ሶከር ታክቲክ | Half-Spaces…

Read Time:5 Minute, 22 Second

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡


ጸሃፊ
– ጄክ አስካም

ትርጉም
– ደስታ ታደሰ

“Half space” የሚለው ስያሜ የእግርኳስን ታክቲካዊ ንድፈ-ሐሳቦች ጠልቀው የተረዱ ጥቂት ባለሞያዎች ብቻ የፈጠሩት የተለየ ቋንቋ ሊመስል ይችላል፡፡ ለጨዋታው መደበኛ ተመልካቾች እንግዳ የሆነ ሐሳብ እንደሆነም ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ ቡድኖች በማጥቃት ሒደት ላይ ክፍት ቦታዎችን ለመጠቀም እንደሚጥሩ ስንረዳ የ”Half space”ን መሰረታዊ ጽንሰ-ሐሳብ መገንዘብ እንችላለን፡፡ “Half Spaces” ቡድኖች ኳስ በሚይዙበት ጊዜ እጅግ ሊጠቅሙ ከሚያስችሉ የሜዳው ክፍሎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ መገኛቸውም ሜዳውን በቁመት በሚያጋምሰው የመሀል ክፍል እና በሜዳው ስፋት ግራና ቀኝ በሚገኙት መስመሮች መካከል ነው፡፡

     “Half Spaces” ምንድን ናቸው?

የ”Half-Spaces”ን ምንነት በዝርዝር ትንተናዎች ከማብራራታችን በፊት የእግርኳስ መጫወቻ ሜዳን በተለያዩ ቀጠናዎች መከፋፈል እንደሚያስፈልግ መረዳት አለብን፡፡ ከዚህ አንጻር አንድን የእግርኳስ ሜዳ በአስራ ስምንት ክፍሎች መሸንሸን የተለመደው መንገድ ነው፡፡ ሜዳውን በዚሁ የአሸናሸን ዘዴ ካዘጋጀን በኋላ “Half-Spaces”ን በዝርዝር ለመተንተን እንችላለን።

ከታች በምስሉ በቀረቡት የሜዳው ክፍሎች “Half Spaces” ይታያሉ፡፡ እነዚህ ቦታዎች ላይ  በአብዛኛው የሚጫወቱት እንደ ዴቪድ ሲልቫ፣ ፊሊፕ ኮቴኒሆ፣ ሜሱት ኦዚል እና ኤደን ሃዛርድን የመሳሰሉት የፈጠራ ክህሎታቸው ላቅ ያሉት የአጥቂ አማካዮች ናቸው፡፡

እነዚህን ቦታዎች በቀላሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ  ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንደኛው የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች “Half Spaces” ውስጥ የሚገቡትን ተጫዋቾች በ”Marking” ሲስተም በቅርብ ርቀት ሆነው ጥብቅ ክትትል ለማድረግ የትኛውን ተጫዋች መያዝ እንዳለባቸው እርግጠኛ አለመሆናቸው ነው፡፡ ከታች የቀረበውን ምስል እንደ ናሙና እንውሰድ፡፡

ለምሳሌ፦ ለቀዩ ቡድን- ኳሱ በሜዳው ቁመት በተሰለፈው የግራ መስመር-የአጥቂ አማካዩ እግር ሥር ሲሆን በቅርቡ ሦስት የሰማያዊ ቡድን ተከላካዮች ይኖራሉ፡፡ ለአጥቂ አማካዮች እነርሱ የሚፈልጉትን አልያም የሚያስፈልጋቸውን ክፍት ቦታ እንዲያገኙ ቸል ማለት ከባድ አደጋ ያስከትላል፡፡ በተለይም ከፍ ባለ ደረጃ በሚገኙ ቡድኖች ውስጥ ለሚጫወቱ የአጥቂ አማካዮች ትንሽም ክፍት ቦታ መተዉ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ስለዚህም ከሦስቱ ተከላካዮች አንደኛው የአጥቂ አማካዩ ላይ ጫና ለማድረግ ከነበረበት ቦታ ይንቀሳቀሳል፡፡ ይህ ድርጊቱ ሌሎቹም ተከላካዮች የቀደመው ተከላካይ የተወውን ክፍተት ለመድፈን ሲሉ መሸጋሸግ ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ የአጥቂ አማካዩ በ”Half Space” አካባቢ ኳስ ካገኘ የተለያዩ ሶሥት አማራጮችን ማሰብ ይችላል፡፡


አማራጭ ኹነቶች

ከታች በሚቀርበው አንደኛው አማራጭ በጥቁር መስመሮች በተከፋፈሉት የሜዳው ግራና ቀኝ አረንጓዴ ቦታዎች የሚታየው የጨዋታ ሒደት በቀይ ቀለም የተወከለው ቡድን በማጥቃት ላይ ሲሆን  በሰማያዊ ቀለም የተወከለው ቡድን ደግሞ  በመከላከል ላይ እንደሆነ ያሳያል፡፡ የተጠቀሰው የጨዋታ ሒደት እየተካሄደ የሚገኘው በ”Half Space” ነው፡፡ ቀዩ ቡድን ከመስመራቸው እየተነሱ ወደ መሃከለኛው የሜዳ ክፍል በመግባት የሚጫወቱ አማካዮችን የሚያካትት መደበኛ የ4-2-3-1 ፎርሜሽን ይጠቀማል፡፡ በተጨማሪም በሜዳው ስፋት በማጥቃት ሒደቱ ተጋጣሚው ላይ ብልጫ ለመውሰድ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ከኋላ በመነሳት ወደፊት እየገፉ እንዲጫወቱ ያደርጋል፡፡ በ”Half Spaces” ሁለቱን የመስመር አማካይ-አጥቂዎች በአንክሮ ስንመለከት በአራት የተጋጣሚዎቻቸው ተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ አቋቋም ሳቢያ በተፈጠረ የጎነ አራት ሳጥን መሃል መገኘታቸውን እንረዳለን፡፡ የአጥቂ አማካዩ ወይም የመስመር አጥቂው በዚህ ቦታ ላይ ሲገኝ ለቡድን አጋሮቹ የተለያዩ የማጥቃት አማራጮች ይፈጥራል፡፡

“Half Space” ላይ ካሉት የአጥቂ አማካዮች አንደኛው ላይ (የቀኝ መስመር አጥቂውን) ጫና ለማሳደር ከሚከላከለው ቡድን የግራ መስመር ተከላካዩ ወደ ሳጥኑ ውስጥ ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ የግድ ከኋላው ክፍት ቦታ ይተዋል፡፡ ይህም ከሚያጠቃው ቡድን የቀኝ መስመር ተከላካይ ሊጠቀምበት የሚችለውን ቦታ እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡


ሌላኛው “ሊሆን በሚችል” አማራጭነት የሚቀርበው ሐሳብ የተጋጣሚ ቡድን የተከላካይ አማካዩ “Half Space” ውስጥ ያለውን ተጫዋች በቅርበት ለመቆጣጠር ይሄዳል፡፡ ይህም በሜዳው መሃለኛው ክፍል ክፍት ቦታ እንዲፈጠር ያደርጋል፤ በተለይ በ”ቀጠና 14″ ላይ የተጋጣሚ ቡድን አማካዮች እጅጉን ሊጠቀሙበት የሚችሉት ቦታ ያገኛሉ ፡፡

በመጨረሻም የሚያጠቃው ቡድን የቀኝ መስመር የማጥቃት አማካይ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ከተጋጣሚው በግራ መስመር በኩል የሚሰለፈውን አማካይ እንዲቆጣጠር ይደረጋል፡፡እዚህ ጋር አንድ እምብዛም ያልተለመደ ኹነት ማስተዋል ይቻላል፡፡ ይኸውም የማጥቃት አእምሮ የያዘ ተጫዋች በመከላከል የጨዋታ ሒደት ላይ ተሳትፎ በማድረግ እንደ እርሱው በማጥቃት አእምሮ የተቃኘን የተጋጣሚ ቡድን አማካይ ለመቆጣጠር መጣሩ ነው፡፡ በመከላከል እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፍ ኃላፊነት የተጣለበት የአጥቂ አማካይ ቅጽበታዊ ሚናውን ካለመላመዱ የተነሳ ለቦታ መክፈት አጋጣሚ ይጋለጣል፡፡ በዚያ ላይ እንደ እነዚህ አይነቶቹ ተጫዋቾች በመሮጥ ሙሉ ሜዳ የሚያካልሉ ባለመሆናቸው የተዉትን ክፍተት መልሶ ለመዝጋት አቅም ያጣሉ፡፡ የተጋጣሚያቸው ተጫዋች የሚሄድበት ድረስ በመከተል ጫና ሊፈጥሩበትም አይሞክሩም፡፡ ስለዚህ በእነርሱ ክፍተት የመሸፈን ድክመት ሳቢያ ሁለት የመስመር ተከላካዮች እርስ በእርሳቸው 1-ለ-1 በሆነ አጋጣሚ የሚጋፈጡበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

ከላይ በቀረቡት ሦስቱም አማራጮች በጨዋታ የመከላከል ሒደት ላይ የሚገኝ የትኛውም ተጫዋች “Half Space” ውስጥ የገባ ባላንጣውን ለመቆጣጠር ሲመጣ የባላጋራው ቡድን የሚጠቀምበት ክፍት ቦታ መፍጠሩ አይቀሬ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ማንኛውም ቡድን በማጥቃት ሒደት ላይ ሳለ “Half Space”ን ለመጠቀም የተጫዋቾችን እንቅስቃሴ ኳሷ ከምትሄድበት አቅጣጫ እና ከተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ የቦታ ቅይይርና አቋቋም አንፃር መቃኘት አለበት፡፡   ላይ ክፍተቶችን ለመጠቀም የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማዘጋጀት አለበት፡፡ ቀጥዬ ይህንን ሐሳብ በዝርዝር ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
“Half Space”ን የመጠቀም እቅድ ውጤታማ መሆን የሚችለው በትክክልም ቦታው በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች በማይያዝበት ቅጽበት ብቻ ነው፡፡ በአጥቂውና በአጥቂ አማካዩ መካከል የሚኖረው መናበብ በጣም አስፈላጊ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የአንድ አጥቂ የፊትለፊት እንቅስቃሴ ወደ “Half Spaces” ከሆነ የአጥቂ አማካዩ ሊጠቀምበት የሚችለው ቦታ ላይ የተጫዋቾች መደራረብ ይከሰታል፡፡ ስለዚህም በጨዋታ ወቅት በጣም ውጤታማ የሆኑት አጥቂዎች ከኳስ ውጪ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የፊት ለፊት ሩጫ ወይም የማፈትለክ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ይሄኔ “Half Spaces”ን በስኬታማነት ለመጠቀም የሚያስችሉ ሁኔታዎች ይገኛሉ፡፡

የሜዳ ክፍሎችን “Half Space” ብለን እንድንፈርጅ የሚያደርገን መስፈርት ምንድን ነው?

ብዙዎች አንድን የሜዳ ክፍል “Half Space” ብሎ ለመፈረጅ የተለያዩ ሃሳቦች አሏቸው፡፡አንዳንዶች “Half Space” በሜዳው ቁመት ከአንደኛው የሜዳ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ያለው ክፍል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ “Half Space” የሚገኘው በሜዳው ግማሽ ቁመት ውስጥ ሆኖ ከግቡ ቋሚዎች እስከ መሃለኛው ሜዳ ድረስ ካለው ርቀት እኩሌታ አካባቢ ያለው ቦታ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡ እኔ ከሁለቱም የተለየ ሐሳብ አለኝ፡፡ “Half Space” ሜዳ ላይ የሚገኙ ውስን ቦታዎች ስለመሆናቸው  አላስብም፡፡ ይልቁንም አንድ ቡድን በመከላከል ሒደት ላይ ሲሆን በሚኖረው የመከላከል መስመር ላይ ተመስርተው በየጊዜው የሚዋልሉና የሚቀያየሩ የሜዳው ክፍሎች ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ እምነቴ ተነስቼ እጅግ ውጤታማው “Half Space” ከመጨረሻው የመሃል ተከላካይ አምስት ሜትሮች ያህል ከፊቱ ርቆ እና ከመስመር ተከላካዩ ደግሞ ይህንኑ ያህል ሜትሮች ወደ ጎን ርቆ የሚገኘው አካባቢ ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንዲያውም “Half Space” በፍፁም ቅጣት ምት ክልል የሚገኝ የሜዳ ክፍል እንደሚጀምር ይከራከራሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ዋነኛ የመከራከሪያ አጀንዳቸው “Half Space” የማጥቃት መርህ በመሆኑ አንጻራዊ መገኛው የጨዋታው የማጥቃት ሒደት የሚተገበርበት ክልል መሆኑን አበክረው ይገልጻሉ፡፡ ከታች በምስሉ “Half Sapce” ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል በሚጀምር የጎነ አራት ምስል ተመልክቷል፡፡


ሌሎች ተከራካሪዎች ደግሞ “Half Sapce” በሜዳው ቁመት በመስመሮችና በመሃለኛው ክፍል መካከል የሚገኝ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡ እነዚህኞቹ ወገኖች በሚያስቀምጡት የ”Half Sapce” ልኬት የርዝመቱ መብዛት ለማጥቃት ሒደቱ ጠቃሚ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ከታች በምስሉ እንደተመለከተው በሜዳው ቁመት ሙሉ የሚዘረጋው ቦታ የ”Half Sapce” ክልል ነው፡፡

ኔlce” የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች በመከላከል የጨዋታ ሒደት በእንቅስቃሴ ላይ ሳሉ በአንጻራዊ ሁኔታ እንደሚቆሙበት ቦታ የሚለዋወጥ ክልል በመሆኑ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ “Half Sapce” የሚፈጠረው በመስመር ተከላካዮች፣ በመሃል ተከላካዮችና በተከላካይ አማካዮች እንቅስቃሴ አማካኝነት እስከሆነ ድረስ ዋላይነቱ አጠያያቂ አይሆንም፡፡


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

About Post Author

desta

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
ያጋሩ
error: Content is protected !!