ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወሳኝ ዝውውር ገበያውን ተቀላቅሏል

የሦስት ጊዜ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ንግድ ባንክ ሁለት ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአስር ነባር ተጫዋቾችንም ውል አራዝሟል።

በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በዛሬው ዕለት በይፋ የዝውውር ገበያውን ተቀላቅለዋል። መጀመሪያ ቡድኑን ለመቀላቀል ተስማምታ በዛሬው ዕለት ፊርማዋን ፌዴሬሽን ተገኝታ ያኖረችው ተጫዋቸ ሰናይት ቦጋለ ናት። በኮካ ኮላ ውድድር ታይታ ቢኒ ትሬዲንግ ቡድንን የተቀላቀለችው ሰናይት ጥሩ ብቃቷን በማሳየት ወደ ደደቢት በማምራት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ መጫወት መጀመሯ ይታወሳል። እስከ 2010 በቆየችበት ደደቢትም ሦስት ጊዜ የሊጉን ዋንጫ አንስታለች። ከዛም ወደ አዳማ ከተማ በመጓዝ ተጨማሪ የሊጉን ዋንጫ 2011 ላይ ከፍ አድርጋለች። 2010 ላይ የሊጉ ኮከብ ተብላ የተመረጠችው ይህች ተጫዋች ለሁለት ዓመት በባንክ ቤት ለመቆየት ፊርማዋን አኑራለች።

ክለቡን የተቀላቀለችው ሁለተኛዋ ተጫዋች አያንቱ ቶሎሳ ነች። በተቋረጠው የውድድር ዓመት ከአዲስ አበባ ተስፋ ዋናውን የአዲስ አበባ የሴቶች ቡድን የተቀላቀለችው ይህቺ ግብ ጠባቂ ያሳየችውን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ተከትሎ ባንክን በተመሳሳይ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ለማገልገል ፊርማዋን አኑራለች።

ክለቡ ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ከመቀላቀሉ በተጨማሪ የ10 ነባር ተጫዋቾችን ውል ማራዘሙ ተሰምቷል። ውላቸውን ያራዘሙትም ተጫዋቾች ጥሩአንቺ መንገሻ፣ ገነሜ ወርቁ፣ ታሪኳ ደቤሶ፣ ብዙሃየሁ ታደሰ፣ ብዙነሽ ሲሳይ፣ ትግስት ያደታ፣ እመቤት አዲሱ፣ ሽታዬ ሲሳይ፣ ረሂማ ዘርጋው እና ብርቱካን ገብረክርስቶስ ናቸው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!