ለምትወደው ሙያ ራሷን የሰጠች፣ በሳል፣ ንቁ እና ልበ ሙሉ ዳኛ የነበረችው፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሀገሯን በመወከል ያገለገለችው፣ የቀድሞ የሉሲዎቹ ግብጠባቂ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትርሀስ ገብረዮሐንስ የዛሬው የዳኞች ገፅ አምድ እንግዳችን ናት።
በሴቶች ቡድን ውስጥ ከተለያዩ ክለቦች እስከ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በግብጠባቂነት አገልግላለች። ከተጫዋችነቷ ጎን ለጎን ወደ ዳኝነቱ በመግባት በከፍተኛ ፍጥነት ካሳየቸው ብቃት የተነሳ እስከ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት መድረስ ችላለች። በሀገር ውስጥ ከሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንስቶ የወንዶች ፕሪምየር ሊግን በጥሩ መንገድ ስትዳኝ ቆይታለች፣ ከሀገር ውጭ በካፍ እና በፊፋ በሚካሄዱ የዓለም አቀፍ ውድድሮች ለቁጥር የሚበዙ የአፍሪካ፣ የዓለም የሴቶች ዋንጫን ተመድባ በጥሩ ብቃት ተሳትፎ አድርጋ ተመልሳለች። ምን አልባትም በድንገት ዳኝነት አቆመች እንጂ ከዚህ በላይ በትላልቅ መድረኮች ሀገሯን የመወከሏ ዕድሏ ከፍተኛ መሆኑ መገመት ይቻላል። በ2006 በካናዳ አስተናጋጅነት ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ለመዳኘት በሄደችበት አጋጣሚ በደረሰባት የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ህክምና እያደረገች እዛው ለመኖር ተገዳለች። ከሀገሯ ከወጣች ሰባት ዓመት የሆናት ትርሀስ ገብረዮሐንስ ካለችበት ሀገረ ካናዳ አግኝተናት በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን እንግዳ አድርገናት እንደሚከተለው ሀሳቧን አጋርታናለች።
ትውልድ እና ዕድገትሽ ከየት እንደሆነ እንድትገልጪልኝ በመጠየቅ ልጀምር
ለቃለመጠይቁ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ። የተወለድኩት አዳማ በቀድሞ አጠራር ናዝሬት ልዩ ስሙ ቀበሌ አስራ አምስት ቆርቁራ በሚባል ሰፈር ውስጥ ነው። በዚሁ አካባቢ ለእግርኳስ ከነበረኝ ፍቅር የተነሳ እጫወት ነበር። በኃላም ከፍ ስል በተለያዩ ክለቦች እስከ ብሔራዊ ቡድ ድረስ መጫወት ችያለው።
በቀጥታ ዳኛ ከመሆንሽ በፊት እግርኳስ ተጫዋች ነበርሽ። እስቲ የእግርኳስ ህይወትሽን በጥቂቱ አካፍይኝ?
ጥሩ የእግርኳስ ህይወት ነበረኝ። በተለያዩ ክለቦችም በግብጠባቂነት ተጫውቻለው ለምሳሌ ኤግልስ፣ አለቤ-ሾው፣ ኢትዮጵያ ቡና በሌሎችም ክለቦች ተጫውቻለው። ከወረዳ እና ዞን ጀምሮ እስከ ኦሮሚያ ምርጥ ድረስ ተጫውቻለው። እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብጠባቂነት መጫወት ችያለው።
የዳኝነት አጀማመርሽ እንዴት ነበር ?
ዳኛ ለመሆን የቻልኩት በአጋጣሚ ነው። ከጓደኛዬ ጋር ሆነን ጨዋታ ለመመልከት ወደ አዳማ ስንሄድ ግቢ ውስጥ የዳኝነት ኮርስ ስልጠና እንደሚሰጥ ማስታወቂያ እንመለከታለን። ለምን አንመዝገብም በማለት በአጋጣሚ ለቀልድ ብለን እንጂ ዳኛ እሆናለው ብዬ አላሰብኩም ነበር። ተመዝግበን ስታዲየም ስንመጣ ግን በርካታ ዳኞች እና ትልልቅ ሰዎች ተሰብስበው ተመለከትን። በጣም ፈራን፤ ልጅነትም ስለነበር” በኃላ ባልሳሳት ኢንስትራክተር ለገሰ መኮንን ይባላሉ አሁን በሕይወት የሉም ነፍሳቸውን ይማር “ምን ልትሰሩ መጣችሁ” ሲሉ “ዳኛ ለመሆን ተመዝገብ ነበር የመጣነው” አልናቸው፤ እሳቸውም በጣም ደስ አላቸው። በወቅቱ ብዙ ሴት ዳኞች ስላልነበሩ በጣም ደስ ብሏቸው “እንዳትቀሩ ኑ” እያሉ እያበረታቱን መምጣት ጀመርን። በነገራችን ላይ ፈቲያ ትባላች ጓደኛዬ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናት እወዳለው። እርሷ ናት እንድቀጥል በርቺ እያለች ትመክረኝ የነበረው። ኮርሱን ወሰድኩና አለፍኩ። በቃ ሰፈር ውስጥ ማጫወት፣ አዳማ ሲ ቡድን ሌሎች የወዳጅነት ጨዋታዎች ማጫወት ጀመርኩ። በቃ ዳኝነትን እየወደድኩት መጣሁ። ከዛም አዳማ ላይ በኢንስትራክተር ለገሰ መኮንን አማካኝነት መምርያ ሁለት ኮርስ መውሰድ ችያለው።
ከፍ ወዳሉ የዳኝነት ደረጃዎች እና ወደማጫወት መቼ መሻገር ቻልሽ ?
መምርያ ሁለት እና አንድ ከወሰድኩ በኃላ ከፍ ያሉ ውድድሮችን በአዳማ ከተማ ላይ እያጫወትኩ እስከ ወንጂ ድረስ እየሄድኩ አጫውት ነበር። በኃላ የዳኞች ኮሚቴ የነበሩት አቶ ፀሐዬ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበሩ። እርሳቸው እድሉን አመቻችተውልኝ አዲስ አበባ በመምጣት የማሻሻያ ኮርስ እንድወስድ ተደረኩ። እናቴ አዲስ አበባን ስለማላቀው ለሚኪኤሌ አርዓያ አደራ ብላ ሰጠችው። በዚህ አጋጣሚ እርሱንም አመሰግናለው። ኮርሱን ወስጄ አስታውሳለው በአዲስ አበባ ስታዲየም የወዳጅነት ጨዋታ በትልቅ ደረጃ መምርያ አንድ ሆኜ ልምድ እንዳገኝ ተብሎ በወቅቱ ከነበሩ ጋር አራተኛ ዳኛ ሆኜ የማጫወት እድል አገኘሁ። ከዛም በመቀጠል የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሰው ሲጎድል ወንጂ ላይ አራተኛ ዳኛ ሆኜ የማጫወት አጋጣሚ አግኝቻለው።
ፌደራል ዳኛ ለመሆን ብዙ ጊዜ ወሰደብሽ ወይስ ወድያውኑ ብዙ ሳትቆዪ እድሉን ያገኘሽው?
ብዙ አልቆየሁም። ፌደራል የሆንኩት በ1996 ቢሾፍቱ ላይ በተዘጋጀ ስልጠና ነው። የቢሾፍቱ የዳኞች ኮሚቴን አመሰግናለው። ከአዳማ ወደ ደብረዘይት መጥቼ ኮርሱን እንድወስድ ፈቅደውልኝ አንድ ዓለምገነት የምትባል ጓደኛ ነበረችኝ፤ ያለምንም ወጪ ቤቷን ፈቅዳ እርሷ ጋር አርፌ እየተመላለስኩ የፌደራል ኮርስ መውሰድ ቻልኩ። አሁንም በድጋሚ ዓለም ገነትን ከነ መላው ቤተሰቦቿ ሳላመሰግን አላልፍም። ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱን እንዲሁ መምርያ አንድን እና ፌደራል ኮርሱን የሰጡኝ እርሳቸውን ማመስገን እፈልጋለው። ፌደራል ከሆንኩ በኃላ የተለያዩ ጨዋታዎችን ለሦስት ዓመት ማጫወት ችያለው።
እግርኳሱን አቁመሽ ነው ዳኛ የሆነሽው ወይስ ሁለቱን አማክለሽ ትሰሪ ነበር ?
ዳኛ ሆኜ እግርኳስን አላቆምኩም ነበር። ተደብቄ ኳሱን እጫወት ነበር። ይሄን ያህል በዳኝነቱ ረጅም ርቀት እሄዳለው ብዬ አላሰብኩም ነበር። ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆኜ ሁሉ እግርኳሱን እጫወት ነበር። በኃላ “አቁሚ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆነሽ ትልልቅ ውድድሮች ከሀገር ውጭ ቢመጣልሽ አይሆንም” ተባልኩና እሺ ብዬ እግርኳሱን አቆምኩ። ከዛም ነበር ሙሉ ለሙሉ ወደ ዳኝነቱ አዘንብዬ ማጫወት የቻልኩት።
ወደ ኢንተርናሽናል ዳኝነቱ እንዴት ገባሽ?
ወድያው ወድያው ነው ደረጃውን እያገኘሁ ወደ ኢንተርናሽናል ዳኝነቱ ከፍ እያልኩ የመጣሁት። በፌደራል ዳኝነት የተለያዩ ውድድሮችን እያጫወትኩ እያለው በ1999 በእኛ በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ይመስለኛል ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆንኩ። ከዚህ በኃላ በወቅቱ ከነበሩት ሊዲያ፣ ጽጌ፣ ሰርካለም፣ ሳራ፣ ተስፋነሽ እና ሌሎችም ዳኞች ጋር ሆነን የተለያዩ አፍሪካ ውድድሮች በመሄድ ማጫወት ጀመርኩ። የመጀመርያ ጨዋታዬ ግብፅ ላይ ይመስለኛል።
በፊፋ ውድድር በረዳት ዳኝነት ያጫወትሽ የመጀመርያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት ረዳት ዳኛ ነሽ ?
አዎ ኢንተርናሽናል ዳኛ ከሆንኩ በኃላ የተለያዩ ውድድሮችን በተለያዩ ሀገሮች ብቻዬንም በመሆን ከነ ሊዲያ፣ ጽጌ፣ ሰርካለም፣ ተስፋነሽ፣ ሳራ ጋርም እየሆንኩ እያጫወትኩ ሳለ ካሜሩን ላይ በተካሄደው የአፍሪካ የሴቶች ዋንጫ ማጫወት ችያለው። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። በዚህ ውድድር ባሳየሁት አመርቂ ተሳትፎ በረዳት ዳኝነት አንደኛ በመሆን የዓለም ዋንጫን ለማጫወት የመጀመርያዋ ሴት ኢትዮጵያዊ በመሆን ተመረጥኩ። በፊፋ ደረጃ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን የወከለ ዳኛ አልነበረም እኔ የመጀመርያ ሆንኩኝ። በኢትዮጵያ 2006 ካናዳ ላይ የተዘጋጀውን ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ለማጫወት ችያለው።
የመጀመርያዋ ሴት የፊፋን ውድድር የመራሽ ረዳት ዳኛ በመሆንሽ ምን ተሰማሽ ?
የመጀመርያዋ የፊፋን ውድድር ያጫወትኩ ኢትዮጵያዊ ሴት ረዳት ዳኛ በመሆኔ እውነት ለመናገር በጣም ነው ክብር የተሰማኝ፣ ደሰም ያለኝ። ካናዳም ጥሩ ቆይታ ነበር ያደረኩት። ወደ ካናዳ እሄዳለው ብዬ አልጠበኩም ነበር።
የወንዶች ፕሪምየር ሊግን አጫውተሻል ?
አዎ በብዛት የወንዶች ፕሪምየር ሊግ ነው ያጫወትኩት። ኢንተርናሽናል ከሆንኩ በኃላ ትላልቅ ጨዋታዎች ለምሳሌ ቡና፣ ጊዮርጊስ፣ መከላከያ ሌሎች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችን አጫውቻለው። የመጀመርያው የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ያጫወትኩት መድን ከ ባንክ ነበር።
ኮከብ ዳኛ በመሆን ወይም በተለያዩ ስልጠናዎች ላይ ስላገኘሻቸው ሽልማቶችን አጫውቺኝ ?
ዓመተ ምህረቱን አላስታወስኩም እንጂ በወንዶችም፣ በሴቶችም ኮከብ ረዳት ዳኛ ተብዬ ሽልማት አግኝቻለው። በተለያዩ የኤሊት ኮርሶች ላይ በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገር በመውሰድ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቻለው። በአንድ ወቅት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ ሳህሌ የኳስ ሽልማት እንደሸለሙኝ አስታውሳለው። ለመላው አፍሪካ ውድድር ከመሄዳችን በፊት በተሰጠ ኮርስ ላይ ስልጠናውን ከወሰዱ ሰልጣኞች በጥሩ ውጤት ተሸላሚ ሆኛለው። እንዲሁም የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ረዳት ዳኛ ሆኜ ተተሸልሜያለው።
በዳኝነት ህይወትሽ የማትረሽው ገጠመኝ አለሽ ?
ብዙ ቢኖርም ከሊዲያ ጋር የመላው አፍሪካ ውድድር ለመዳኘት ሄደን ነበር። እንደሚታወቀው የመላው አፍሪካ ውድድር ወንዶችም፣ ሴቶችም የሚወዳደሩበት ብዙ በሺህ የሚቆጠሩ ስፖርተኛ የሚሳተፉበት ውድድር ነው። ኤርፖርት ሆኖ የሚቀበለን በኃላም ወደ ዳኞች ካምፕ ይዞን የሚሄድ አንድ ሰው ተመድቦልን ነበር። ከኤርፖርት ተቀብሎን ወደ ማረፊያችን ይዞን እንዲያሳየን የተመደበው ሰው ቦታው ጠፍቶበት ሲያንከራትተን ያመሸውን መቼም አረሳንም። እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ድረስ ማረፊያችንን ፍለጋ ስንዞር አመሸን እንደገባችሁ ደግሞ ሪፖርት አድርጉ ተብለናል። በቃ እኔ እና ሊዲያ ፈራን። ምንድነው ይሄ ሰውዬ ብለን ተጨንቀን ስንከራተት በየመንገዱ ሲያዞረን ሲጠይቅ አምሽቶ በመጨረሻ አንዲት ግብፃዊ ተጠይቃ እርሷ አሳየችን። ምግብ የሚበላው በህብረት ነበር። አልቆ ሳንበላ ያደርንበትን ጊዜ መቼም አረሳውም። እርግጠኛ ነኝ ይህን ገጠመኝ ሊዲያም ታስታውሰዋለች (…እየሳቀች)
ሌላው ያጋጠመኝን አስቂ ነገር ልንገርህ ካሜሩን ከጋና ጋር መሰለኝ እየተጫወቱ ሊዲያ ዋና ዳኛ፣ እኔ ረዳት ነበርኩ። ጨዋታው የግማሽ ፍፃሜ ነበር። በወቅቱ ከፍተኛ፣ ኃይለኛ ሙቀት ነበር። ብንለው ብንለው ጨዋታው አላልቅ አለን። ሙቀቱ ከፍተኛ ነው። ጨዋታውን ካሜሩን አንድ ለዜሮ እየመራች ሊያልቅ አንድ ደቂቃ ጭማሪ ተሰጠ። አለቀ በቃ ስንል አንዷ ነፃ ኳስ አግኝታ ወደ ጎል ስትሮጥ ያው የጆሮ የሬዲዮ መገናኛ አለን በዛ ነው የምናወራው ሊዲያ “ወይኔ ሄደችልሽ ልታገባው” ብላ ተናገረች። ያው ጎል ከገባ አቻ ሆነው ጭማሪ ደቂቃ ሊሰጥ ነው። እኛ ደግሞ ሙቀቱን አልቻልነውም። ጎል ከገባ ደቂቃ ተጨምሮ መቆየት ከሙቀቱ አንፃር ከባድ ነበር። ሊዲያ ሄደችልሽ እያለች ስትነግረኝ አይዞሽ እመቤቴ አለች አታገባውም ያልኩበት አጋጣሚ (… እየሳቀች) በጣም የሚያስቀኝ ገጠመኝ ነው።
የሚያውቁሽ ያውቁሻል። ግን ለማያውቁሽ ግን ትርሀስ ምን ዓይነት ዳኛ ነበርሽ እስቲ ራስሽን ግለጪልኝ ?
ስለ ራስ መናገር በጣም ከባድ ነው። ተናገሪ ካልከኝ ግን ትርሀስ ማለት በሥራ የምታምን፣ ላመነችበት ሙያ መስጠት የሚገባውን ለመስጠት መስዋዕትነት የምትከፍል፣ በዲሲፕሊን ረገድ ራሷን ለሙያው ያስገዛች፣ ልምምዷን በሚገባ የምትሰራ፣ በየጊዜው የሚወጡ የተሻሻሉ ህጎችን ለማወቅ የምትጥር፣ ሙያው የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ራሷን ያዘጋጀች ዳኛ ነበረች።
በዳኝነት ህይወትሽ እዚህ ለመድረስሽ የስኬቴ ሚስጢር ምድነው ትያለሽ?
መሠረቴ ይመስለኛል። በኮተቤ ኮሌጅ በስፖርት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዲፕሎማ አለኝ። እርሱ የራሱ አስተዋፅኦ ነበረው። እግርኳስ ተጫዋች ሆኜ በማለፌ የረዳኝ ነገር ቢኖርም ለዳኝነት ካለኝ ፍቅር የተነሳ በሁሉም መልኩ የነበረኝ ጥረት ስኬታማ አድርጎኛል።
ከሀገርሽ ከወጣሽ ምንያህል ጊዜ ሆነሽ?
ከሀገሬ ከወጣው አሁን ወደ ስድስት ዓመት አካባቢ ሆኖኛል። የምኖረውም በካናዳ ነው። የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ለዓለም ዋንጫ ሄጄ እንዳጋጣሚ የጡንቻ መሰንጠቅ አጋጥሞኝ በዛው እየታከምኩ ትዳር መስርቼ እየኖርኩ ነው። የዳኝነት የመጨረሻ ጨዋታዬ ፈረንሳይ ከ ኔዘርላንድ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ነው። ፈረንሳይ 4-1 ያሸነፈችበት ጨዋታ ነበር።
ዳኝነትን ቶሎ ነው ያቆምሽው ማለት ይቻላል። ብትቆዪ ብዙ ተጨማሪ ስኬቶች ይኖሩሽ ነበር?
አዎ! ብቀጥል እንደነበረኝ አቅም እና ደረጃ ብዙ ሥራ እሰራ ነበር፤ እንዳውም ከጉዳቴ በፍጥነት የምመለስ መስሏቸው ፖርቹጋል እና ኳታር የፊፋ ኮርስ መጥቶልኝ ነበር። አለመዳኔን ነግሬያቸው ነው በኔ ምትክ አንዲት አፍሪካዊት ዳኛ በተጠባባቂነት ስለነበረች ነው እርሷ የገባቸው እንጂ የአፍሪካም የዓለም ዋንጫም እሰራ ነበር። ፈጣሪ አልፈቀደውም። አሁንም ዳኝነትን አልፎ አልፎ በምኖርበት ከተማ አጫውታለው። በተለይ በ2009 በካናዳ በተካሄደው የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ውድድር ላይ በዳኞች ኮሚቴ በማስተባበር፣ በማጫወት ከመክፈቻው ጨዋታ ጀምሮ እስከ ፍፃሜ የዋንጫ ጨዋታ ድረስ በረዳትም በዋና ዳኝነትም ከአንድ ኤርትራዊ ተሀ ይባላል ዳኛ ጋር ሰርቻለው። በዚህ አጋጣሚ ተሀን ማመስገን እፈልጋለው። የውድድሩን የፍፃሜ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት የዘጋሁት እኔ ነኝ። በመቀጠልም የተለያዩ የከተማውን ውድድር እያጫወትኩ ልጅ መጣ፣ ኮቪድም መጣ። ለጊዜው አሁን ዳኝነትን አቁሜለው።
ካለሽ ዓለም አቀፍ ልምድ አኳያ በዚህ ዘመን ለሚገኙ እና ለወደፊቶቹ ዳኞች ምን ምክር ታስተላልፊያለሽ?
አንደኛ የሙያው የሚፈልገውን ነገር ማድረግ። በማንኛውም ነገር ሊሆን ይችላል። ህጎችን ማወቅ ሊሆን ይችላል፤ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ይሆናል። እንዲሁም የቀለም ትምህርታቸው ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው። በምንም ሁኔታ ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ ተስፋ ሳይቆርጡ ከትንሽ ደረጃ ተነስተው ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚችሉ አዕምሯቸውን አሳምነው ይቻላል በሚል መንፈስ ያለምንም መሰልቸት ለሙያው ራሳቸውን አስገዝተው መስራት አለባቸው። ሰው የደረሰበት ደረጃ መድረስ እንችላለን የሚል ዓላማ ሊኖራቸው ይገባል።
ጥያቄን ወደ ማጠቃለሉ እየደረስኩ ነው። የቤተስብ ህይወትሽ ምን ይመስላል?
የቤተሰብ ህይወቴን በተመለከተ ባለቤቴ አቤል ወርቅነህ ይባላል። እንደኔ የእግርኳስ ዳኛ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ እያለ በብዙ ደረጃ የሚጠበቅ ዳኛ ነበር። በፌደራል ፓሊስም የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ነበር። አሁን አብሮኝ ነው ካናዳ ያለው። ልጄ ኤልዳና አቤል ትባላለች፤ ሦስት ዓመት ሆኗታል።
በዳኝነት ህይወትሽ የምታመሰግኛቸው አካላት ካሉ በዚህ አጋጣሚ እድሉን ልስጥሽ
አዎ! እዚህ ደረጃ ለመድረሴ በጣም የማመሰግናቸው ሰዎች አሉ። በመጀመርያ ከታች ጀምሮ እዚህ ደረጃ ያደረሱኝ ቤተሰቦቼን እናት አባቴ፣ እህት ወንድሜ አመሰግናለው። እንዲሁም ባለቤቴ አቤል ወርቅነህን ላመሰግነው እወዳለው። በብዙ መንገድ የረዳኝ እርሱ ነው። አዳማ ለሚገኙ የዳኞች ከሚቴ ፣ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሠራተኞች፣ ለብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ፣ ለአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዳኞች ኮሚቴ እና አብረውኝ ሲያበረታቱኝ ለነበሩ የሙያ ጓደኞቼ በጣም አመሰግናለው። በስም ዘርዝሬ መጥራት ስለማልችል ነው። ምክንያቱም በዙርያዬ ብዙ ሰዎች ነበሩና ነው። በተለይ ግን ወደ ካናዳ ልሄድ ስል የጡንቻ መሰንጠቅ አጋጥሞኝ ህክምናውን ተከታትለውልኝ በፍጥነት ወደ ጤንነቴ እንድመለስ የረዱኝ ፊዚዮትራፒስት ይስሐቅ ሽፈራው፣ ዶ/ር አያሌው እና የፌደራል ማረሚያ ስፖርት ቤት ፊዚዮትራፒስት ጥበበ ዓለሜን በጣም አመሰግናለሁ። እንዲሁም ቸርነት እና ኃይለመላክን ወደ ካናዳ እንድሄድ በአካል ብቃቱ ሲያዘጋጁኝ ቆይተዋል፤ እና አመሰግናቸዋለው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!