የቼልሲ ፊትነስ ኤክስፐርት ለሀገራችን አሰልጣኞች ስልጠናን ሰጥቷል

ኢትዮጵያዊው የቼልሲ የፊትነስ ኤክስፐርት ኃይሉ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች በአካል ብቃት ትግበራ ላይ ያተኮረ ስልጠናን ማምሻውን ሰጥቷል፡፡

በካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ እና በአሜሪካ የሳክሪሜንቶ አካዳሚ የሴቶች እግር ኳስ ዳይሬክተር አምሳሉ ፋንታሁን የግል ጥረት በሀገራችን ያሉ አሰልጣኞች በኮቪድ 19 ምክንያት የተነሳ ራሳቸውን የሚያበቁበት ስልጠናና የማሻሻያ ትምህርቶችን ባለመኖራቸው በሁለቱ ትልልቅ የእግር ኳስ ባለሙያዎች አነሳሽነት በቪዲዮ ውይይት (ZOOM) የተለያዩ ስልጠናዎችን በማመቻቸት እያሰጡ ይገኛሉ፡፡

ስልጠናው ዛሬ ምሽት ከ12፡30 ጀምሮ እስከ 2:00 ድረስ የቆየ ሲሆን በቅድመ ውድድር ዝግጅት ወቅት ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች በአካል ብቃት አሰራሮች ዙሪያ ለተጫዋቾቻቸው በምን መልኩ መስጠት አለባቸው፣ ምን ምን አሰራሮችን መጠቀም አለባቸው፣ ምንስ ሊከተሉ ይገባል በሚል ርዕስ ነው የተሰጠው። ይህን ስልጠና ተጋብዘው የሰጡት በቼልሲ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ በታዳጊዎች እና በወጣቶች ላይ የፊትነስ ኤክስፐርት በመሆን እየሰሩ የሚገኙት ኢትዮጵያዊው ኃይሉ ቴዎድሮስ የቼልሲን ክለብ እና በአውሮፓ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ክለቦችን ተሞክሮ በማቅረብ የሀገራችን አሰልጣኞች ከኮቪድ በኃላ ወደ ልምምድ ሲገቡ መስራት ባለባቸው የአካል ብቃት እና የፊትነስ ልኬት እና አተገባበር ላይ ትኩረት በማድረግ በስፋት ገለፃ አድርገዋል። በስልጠናው መሰጠትም እጅግ መደሰታቸውን ተካፋይ የነበሩ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!