ሱፐር ስፖርት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የማስተላለፍ መብትን ሙሉ ለሙሉ ማሸነፉን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አ/ማ የሊጉን የቴሌቭዥን መብት ለሱፐር ስፖርት መሸጡን ይፋ አድርጓል።

አንድ ዓመት የሞላው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የሊጉን የቴሌቪዥን ስርጭት መብት መግዛት የሚፈልጉ ተቋማትን በግልፅ ጨረታ አወዳድሮ ነበር። DStv’ም ከተወዳዳሪዎቹ የተሻለ ፋይናንሻል እና ቴክኒካል ፕሮፖዛል በማቅረብ መብቱን መግዛቱ ሲሰማ ቆይቷል። ከደቂቃዎች በፊት ሱፐር ስፖርት በድረ-ገፁ ባወጣው መረጃ መሠረት ይህ ግዙፍ ኩባንያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ለማስተላለፍ መብቱን በብቸኝነት መግዛቱን አስታውቋል።

የደቡብ አፍሪካን ፕሪምየር ሶከር ሊግ (PSL) ጨምሮ በርካታ የአህጉሪቱን የእግርኳስ ክንውኖች በቀጥታ የሚያስተላልፈው ሱፐር ስፖርት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በአጠቃላይ ከሰሃራ በታች አፍሪካ (Sub-Saharan Africa) እና ፍላጎት ባላቸው አጎራባች ደሴቶች ለማስተላለፍ ተስማምቷል።

የመልቲ ቾይዝ ግሩፕ ስራ አስፈፃሚ ካልቮ ማዌላ ለሱፐር ስፖርት በሰጡት አስተያየት ስምምነቱ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ይዞት የሚመጣውን ጠቀሜታ አስረድተዋል።

“ስፖርታዊ ክንውኖችን በአፍሪካ በማስተላለፍ እኛ ቀዳሚዎቹ ነን። ስራዎችንም በዋናነት የምንሰራው ከስፖርቱ ጋር በተገናኘ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ስርጭታችንን ይከታተላሉ። ይህ ስምምነት ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በአህጉሪቱ በደንብ እንዲታይ ያደርገዋል።

“ይህ ለመልቲ ቾይዝ ግሩፕ በጣም ጠቃሚ ስምምነት ነው። ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በአህጉሪቱ እየሰራን ያለነውን ስራ የሚገልፅ ነው። በኢትዮጵያ የሚገኘውን ብቃት ታች ድረስ ወርደን በሃገረኛ ቋንቋ ለማሳየት እንሞክራለን።”

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሰብሳቢ የሆኑት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በበኩላቸው ሊጉ በቴሌቪዥን በመተላለፉ የሚሰጠውን ነገር ከስራ አስፈፃሚዋ በመቀጠል አብራርተዋል።

“ሊጉ በቴሌቪዥን ቢተላለፍ የሚሰጠውን ጠቀሜታ አጢነናል። በተለይ የሊጉን ጥራት በማሳደግ እና በሊጉ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ብቃት አውጥቶ ለማሳየት ጥሩ ጥቅም ይሰጣል። ይህ ስምምነት ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንድ እድገት የሚያመጣ ነው። በአጠቃላይ የተጫዋቾችን ራዕይ የሚያፈካ፣ ኢንዱስትሪውን የሚያነቃቃ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ዓለም ወደ ደረሰበት የሚያስጠጋ ነው።”

የመልቲ ቾይዝ ኢትዮጵያ ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ገሊላ ገብረሚካኤል በበኩላቸው ተከታዩን ሃሳብ ለድረ-ገፁ ሰጥተዋል።

“ይህ ስምምነት ለDStv ጥሩ ነገር የሚሰጥ ነው። በተለይ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ደንበኞቻችን። እኛም ይህንን አማራጭ በሃገራችን ለሚገኙ የስፖርት አፍቃሪያ በቀላሉ እንዲደርስ እናደርጋለን።”

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሱፐር ስፖርት ሲተላለፍ በሃገርኛ ቋንቋ እንደሆነም ተነግሯል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!