የዳኞች ገፅ | የዳኞች አባት ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ

👉 ፌደራል ዳኛ ሆኖ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ያጫወተ የመጀመርያ ዳኛ፣ ኢንስትራክተር ሆኖ ኢንስትራክተር መፍጠር የቻለ አባት፣ የኢትዮጵያ ዳኝነትን ወደ ዘመናዊነት ያሻገረ …

👉 “… የኢትዮጵያ ደም ስላለኝማ ነው ይህን ጨዋታ እያስከበርኩ ያለሁት። የኢትዮጵያ ደም ውሸት ሥሩ ይላል?”

👉 “…የያኔዎቹ ሁለት ሴት ልጆች ሊዲያ ታፈሰ እና ሳራ ናቸው”

👉 “ኮሚሽነር እርሱ… ኢንስትራክተርም እርሱ… አርቢትር ኮሚቴ እርሱ.. የዳኞች ኮሚቴ ፀሐፊ እርሱ…”

👉 ” ሥራ፤ ለመሳሳት ግን አትግባ። ከተሳሳትክ ደግሞ ስህተትህን በሌላ ስህተት አታስተካከል።”

ከአምሳ ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ከመጀመርያ ዳኝነት አንስቶ እስከ ኢንስትራክተርነት ማዕረግ ደርሷል። በርካታ ትውልድ በሙያው መፍጠር የቻለው እና ለየትኛውም የዳኝነት ሕግ ውይይት በቀዳሚነት ተጠያቂ (ምስክር) መሆን የሚችለው አንጋፋው የሙያ አባት ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳችን ነው።

የኢትዮጵያ ዳኝነት እዚህ እንዲደርስ ብዙዎች መስዋዕት ሆነዋል። ለዕድገቱ ደፋ ቀና በማለት እንደ ሻማ ቀልጠው ሙያው እንዲከበር ብዙ ታግለዋል። የዚህ ታሪክ አካል የሆነው የዛሬው የዳኞች ገፅ እንግዳችንን ማዋራት እና ታሪኩን መፃፍ በጣም ይቸግራል። ምክንያቱም እርሱ ከልጅነት እስከ አሁኑ ዕድሜው ድረስ በኢትዮጵያ ዳኝነት ያበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ተዘርዝሮ የማያልቅ በመሆኑ ፅሁፍ ማዘጋጀት ባህርን በጭልፋ እንደመጨለፍ ነው። በዳኝነት ሕይወቱ ከመምርያ እስከ ፌዴራል በኃላም ኢንተርናሽናል ዳኛ እስከመሆን ደርሷል። ከዳኝነት በኃላም ከጨዋታ ታዛቢነት እስከ ኢንስትራክተር ማዕረግ ይዟል። እጅግ ለቁጥር የሚታክቱ ትውልዶችን በሙያው ወልዶ አሳድጓል።

በተለያዩ ጊዜያት የዳኞች ብሔራዊ ኮሚቴ ፀሐፊ፣ አባል በመሆን አገልግሏል። በዚህም ብቻ ሳያበቃ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሲጠራ በፍጥነት በመሄድ ያለውን ከፍተኛ ልምድ እና ዕውቀት ለአድማጭ ተመልካች በማይጠገብ አንደበቶቹ ፈትፍቶ አስተምሯል። ስለ ሀገር ውስጥ እግርኳስ እንነጋገር በሚለው የኤፍኤም 96.3 ላይ ዘወትር ሐሙስ ለረጅም ዓመት ከማስተማሩ በተጨማሪ በቀጥታ የጨዋታ ስርጭት በተለይ ከመሰለ መንግስቱ ጋር እግርኳስን በሬድዮ ተመልከቱ ፕሮግራማቸው በሸገር ኤፍኤም፣ በፋና ኤፍኤም ሀገር አቀፍ ስርጭት፣ አሁን ደግሞ በብስራት ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ በጨዋታዎች ዙርያ የዳኘነትን ሁኔታ ትንታኔ ሰጥቷል፤ እየሰጠም ይገኛል። በቃል ያለ ይረሳል በፁሑፍ ያለ ይወረሳል በሚለው ብሒል ዘመን የማይሽረው 348 ገፅ የያዘ የእግርኳስ ዳኝነት ሚስጢር የሚል መፅሐፍ አሳትሞ ለትውልዱ በስጦታ አበርክቷል። እጅግ የተከበረው የሙያ አባት ኢንስትራክተር ሽፈራው እሸቱ የዳኝነት ሕይወቱ እና አጠቃላይ ጉዞውን አስመልክቶ ከእኛ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ቆይታ!

ትውልድ እና እድገት?

በደሴ ከተማ ሆጤ ሜዳ አካባቢ በ1942 ተወለድኩ። የመጀመርያ ሁለተኛም ደረጃ ትምህርቴን በደሴ ወ/ሮ ስህን ትምህርት ቤት ተከታትዬ በኃላም በተማርኩበት ትምህርት ቤት በንግድ ሥራ ትምህርት መምህርነት አገልግያለሁ። በተጓዳኝም ታዋቂነት ባተረፈው እና ባህልን ለማስተዋወቅ እና ጊዜያችንን በቁም ነገር እንድናሳልፍ በተቋቋመው የትምህርት ቤቱ የባህል ማዕከል የሙዚቃ ጓድ የትንፋሽ መሣሪያ ትራምፔት ተጫዋች፣ የመድረክ አስተዋዋቂ፣ ዳንኪራ ተጫዋችነት እና የሠልፍ መሪ (ኮንዳክተር) በመሆን በየደረጃው አገልግሎት ሰጥቻለሁ። በተጨማሪ የትምህርት ቤቱ እግርኳስ ተጫዋች በመሆን አሳልፌያለሁ።

ብዙ ዳኞች አንተን አይተው ወይም ስትዳኝ ባያዩም ምክንያት ሆነሀቸው በወደ ዳኝነቱ ገብተዋል። ለመሆኑ አንተ ራስህ ወደ ዳኝነቱ ሙያ እንድትገባ ምን ምክንያት ሆነህ?

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ ነው ዳኛ ለመሆን የወሰንኩት። በተወለድኩበት አካባቢ ከቤታችን ቅርበት ሆጤ ሜዳ ስላለ ጨዋታዎችን ለመከታተል ሁሌም እሄዳለሁ። አንድ የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው አረብ ይሁን ብቻ አላውቅም መልኩ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ እየመጣ ይዳኝ ነበር። ቅንቅስቃሴው፣ ፊሽካው፣ በካርዱ ተጫዋች ሲያሰወጣ… የሚገርምህ አሁንም ድረስ እንቅስቃሴው አዕምሮዬ ውስጥ አለ። እርሱን እያየሁ እኔ እንደርሱ መሆን እችላለሁ እያልኩ ከልጅነቴ ጀምሮ የእርሱን አቅጣጫ እያያዝኩ ጀምሬ ነው ወደ ዳኝነቱ የተገፋፋሁት። ይህ የሆነው በ1960 ማለት ነው። ከዛም የሰፈር ልጆች ተሰብስበን ኳስ ስንጫወት የአስር ሳንቲም ፊሽካ ገዝጄ ማጫወት ጀመርኩ።

አንተ ብዙዎችን በዳኝነት ስልጠና ኮርስ እየሰጠህ ብዙ ትውልዶችን ከፌዴራል እስከ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ከዛም አልፎ ኢንስትራክተርነት አብቅተሀል። ያኔ ለአንተ የዳኝነት ኮርስ የሰጠህ ማነው ?
ዳኝነት ፍላጎቴ እየጨመረ ሄዶ በ1961 እዚሁ ደሴ ከተማ የዳኝነት ኮርስ እንደሚሰጥ ማስታወቂያ ሲነገር ተመዝግቤ መምርያ ሁለት ኮርስን ወስጃለሁ። ይሄንንም ኮርስ የሰጡን አቶ ዓባይ ተሾመ ይባላሉ። የፌዴሬሽኑ ም/ፕሬዝደንት እና የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበሩ። ካላቸው ልምድ እንዲሁም በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ሥር ያለፉ በመሆናቸው ጥሩ ትምህርት ነው የሰጡን። ይገርምሀል ያን ጊዜ የሰጡን መሠረታዊ ትምህርት አሁንም ድረስ አለ። በእርሱ ላይ ነው የጨመርኩበት። በኃላ በ1965 አቶ አሰፋ ንጉሴ በሚባሉ አሰልጣኝ የማሻሻያ ኮርስ ወሰድኩ። ከዛም በ1967 መምርያ ሁለትን ወሰድኩና ወደ አዲስ አበባ መምጣት ጀመርኩ። በዛን ጊዜ የክለቦች፣ የክፍለ ሀገራት ውድድሮች አዲስ አበባ ይዘጋጅ ስለነበረ መዳኘት ጀመርኩ። ቅድም ለጠየቅከኝ ለዳኝነት መነሻዬ የሰጠሁህ ምላሽ እንዳለ ሆኖ አሁን ደግሞ ወደ ዳኝነቱ ስገባ ብዙ አይደሉም ትንሽ ናቸው። ግን የተከበሩ ታዋቂ የነበሩ ዳኞች አየለ ተሰማ (ጅቦ)፣ ተስፋዬ ገብረየሱስ፣ ኮሎሬል ደመቀ (በህይወት የሉም ነፍሳቸውን ይማር) እነዚህ እነዚህን እያየሁ መጣው። በኃላም አንድ አርዓያ የማደርገው ጌታቸው ገብረማርያም ጨዋታ አጫውቶ አስመራ ላይ ጉቦ አልቀበልም ብሎ ጋዜጣ ላይ “ዳኛው ጉቦ መለሱ” የሚል ፁሑፍ አነበብኩ። ይህ ደግሞ የበለጠ እንደርሱ ሆኜ ዳኝነቱን እቀጥላለው የሚል ሞራል እየሰጠኝ እየባሰብኝ መምጣት ጀመረ። በኃላም ዳኝነትን ቀድመው ቢጀምሩም ጓደኞቼ ናቸው፤ በቀለ ኪዳኔ፣ መኮንን አስረስ፣ ይሸበሩ ብሩ፣ ኃይሉ ተሰማ፣ ዓለም አሰፋ… በቃ አብረን ሆነን ከትልልቆቹ ዳኞች በመቀጠል ወደ ዚህ ሙያ መግባት የቻልነው። በደሴ ቀድሞ ዳኛ የነበሩ አቶ ሐሰን አየለ እና አቶ አበራ ባንጀን በመከተል ዳኝነትን ጀመርኩ።

ፌዴራል ዳኛ መቼ ሆንክ? ምን ያህል ጊዜስ በፌዴራል ዳኝነቱ አገለገልክ ?

በ1970 የፌደራል ዳኛ ዲፕሎማን አገኘሁ። ከዚህ በፊት በዋናም በረዳትም የተለያዩ ውድድሮችን ስዳኝ ቆይቻለው። የሚገርምህ በፌደራል ዳኝነቱ ረጅም ዓመት ያገለገለ እኔ የመጀመርያው ሳልሆን አልቀርም። ሌሎቹ ትዕግስቱን አጥተው እያቋረጡ ወጥተዋል። ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመሆን ቢበዛ ስምንት ዓመት በሙሉ ዳኝነት ማገልገል አለብህ። ይህ ማለት እስከ ሦስት ዓመት ቢቆይ መልካም ነው። ሆኖም ኢንተርናሽናል መሆን እየተገባን ከጓደኞቼ ጋር ረዘም ላለ ዓመት እንድንቆይ በመደረጉ እየተበሳጩ ትተውታል። እኔ ግን አላማ አለኝ፤ እዛ ሳልደርስ አልተውም፤ ኢንተርናሽናል የምሆንበት ቀን ይመጣል ብዬ አስራ አራት ዓመታት በፌዴራል ዳኝነት ቆይቻለው። አስቀድሞ ኢንተርናሽናል ብሆን ብዙ የማገለግልበትን ጊዜ አብዛኛው በፌደራል ዳኝነት ቆይቼበታለሁ።

ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ይሄን ያህል ዓመት በፌዴራል ዳኛ የቆየህበት ምክንያት ምድነው ?

በጣም ከባድ ነበር። ሃያ ሁለት ዓመት በኢንተርናሽናል ዳኝነት ሳይለቁ የቆዩበት ዘመን ነበር። የእኛ ወቅት አስበው እንግዲህ ለሌሎች እድል ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። አንድ ሰው ሃያ ሁለት ዓመት በኢንተርናሽናልነት ከቆየ መቼ ነው የሚደርስህ። እኛ ወደ ኢንተርናሽናልነቱ የገባነው ፈጣሪ ሲፈቅድ በ1983 ካፍ እድሜ ሲያጣራ ብዙዎች ከአርባ አምስት በላይ ሆነው ስለነበር እነርሱን ሁሉ አነሳቸው። አራት አምስት የሚሆኑ ዳኞች ከኢትዮጵያ ሲሰረዙ ያን ግዜ ለመሆን ቻልን። አሁን ለምሳሌ እኔ አስር ጊዜ ነው ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመሆን ለፈተና የቀረብኩት። አስር ጊዜም ተፈትኜ የምወጣው ሰባተኛ፣ ስምተኛ ሁሌም ተጠባባቂ እየሆንኩ ነበር። ያው በወቅቱ የነበረው የአሰራር ሲስተም ምክንያት ሃያ ሁለት ዓመት እና ከዛ በታች በኢንተርናሽናል የቆዩ ዳኞችን አንስቶ እኛ ወጣቶቹን በዛ ቦታ ማምጣት አልተፈቀደም። የኮምፒተሩ የእድሜ ጉዳይ ሲመጣ እነርሱ ሲወጡ እኛ ነበርን የምንገባው። ከ1984 እስከ 87 ለአራት ዓመታት በኢንተርናሽናል ዳኝነት አገልግያለው።

ፌደራል ዳኛ ሆኖ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ያጫወተ የመጀመርያ ዳኛ ነበርክ። ዕውነት ነው?

አዎ! ይህ ትልቅ ዕድል ነው። ካፍ ጥሩ አቅም ያላቸው ዳኞች ልምድ እንዲያገኙ በማሰብ ያመቻቸውን ዕድል ተጠቅሜ በ1975 ግብፅ ላይ የተካሄደውን ጨዋታ ተስፋዬ ገ/የሱስ ዋና በቀለ ኪዳኔ እና እኔ ረዳት ሆነን አገልግለናል። ይህ እኔን የመጀመርያ ያደርገኛል፤ ፌዴራል ሆኖ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ያጫወተ። ከዛ በኃላ ሌሎች ተከትለዋል። በድጋሚ በ1980 ፌዴራል ዳኛ ሆኜ ዚምባብዌ ሄጄ አጫውቼ ተመልሻለው። በኃላ ካፍ ፌዴራል መሆኑ ቀርቶ ኢንተርናሽናል ዳኞችን መመደብ ጀምሯነው።

በኢንተርናሽናል ዳኝነትህ የነበሩ ጨዋታዎችን በመጠኑ ግለፅልኝ ?

በኢንተርናሽናል ዳኝነቱ የቆየሁበት አጭር ቢሆንም በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመዞር በረዳትም በዋና ዳኝነትም አጫውቻለው። ከማልዘነጋቸው ናይሮቢ ላይ ኬንያ ከዩጋንዳ ጋር ስናጫውት ዩጋንዳዎች ከተፈቀደላቸው ዕድሜ በላይ ተጫዋች ተጠቅመዋል በማለት ኬንያዎች ክርክር በማንሳታቸው ሁኔታውን ለካፍ ሪፖርት ለማድረግ ችግር አለባቸው የተባሉት ዘጠኝ ተጫዋቾችን ጋር ዘጠኝ ጊዜ የተነሳሁት ፎቶግራፍን አልረሳውም። ሌላው ዓለም አሰፋ እና ከአበበ አየለ ጋር ዛምቢያን ከዚምባብቤ ሐራሬ ሄደን በሃምሳ ሺህ ተመልካች ፊት ማጫወታችን ለሁላችን እንግዳ የሆነበት ታሪካዊ ጨዋታን አስታውሳለው።

ከዳኝነትህ ገጠመኝ ወይም ከፈታኝ ጨዋታዎችህ መካከል የተወሰነውን ንገረኝ?

በካታንጋ አባባቢ ረዳት ዳኛ ሆኜ ቡና ከምድር ጦር ይመስለኛል በጣም ጠንካራ ጨዋታ ነበር። ያኔ ትራክ አልተነጠፈም መሮጫው ላይ አቧራ ይቦናል። አንድ ኳስ ሲመጣ ሳይ ተከላካይ እና አጥቂ ለመመታታት ይፈላለጋሉ። እኔ ደግሞ እዚህ ላይ ሲርየስ ነኝ፤ ረዳትም ሆነ ዋና ዳኛ ብሆን ቶሎ ነው ሄጄ ቀይ ካርድ ለማውጣት የምገባው ምንም ማቅማማት የለኝም። እነርሱም ተመልካቹም የሚያምኑት ነው። ለምን አስወጡት ብሎ የሚከራከር የለም። እና ይመታቱ ይሆን እያልኩ እየተከታተልኩ ባለሁበት ሰዓት በፍጥነት የሆነ ኳስ ተቆርጦ መጥቶ በመስመር አንድ ልጅ ኳሱን ይዞ ወደ ፊት ይገባል። እኔ ወደ እርሱ ሳይ አምልጦኝ ኳሷን ይዞ ይሄዳል። ተመላካቹ ይጮሀል፤ የተለያዩ ቁሳቁሶች ይወረውራል። እንዳውም የሆነች ድንጋይ ጀርባዬን ሳትመታኝ አልቀረችም በቃ ህዝቡ ዓይን የለህም እንዴ እያለ ይጮሀል። ለምድነው ሰዉ የሚጮህው ብዬ በኃላ ሳስብ ሰውዬው አምልጦኝ እንዳለፈ አስታወስኩ። ይህ ትምህርት ሰጥቶኝ ያለፈ ነገር ነው።

ሌላው በ1981 የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ተደርጎ በአየር ኃይል እና ጦር ሠራዊቱ መካከል ግጭት ተፈጥሯል። የመንግስት ግልበጣውን አየር ኃይል ነው የፈፀመው መሰለኝ በኃላ ከሽፏል። በዓመቱ ግንቦት ወር ላይ አየር ኃይል እና መቻል በጨዋታ ተገናኙ። ስታዲየም ውስጥ ሰዉ ተደናግጧል። አንዳንዱ ደግሞ ይሄ ከባድ ጨዋታ ነው እያለ ተጨንቆ ያወራል። እኔ ደግሞ ‘ምንድነው ከባድ የሚሆነው፤ አልሸከመው። ምን ጉዳይ አለኝ “እላለሁ። ይህ ቀን ከምን ጋር ግኑኝነት እንዳለው አላውቅም፤ ጨዋታዬን ብቻ አጫውታለው። የመጀመርያው አርባ አምስት ትርምስ የሚታይበት እኔ የማልፈልገው አይነት ጨዋታ ሆኖ እንደምንም አልቆ እረፍት ሆነ። አንድ ጓደኛዬ ጠጋ አለና “ሽፌ ቀኑን አስተውሰህዋል?” ይለኛል። “እንዴ የምን ቀን?” አልኩት። “አይ ይህ ቀን የዛሬ ዓመት ጦር ሠራዊቱ እና አየር ኃይሉ የተፋለሙበት ቀን ነው። አንደኛ ዓመታቸውን አንተ ላይ ሊያከብሩብህ ነው ” ሲለኝ ደነገጥኩ። አታውቅም የሚመጣውን ነገር። ስጋቱን ይዤ ከእረፍት በኃላ ወደ ሜዳ ስንገባ የሁለቱንም ቡድኖች አንበል እና ቡድን መሪዎችን ጠርቼ ኮስተር ብዬ “በፊት እንደምንተዋወቀው ተጫወቱ እንጂ ምንድነው ነገሩ? አሁን ያላችሁት ኳስ ሜዳ ነው። እናንተ ያልተጨነቃቹሁለትን እግርኳስ እኔ አልጨነቅለትም። ከዚህ በኃላ እርምጃ እወስዳለው። እንድታቁት ብዬ ነው።” ብዬ አስጠነቀቅኋቸው። በኃላም እነርሱም ተመካከሩና ያ ሁሉ ግርግር እና ስሜቱ ቀዝቀዝ ብሎ ጨዋታው ቀጠለ። ሆኖም አንድ ሰባት ደቂቃ ሲቀረው አየር ኃይል ጎል አስቆጠረና ደህና ቀዝቅዞ የነበረው ጨዋታ ጎል ሲቆጠር እሳት ሆነ። ምንድነው አሁን የማደርገው ብዬ ጨዋታውን በትኩረት እከታተላለሁ። የሆነ ቦታ ላይ አንዱ አንዱን ይመታዋል። አሁን በዚህ እሳት መሐል ይሄን ነገር ልለፈው ወይስ ምን ላድርግ ብዬ ከራሴ ጋር ተማክሬ አይ አይሆንም ብዬ ሁለቱንም በቀይ ካርድ አስወጣኋቸው። መጨረሻው ላይ ደርሷል፤ አሁን መንፋቴ ነው እያልኩ ደህና ኳስ ይዞ የሚሄደውን ልጅ አንድ የአየር ኃይል ተጫዋች በጥፊ አይመታውም?! እኔ ያላየሁት መስሎታል። እኔ ደግሞ በእዚህ ነገር አስቸጋሪ ነኝ። ብዙ ጊዜ ኳሱ ከተመታ በኃላ ዳኞች ወደ ኳሱ ወደ ተመታበት ይሮጣሉ ይህ መሆን የለበትም ዞር ብለው ኳሱ መጀመርያ የተመታበትን ቦታ ማየት አለባቸው። ይሄ አንዳንዴ የምመለከተውን ነው። ተጫዋቾች ኳስ ከተመታ በኃላ ዳኛው አያየኝም በማለት የሚፈፅሙት የተለመደ ጥፋት አለ። እኔ ዞር ስል ሲመታው አየሁት። ወድያውኑ ፍፁም ቅጣት ምት ለምድር ጦር ሰጠሁ። የበለጠ ግርግር ተፈጠረ። ተማቺው ጥሩ ተጫዋች ነበር። “የዳኛው ውሳኔ ትክክል ነው። አያየኝም ብዬ ነበር የመታሁት። አይቶኛል ውሳኔው ትክክል ነው” ብሎ ነገሩን አበረደው። ፍፁም ቅጣት ምቱ ተቆጠረና አንድ ለአንድ አለቀ። ይህ ማለት ከሜዳ ውጭ ያሉ አንዳንድ ትኩሳቶች ሜዳ ውስጥ መጥተው ሊረብሹ ስለሚችሉ የጨዋታ መቆጣጠር ዘዴዎች በጣም ያስፈልጋሉ።

በነገራችን ላይ ኢንስትራክተር የዘመናችን የዳኝነት ፈተና አንዱ ከሜዳ ውጭ ያሉ የተለያዩ አመለካከቶች ተጫዋቾቹ እና ደጋፊዎቹ ላይ እየተንፀባረቁ የዳኞችን ሥራ ያከብዳሉ። በዚህ ላይ ያለህ አስተያየት?

ዕውነት ነው! የአሁኑማ የባሰ እና አስቸጋሪ ነው። ብዙ ሰዎች ምን ይላሉ በእናተ ጊዜ ዳኝነት አሁን ያለው ዳኝነት እንዴት ነው ይላሉ። በኛ ጊዜ ስታጠፋ ህዝቡ አይለቅህም። በዛ ላይ ሁለት ፀጉር ያበቀሉ፣ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች፣ ባለ ሀብቶች፣ የጦር መሪዎች ነበሩ የሚከታተሉት። አሁን ያሉትን ደጋፊዎች ባላቅም። በዚህ ዘመን ከባዱ የዳኝነት ፈተና አንደኛ “ተጫዋቾች፣ የቡድኑ አባላት እና ደጋፊዎች የዳኝነት ህጉን ያውቁታል ወይ?” የሚለው ነው። ሌላው ከሜዳ ውጭ አንተ እንዳልከው የተለያዩ አስተሳሰቦች፣ ፍላጎቶች ሜዳ ውስጥ ያንፀባርቁና ጨዋታውን ወደ አላስፈላጊ መንገድ ይመሩታል። ይህ ለዳኞች ጨዋታውን በነፃነት ለመምራት አያመችም። ትክክለኛ ውሳኔያቸው በሌላ መንገድ እየታየ ሥራቸውን አክብዶታል። ለዚህ መፍትሔም ምንድነው፤ አንደኛ ዳኞች የጨዋታውን መንፈስ በተቀመጠው መንገድ መምራት እና ተረጋግቶ ማጫወት ሲሆን ዋናው ግን ሁሉም የስፖርቱ አካላት የእግርኳስን መርህ እና ዓላማ በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ለእግርኳስ ዕድገት ሊጨነቁ ያስፈልጋል። የዕለት ውጤት እና ስሜትን ብቻ ማሰብ የለባቸውም።

በዳኝነቱ ምን ያህል ዓመት ሰራህ ? የመጨረሻ ጨዋታህን ታስታውሰዋለህ ?

እንግዲህ ኮርስ መውሰድ ከጀመርኩበት ከ1962 ጀምሮ እስከ 1987 ድረስ በዳኝነት ውስጥ ቆይቻለው። እንግዲህ ረጅም ዓመት አገልግያለው። የመጨረሻ ጨዋታዬ አስታውሳለው። በ1987 የኢትዮጵያ እና የዩጋንዳ የወዳጅነት ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም ነበር። ጨዋታው ከወዳጅነት መንፈስ ወጥቶ መሸናነፍ አይፈልጉም ነበር። ለምን በጨዋታው ዋንጫ በመኖሩ የኛ ሀገር ተጫዋቾች በሜዳችን ዋንጫ ማጣት የለብንም በሚል ይረብሹ ነበር። እኔ ደግሞ ልጄቼ ቢሆኑም በህግ መተዳደር ስላለባቸው እኔ ጋር ለቀቅ የማድረግ ነገር የለም። አንድ የኛ ሀገር ተጫዋች ጥፋት ሲያጠፋ ላልፈው አልፈለግኹም። ምክንያቱም ጥፋቱ ትንሽ ከበድ ያለ ስለነበር የማስጠንቀቂያ ካርድ ሰጠሁት። ከዛ ቀጠለና ጨዋታው ወደ ማለቂያው አካባቢ ይኸው ልጅ ሌላ ጥፋት ፈፀመ። ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ልሰጠው ስል ከበባው መጣ። “እንዴ አንተ ኢትዮጵያዊ አይደለህም? ኢትዮጵያዊ ደም የለህም እንዴ ? ” ሲሉኝ “የኢትዮጵያ ጨዋታ እና ይህ ደም ምን አገናኘው? የኢትዮጵያ ደም ስላለኝማ ነው ይህን ጨዋታ እያስከበርኩ ያለሁት። የኢትዮጵያ ደም ውሸት ስሩ ይላል?” ብዬ ተናገርኩ። ጨዋታው እስከመቆም ደረሰ። በኃላ አመራሮቼ መጥተው “አይ ይሄን ነገር እንደምንም ብለህ እለፈው” አሉኝ። እኔም “ምን ልበለው፤ አጥፍቷል ተማቷል ልጁ በቃሬዛ ወጥቷል። ምን ላድርገው?” ብዬ መለስኩላቸው። “አይ እለፈው”… “እኔ አላልፍም፤ እናንተ እንደፈለጋችሁ ማድረግ ትችላላችሁ” አልኩ። በኃላ እነርሱ ሄዱና ጨዋታው በቅጣት ምት እንዲጀምር አድርጌ ካረጋጋው በኃላ ልጁን ጠርቼ “የሰራህው ሥራ ላልፍህ የምችለው አይደለም” ብዬ በሁለት ቢጫ አስወጣሁት። ጨዋታውም አለቀ። አስቀድሜ ከጨዋታው በፊት ራሴን ከዳኝነቱ ለማግለል ወስኜ ስለነበር ጠዋት ማመልከቻ ፅፌ “እስካሁን በቆየሁበት የዳኝነት አገልግሎት ይሄን ይሄን ሰርቻለው። ፌዴሬሽኑ ተባብሮኛል አመሰግናለሁ። ወደፈፊት በሙያው የሚሰጡኝን ሥራዎችን ለመስራት ዝግጁ ነኝ።” በማለት ራሴን ከዳኝነቱ አግልያለሁ። ይህ የሆነው መጋቢት 14 ቀን ነው።

ከዚህ በመቀጠል በዳኝነት ያገኘኸውን ከፍተኛ እውቀት እያሳደግህ ከኮሚሽነርነት እስከ ኢንስትራክተርነት በመድረስ አሁንም ድረስ ብዙ የሙያ ልጆችህን እያወጣህ ነው። እስቲ ከዳኝነት በኃላ የነበረው ጉዞህን ንገረኝ ?

አሁን ወደ ሦስተኛ የዳኝነት ምዕራፍ ተሻግሬያለሁ። የመጀመርያው ምዕራፍ ከመምሪያ ጀምሮ ፌዴራል ዳኝነት እና ትልልቅ ጨዋታዎችን ማጫወት ይደርሳል። ሁለተኛው ከፌዴራል ኢንተርናሽናል ዳኛ የመሆን ፍላጎት ነው። ይሄንንም ለአጭር ጊዜ ቢሆንም ኢንተርናሽናል ሆኜ ተሳክቷል። አሁን ደግሞ ዳኛ በነበርኩበት ጊዜ ከካፍ እና ከፊፋ የሚመጡ ኢንስትራክተሮችን ሳይ እንደነርሱ መሆን አለብኝ ብዬ አሰብኩና መፃፉም፣ ማናገሩም ከ1967 የጀመርኩት በመሆኑ የካፍ ኢንስትራክተር ለመሆን ትኩረቴ እርሱ መሆን ጀመረ። ሁሉም እንደ ፈጣሪ ፍቃድ ወቅቱን ጠብቆ ሆኗል። የካፍ እና የፊፋ ኤሜ ኢንስትራክተር ሆንኩ። እንግዲህ ጥሩ ጥሩ ዳኞችን አፈራው። ምኑን ልጥቀስልህ በርካታ ናቸው። አሁንም መምርያ ሁለት ሆነው እንኳን መፅሐፉን በመግዛት እና በስም በማወቅ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ደውለውልኝ የማስተምራቸው አሉ። በኔ ያላለፈ ዳኛ የለም። መጠኑ ይብዛ ይነስ እንጂ ብዙዎቹን በፊት የነበሩ አሁንም ድረስ ያሉ ዳኞች በእኔ ሰልጥነው ተምረው አልፈዋል። በኢንስትራክተርነቱም እነ ይግዘው ብዙ፣ ግዛቴ ዓለሙ፣ ፍቃዱ ግርማ፣ ሌሎችም አሉ እኔ ያስተማርኳቸው። አሁን እየመጡ ያሉ እነ ፍስሀ፣ ጌታቸው የማነ ብርሀን፣ ሰላሙ በቀለ፣ ዓለማየሁ ጥሩ ጥሩ ወደ ፊት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ የሚያስጠሩ ሰዎች ናቸው።

አንተ የተለየ ሰው ነህ… ዳኛ ብቻ ሳይሆን ኢንስትራክተር የሆኑ ባለሙያዎችን አስተምረሀል። ይህ በመሆኑ ምን ይሰማሀል?

በጣም ነው ደስ የሚለኝ። የሚገርምህ ነገር ካስተማርኳቸው ተማሪዎች ውስጥ ጥሩ ስም ይዘው ትልቅ ደረጃ ሲደርሱ ሳይ የሚሰማኝ ስሜት ቀላል አይደለም። አንድ ምሳሌ ልንገርህ። ጅማ ለማሰልጠን ሄጄ የስፖርት ኮሚሽን ግቢ ውስጥ የቅርጫት ኳስ ሜዳ አለ። እኔ አዳራሽ ውስጥ ኮርስ እየሰጠሁ ሁለት ቅርጫት ኳስ የሚጫወቱ ትንንሽ ልጆች እኔ ሳስተምር በየቀኑ እየመጡ ቆመው ያያሉ። ከሚማሩት ውስጥ “አንቺ ምን ቆመሽ ታያለሽ? አትረብሹን ሂዱ” ይላቸዋል። ማስተማሩ ሲታወክብኝ ሄድኩኝና “ምንድነው የምትፈልጉት?” አልኳቸው። “አይ የሚፈቀድልን ከሆነ መማር እንፈልጋለን” አሉ። “መማር ትፈልጋላችሁ?”…”አዎ” … “በቃ እኔም እንደናንተ ያሉ ልጆችን ማስተማር እፈልጋለው” ብዬ ገቡ። ያመለጣቸውን ቀድመው ከተማሩት እንዲወስዱ አድርጌ የቀረውን ተማሩ። ስሜታቸው እየጨመረ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ሆነ ፈተናውን በጥሩ ውጤት አለፉ። እነዚህ የገለፅኩልህ ሁለት ሴት ልጆች ሊዲያ ታፈሰ እና ሳራ ናቸው። ዛሬ ሊዲያ እዚህ ደረጃ ደርሳ ሀገሯን በዓለም አቀፍ መድረክ ስታስጠራ ከማየት በላይ የሚያስደስት ምን ነገር አለ? እርሷን ብትጠይቅ አባቴ ነው የምትለው። ብቻ ስማቸውን ጠርቼ የማልጨርሰው ብዙ ናቸው። በጣም ነው ደስ የሚለኝ። አንዳንዴ ደስታን በምን መልክ እንደምገልፀው አላውቅም። አንድ ወታደር በጦርነት ላይ ጥሩ ጀብዱ ሰርቶ ሀገሩን ነፃ ከወጣ በኃላ ሀገር ተረጋግቶ “ማነው ባለውለታ ሀገሩ እንድትረጋጋ ያደረገው? እስኪ ምስጋና እና እውቅና ፕሮግራም እናዘጋጅ” ቢባልና ያ ወታደር በክብር ተጠርቶ የሚሰማው ደስታ ያህል ነው የሚሰማኝ። ምክንያቱም እኔ ምን እንዳደረኩ አውቃለው። ሀሳቤ እንደተሳካ አውቃለው። ብዙ ወቀሳዎችን ተቋቁመን እነርሱም ሳያሳፍሩኝ ስቀር እደሰታለው።

በኃላፊነት የሠራህባቸው ዓመታት አሉ። እነርሱን በተወሰነ መልኩ አጫውተኝ ?

በተለያየዩ ዘመናት የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዳኞች ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ የዳኞች ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ዋና ፀሐፊ ሆኜ አገልግያለው። እንዲያው አንዳንዴ “ኮሚሽነር እርሱ… ኢንስትራክተርም እርሱ… አልቢትር ኮሚቴ እርሱ.. የዳኞች ኮሚቴ ፀሐፊ እርሱ… ወዘተ” እያሉ የሚያነሳሱ ጓደኞቼ ነበሩ። እኔ ደግሞ “ሰው ከሌለ ታዲያ ምን ላድርግ? ኑና ውሰዱት። እኔ አልያዝኩት” እያልኩ በቀልድ አወራ ነበር። በአጠቃላይ አሁን የሚገለገሉበትን የፌደራል ዳኞችን ያነቃቃል የፉክክር ስሜት ይፈጥራል ብዬ በማሰብ በሀገራችን ለመጀመርያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለውን ከነዲዛይኑ አዘጋጅቼ ያቀረብኩት የፌዴራል ዳኞች ባጅ ተግባራዊ ሆኖ በማየቴ ደስታ ይሰማኛል። ከዚህ በተጨማሪ በርከት ያሉ ሥራዎችን በኃላፊነት ዘመኔ ሠርቻለው።

በዳኝነትህ አንስቶ እስካሁን ያገኘሀቸው ሽልማቶችን በተወሰነ መልኩ አጫውተኝ ?

በርከት ያሉ ሽልማቶችን የምስክር ወረቀቶችን አግኝቻለሁ። የ1997 የሴካፋ አላሙዲን ሲኒየር ቻሌንጀ ካፕ ዋንጫኔ ሀገራችን ባዘጋጀች ወቅት የዋንጫው ባለ ድል ስንሆን በዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢነቴ በሸራተን በተካሄደው ዝግጅት ከቀድሞ ጠቅላይ ሚንስተር እጅ ሽልማት ተቀብያለው። የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማትን ጨምሮ በርከት ያሉ ሽልማቶችን በተለያዩ መንገዶች አግኝቻለሁ።

በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ቀርበህ ያለህን ዕውቀት እና ልምድ ለትውልዱ ስታካፍል ከቆየህ ረጅም ዓመት ሆኖሀል። ይህን ልምድ ከየት አዳበርከው ?

ወደ አዲስ አበባ ከመጣው ከ1967 ጀምሮ እኔ የማቀውን (የተማርከትን) ሌሎች ማወቅ አለባቸው በሚል ከ1972 ጀምሮ በአዲስ ዘመን፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ እና በሌሎቹም መንገዶች ዳኛ ሆኜ እውቀቴን አካፍል ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት ማስጠንቀቂያ ደርሶኝ ነበር። ወይ ዳኝነቱን ተወው እና አስተማሪ ሁን የሚል ተግሳፅም ነበር። “አይ ጋሼ ምን አጠፋው? የምናገረውን ሳልሰራው ከቀረሁ ሕጉ እንዲህ ይላል። አንተ ግን የሠራህው እንዲህ ነው በሉኝ። በተረፈ ምን አጠፋሁ?” እል ነበር። በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን በመጠቀም በጥያቄ እና መልስ እንዲሁም በጨዋታ ተንታኝነት ሠርቻለው።

አሁን ያለው የዳኝነት ሁኔታ በአንተ እንዴት ይገለፃል? የአንተ አስተያየት በጣም ጠቃሚ ስለሆነ…?

ዳኞች ፈተናውን ተፈትነው አልፈዋል ብሎ ለማረጋገጥ የአካባቢው ሁኔታ ወሳኝነት አለው። የዲሲፕሊን ሁኔታ ወሳኝነት አለው። ድሮ ቀበሌ ሜዳ (ጃን ሜዳ) ማጫወት እና አዲስ አበባ ስታዲየም ማጫወት በጣም ይለያያሉ። በተለያዩ አካባቢዎች ስታጫውት የፀጥታ ሁኔታው አስተማማኝ አይደለም፣ ጫናው አለ፣ አጥር የሌለው ደጋፊው ዘሎ የሚገባበት የተለያዩ ነገሮች የሚፈፀምበት ነው። ይሄን ሁሉ ነገር አልፎ አዲስ አበባ ስታዲየም ገብቶ የሚያጫውት ዳኛ ዕድለኛ ነው። ይሄን የምለው ጥሩ ፀጥታ ካለ፣ ሥርዓት ያላቸው ተጫዋቾች ካሉ ጥሩ ነው። አሁን ያለው ችግር ግን የዳኝነት ህጉን የሚያቀው ዳኛው ብቻ ነው። ተጫዋቾቹ፣ የቡድን አሰልጣኞች፣ አመራሮቹ፣ ደጋፊዎቹ ይሄን ያቃሉ ወይ የሚለው መልስ ይፈልጋል። ከጨዋታ ታክቲክ ጋር ዳኞቹ ያማረ ዳኝነት እንዲሰጡ ህጉን ማወቅ ያስፈልጋል። አሁን ያለው ዳኝነት እኛ ከነበርንበት ዳኝነት ጋር የሚነፃፀር አይደለም። እኛ በጎ ፍቃደኞችን ፈልገን እነርሱ አስተምረውን ወይም በራሳችን ጥረት ፈልገነው የምንማረው። አሁን የኤሌክትሮኒክስ ዘመን ነው። ብዙ ዕውቀት የምታገኝባቸው አማራጮች ሞልተዋል። ራስህን ከዓለም ጋር የምታቀራርብበት ነው። ስለዚህ ጥሩ ጥሩ ዳኝነቶች እመለከታለው። በዓለም አቀፍም መድረክ እንደነ ሊዲያ፣ በዓምላክ ሌሎችንም ጨምሮ የሀገራቸውን ስም ከፍ አድርገው የሚያስጠሩ ወደፊትም ጥሩ ጥሩ ዳኞች ይፈራሉ ብዬ አስባለሁ።

የቤተሰብ ህይወትህ ምን ይመስላል?

ፈጣሪ ይመሰግን በቤተሰብ ሕይወቴ ደስተኛ ነኝ። ሁሉም ልጆቼ ደርሰው ራሳቸውን ችለዋል። አሁን ደግሞ ወደ አስራ ሁለት የልጅ ልጆችን ማየት ችያለው። አሁን ጨዋታዬ ከልጆቼ ጋር መሆኑ ቀርቶ ከልጅ ልጆቼ ጋር ሆኗል። አንዱ ትልቁ ልጄ ዳኝነትን ለመጀመር ሞክሮ ነበር። መጨረሻ ላይ ደስ አላለውም። የነበረው ረብሻ፣ ዳኛ ተደብድቦ እንዲህ ሆኖ ተብሎ በሚያያቻው እና በሚሰማቸው አንዳንድ ነገሮች ደስተኛ ሳይሆን እየተማረ አቁሞታል። ሦስተኛ ልጄ ኳስ ይወድ መጫወትም ጀምሮ ነበር። ለትምህርቱ ጊዜ ስላልበቃው ለማቆም ችሏል። ሁለተኛ ሴት ልጄ ስፖርተኛ ነበረች። ሰርከስ ኢትዮጵያ ትሰራ ነበር። ትዳሯን ያዘች ልጅ ወለደች አሁን አሜሪካ ነው ያለችው። የልጅ ልጆቼም ሳይቀር በስፖርቱ አሉ። አንዷ ኳስ ትጫወታለች። አሜሪካ በሄድኩበት ሰዓት ትምህርት ቤቷ ስትጫወት አያታለው። ከልጆቼ ይልቅ የልጅ ልጆቼ የበለጠ እንደ አያታችን ነው የምንሆነው በማለት በስፖርቱ ገፍተው ሄደዋል።

አንተን ማውራት እና ማናገር መቼም አይጠገብም፣ አይሰለችም። የሰራሀቸው ሥራዎች በርካታ ናቸው። እነዚህን ሁሉ መዳሰስ ባህርን በጭልፋ እንደ መጨለፍ ነው። በመጨረሻ ግን ለዳኞች የምታስተላልፈው አባታዊ መልዕክት ካለህ ልቀበል?

ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም ሁሌም ልምምዳቸውን ሳያቋርጡ ሁልጊዜ መሥራት ያስፈልጋል። በሚሰጣቸው (በሚመደቡበት) ጨዋታ ሁሉ በሚሠሯት አንድም ጊዜ ቢሆን ጥሩ ነገር ከሠሩ እነርሱን ታስመርጣለች። ስለዚህ ሁልግዜ አካል ብቃታቸውን ዝግጁ ማድረግ አለባቸው። ሌላው የጨዋታ ህጎችን (Lows of The Game) እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ቁጭ አድርገው ሁሌም ማንበብ አለባቸው። ምክንያቱም ህግ በየጊዜው ይለወጣል፣ ይሻሻላል። ስለዚህ የጠራ ነገር ይዘው ለመውጣት ሁሌ ማንበብ ያስፈልጋል። ሌላው በብቸኝነት ዳኛ መሆን አይቻልም። ጨዋታዎችን ገብቶ ማየት፣ ከሌሎች ጓደኞች ጋር አንድ ላይ መገናኘት እንዲተቿቸው ልባቸውን መክፈት አለባቸው። ለምን እንዲህ አለኝ ብሎ መቀየም የለባቸውም። ይህ አስፈላጊ አይደለም። በግልፅ ክፍት ሆነው አንዳቸው ለአንዳቸው መነጋገር አለባቸው። ሌላው ደግሞ በዚህ ዘመን በመገናኛ ብዙኃን ስለሚናገሩት ነገር መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ባለመቸኮል የሚሠራውን ሥራ ከህግ ጋር አድርገው መሥራት አለባቸው። ይህ ጥቅም ስላለው ነው። ስለዚህ በዲሲፕሊን የተሞላ አቀራረብ እና ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል። ትዕግስተኛ አና ሆደ ሰፊ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። ለዳኝነቱ ፍቅር ካለን ከወደድነው ለእርሱ የሚከፈለውን መስዋትነት በመክፍል ያሰቡበት ቦታ ለመድረስ መጠበቅ ነው እንጂ በመሐል ማቋረጥ በመሐል ሌላ ነገር አስቦ “እኔን አይመድቡኝም፤ እንደሌሎቹ አይደለሁም። ለእነርሱ እንዲህ እያደረገ እኔን ትቶ” ሌልም ሌላም ነገር አይሰራም። ምንም አይጠቅምም። በሥራ ለማሸነፍ መሞከር ነው። ሌላው ጨዋነት ያስፈልጋል። ሲበሉ፣ ሲሄዱ፣ ሲናገሩ በሁሉም ነገር ላይ ጨዋነት ያስፈልጋል። በማይሆኑ ነገሮች ታይተህ “ይሄ ነው ወይ ዳኛው?” የሚያሰኝ መልዕክት ይዘህ እንዳትሄድ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሁሉም ቦታ ራስን አስከብረህ የምትናገረውን ቆጥበህ አስተውለህ መኖር ያስፈልጋል።

በጣም አደራ የምለው መሳሳት እንዳይኖር ነው። የዛሬ ሁለት ዓመት የዓለም ዋንጫ የሚሄዱ አስራ አምስት ዳኞች ተመድበው ከመሄዳቸው በፊት በነበረ ጨዋታ በጉቦ ቅሌት በስድስት መቶ ዶላር ምክንያት ከዳኝነቱ ተሠረዙ። የዓለም ዋንጫ ቢሄድ የሚያገኘውን ከፍተኛ ጥቅም በትንሽ ነገር ከምንም በላይ የራሱን፣ የቤተሰቡን፣ የማኅበረሰቡን እና የሀገሩን ክብርን አጣ ማለት ነው። ስለዚህ እዚህ ነገር ላይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በጨዋነት ስትሰራ ልትሳሳት ትችላለህ። ፊፋ አሁንም ድረስ ዳኛውን ከነ ጥፋቱ ተቀበሉት ነው የሚለው። ሥራ፤ ለመሳሳት ግን አትግባ። ከተሳሳትክ ደግሞ ስህተትህን በሌላ ስህተት አታስተካከል። እዚህ ላይ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።










© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!