የቀድሞ ድንቅ ተጫዋች እና በቅርቡ በህይወት ያጣነው ተስፋዬ ኡርጌቾ ታናሽ ወንድም ነው። አንድ አጥቂ ሊያሟላ የሚገባውን ነገሮች ሁሉ አሟልቶ እንደያዘ የሚነገርለት የዘጠናዎቹ ድንቅ አጥቂ ተከተል ኡርጌቾ ማነው?
በኢትዮጵያ እግርኳስ የራሷን አሻራ አሳርፋለች። ብዙ እግርኳሰኞችን መፍጠር ችላለች፤ ቀድሞም ብቻ አልቀረም በዚህ ዘመንም በክህሎታቸው የዳበሩ ጥበበኞችም እየፈጠረች ትገኛለች። የምስራቋ ፈርጥ፣ በስኳር ምርቷ የምትታወቀው ወንጂ ከተማ ናት። በዙርያዋ በርከት ያሉ ሜዳዎች መኖራቸው ለብዙ እግርኳስ ተጫዋቾች መፈጠር ምክንያት እንደሆነ ይነገራል። በዚህች ከተማ እግርኳስን እየተጫወቱ ካደጉ እና በትልቅ ደረጃ መጫወት የቻሉ የአንድ ቤተሰብ ሦስት እግርኳሰኞች ነበሩ። ተስፋዬ፣ ተከተል እና ታገስ ኡርጌቾ ይባላሉ።
ታላቅ ወንድምቸው ተስፋዬ ኡርጌቾ በራሱ ጥረት እና ብቃት በወንጂ፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ የእግርኳስ ዘመን እያሳለፈ መምጣቱ ለታናናሽ ወንድሞቹ ምሳሌ በመሆን ወደ እግርኳሱ እንዲሳቡ መነሻ ምክንያት ሆኗል። ብዙም አልዘለቀበትም እንጂ ታገሰ ኡርጌቾ ከቡና እና ንግድ ባንክ “ቢ” ቡድን እስከ መትሐራ ቡድን ድረስ መጫወት ቢችልም ብዙም ሳይቆይ እግርኳስን አቁሟል። ዋናው የዛሬው ትኩረታችን የሆነው የዘጠናዎቹ ኮከብ እንግዳችን ተከተለ ኡርጌቾ የወንድሙን ፈለግ በመከተል በእግርኳሱ ረጅም ርቀት በመጓዝ አንቱታ በማትረፍ ተሳክቶለታል። ተከተል እግርኳስ ተጫዋችነትን በክለብ ደረጃ መጫወት የጀመረው በወንጂ ከ1984-87 ድረስ ነበር። በአራት ዓመት የወንጂ ቆይታ በኋላ ራሱን ከበርካታ ህዝብ ጋር እንዲሁም ከትላልቅ አሰልጣኞች ጋር የመስራት ዕድል ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአሰልጣኝ ሥዩም አባተ ለሚመራው ኒያላ ለአንድ ዓመት መጫወት ችሏል።
በአንድ ክለብ ረዝም ላለ ጊዜ ተረጋግቶ አለመጫወቱ በእግርኳስ ዘመኑ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት የሚነገረው ተከተል በኒያላ ብዙም ሳይቆይ በ1989 እርሻ ሠብልን ተቀላቅሎ መጫወት ቻለ። በእርሻ ሠብል ቆይታው ስኬታማ የነበረው ተከተል በእግርኳስ ህይወቱ ሁሌም የሚጠቀሰውን ብቸኛው ስኬቱን በከፍተኛ ዲቪዝዮን አስራ ሁለት ጎል በማስቆጠር ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል። ድራማዊ በሆነው በዚህ የከፍተኛ ጎል አግቢነት ፉክክር ተከተል አስራ ሁለት ጎል አስቆጥሮ ጨዋታውን ጨርሶ ቁጭ ብሏል። የእርሱ ተፎካካሪ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ ዮሴፍ ተስፋዬ በሦስት ጎል አንሶ የመጨረሻውን ጨዋታውን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያደርጋል። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የቡድኑ አባላት በሙሉ ዮሴፍ ተስፋዬ ጎል አስቆጥሮ የጎሉን መጠን ከፍ አድርጎ የኮከብ ጎል አግቢነቱን ክብር ያገኛል በሚል ጓጉተዋል። በመጀመርያው አጋማሽም ዮሴፍ ሁለት ጎል አስቆጥሮ ደረስኩ ቢልም በጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢ ጉዳት አስተናግዶ ከሜዳ በመውጣቱ እና ተጨማሪ ጎል ሳያስቆጥር በመቅረቱ በስታዲየም ቁጭ ብሎ ጨዋታውን ይከታተል የነበረው ተከተል ኡርጌቾ በአንድ ጎል በልጦ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን የፊሊፕስ ቴሌቭዥን ተሸላሚ መሆኑ ይታወቃል።
ምንም እንኳ በክለብ አብሮት መጫወት ባይችልም በአንድ ወቅት የኮከብ ጎል አስቆጣሪ ተፎካካሪ በመሆን ከተከተል ኡርጌቾ ጋር ስሙ በጋራ የሚጠራው የወቅቱ ድንቅ አጥቂ ዮሴፍ ተስፋዬ ስለ ተከተል እንዲህ ምስክርነቱን ይሰጣል። “ተከተል በጣም ጎበዝ አጥቂ ነው። የነበረው ፍጥነት፣ ከርቀት በሚመታቸው ኳሶች የሚያስቆጥረው ጎሎች፣ የግንባር ጎሎች የእርሱ መለያዎቹ ነበሩ። ከእኔም ጋር በ1989 ለኮከብ ጎል አግቢነት እስከ መጨረሻው እንፎካከር የነበርን አጥቂዎች ነበርን። በአጠቃላይ ተከተል አንድ አጥቂ ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮችን አሟልቶ የያዘ ከሜዳ ውጭ ጓደኛዬ የሆነ በጣም ተግባቢ፣ ቀልደኛ እና ፎጋሪ የሆነ ተጫዋች ነው።”
የኢትዮጵያ እግርኳስ የወድድር አቀራረብ በአዲስ መልክ ለውጥ ተደርጎበት መካሄድ ከጀመረበት ከ1990 ጀምሮ እግርኳስን እስካቆመበት ጊዜ ድረሰ ተከተል በኢትዮጵያ መድን፣ ንግድ ባንክ፣ ትራንስ፣ መከላከያ፣ ብርሃን እና ሰላም ለአጭር ኮንትራት ከተጫወተ በኃላ ጉዳት አስተናግዶ ለአንድ ዓመት ከሜዳ እርቆ ቆይቶ ዳግመኛ ወደ ሜዳ በመመለስ ለሐረር ቢራ ከተጫወተ በኃላ በ1996 መጨረሻ ላይ እግርኳስ ለማቆም ችሏል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ተከተል በተለይ በ1989 የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን ተመርጦ ቦትስዋና ጋቦሮኒ በማቅናት ለግማሽ ፍፃሜ ደርሶ በአሳዛኝ ሁኔታ ለፍፃሜ ሳይደርስ በደረጃ ጨዋታ አራተኛ ሆኖ በጨረሰው ቡድን ውስጥ ከስንታየሁ ጌታቸው “ቆጬ” ጋር የነበረው ጥምረት ልዩ ነበር።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በሀዋሳ ከተማ፣ በኒያላ እና በተለያዩ ክለቦች በብሔራዊ ቡድን ጭምር ሲጫወት የምናቀው ፀጋዬ ዜና ስለ ተከተል ሲናገር “ተከተል ሜዳ ውስጥ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን የሚቻለውን ሁሉ የሚያደርግ፤ ጉልበት እና ፍጥነት የነበረው፤ አንድ አጥቂ የሚያሟላውን ነገር ሁሉ የያዘ ጎበዝ አጥቂ ነው። ከሜዳ ውጭ እንደኔ ሰይጣን የነበረ በጣም ቀልደኛ፣ ፎጋሪ ነው። እርሱ ከአንተ ጋር አብሮ ካለ በቃ መሳቅ መጫወት ነው።” ብሎለታል።
እግርኳስን ካቆመ በኃላ ወደ አሰልጣኝነቱ ለመግባት ኮርሶችን የወሰደ ቢሆንም በኃላም ወደ ግል ሥራው በመዞር በአንድ አነስተኛ ታክሲ በሥራ ላይ ይገኛል። በቅርቡ በወሊድ ምክንያት ባለቤቱን በህይወት ያጣው ተከተል ሦስት ህፃናት ሴት ልጆቹን የማሳደግ ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎበት በችግር ውስጥ ሆኖ በማሳደግ ላይ ይገኛል። ይህ የዘጠናዎቹ ኮከብ የነበረው ተከተል ኡርጌቾ በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ አናግረነው ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።
“በእግርኳሱ ዕድለኛ አይደለሁም። አንድ ተጫዋች ስሙ ነው የሚተርፈው። ከእከሌ ቡድን ጋር ይህን ዋንጫ አንስቼ፣ ኮከብ ተጫዋች፣ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኜ ብሎ ያወራል። በመጨረሻ ስሙ ነው የሚተርፈው። አሁን እኔ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኜ በመጨረሴ አንድ ታሪክ ያለኝ ቢሆንም ዋንጫ አለማንሳቴ ትንሽ ይሰማኛል። ከኢትዮጵያ ውጭ ተስፋዬ ኡርጌቾ ፊላንድ ሄዶ ሙከራ አድርጓል። እኔም ይህ እድል አለመፍጠሬ ይቆጨኛል። ለምን ሁሉ ነገሩ ነበር። ይህን አለማሳካቴ ትንሽ ይሰማኛል። ከሞላ ጎደል የነበረኝ የእግርኳስ ህይወት ግን ጥሩ ነበር።
“የቦትስዋና ጋቦሮኒ ቆይታችን በጣም ጥሩ ነው። በውጤትም በነበረንም የቡድን እንቅስቃሴ መልካም ነበር። በአንዳንድ ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮች በግብፆች ዳኛ መደገፍ እንጂ እስከ ፍፃሜው በመድረስ በታሪክ የመጀመርያውን ዋንጫ ይዘን የመመለስ ዕድሉ ነበረን። የቦትስዋና ህዝብ አጨዋወታችንን ከመውደዱ የተነሳ የአፍሪካ ብራዚል እያለ ይጠራን ነበር። በጣም የሚገርም ስብስብ ነበረን። በየቦታው የሚጫወቱ ጥሩ ጥሩ ልጆች ነበሩ። አይደለም የመጀመርያ አስተላለፍ የገባነው በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩት ሳይቀር በጣም ብቃት ያላቸው ነበሩ። ለዛም ነው ከቦትስዋና እንደተመለስን የተወሰነ ልምድ ያላቸው ኤልያስ ጁሀር፣ አሰግድ ተስፋዬን ግብጠባቂ ስንታየው ሥራብዙ፣ አንዋር ሲራጅን በመቀላቀል ዋና ብሔራዊ ቡድን እንድንጫወት የሆነው።
” የኮከብ ጎል አግቢነቱ ፉክክር አስጨናቂ ነበር። ከዮሴፍ ተስፋዬ ጋር የነበረው ትንቅንቅ የማይረሳ ነው። እኔ አስራ ሁለት ጎል አስቆጥሬ እየመራሁ ጨዋታዬን ጨርሻለው። እርሱ ደግሞ የመጨረሻ ጨዋታውን ከንግድ ባንክ ጋር ይጫወታል ዘጠኝ ጎል በማስቆጠር እየተከተለኝ ነው። የፌዴሬሽኑ አመራሮች አይደርስበትም ብለው ጨዋታውን እንድከታተል ጋብዘውኝ በአዲስ አበባ ስታዲየም ቁጭ ብያለው። የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በሙሉ ዮሴፍ ጎል እንዲያስቆጥር እየረዱት የእርሱም ጥሩ ችሎታ ተጨምሮበት ከእረፍት በፊት ሁለት ጎል አስቆጥሮ ልዩነቱን በአንድ ጎል አጥብቦ ነበር። በቃ በቀረው ደቂቃ ተጨማሪ ጎሎች አስቆጥሮ ኮከብነቱን እንደሚያገኝ እርግጠኛ ነበርኩ። ሆኖም ባልተጠበቀ ሁኔታ ከዐቢይ ሃይማኖት ጋር ተጋጭቶ ተጎድቶ መውጣቱ እኔን ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆን እንዳጠናቅቅ አድርጎኛል እንጂ እኔ ተጨማሪ ጎል አስቆጥሮ ሽልማቱን ይወስዳል ብዬ ነበር። በወቅቱ ግን ስታዲየም ቁጭ ብዬ ጨዋታውን መመልከት አልነበረብኝም፤ በጣም ነው የሚያስጨንቀው። ተመልካቹ እኔን ነው የሚያየው። ከአሁን አሁን ይወጣል እያለ ይመለከተኛል። በቃ በጣም ደስ የማይል ሁኔታ ነበር። ተጫውተህ ራስህ የምትወስነው ቢሆን የተሻለ ነበር።
“ዮሴፍ ጎል እንዳያስቆጥር ፀሎት አድርገሀል ሲባል እሰማለሁ። በፍፁም! እንዴት ሰው አታግባ ተብሎ ይፀለያል። እኔ ብሆን እዛ ቦታ ላይ ላግባ ብዬ ነው የምፀልየው። እንዴት ሰው አታግባ ተብሎ ይፀለያል። ፈጣሪም አይሰማህም ስሜቱ ግን አስቸጋሪ ነው። የተመልካቹ ሁኔታ፣ ቁጭ ብሎ መመልከቱ ራስህ የማትወስነው መሆኑ በጣም አስጨናቂ ነው። ዮሴፍ ጎበዝ አጥቂ ነው። ከእኔ የተሻለ ሆኖ ቢያጠናቅቅ ደስተኛ ነው የምሆነው።
” በአንድ ክለብ አጭር ጊዜ ብቻ በመቆየት እና በተደጋጋሚ ክለብ መቀያየሬን አሁን ሳስበው ትክክል አለመሆኔን ተረድቻለው። አንድ ቡድን ባህሪውን ለመልመድ ብዙ ጊዜ ያስፈልጋል። እኔ ደግሞ ወንጂ ብቻ ነው አራት ዓመት የተጫወትኩት። የተቀሩት ጋር ቢበዛ ሁለት ዓመት ብቻ ነው የቆየሁት። የተቀረውን አብዛኛውን ማለት ይቻላል አንድ ዓመት ነበር የምቆየው። ይህ ለረጅም ዓመት በተለይ ተጨማሪ ስኬቶችን እንዳላገኝ እንቅፋት ሆኖብኛል።
“የእኔ እና የዳግማዊ አማረ አብሮ ክለብ መቀያየር እና አብሮ በየክለቡ ሄደን መጫወት ምክንያቱ የእኔን አጨዋወት በደንብ ጠንቅቆ የሚያቀው እርሱ በመሆኑ ነው። እኔን በጎል አግቢነት ፈልገው ሲቀጥሩኝ እኔን ብቻ አይወስዱም፤ እኔን ሲፈልጉ ዳግማዊ አማረም አብረው ያስፈርማሉ። ሲያደራድሩንም በጥቅማጥቅም እንኳን በተናጥል አያዋሩንም፤ አንድ ላይ ነው። እንግዲህ ከእርሻ ሰብል አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ አብረን መጫወት ችለናል።
” የተስፋዬን ችሎታ እና አቅም እንደ ወንድሜ አይደለም የምነግርህ ልክ እንደ አንድ ተመልካች ወይም ሌላ ሰው ሆኜ ስገልፅልህ ተስፋዬን የሚመስል ተጫዋች የለም። የአማካይ ተጫዋች ሆኖ አንድ ኳስ ድሪብል አድርጎ ሁለት ተጫዋች የሚያልፍ አይቼ አላቅም። ብቃቱ እና የሰውነት ቅልጥፍናው የሚገርም ነው። እኔ በዘመኔ እርሱን እና ጠንክር አስናቀን የመሰሉ ተጫዋቾችን አይቼ አላቅም።
” ከወንድሜ ጋር ቅዱስ ጊዮርጊስ እንድጫወት ክለቡ ጥያቄ አቅርቦልኛል። ሆኖም ግን መግባት አልፈለኩም። ለምሳሌ ወንድማማቾች ሆነው አንድ ክለብ የተጫወቱ አሉ። ይህ ጥሩ ትውስታ ነው። እኔ ግን በባህሪዬ የወንድሜን ክፉ መስማት አልፈልግም። ክለብ ውስጥ ደግሞ በቀጥታም በተዘዋዋሪ መንገድ የተለያዩ ነገሮች አሉ። ያ ነገር ደግሞ እኔ ላይም እርሱ ላይም ተፅእኖ ስለሚፈጥር ፈፅሞ መግባት አልፈለኩም። የእርሱን ክፉ ማየትም መስማትም አልፈልግም ብዬ እኔም ዳግማዊ ተጠይቀን አንፈልግም ብለን ሳንቀበል የቀረነው።
“ከታላቅ ወንድሜ ጋር በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ሆኜ ተገናኝተን እናውቃለን። አንድ ሁሌ የማልረሳው ትውስታ አለኝ። አንድ ፎቶ አለ ወንጂ በነበርኩበት ሰዓት እርሱ ጊዮርጊስ እያለ ተገናኝተን ነበር። አጥቂ ብሆንም ያው ልጅነት ስለነበረ በጣም ፋውለኛ ነበርኩ። እዛው ሜዳ ውስጥ መጥቶ በጨዋታው መሐል “ተረጋግተህ ተጫወት አትቸኩል እንደዚህ አይደለም መጫወት ያለብህ ፋውል አታብዛ” እያለ የመከረኝን አስታውሳለው።
“ከወቅቱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ወንጂ አብረን ተጫውተናል። የሚገርምህ ምርጥ ድምፃዊ እና ክራር ተጫዋች ነው። ወንጂ ሜዳ አካባቢ የተጫዋቾች ማደርያ ካምፕ ነበር። እዛ ሁላችንንም ክራር በእርሱ አማካኝነት እንማር ነበር። የእርሱ ግን የሚዘፍነው ዘፈን – ዘፈን እንዳይመስልህ፤ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ያቁታል። በጣም ጥሩ ድምፅ ነበረው። ከልምምድ በኃላ ተሰብስበን እርሱ ይመጣል ይዘፍናል በቃ አሪፍ ጊዜ ነበር። ዛሬ በጥረቱ እዚህ ስኬት ላይ በመድረሱ በጣም ደስተኛ ነኝ።
“የአሰልጣኝነት ኮርስ ወስጃለው። ከዮሴፍ ተስፋዬ እና ስንታየው ሥራብዙ ጋር ሆነን የሥዩም አባተ ወንድም ሰለሞን አባተ ኮርሱን ሰጥቶኝ ነበር። ሆኖም ወደ አሰልጣኝነቱ ለመቀጠል ኢኮኖሚ ወሳኝነት አለው። ቤተሰብ ልጆች ስለነበሩኝ የምትከፍለው ዋጋ ስላለ ተቀማጭ ገንዘብ ያስፈልጋል። ስለዚህ ኮርሱን ከወሰድኩ በኃላ ተመልሼ ወደ እዛ ዞር ብዬ አልተመለስኩም። አሁን ግን ትልቅ ሀሳብ አለኝ። ደሰላኝ ገብረ ጊዮርጊስ በጣም ጥሩ ሰው ነው። ውበቱ አባተ ተጨምሮበት ግዴታ ኮርሱን ወስጄ ወደ እዛ ሊያመጡኝ እየተነጋገርን ነው። ምን አልባት ወደፊት ወደ አሰልጣኝነቱ ብቅ እላለው ብዬ አስባለው።
” አሁን ያለሁበት ሁኔታ ጥሩ አይደለም። በግል ሥራ አንድ ደከም ያለች ታክሲ እሰራለው። ሦስት ሴት ልጆች አሉኝ። ባለቤቴ ከሦስት ዓመት በፊት በወሊድ ምክንያት ህይወቷ አልፏል። ነፍሷን ይማረው በጣም ያሳዝናል። ሦስት ልጆች ብቻዬን ይዤ እየኖርኩ ነው። በዛላይ ደግሞ የተስፍሽ ሞት ኑሮውን የበለጠ አክብዶብኛል። ለምን ተስፍሽ ትንሽም ቢሆን በየወሩ እኔንም እናታችንንም ይደጉም ነበር። ይሄም ቀረ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለሁት”።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!