስ አበባ ምርጥን ወክላ በመጫወት ላይ እያለች በቀድሞው አንጋፋ አሰልጣኝ ማስተር አዳነ ተመልምላ ለሀገሯ ጥሪ ቀረበላት፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል የመሆን ዕድሉን 1994 ላይ አግኝታ ሀገሯን የመራችው እየሩሳሌም በሁለት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ተሰልፋ ከተጫወተች በኃላ እግሯ ላይ ከባድ ጉዳት ስለገጠማት ቀጣዩ የእግር ኳስ ህይወቷ በፈተና የተሞላ ሆኖባታል፡፡ “ለመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን የተመረጥነው ተጫዋቾች ብዛት ከ30 እንበልጣለን፤ ለስድስት ወራትም አብረን ቆይተናል። የመጀመሪያ ጨዋታችን ከስዋዚላንድ ነበር። አጋጣሚ የፎርፌ ዕድል አገኘንና አብረን መቆየት ቻልን። ከዛም ደብረዘይት እና ናዝሬት እየተቀያየርን እየሰራን ቆየን ፤ ጥሩ ጊዜም ነበር። እስከ አሁንም የሚወራ የሚነሳ ታሪካዊ ጊዜ ነበረን። ልጆች ሲቀነሱ በለቅሶ ተሸኛኝተን ሻንጣቸውን ይዘን እስከ መሸኘት ነበር ህብረታችን።” ስትል ስለ መጀመሪያው የብሔራዊ ቡድን ጊዜዋ መለስ ብላ ታነሳለች፡፡

በ17 ዓመቷ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጠርታ የልጅነት ህልሟን እንዳሳካች የምትናገረው እየሩሳሌም ከ1996 እስከ 2000 ድረስ ከኩዊንስ በኃላ በኢትዮጵያ ቡና በመጫወት ያሳለፈች ሲሆን በርካታ የዋንጫ ድሎችን በክለቡ ቆይታዋ አግኝታለች፡፡ የብሔራዊ ቡድን ጥሪን ተከትሎ መጠነኛ ጉዳት ቢገጥማትም ዳግም ከሁለት ዓመት በኃላ 1996 ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ትጠራ እንጂ ከዝግጅት ያለፈ ዕድሜ በሉሲዎቹ ስብስብ ሊኖራት አልቻለም፡፡ ጉልበቷ ላይ የገጠማት ጉዳትም ለአፍሪካ ዋንጫ የደቡብ አፍሪካው ውድድር እክል ሆኖባታል። ይሁን እና ለውድድሩ እንደምንም ለመድረስ በዶክተር ኤልያስ አማካኝነት ተጓዳኝ ስራዎች እና የጤና ክትትልን ብታደርግም ያሰበችው መሆን ሳይችል ቀርቷል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀዳሚ ተመራጭ ብትሆንም ጉዳት ቀስ በቀስ ያራቃት ተከላካይዋ በክለብ የኢትዮጵያ ቡና ቆይታዋ ምንም እንኳን ስሜቱ ሳይጠፋ ለክለቧ ታምና ራሷንም መስዋዕት አድርጋ ብትጫወትም በመጨረሻ ጉዳቷ እየባሰ በመምጣቱ ከጨዋታ ዓለም ለመራቅ ተገደደች። “ወደ እግርኳሱ ለመመለስ በደንብ ጥረት አድርጌያለው። ለመጫወት እሞክራለሁ አልችልም፣ ለመቆም እሞክራለሁ አልችልም ፤ ተመልሶ ይወልቃል። አንድ ሳምንት ክራንች እይዛለሁ፤ አልችልም፤ ተደብቄ ለመጫወትም እሞክራለው አልችልም። በጣም አሳዛኝ ህይወት ነበር የነበረኝ። ክትትል የሚያደርግልን ይስሀቅ ነበር። 1998 ላይ ነበር በጣም የተጎዳሁት። ተጎድቼ ቡና ነበር የምጫወተው። ጉዳት ላይ ሆኜ እንደ ምክትል አሰልጣኝ እንደ ቡድን መሪ፣ እንደ አምበል ነበርኩ። በሆነ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ቡና ሰዎች እግሬ ተጎድቶ መጫወት እየቻልኩ እንዳልሆነ ጋዜጣ ላይ ያነባሉ። ከዛም በቃ ራሳችን ውጪ ልከን እናሳክማታለን የሚል ሀሳብ አነሱ። 1999 ላይ ወደ ሳውዲ አረቢያ ልከው አሳከሙኝ። ይሄ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተደገመ ነው ፤ ሴት ተጫዋች ወደ ውጪ ልኮ በማሳከም። እንዲህም በማድረጋቸው ለእኔ ያላቸውን ቦታ ያሳየ ነበር። ታክሜ ከተመለስኩ በኃላ ግን ትልቅ ችግር የሆነብኝ አብሮ የሚያግዘኝ ሰው ባለመኖሩ በራሴ የልጅነት አቅም ዋናውንም የጂሙንም ሁሉንም ቡና ነው የቻለው። ይሄንን እኔም በግሌ ለማድረግ ጣርኩ። ከዛ ግን በድጋሜ አልቻልኩም። 2002 ላይ ማንም እንደሚያውቀው ከእግርኳስ ተለያየው። የኢትዮጵያ ቡና ጥረትም ሆነ የኔ ጉጉት ሳይሳካ ከእግርኳስ ተጫዋችነት ተለያየው።” በማለት ስለ አሳዛኙ ወቅት አውስታለች፡፡

እግር ኳስን በመጫወት ረጅም ህልምን ለማሳካት ብታትርም ነገሮች አልጋ በአልጋ ሊሆኑላት ያልቻለችው እንስቷ ለአምስት ዓመታት ከእግር ኳሱ ዓለም ጠፍታ 2007 ላይ በወሰደቻቸው የአሰልጣኝነት ኮርሶች ወደምትወደው ኢትዮጵያ ቡና ተመልሳ የአሰልጣኝ መርሻ ሚደቅሳ ረዳት በመሆን የሥልጠናውን ዓለም መቀላቀል ቻለች። 2008 ደግሞ የዋና አሰልጣኝነት ሚና ተሰጥቷት ክለቡን አሰልጥናለች፡፡ ጥሩ የሆነ ቡድን ገንብታ በውጤት ረገድ ባይሳካላትም በሦስቱ ዓመታት ግን ለክለቡ አቅም ያላቸው አዳዲስ ፊቶችን በማብቃቱ ረገድ የነበራት ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ በዚህም ፈጣን ግን አጭር የአሰልጣኝነት ዕድሜዋ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ረዳት አሰልጣኝም ሆኖ የመስራት ዕድሉ አላመለጣትም። ከአሰልጣኝ መሠረት ማኒ ጋር በጣምራ ሀገሯን ካገለገለች በኃላ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ አምርታ ክለቡን በዋና አሰልጣኘነት ተቀጥራ መስራት የቻለች ሲሆን በክለቡ ቆይታዋም ውል እያላት በመሰናበቷ በርካታ ውዝግቦች የተነሱበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል፡፡ሆኖም በስተመጨረሻ በፌድሬሽኑ ጉዳይዋ ውሳኔን ካገኘ በኃላ ከአሰልጣኝነት ለመራቅ ተገዳለች።

“የተሻለ ክለብ ከመጣ እና ቀስ በቀስ ለአዳዲስ ተጫዋቾች ትኩረት የሚሰጥ ክለብ ካለ አሁንም ለማሰልጠን ዝግጁ ነኝ” የምትለዋ አሰልጣኝ እየሩሳሌም ከአሰልጣኝነት ባለፈ በሴቶች አዕምሯዊ ዕድገት ላይ ለመስራት በትምህርት ላይ የምትገኝ ሲሆን በቀጣዩ በስፋት ፕሮፌሽናል አስተሳሰብን ተግባራዊ ለማድረግ በምትማርበት የትምህርት መስክም ሆነ በአሰልጣኝነት ህይወቷ ለመስራት ዕቅድ መያዟን ነግራናለች፡፡ ከዚህም በዘለለ በሴቶች ላይ በርካታ ለውጦች የሚያመጡ የመሪነት ሀሳቦች ላይ እና የማማከር ሥራንም በተጨማሪነት ለመሥራት ማቀዷን ገልፃልናለች፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ያጋሩ