የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚጫወትበት ስታዲየም ታውቋል

በኅዳር ወር የመጀመሪያ ቀናት የኒጀር አቻቸውን የሚገጥሙት ዋሊያዎቹ ዝግጅታቸውን የሚያደርጉበት እና ጨዋታውን የሚከውኑበት ስታዲየም ታውቋል።

በኮቪድ-19 ምክንያት የተራዘሙት የ2021 (ወደ 2022 የተሸጋገረው) የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከአምስት ሳምንታት በኋላ መከወን ይጀምራሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታዎች ለመከወን አዲስ አሰልጣኝ በመሾም እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል። አሠልጣኙም ለጨዋታዎቹ የሚመረጡ 41 ተጫዋቾችን በያዝነው ሳምንት አጋማሽ አስታውቀዋል።

በአዲሱ የቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ የቀረበላቸው 41 ተጫዋቾች በነገው ዕለት ሪፖርት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተላልፏል። ተጫዋቾቹም ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ወደ ሆቴል በቀጥታ እንዲገቡ ተደርጎ የኮቪድ-19 ምርመራ እንደሚደረግላቸው ታውቋል። የምርመራው ውጤቱም በ24 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ከደረሰ በኋላ ከቫይረሱ ነፃ የሆኑት ተጫዋቾች ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልህቀት ማኅከል እንዲገቡ ተደርጎ መደበኛ የልምምድ ጊዜ እንደሚጀመር ሰምተናል። ብሔራዊ ቡድኑም በልህቀት ማኅከሉ ለ10 ቀናት ቆይታን ካደረገ በኋላ ለኒጀሩ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚረዳውን ዝግጅት በወጥነት ለመከወን 580 ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ ባህር ዳር እንደሚከትም ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።

ብሔራዊ ቡድኑ በጥቅምት ወር መጨረሻ የሚደረገውን የምድቡ ሦስተኛ ጨዋታ ወደ ኒያሜ ተጉዞ ካከናወነ በኋላ ኅዳር በገባ በመጀመሪያ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የሚደረገውን ቀጣይ የምድቡ መርሐግብር (የምድቡ አራተኛ ጨዋታ) በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም እንደሚያከናውን የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ገልፀውልናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ያጋሩ