አስተያየት | ‹‹ውሐውን የሚያስጮኸው ድንጋዩ ነው!››

Read Time:19 Minute, 22 Second

አስተያየት፡ በሳሙኤል ስለሺ

‹‹ልጄ ሆይ፤ ማንም ሰው ቢሆን ባንተ ላይ የሐሰት ወሬ ሲያወራብህ የሰማህ እንደሆነ ታገሰው፡፡ መታገስ ባትችል ግን ጠብህን በግልጥ አድርገውና ሰው ሁሉ ይወቀው፡፡ ጠብህን ካስታወቅህ በኋላ፤ ምንም ክፉ ወሬ ቢያወራብህ እውነት ነው ብሎ የሚቀበለው ሰው አይገኝም››

ለልጅ ምክር፤ለአባት መታሰቢያ

1910 ዓ.ም: ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ


ባለፉት 3 ሳምንታት በዚሁ በሶከር ኢትዮጵያ ላይ ‹‹ለእግር ኳሳችን የማይጠቅመው የባለሙያዎቻችን ንትርክ›› በሚል ርዕስ የግል አስተያየታቸውን በሁለት ክፍሎች ያቀረቡት አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ በጥቅሉ መልካም የሚባል እንድምታ ያለው ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ሐሳብን ከንግግር ይልቅ እንዲህ ባማረ ፅሁፍ መግለፅ መቻላቸው ደግሞ ክርክሩን አንድ ደረጃ ከፍ አድርጎ መፃፍ እና ማንበብ በሚችሉ ሰዎች ብቻ እንዲገደብ ስለሚያደርግ በንግግር ላይ የተጠመዱ አላስፈላጊ ሰዎችን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ ሆኖም ግን ካለመረዳት ይሁን ወይም ገለልተኛ ሆኖ ለመቅረብ ካደረጉት ሙከራ ባይገባኝም አውዱን የሳተ መከራከሪያዎችን አቅርበው ተመልክቼያለሁ፡፡

የእርሳቸውን ፅሁፍ መሰረት አድርጌ አስተያየት መስጠት ከፈለኩኝ ቆየት ብልም ‹‹አስፈላጊ›› ነው ወይስ ‹‹አይደለም›› በሚል ግላዊ አተካሮ (Self Dispute) እስኪብርቶዬን ስጥልና ሳስቀምጥ ቆይቻለሁ፡፡ ይህም የሆነው አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ እጅግ ከማከብራቸው፣ ብዙም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በሌለው የታዳጊዎች ፕሮጀክት ላይ ለረዥም አመታት ተሰማርተው ከሚሰሩ እና ውጤታማ ከሆኑ፣ በተግባር የኢትዮጵያን እግር ኳስን ለማገዝ ከሚጥሩ ጥቂት ሰዎች መሀከል አንዱ በመሆናቸው ሲሆን የፅሁፋቸውም ጭብጥ ለመልካም መሆኑን በማሰብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለተከታታይ ሳምንታት ሶከር ኢትዮጵያ የፈጠረውን መልካም እድል በመጠቀም ብዙዎች የሚማሩበትን የተለያዩ አስተማሪ ፅሁፎችን የሚፅፉ ባለሙያ በመሆናቸው ገና ለገና በአንድ ፅሁፍ ልዩነት ስላገኘሁባቸው ተቃዋሚ ሆኜ መቅረብን አልፈለኩም ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የሙያ ባልደረቦቼ ‹‹አስተያየታችንን እናስቀምጣለን›› በማለታቸው ሁሉም ቦታ ላይ ‹‹ካልገባሁ›› ማለት እንዳይመስልብኝ ስል ሌሎችም ሐሳባቸውን እንዲያካፍሉ ለማየት ጓጉቼ ነበር፡፡

የደስታ ታደሰ ፅሁፍ (ክፍል 1 | ክፍል 2)

በእነዚህ እና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ከመፃፍ አለመፃፍን መርጬ ለመቀመጥ ብሞክርም ፅሁፋቸው ለብዙዎች የተሳሳተ መልዕክት የሚያስተላልፍ እና ፅሁፉ ለዓመታት በታሪክነት የሚቀመጥ ሆኖ ስላገኘሁት በተረዳሁት እና በገባኝ ልክ ማረም እንደሚገባኝ በመወሰን ይህንን ፅሁፍ ከትቤያለሁ፡፡

ፀሀፊው ‹‹እዚህ ጋር እንዲታወቅልኝ የምፈልገው አስተያየቴ የሚመለከተው በዚህ ክርክር ውስጥ ይብዛም ይነስ እየተሳተፉ ያሉትን አካላት ነው፡፡›› የሚል አስተያየት በመስጠታቸው እና እኔም እንደ ስፖርት ባለሙያ በዚህ ጉዳይ ላይ በሬድዮ፣ በቴሌቪዥን እና በተለያዩ መድረኮች ላይ በመሳተፌ ማረሚያ ለመስጠት ተጨማሪ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ‹‹አትቸኩል! አስበህ ተናገር›› የሚባለው ብሒል ቢማርከኝም ‹‹አስበህ ተናገር፤ ግዜ እንዳያልፍብህ ግን ፍጠን›› የሚለው የራሴ አባባል ደግሞ የበለጠ እቀበለዋለሁ እና ፀሀፊው ‹‹ስተዋቸዋል፣ በአግባቡ አልተረዷቸውም ወይም ሸፋፍነዋቸዋል›› ብዬ የማምንባቸውን ስድስት ነጥቦች እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ፡፡

1- ያሉ የሚመስሉ የሌሉ ቡድኖች

ከቅርብ አመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ እጅግ እየጎሉ ከመጡ አስተሳሰቦች መሀከል ‹‹የተጫወተ››፣ ‹‹የተማረ››፣ ‹‹ያልተጫወተ››፣ ‹‹ያልተማረ››፣ ‹‹በሙያው ያለፈ››፣ ‹‹በትምህርት ያለፈ›› እና የመሳሰሉ ቃላቶችን እየለጠፉ በድኖች የተፈጠሩ ለማስመሰል የሚደረግ የጥቂት ሚዲያዎች ዘመቻ አንዱ ነው፡፡ ይሄ የጥንድ አስተሳሰብ (Dual Thinking) የስነ ልቦና መታወክ (Psychological Disorder) ሲሆን ነገሮችን በሁለት ብቻ ከፍሎ የማየት መጥፎ አባዜ ነው፡፡ ጥቁር ካልሆነ ነጭ ነው፤ ረዥም ካልሆነ አጭር ነው፤ ደጋፊ ካልሆንክ ተቃዋሚ ነህ፣ ግራ ካልሆንክ ቀኝ ነህ….የሚል አስተሳሰብ የጭንቅላት አድማስ ማነስን (Non Refelectiveness) የሚያሳይ ሲሆን በተከታታይ መድሐኒት አልያም ልምምድ ብቻ የሚቀረፍ ነው፡፡

እነዚህን በተጨባጭ የማይገኙ ሁለት ፅንፎችን የፈጠሩት የጥንድ አስተሳሰብ ሰለባዎች፣ በሚዲያ በኩል አጀንዳ የቀረፁልን የውጊያው ጄኔራሎች እና ተባባሪዎች በቁጥር እጅግ ጥቂት ሲሆኑ አራጋቢዎቻቸውን ጨምሮ ከአንድ እጅ ጣት አይበልጡም፡፡ ብዙ ሰው የተከፋፈለ ቡድን እንዳለ እና ከትምህርት ቤት የመጣው የተጫወተውን እንደሚያሳድደው፤ የተጫወተውም ከትምህርት ቤት የመጣውን እንደሚጠላው አድርጎ ለማቅረብ የሚደረጉ ሙከራዎች እና መረጃዎች መሰረተ ቢስ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች እየተከተሉት ያለው ‹‹የከፋፍል›› አካሄድ ፖለቲከኞቻችን ተግብረውት ሐገርንም ሆነ ሕዝብን ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ያደረገ ሲሆን የተከተሉትም መርህ ‹‹የተጫዋተ›› ሁሉ ‹‹እንዳልተማረ››፤ ‹‹የተማረ›› ሁሉ ‹‹እንዳልተጫወተ›› አድርጎ የመፈረጅ አባዜ የተጠናወተው ነው፡፡

ፀሀፊው ምንም እንኳን በቅንነት በዚህ የሚዲያ ውዥንብር ሰለባ ሆነው ቡድን የተፈጠረ አድርገው በመጀመሪያ ፅሁፋቸው አንቀፅ 1 ላይ ‹‹ጥቂት የማይባሉ የሀገራችን እግር ኳስ ባለሙያዎች ጎራ ለይተው በአንድ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ውዝግብ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል፡፡››፣ አንቀፅ 9 ላይ ‹‹ጎራ ለይቶ እኔ አውቃሁ እኔ አውቃለሁ እያሉ ተመልካችን ግራ ማጋባት›› እና በሁለተኛ ፅሁፋቸው አንቀፅ 1 ላይ ደግሞ ‹‹ተጫውተው ያለፉ እና የስፖርት ሳይንስ የተማሩ›› በማለት ማቅረባቸው፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ፅሁፋቸው መሰል ስሜትን ይዘው መተንተናቸው እንደ ቀዳሚ ስህተት ቆጥሬ ግለሰቦች ለትግል ስልት የፈጠሩት ድባብ እንጂ የተጠቀሱት ቡድኖች በተግባር መሬት ላይ እንደሌሉ አውቀው ማስተካከያ እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ፡፡

አሁንም ቢሆን ፀቡ ያለው ይኼንን አለም ላይ የሌለ አሰራር እንዳለ አድርገው በድፍረት የሚናገሩ፣ ዝም ብለን ስለሰማን የማናውቅ አድርገው የቆጠሩን፣ እኛ በተማርንበት ሐገር፣ እኛ በኖርንበት አለም ‹‹የተጫወተ ብቻ ነው የሚያሰለጥነው›› በማለት ቡድንተኝነት እንዲያቆጠቁጥ በሚተጉ ሰዎች እና በእኛ ‹‹ፈቃድ ያለው ሰው ሁሉ ማሰልጠን ይችላል›› በምንለው መሀከል ነው፡፡

ፀባችን ያለው ባገኙት መድረክ ሁሉ ‹‹ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገር አለብን›› በማለት የጦርነት ነጋሪት በሚጎስሙ፣ በቁጥር ከአንድ እጅ ጣት በማይበልጡ እና እድሉን አግኝተው ፕሬዝዳንት አልያም ቴክኒክ ዳይሬክተር ቢሆኑ ምንኛ ሊያሳድዱን እንደሚችሉ ስናስብ ከሚዘገንነን ሰዎች ጋር ብቻ ነው፡፡ ወደ ሐገር ቤት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ‹‹የተጫወተ፣ ያልተጫወተ፣ የተማረ፣ ያልተማረ፣ በፕሮፌሽናል ደረጃ የተጫወተ፣ በፕሮፌሽናል ደረጃ ያልተጫወተ…›› በማለት ከፋፍለውን ሲያበቁ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በፕሪሚየር ሊግ እና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ማሰልጠን የምንችለው ሰዎች ከሶስት አንበልጥም›› በማለት በድፍረት ከሰደቡን ግለሰቦች ጋር እንጂ ንግግራችን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ካሉ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ባለሙያዎች ጋር አይደለም፡፡

ከነሱም በተጨማሪ ‹‹ካለው የደገመው›› እንዲባል ሁሉ እነሱ የተናገሩትን ሳያጣሩ እና ሳይመረምሩ ሚዛናዊ ባልሆነ ጠረጴዛ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ካስተላለፉ ግለሰቦች ጋር ብቻ ነው ንትርካችን፡፡ ስለሆነም ‹‹የተጫወተ-ያልተጫወተ››፣ ‹‹በትምህርት የመጣ- በእግር ኳስ የመጣ›› የሚሉ ቡድኖች እንደተደራጁ አድርጎ በማስመሰል የሚቀርቡ ዜናዎች፣ ዘገባዎች፣ ፅሁፎች፣ አስተሳሰቦች በሙሉ የተሳሳቱ እና ለማታገያ ብቻ የቀረቡ ‹‹የባንኮኒ አጀንዳዎች›› እንደሆኑ የስፖርት ቤተሰቡ እንዲሁም ፀሀፊው ሊረዱ ይገባል፡፡

ተጨዋቾችን የማያከብር እና የሚንቅ ሰው ተማረም፣ አልተማረም፣ ከዲግሪ እስከ ፒኤችዲ ደፋም አልደፋም፣ ጥቁር ጋውን ለበሰም አለበሰም በየትኛውም መመዘኛ እንኳን አሰልጣኝ ጥሩ ተመልካች መሆን አይችልም፡፡ ማናችንንም ቢሆን እግር ኳስ እንድንወድ ያደረጉን ኳሱን የሚገፉት ተጨዋቾች፣ ጥበቡን የሚያሳዩት ኳስ ነጂዎች እንጂ ሜዳው ወይም የካታንጋ ሐሩር አልያም የዳኛው ፊሽካ አይደለም፡፡ ተጨዋቾች ማህበራቸውን እንኳን እራሳቸው የማይመሩበት በቅኝ ግዛትም ይባል በሞግዚት አስተዳደር ስር በወደቁበት ሐገር ውስጥ የበለጠ የሚደገፉ እንጂ የሚነቀፉ አይደሉም፡፡ እኔ እና በክርክሩ ላይ የተጠመድነው ሰዎችም ተጨዋቾችን የምናከብር፣ የበለጠ ሊታገዙ እንደሚገባ ባገኘነው መድረክም ሆነ ባዘጋጀናቸው የመንግስት ሰነዶች ሁሉ አጥብቀን የተከራከርን እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ግለሰቦች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ተጨዋቾችን እንደ ጫካ በመጠቀም የሌሉ ቡድኖች እና አንጃዎች እንደተፈጠሩ አድርገው ማቅረባቸው ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ በተከራከርንባቸውም የትኛውም መድረኮች ላይ ተጨዋቾችን፣ ተጫውተው ያሳለፉ ሰዎችን አሳንሰን አይተን የማናውቅ ሲሆን እንዴውም በጣም የተሳካላቸውን የምንቀናባቸው ያልተሳካላቸውን ደግሞ በሐዘኔታ የምንመለከት የስፖርት ባለሙያዎች ነን፡፡

2- ‹‹ጉንጭ አልፋ››

ፀሀፊው ስተውታል ብዬ ከማስባቸው ቁልፍ ነጥቦች መሀከል አንዱ እና ዋንኛው በተለያዩ ሚዲያ ላይ እየቀረብን የምናደርጋቸውን ክርክሮች አለፍ ሲልም ውዝግቦች ‹‹ጉንጭ አልፋ››፣ ‹‹ትርጉም የለሽ››፣ ‹‹ብርቱ አጀንዳ የያዙ ይመስል››፣ ‹‹እርባና ቢስ ክርክር››፣ ‹‹ረብ የለሽ ክርክር››፣ ‹‹በከንቱ እዬዬ ጊዜያቸውን እያባከኑ›› የሚሉ እና መሰል ቃላቶችን እየተጠቀሙ ማጣጣላቸው ነው፡፡ ክርክሩን በአፀፋው መላሾች ጫማ ላይ ሆነው ማየት አለመቻላቸው (Lack of Empathy) ለዚህ የዳረጋቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ገለልተኛ መስሎ ለመቅረብ ያደረጉት ሙከራም እንደሆነ ይገባኛል፡፡ የክርክሩን መንስኤም ሆነ ምክንያት እንደማያውቅ በመሆን ሸፍነው ለማለፍ ያደረጉት ጥረት ‹‹ገለባን እሳት ውስጥ እንደመሸሸግ›› ሆኖ ታይቶባቸዋል፡፡

እውነት ነው እረዳቸዋለሁ፤ ላይ ላዩን ክርክሩን ለሚያስተውል ሰው ‹‹ጉንጭ አልፋ›› ቢመስል አይገርምም፡፡ በእሳቸው ደረጃ ጠለቅ ያለፅሁፍ እና ትንተና ለመፃፍ እንደቻለ ሰው ግን በእኛ በኩል ያለው ክርክር በዚህ መልኩ ተቃሎ ሊገለፅ የሚገባው ጉዳይ አይደለም፡፡ ምን አልባትም ጩኸታችንን በዚህ መልኩ የተረዱ ካሉና የእርሳቸውን ፅሁፍ አምነው የተቀበሉ ሰዎች ከተገኙ፤ ማስተካከያ ለማድረግ ይህ ‹‹ጉንጭ አልፋ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ክርክር ለእኛ ለአፀፋ ሰጪዎች ከጉንጭ አልፎ ከጉሮሮ እና ከኑሮ ጋር የሚያያዝ የህልውና ክርክር እንደሆነ ለማስረዳት ልሞክር፡፡

ከላይ የጠቀስኳቸው እና ቁጥራቸው ከአንድ መዳፍ ጣቶች የማይበልጡ ግለሰቦች በተከታታይነት በሚዲያ እየወጡ እጅግ ከፍተኛ ድፍረት በተሞላበት መልኩ ሙያን በማጣጣላቸው እና ሙያተኛን በማንቋሸሻቸው ብቻ ነው ወደዚህ ውዝግብ የገባነው፡፡ ‹‹የጥቁር አምበሳ ዘበኛ “ሆስፒታል ነው የምሰራው” ብሎ ማውራት ይችላል፤ ቀዶ ጥገና ላድርግ ማለት ግን አይችልም›› በማለት አስተያየት የተሰጠው በእነዚህ ሰዎች ብዙዎች በሚከታተሉት መገናኛ ብዙሀን ነው፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ‹‹ዘበኛ›› መባል እና መሆን ምንም ነውር እንደሌለው ስራውም ክቡር እንደሆነ ብናምንም ንግግሩ ያዘለውን ‹‹መርዝ›› ግን ጠንቅቀን እንረዳለን፡፡ እስከ አራተኛ ክፍል ተምረን እስከ ሶስተኛ ክፍል የተማሩ ሰዎች የሚሸርቡት ሴራን መረዳት ካቃተንማ ምንም ዋጋ የሌለን፤ እንደሚሉትም ‹‹አቅመ ቢሶች›› ነን፡፡

‹‹በተግባር የሌሉ››፣ ‹‹የቲዮሪ ሰዎች ናቸው››፣ ‹‹እጅ እና እግር የሌላቸው ተማሪዎችን እያስመረቁ›› የሚሉ እና መሰል መርዛማ አንደበቶችን ለማርከስ ስንል ወደ ውዝግቡ ለመግባት እንደተገደድን ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይህ እና መሰል መጥፎ አስተሳሰቦች ታናናሾቻችን ውስጥ እንዳይሰርፅ፣ ዜጎችን እንዳያታልል፣ የባለሙያ ሞራል እንዳይሰብር፣ የተማሪዎቻችንን ስሜት እንዳይጎዳ ለመጠበቅ የገባንበት ክርክር ለእኛ ለባለሙያተኞቹ ፀሀፊው እንዳሉት ‹‹ትርጉም የለሽ›› ወይም ‹‹እርባና ቢስ›› ክርክር አይደለም፡፡

እንደ ትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ 26 ሚሊየን ተማሪዎችን የሚያስተምሩ ከ50ሺህ በላይ የትምህርት ተቋማት በሐገራችን ይገኛሉ፡፡ ምን አልባትም በየአንዳንዱ ተቋም ውስጥ አንድ አንድ የስፖርት መምህር ቢኖር ለ50 ሺህ መምህራን ጠበቃ ሆነን የቀረብንበት ክርክር ፀሀፊው እንደሚሉት ‹‹በከንቱ እዬዬ›› ጊዜ ማባከን አይደለም፡፡ በ27 ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ከ5ሺህ በላይ የስፖርት ሳይንስ ተማሪዎችን ተከላክሎ ዘመን አፈራሹን እና የመንግስት ብልሹ አስተዳደር ውጤት የሆነውን ‹‹ትምህርት፣ ተማሪ እና አስተማሪ ጠል›› የሆነን አመለካከት በይፋ ማውገዛችን ለእኛ ለባለቤቶቹ ተቃሎ የሚታይ አጀንዳ አይደለም፡፡

ብዙዎቻችን ቴሌቪዥን ላይ ካሁን ካሁን ልንሰደብ ነው ብለን የምንሳቀቅበትን፣ ከቤተሰቦቻችን ጋር ቴሌቪዥን እየተመለከትን የምንዋረድበትን፣ የተከታታይ ሬዲዮ ፕሮግራም ማዳመቂያ የምንሆንበትን፣ ለስፖንሰርሺፕ ጋጋታ ማቀጣጠያ የተደረግንበትን ሐሰተኛ መረጃን ፊት ለፊት መጋፈጥ እና እርማት መስጠት ፀሀፊው እንደሚሉት ‹‹እርባና ቢስ ክርክር›› አይደለም፡፡

እነርሱ ቤታቸውን በግንብ እየሰሩ በእኛ ሳር ቤት ላይ ክብሪት የሚጭሩ፣ እነርሱ የታሸገ ውሐ እየጠጡ የእኛን ኩሬ የሚያደፈርሱ፣ እነርሱ በ2.5 ሚሊየን ብር የፊርማ ክፍያ ከክለብ ክለብ እየዞሩ (ይህ የአንድ ቀን ክፍያ ለአንድ አማካኝ የስፖርት መምህር የ29 አመት ደሞዝ እንደሆነ ልብ ይሏል) እኛ ተማሪዎቻችን እና ሰልጣኞቻችን ፊት እንዳንቆም የሚያደርጉ ሰዎችን ማሳቀቅ እና አሳንሰን ማሳየት መቻላችን ለእኛ እና ወዳጆቻችን ቁልፍ ሙያዊ ስኬት ነው፡፡

የእነርሱ ልጆች ጥሩ ትምህርት ቤት እየተማሩ የእኛ ልጆች የትም እንዲወድቁ የሚተጉ፣ እነርሱ ባንኮክ እና ታይላንድ እየታከሙ እኛ የመንደር ጤና ጣቢያ እንኳን መታከሚያ እንድናጣ የሚሰረስሩ ሰዎችን ፊት ለፊት የታገልን ከዚህ በኋላም እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ ለመታገል የምንሰራ፤ ላለፉት አመታት ያሸረቡትን ሴራ የጎሰሙትን ጦርነት በይፋ ይቅርታ ጠይቀው ካላቆሙ የማንቆም እንደሆነ በዚህ አጋጣሚ ሊረዱት ይገባል፡፡

ጩኸታችን ፀሀፊው እንደሚሉት ‹‹እርባና ቢስ›› ሳይሆን ቤቱ ተሰብሮ በሌባ እንደተዘረፈ አንድ ምስኪን ጩኸት ሊደመጥ የሚገባው ሲሆን ምንም እንኳን ሌሎችን ከሞቀ እንቅልፍ ቀስቅሰን ምቾት ብንነሳቸውም በውድቅት ሌሊት ልንቀማ የነበረውን ንብረታችንን ለማስጣል የቻልንበት ድምፅ ነው፡፡

ፀሀፊው ይሄንን ሁሉ ስንሰደብ ‹‹ተው! አደብ ግዙ!›› በማለት ሁለት መስመር ለመፃፍ ሳይፈልጉ ዛሬ በሁለት ክፍል መልስ በመስጠት ወደ መድረክ መምጣታችንን እንደዚህ ማብጠልጠላቸው ልረዳው ያልቻልኩት ሚስጢር ሆኖብኛል፡፡ ‹‹አይ! ለኢትዮጰያ እግር ኳስ ስትሉ›› ቢባል እንኳን አራት አመታት ያህል በመታገስ ነገሮች በአግባቡ እንዲፈቱ ሙከራ አድርገናል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሐሳባችንን ተቀብለውናል›› በማለት መናገር መጀመራቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ አቋማቸውን በይፋ እንዲያሳውቁ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል በኩል ጥረት አድርገናል፡፡ አለፍ ሲልም ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ የፌዴሬሽኑን ፅ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም የወቅቱን የቴክኒክ ዳይሬክተር ሁሉም ያገባኛል የሚል የስፖርት ማህበር እና ባለሙያዎች የሚሳተፉበት አለም አቀፍ ተሞክሮዎች በጥናት የሚቀርቡበት ሴሚናር ወይም ወርክሾፕ እንዲዘጋጅ ጠይቀናል፡፡ ይሁንና ተቋሙ ይሄ አጀንዳ የሚረግብበትን መንገድ ለመፈለግ ዳተኝነት ስላስተዋልንበት እኛም ወደ ሚዲያ ሄደን ማስተካከያዎች እንዲደረጉ ጥረት አድርገናል፤ ለውጥም አይተንበት በዚሁ በሶከር ኢትዮጵያ ‹‹ማህበራችን ያልተጫወተ አያሰልጥን የሚል አቋም የለውም›› በማለት የማህበሩ ፀሀፊ በይፋ ከአመራሮቹ የተለየ አቋም እንዲይዙ እና የግንባሩን ግራ መጋባት እንድናይ አስችሎናል፡፡

3- አሰልጣኝ ማን ነው?

ፀሀፊው ‹‹ጉንጭ አልፋ›› ብለው ወደሰየሙት ክርክር ካስገቡን ነጥቦች መሀከል አንዱ እና ዋንኛው ‹‹እግር ኳስን ተጫውቶ የማያውቅ ሰው የአሰልጣኝነት ፈቃድ ሊሰጠው አይገባም፤ የትም አለምም የለም›› የሚል ትርክት በእግር ኳስ ማህበረሰቡ ዘንድ እንዲሰራጭ በመደረጉ እና ‹‹ፒያኖ ተጫውቶ የማያውቅ ሰው የፒያኖ አሰልጣኝ እንዴት መሆን ይችላል?›› የሚሉ ‹‹የእግር ኳሳችን ሞዛርቶች›› በመፈጠራቸው ነው፡፡ ‹‹እኛ በሙያው ያለፍን፣ የደማን እና የቆሰልን እያለን እንዴት ኳስ መተው ማሳየት የማይችሉ የዩኒቨርሲቲ ሰዎች አሰልጣኝ ይሆናሉ›› የሚሉ አጣጣይ አስተያየቶች በተለያዩ መድረኮች እና ሚዲያዎች መስማታችን ወደ ውዝግቡ እንድንገባ አድርጎናል፡፡ ይህ መጥፎ ትርክት በተጨዋቾች እና በእግር ኳስ ቤተሰቡ ስር ሳይሰድ ለመቅረፍ መሞከራችን ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ለዚህ እንደማሳያ ከወራት በፊት በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን በሚተላለፈው ‹‹ሰይፉ ሾው›› ላይ አመለሸጋው እና የቀድሞው የብሄራዊ ቡድናችን አማካኝ አዲስ ህንፃ እንግዳ በመሆን ቀርቦ ነበር፡፡ በሐገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተነሳውን ሁከት እና ብጥብጥ ተከትሎ በተጨዋቹ መኖሪያ ቤት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማሳየት ብሎም ስፖርተኛውን ለማገዝ በተዘጋጀው በዚህ ፕሮግራም ላይ አንድ ከርዕሱ ወጣ ያለ እና እንደ ማዋዣ የቀረበ ቃለ ምልልስ ነበር፡፡

ሰይፉ፡- ‹‹ጫማህን ስትሰቅል አሰልጣኝ የመሆን ሐሳብ አለህ?››
አዲስ፡- ‹‹አይ እኔ አልፈልግም››
ሰይፉ፡- ‹‹ለምን?››
አዲስ፡- ‹‹እኔ አልፈልግም፤ ባይሆን አማካሪ ልሆን እችላለሁ››
ሰይፉ፡- ‹‹ሰሞኑን እንደምሰማው ከሆነ ግን በፕሮፌሽናል ደረጃ የተጫወቱ ብቻ ናቸው አሰልጣኝ መሆን ያለባቸው እየተባለ ነው››
አዲስ፡- ‹‹አዎ እሱን እኔም ሰምቻለሁ››

ይሄ ቃለ ምልልስ አንድ ሐሰተኛ ሀሳብን አንስቶ በማራገብ እንዴት ሰው አዕምሮ ውስጥ ማስቀመጥ እንደሚቻል (Availability Heuristic Bias) ለማሳየት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በፖለቲካው ቋንቋ ‹‹ትርክት›› እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ሰይፉ እና አዲስ ህንፃ አንድ ሐሰተኛ ትርክትን ደጋግመው በመስማታቸው እውነት አድርገው ወስደውት በየዋህነት ለሌሎች አስተጋብተውታል፡፡ እንግዲህ ‹‹ውሀ የማያነሳ›› በተባለው ክርክራችን ለመግታት የሞከርነው ይሄንን የሐሰት ጎርፍ ነው፡፡

ምንም እንኳን ፀሀፊው በመጀመሪያ ፅሁፋቸው ‹‹የተጫወተም ሆነ ያልተጫወተ ማሰልጠን ይችላል፤ አለም አቀፍ ተሞክሮውም ይህ ነው›› በማለት እኛ ላቀረብነው ሐሳብ ምስክርነታቸው ከ40 በሚበልጡ መስመሮች ቢገልፁም ‹‹በመሰረቱ እኔ የየትኛውም ጎራ ደጋፊ አይደለሁም›› በማለት ሐሳባቸው ከእኛ ሐሳብ ጋር እንደማይስማማ አድርጎ ለማለፍ መሞከራቸው አስገርሞኛል፡፡ ፀሀፊው ‹‹የአስተያየቴ አላማ መተቸት ብቻ ሳይሆን ባለሙያዎቹ ቆም ብለው ስህተታቸውን እንዲያዩ እና አቅጣጫቸውን እንዲያስተካክሉ ይሆናል›› በማለት በሁለተኛው ፅሁፋቸው አንቀፅ 5 ላይ ቢያስቀምጡም የተሳሳተውን በልበ ሙሉነት ‹‹ተሳስቷል››፣ ከእሳቸው ሐሳብ ጋር የሚሄደውን ደግሞ በልበ ሙሉነት ‹‹ትክክል ነው›› ለማለት ድፍረቱ ሲያንሳቸው ተመልክቻለሁ፡፡

አሁን አሁን በሐገራችን ያሉት የሐሰተኛ ትርክት መራሾች ‹‹ዲግሪ እና ማስተርስ የሌለው አያሰልጥን›› ብለን እንደምንከራከር አድርገው በማስመሰል ከተጨዋች እና ከሚዲያ ጋር ለማጣላት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ እኔ እና የስራ ባልደረቦቼ እንደምናምነው፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደተናገርነው እግር ኳስ ተጨዋቾች አሰልጣኝ ለመሆን እጅግ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ በጨዋታ ዘመናቸው ያገኟቸው እውቀቶች፣ ክህሎቶች፣ አስተሳሰቦች እና ስሜቶች እጅግ ከፍተኛ ጥቅም አላቸው፡፡ የአሰልጣኞች ስልጠና እና ፈቃድ ወስደው ወደ ሙያው ቢገቡ ብዙ ዕድሎችን ይዘው እንደሚመጡ እሙን ነው፡፡ ለዚህም ከፍተኛ እድል ሊመቻችላቸው፣ የስልጠና እና ትምህርት እድል ሊከፈትላቸው ይገባል በማለት በኢትዮጵያ ስፖርት ሪፎርም ሰነድ ላይ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ እንዲሆን በማድረግ ያገኘነውን የሙያ እድል በመጠቀም አስፍረናል፡፡

ክለቦች የተጨዋቾች ብቻ ሳይሆን የአሰልጣኞች መፍሪያ እንደሆኑ በደንብ ይገባናል፤ አለም ላይ ያለውም ተሞክሮ ይኸው ሲሆን ‹‹እንካደው›› ቢባል እንኳን ልንክደው የማንችለው ሐቅ ነው፡፡ ለዚህ እንደማሳያ እ.ኤ.አ በ1996 የስፓኒሽ ሱፐር ካፕ አሸናፊ ከነበረው የባርሴሎና ቡድን 27 ተጨዋቾች መሐከል አሰልጣኝ መሆን ያልቻሉት 5 ብቻ ናቸው፡፡ ይባስ ብሎ እ.ኤ.አ በ2015 የቻምፒየነስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ተፋላሚ ከነበሩት 8 ቡድኖች መሐከል 4ቱ የሰለጠኑት ከ1996ቱ የባርሴሎና ቡድን ተጨዋቾች ነበር፡፡ ባየርን ሙኒክ በ ፔፕ ጋርዲዮላ፣ ፖርቶ በጁለን ሎፕቴጌዝ፣ ፒ.ኤስ.ጂ በሎውረን ብላ እና ባርሴሎና በሉዊስ ኤንሪኬ እየተመሩ ተወዳድረዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ‹‹መጫወት›› ለማሰልጠን እጅግ ቅርብ እንደሆነ ነው፡፡

4- እግር ኳስ ሳይንስ ወይስ አርት?

የኢትዮጵያ ታዳጊዎች ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾችን የፓስፖርት እድሜን በተሰራ ካልኩሌተር መደመር እና መቀነስ ከብዷቸው ሐገሪቷ ያለ ተቀያሪ ተጨዋቾች እንድትጫወት ያደረጉ ሰዎች ዛሬ ጊዜ ደግ ነውና ‹‹እግር ኳስ ሳይንስ ነው አርት ነው›› የሚል ፍልስፍና ፈጥረው ሊከራከሩ መሞከራቸው በራሱ አስቂኝ ቢሆንም ‹‹አዲስ ርዕዮተ አለም›› በእግር ኳሱ አለም ለመፍጠር ያደረጉትን ትጋት ግን ሳላደንቅ አላልፍም፡፡

ፀሀፊው በዚህ ‹‹አዲስ ርዕዮተ አለም›› ክርክር ውስጥ መግባታችን እንዳልተዋጠላቸው ሲገልፁ ‹‹ከዘመናት አስተሳሰብ ብዙ ሺህ ማይሎችን ርቀን ታች ወርደን መገኘታችን ያሳዝነኛል›› ብለውታል፡፡ እውነት ነው! የፈረስ ስፖርት እንኳን ሳይንስ ሆኖ የፈረሶች ዘረ መል (Genetics)፣ አካላዊ መዋቅር (Anatomy)፣ ውስጣዊ የህይወት አመራር (Physiology)፣ ውጫዊ ገፅታ (Morphology)፣ አካል ብቃት (Physical Fitness) እና ሌሎችም ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች በሳይንስ ጥናትና ምርምር እየተደረገባቸው ልምምድ ሲሰሩ እያየን ከፈረስ ለየት በሚል መልኩ ማህበራዊ (Social)፣ ስሜታዊ (Emotional)፣ አስተሳሰባዊ (Cognition)፣ የጾታዊ ግኑኝነት (Sexual) አፈጣጠር ያላቸውን ሰዎች ማሰልጠን ‹‹ሳይንስ አይደለም፣ ንድፈ ሐሳብም የለውም›› በሚል ክርክር ውስጥ መሳተፋችንን ሳስብ ‹‹ወደ ታች መውረዳችን›› ይታወቀኛል፡፡ ግን አንድ ወዳጄ ነገሩን አያይዞ እንዳስታወሰኝ ከሆነ ‹‹እየሱስም ከደረጃው በታች ታች ወርዶ ነው የሰዎችን ሀጢያት ለማስፀረይ የቻለው›› ብሎኛል፡፡ እኛም በሰውኛ አቅማችን ስህተትን ለማረም እና ሌሎችን ከጥፋት ውሀ ለማዳን ስንል ሰዎች በሚገባቸው ቋንቋ እና በሚፈልጉት ርዕስ ላይ ‹‹ታች ወርደን›› መከራከራችን ምርጫችን ሳይሆን ግዴታችን ነበር፡፡

ምን አልባትም ፀሀፊው ይረዱት አይረዱት ባላውቅም የዚህ ‹‹እግር ኳስ ሳይንስ ነው ወይስ አርት ነው›› የሚለው የመከራከሪያ ጭብጥ በውስጡ ትልቅ መርዝ የያዘ ሲሆን በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠውን የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ለማጥቃት ‹‹እግር ኳስ አርት ነው እንጂ ሳይንስ አይደለም፤ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአሰልጣኝነት ስልጠና ሊሰጥ አይገባም›› ብለው ለሚያቀርቡት መከራከሪያ የሚያገለግል ቀሽም መስፈንጠሪያ ነው፡፡ እንደነሱ ሙግት እግር ኳስ ‹‹አርት›› እንጂ ‹‹ሳይንስ›› ባለመሆኑ ‹‹መጫወት›› እንጂ ‹‹መማር›› አሰልጣኝ ለመሆን ፋይዳ የለውም፡፡ ወደዚህ ‹‹አዲስ ርዕዮተ አለማዊ›› ክርክር የጋበዘንም ይህ ስፖርት ሳይንስ ትምህርትን ከእግር ኳስ ለመነጠል የተደረገው ሙከራ አሳስቦን ነው እንጂ ፀሀፊው እንደሚሉት ተራ ምልከታ መሆኑ ጠፍቶን አይደለም፡፡

ይባስ ብሎ ‹‹አዲሱ ርዕዮተ አለማቸው›› ሩቅ እንደማይወስዳቸው ሲገባቸው ‹‹በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው ትምህርት “ስሙ ነው እንጂ ሳይንስ የሚማሯቸው ትምህርቶች እንደ ቮሊቮል፣ እጅ ኳስ፣ ዋና እና መገለባበጥ የመሳሰሉ የመዝናኛ ተግባራት (Recreational Activities) ናቸው›› ብለው መከራከርም ጀምረው ነበር፡፡ ትምህርታችንን በዩኒቨርሲቲ ሳይሆን በገነት ሆቴል መናፈሻ እንደሚሰጡ የጊዜ ማሳለፊያ ተግባራት ቆጥረው ለእግር ኳስ ፋይዳ ቢስ እንደሆነ አድርገው ከአንዴም ሁለቴ በሚዲያ መሳደባቸውን ተከትሎ ወደ ክርክሩ ልንገባ ተገደናል፡፡ ‹‹እግር ኳስ የተግባር ስራ ነው ምንም ቲዮሪ የለውም›› በማለት የምንሰጠው ትምህርት እርባና ቢስ ሆኖ እንዲታይ ተግተዋል፡፡

ከእነዚህ መራሾች አንዱ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ‹‹እያወራን ያለነው ዩኒቨርሲቲ ተጫውቻለሁ፣ ዩኒቨርስቲ ተምሬያለሁ፣ ዩኒቨርሲቲ አስተምሬያለሁ ስለሚሉ ሰዎች አይደለም…እሱን ተወው አማተሮች ናቸው›› በማለት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን እና ሙያን ካጣጣሉ በኋላ ‹‹አሁን ፍፄን ውሰደው በጣም ኢንተለጀንት ልጅ ነው፤ ዲግሪውን ጥሎ ነው እኛ ጋር የመጣው›› በማለት ፍፁም ገብረማርያምን ለማደናነቅ ሞከሩ፡፡ እውነት ነው ፍፁም እንደሌሎች ተጨዋቾች ሁሉ በራሱ ጥረት ያለምንም ይህ ነው የሚባል ሐገራዊ ድጋፍ ትልቅ ደረጃ የደረሰ ተጨዋች ነው፡፡ ሆኖም ግን ፍፁም እዚህ እንዲደርስ እኔ እና የእኔ የስራ ባለደረቦች የነበረን ሚና እሳቸው እንደሚሉት የሚጣጣል አይደለም፡፡ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የተማሪዎች ውድድር ላይ ወለጋ ዩኒቨርሲቲን ወክሎ ሲጫወት በሙገር የተመለመለው ፍፁም፤ ለእርሱ እዚህ መድረስ እኛ የስፖርት መምህራን በፈጠርነው ሐገር አቀፍ ውድድር፣ ኖራ እያሰመርን ባዘጋጀነው ሜዳ፣ እሱን እና ጓደኞቹን የአቅማችንን በማሰልጠን እና የመጫወት እድል በመፍጠር በልጁ እድገት የበኩላችንን ሚና ተጫውተናል፡፡ ይባስ ብሎም እሱን መልምለው ወደ ሙገር የወሰዱት ጋሽ አዳነ የቀድሞ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት መምህር መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ማክበር ባይቻል እንኳን ማጣጣሉ አስፈላጊ አልነበረም፡፡

ፀሀፊው ክርክራችንን ያጣጣሉት በፍፁም ቅንነት መሆኑን ባምንም የአጀንዳው ጠንሳሾች እና ተሟጋቾች አላማ ግን ትምህርታችንን ለማሳነስ፣ ሙያተኛን ለማንኳሰስ፣ ስፖርት ሳይንስን ከእግር ኳስ ለመነጠል፣ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ምንም ተግባር እንደሌለ ለማስመሰል፣ በአጠቃላይ ሙያ እና ባለሙያን አሳንሶ ለማሳየት እንደሆነ ሊረዱት ይገባል፡፡

5- ‹‹በቂ እድል ተሰጥቷችኋል››

ከተከራከርንባቸው እና ፀሀፊው ደስተኛ ካልሆኑባቸው ነጥቦች አንዱ ‹‹በቂ እድል እየተሰጠን አይደለም›› በማለት ያቀረብነው ምሬት ነው፡፡ ፀሀፊው ‹‹ሁለታችሁም በቂ እድል ተሰጥቷችሁ ፋይዳ ያለው ስራ ልትሰሩ አልቻላችሁም›› የሚል መከራከሪያ በማቅረብ የተለያዩ ማሳያዎችን አስቀምጠዋል፡፡ እውነት ነው፤ በስመ ስፖርት ሳይንስ ዲግሪ፣ ማስተርስ እና ፒ.ኤች.ዲ ብዙዎች የስፖርት ተቋማትን እንዲመሩ፣ በተለያዩ የስፖርት ተቋማት እንዲሁም ክለባት በሀላፊነት እንዲሰሩ እድል ተሰጥቷቸዋል፡፡ እውነቱን ለመናገር አብዛኛው ካባ እና ቆብ ይኑረው እንጂ ወይ በበፖለቲካ አቋሙ፣ አልያም በብሄሩ፣ አለፍ ሲልም በጥቅም እድሉን ያገኘ እንደሆነ ያለፉት 15 አመታት የሙያ ልምዴ ምስክር ነው፡፡

በይፋ በጋዜጣ የወጣ ማስታወቂያ እየተቀለበሰ፣ ማስታወቂያ እየተገነጠለ፣ ማስታወቂያ በሰዎች ልክ እየተሰፋ፣ ማስታወቂያ ከስፖርታዊ ምክንያት ይልቅ በሌላ መስፈርት እየተቀመጠ ብዙዎች የማይገባቸውን ስራ በስመ ስፖርት ሳይንስ፣ በስመ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ የተቻላቸውን ሞክረው ውጤት ለማሳየት የተጉ ቢኖሩም ባልተገባ ባህሪ፣ በስፖርት እውቀት ማነስ፣ ከፍተኛ የሙያ ክህሎት እጥረት፣ በስፖርት ፍቅር እና ስሜት ማጣት እንዲሁም መሰል ምክንያቶች ተቋማትን ይዘው ሲወድቁ ክለባትን ሲያንኮታኩቱ ለመመልከቴ በስም እየጠቀስኩ ምስክር መሆን እችላለሁ፡፡

ሆኖም ግን እነዚህን እና መሰል ሰዎችን ብቻ በማየት ‹‹የስፖርት ሙያተኞች እና ስፖርት ሳይንስ የሚገባቸውን ድርሻ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ አግኝተዋል›› በማለት መከራከር ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ፀሀፊው ከጠቀሷቸው አምስት የስፖርት ተቋማት እና የስራ መስኮች መሀከል አራቱ የመንግስት እንደመሆናቸው ዋንኛው የኢንዱስትሪው አንቀሳቃሽ በሆነው ህዝባዊ አደረጃጀቱ ጋር ያለን እና የነበረን ሚና እጅግ አናሳ ነው፡፡

ብሄራዊ ፌዴሬሽኖች፣ የክልል ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦች የስፖርት ሳይንስ ባለሙያ የመቅጠር ባህላቸው እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን በጥቂቱ ባህሉን ለማዳበር ተነሳሽነት አሳይቶ የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንኳን ባለፉት 18 ወራት ብቻ 4 ባለሙያዎች ለቀውበታል፡፡ እውነት ነው ‹‹ምን ሰሩ?›› ‹‹ለምን ለቀቁ?›› ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ በሐገሪቱ አለ የሚባለው ትልቁ ህዝባዊ የስፖርት ተቋም እና ብዙዎቻችን ተማሪ ሳለን መቀጠርን እንደ ህልም የምናየው ኦሊምፒክ ኮሚቴ በአሁኑ ሰአት በአማተር አገልጋዮች ተሞልቶ አንድ (እርሱም ተንሳፋፊ) የሆነ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያ ብቻ ነው ያለው፡፡ ክለቦች ላይም ቢሆን የስፖርት አስተዳደር፣ የስፖርት ስነ ምግብ፣ የስፖርት ማርኬቲንግ፣ የስፖርት ሳይኮሎጂ፣ የአካል ብቃት ባለሙያ፣ የስፖርት ፊዚዮቴራፒ እና መሰል የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎችን የመቅጠር ባህላቸው እጅግ ደካማ ነው፡፡ እውነት ነው ለዚህ ባህል መዳበር ቀድመው የገቡ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች የተሸከሙት ‹‹ገፊ›› ባህሪ ሲሆን ባለሙያን ከማስፋት ማራቅን መምረጣቸው እና ቦታውን እንደ ርዕስት መያዛቸው ነው፡፡

እንኳን ደሞዝ ያለውን ቋሚ ስራ ማግኘት ቀርቶ ተመራቂ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የስራ ላይ ልምምድ እና ትምህርት የሚያገኙበት፣ ኢንተርንሺፕም ሆነ አፓረንትሺፕ የሚወጡበት ፈቃደኛ ክለብም ሆነ የስፖርት ተቋም ማግኘት የሰማይን ያህል ሩቅ ነው፡፡ ተማሪዎቻችን የተሻለ ትምህር ሊያገኙ የሚችሉበት አሰራር በካሪኩለም ተቀርፆ ቢቀመጥም በስፖርት እና እግር ኳስ ኢንዱስትሪው ገፊነት የወራት ነፃ አገልግሎት እድል ሲነፈጉ ማየት የአመት አመት ተሞክሯችን ነው፡፡ አስታውሳለሁ የሁለተኛ ዲግሪዬን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተማርኩበት ወቅት አንዳችንም አፓረንትሺፕ የምንወጣበት ክለብ ሳናገኝ

የስራ ላይ ልምምድ ያደረግነው እርስ በእርስ በመማማር ነበር፡፡ በውጭ ሐገር የትምህርት ቆይታዬ ግን በአንድ የኢሜይል ግኑኝነት ብቻ ብራዚላዊቷ ማርታ የምትጫወትበት ኤፍ.ሲ ሮዜንጋርድ የተባለ የስዊድን የሴቶች እግር ኳስ ክለብ ውስጥ የስራ ላይ ልምምድ ለማግኘት ችያለሁ፡፡ ልዩነቱ ሰፊ ነው፤ እዚህ በታናናሾቻችን ላይ የምንሰራው ግፍ አይን ያወጣ እንደሆነ የእኔ ሁለት ልምዶች ብቻ ማሳያ ናቸው፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ከስራ ሲባረሩ ወደ ሚዲያ በመውጣት ስፖርት ሳይንስ ትምህርትን እና ባለሙያዎችን በመሳደብ የስራ ማፈላለጊያ የሚያደርጉን ባለሙያዎች ባለፉት አስር አመታት ውስጥ ብቻ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ፣ የኢትዮጵያ ታዳጊዎች ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ፣ የብሄራዊ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተር፣ የክለብ ቴክኒክ ዳይሬክተር፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት ያስቀመጣቸው አዋጆች እየተጣሱ ሁሉ (ይህንን በጊዜው በሰፊው የምመጣበት ሆኖ ይቆየኝ) የተለያዩ አምስት ክለቦች ዋና አሰልጣኝ ሆነው በመስራት በአስር አመት ጊዜ ውስጥ 9 ከፍተኛ የእግር ኳስ ልማት እድሎች የተሰጣቸው እና በአንዱም እንኳን ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል ስራ፣ ውጤት፣ አሰራር፣ ቴክኖሎጂ፣ ስልጠና፣ ፍልስፍና ያላሳዩ ሰዎች ኢፍትሐዊ የሆነ ተደጋጋሚ እድል ሲሰጣቸው ለመታዘብ ይቻላል፡፡

ይሄ ደግሞ ፀሀፊው ‹‹የእግር ኳስ ዘርፍ ላይ በተለይም በአሰልጣኝነት ሙያ የቅጥር መስፈርቱ ችሎታና አቅም አለመሆኑ ያመጣው ችግር ነው›› በማለት ያቀረቡትን ሐሳብ የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ሌሎች እንዲህ ከሽንፈት ሽንፈት እየዘለሉ የሚፈነጩበትን ሴክተር እኛም በእኩል አይን ታይተን ሐገራችንን በተማርንበት ሙያ እንድናገለግል እድል እንደተሰጠን አድርጎ መከራከሩ ሙሉ እውነታውን ቁልጭ አድርጎ አያሳይም፡፡

6- ‹‹አብራችሁ ስሩ!››

ፀሀፊው በፅሁፋቸው ማጠናቀቂያ ላይ ‹‹እናንተም ሥራው በእጃችሁ እስካለ ድረስ ተነጋገሩ፣ ተቀራረቡ፣ ተደጋገፉ፣ አብራችሁ ለመስራት ሞክሩ›› በማለት እጅግ ቅን እና የፅሁፋቸውን ሙሉ ተልዕኮ የሆነውን ሐሳብ አስፍረዋል፡፡ እውነት ነው አብሮ መስራትን እና መማማርን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ይሄንን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ሞክረን እንዳልተሳካ አንድ እውነተኛ ገጠመኝ አሳይቼ ፅሁፌን ላብቃ፡፡

ከአራት አመት በፊት እኔ እና የሙያ ጓደኞቼ በጋራ በመሆን አንድ የውስጥ ጫናን (Internal Load) ለመከታተል የሚረዳ ቴክኖሎጂ ከውጭ ሐገር አምጥተን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የራሳችንን አስተዋፅኦ ለማበርከት ሽር ጉድ ማለት ጀመርን፡፡ በወቅቱ ከየትኛው አሰልጣኝ ጋር ብንሰራ በቀላሉ ተቀባይነት እናገኛለን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በእግር ኳሱ ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ማማከር ጀምረን አንድ አሰልጣኝ ተጠቆምን፡፡ አሰልጣኙ አሜሪካ ኖሮ የመጣ በመሆኑ በቀላሉ ቴክኖሎጂን ሊረዳ ይችላል፣ ከዚህ በፊትም ተጠቅሞበት ሊሆን ስለሚችል እናንተንም ያግዛችኋል በሚል ወደ እሱ እንድንሄድ ተመከርንና እሱን አግኝቶ የማናገር ሐላፊነት ለእኔ ተሰጠ፡፡ እኔም ከውጭ የመጣ ሰውን አግዝፎ በሚያይ ማህበረሰብ ውስጥ መወለዴን እና ማደጌን ተከትሎ እንደሚሳካልን ምንም ባለመጠራጠር ስልካቸውን አፈላልጌ ደወልኩላቸው፤ አልተነሳም፡፡ ደግሜ ደወልኩ፤ አሁንም አልተነሳም፡፡ ወቅቱ የተጨዋቾች ዝውውር ወቅት ስለሆነ የማያውቁትን ስልክ አያነሱ ይሆናል በማለት የፅሁፍ መልዕክት ላኩላቸው፤ አልመለሱም፡፡ ከቀናት በኋላ ደግሜ ላኩት..አሁንም አልመለሱም፡፡ ‹‹እንዴት ይሻላል›› ብዬ ያማከረኝን ሰው ስጠይቅ አዘውትረው የሚገኙበትን ሆቴል ጠቆመኝ እና ወደዛው አመራሁ፡፡

እንግዳ መቀበያው አካባቢ ለሰአታት ካሳለፍኩ በኋላ እንደተባለው አገኘኋቸው፡፡ አለም ላይ አሉ የሚባሉ ክለቦች እንደ ሊቨርፑል፣ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ቫሌንሽያ፣ የእንግሊዝ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን፣ የደቡብ አፍሪካ የራግቤ ቡድን እና የመሳሰሉ የስፖርት ተቋማት የሚጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ እኛ ጋር እንዳለ እና ከሳቸው ጋር አብረን ብንሰራ ደስተኛ እንደሆንን በመግለፅ የሙከራ ጊዜ እንዲሰጡን የያዝኩትን ሰነድ እያሳየሁ ጠየኳቸው፡፡ መልሳቸው አጭር እና ዝግ ነበር ‹‹አያስፈልገኝም›› የሚል፡፡ በሁኔታቸው ተደናግጬ ሆቴላቸውን ለቅቄ ወጣሁ፡፡

በተቃራኒው ሌሎች ለቁጥር በዛ ያሉ፣ ብዙ ያልተባለላቸው እና ከኢትዮጵያ ውጭ ስላልኖሩ ብቻ ቴክኖሎጂውን አያውቁትም ብለን የገመትናቸው ደግሞ ልጆቻቸውን አሳልፈው ሰተው እንድንማርባቸው፣ ትሬኒንጋቸውን ትተው ሰልጣኞቻቸው ላይ እንድንለማመድባቸው እድል ሰተውን ማየቴ በእጅጉ ይገርመኛል፡፡ ከእነዚህ አሰልጣኞች መሀከል አንዱ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆኑት አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ሲሆኑ በአስኮ ፕሮጀክት ሰልጣኞች ላይ ሙከራ እንድናደርግ እና መረጃ ሰብስበን እንድንማር በመፍቀዳቸው በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡

ይህንን ታሪክ እንደማሳያ ያቀረብኩት ከመሰደባችን እና በሚዲያ ከመጨቃጨቃችን በፊት አብሮ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት የነበረን፤ ከውዝግብ ስራን ያስቀደምን እንደሆነ ለማሳየት ነው፡፡ በሙሉ ልብ መናገር የምችለው የኢትዮጵያ እግር ኳስን ለማገዝ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ወጣት የእግር ኳስ ባለሙያዎች በየጥጋጥጉ እንዳሉ ነው፤ የጠፋው የሚያሰራ፣ የሚያስተምር፣ በር የሚከፍት ብቻ ነው፡፡

እንደ ማጠቃለያ…

ብዙዎች በድፍረት መፃፋችን እና መናገራችን ግራ ሲያጋባቸው፣ ‹‹ኸረ ነውር ነው!›› ሲያስብላቸው ማየት የተለመደ ሆኖብኛል፡፡ አንድ መረዳት ያለብን ነገር የአጠፌታ ፕሮፖጋንዳ በባህርዩ ከቀደመው በላይ ይጮሀል፡፡ በእኔ እምነት እግር ኳሳችን እንዲያድግ ከተፈለገ ‹‹አካፋን…አካፋ…›› የማለት ሞራል እና አቅም ልናዳብር ይገባል፡፡ አካፋን በማሞካሸት፣ በማሻሸት፣ በመለማመጥ ኤክስካቫተር ወይም ግሬደር ልናደርገው አንችልም፡፡ አካፋ ነው! አካፋ ነው! ኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ አበል፣ ቱታ፣ የውጭ ጉዞ፣ የቡፌ ምሳ፣ ቲሸርት አለፍ ሲልም የኪስ ገንዘብ፣ ጉዳይ ማስፈፀሚያ ጉርሻ እና የመሳሰሉት ጥቅማ ጥቅሞች ባለሙያዎችን እያሳነሷቸው፤ የወደፊቱን በማለም የሚያስቡትን እንዳይናገሩ እያደረጋቸው እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ‹‹ቢቆርጠኝስ››፣ ‹‹ከጨዋታ ቢያስወጣኝስ››፣ ‹‹ቢያሳድምብኝስ››፣ ‹‹እንዴው አንድ ነገር ሳልይዝ›› በሚሉ አስተሳሰቦች እንዲሸበቡ የተደረጉ ብዙ እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ ካፌ ውስጥ የሚያወሩት ሌላ፣ መድረክ ሲያገኙ ሌላ፣ ማህተብ ሳይኖራቸው ሌላ፣ ማህተብ ሲይዙ ሌላ የሚሆኑ እየበረከቱ፣ አስመሳይነት እየነገሰ በመጣበት ሐገር እና የስፖርት ሴክተር በልበ ሙሉነት መናገር መቻል በራሱ አንድ እርምጃ ወደ ፊት መሄድ ነው፡፡

በስመ ‹‹ማኅበር›› በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቅጥር እና ስንብት፣ በቴክኒክ ዳይሬክተር ቅጥር እና ስንብት፣ በክለብ አሰልጣኝ ቅጥር እና ስንብት፣ በአሰልጣኞች ስልጠና ተሳታፊ የሚሆኑ ሰልጣኞች ምዝገባ እንዲሁም በኢንስትራክተር ደረጃ ሰጪነት ላይ ካልተሳተፍን ከሚሉ እና ተወልደን ባደግንበት ሐገር በተማርነው ሙያ፣ በሰለጠንበት ዘርፍ ሐገራችንን የአቅማችንን ያህል እንዳናገለግል በሐሰተኛ እና አለም አቀፍ ደረጃውን ባልጠበቀ መስፈርት ከሚያሸማቅቁን ሰዎች ጋር ያለንን ጠብ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ ምክር መሰረት በዚህ ደረጃ ግልፅ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

‹‹ልጄ ሆይ፤ ማንም ሰው ቢሆን ባንተ ላይ የሐሰት ወሬ ሲያወራብህ የሰማህ እንደሆነ ታገሰው፡፡ መታገስ ባትችል ግን ጠብህን በግልጥ አድርገውና ሰው ሁሉ ይወቀው፡፡ ጠብህን ካስታወቅህ በኋላ፤ ምንም ክፉ ወሬ ቢያወራብህ እውነት ነው ብሎ የሚቀበለው ሰው አይገኝም››


ስለ ፀሐፊው

ፀሀፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል የስፖርት ስነልቦና እና የእግርኳስ መምህር እንዲሁም ተመራማሪ ሲሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ዲግሪ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመኑ ላይፕዚግ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
ያጋሩ
error: Content is protected !!