የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ልምምዱን ሰርቷል

ዋልያዎቹ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ መሪነት የመጀመርያ ልምምዳቸውን በዛሬው ዕለት አከናውነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዛሬ ከ3፡00 ጀምሮ ለአንድ ሰዓት የፈጀ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን በማሰራት ጀምረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ41 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረገ ቢሆንም ከቅዳሜ ጀምሮ ሰላሳ ስድስት ተጫዋቾች ተገኝተው የኮቪድ 19 ምርመራን ካደረጉ በኃላ አምስቱ ላይ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትላንት ምሽት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

በዛሬው የልምምድ መርሀ ግብር ላይ ከኮቪድ 19 ነፃ የሆኑ ሰላሳ ተጫዋቾች ቀለል ያሉ ልምምዶችን የሰሩ ሲሆኑ በብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውስጥ ከተጠሩት አርባ አንድ ተጫዋቾች መካከል አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ በግል በገጠመው ጉዳይ እስካሁንም ብሔራዊ ቡድኑን አልተቀላቀለም። ሽመልስ በቀለ እና በኢኳቶሪያል ጊኒ በሙከራ ላይ የሚገኘው መስፍን ታፈሰም እስካሁን ወደ ስብስቡ ያልተካተቱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

እንደ ፌዴሬሽኑ ገለፃ ከሆነ የሰበታ ከተማው አንተነህ ተስፋዬ እና የፋሲል ከነማው የመስመር ተጫዋች ሱራፌል ዳኛቸው በዛሬው ዕለት ምርመራውን ካለፉ የዋልያዎቹን ስብስብ የሚቀላቀሉ ይሆናል፡፡ ከ72 ሰዓታት በኃላ ነፃ የተባሉ ጠቅላላ የቡድኑ አባላት በድጋሚ ምርመራ እንደሚደረግላቸውም ተሰምቷል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ 10:00 ላይ ቀጣይ ልምምዱን ያደርጋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!