ባዬ ገዛኸኝ ስለ ባህር ዳር ዝውውሩ እና ተያያዥ ጉዳዮች ይናገራል

የዝውውር መስኮቱ ከመከፈቱ በፊት ለሁለት ክለቦች ለመፈረም ተስማምቶ የነበረው ባዬ ገዛኸኝ በመጨረሻም የባህር ዳር ከተማ ንብረት ሆኗል። ተጫዋቹም በዝውውር ሒደቱ ላይ የተፈጠሩትን ነገሮች ለሶከር ኢትዮጵያ ግልፅ አድርጓል።

የቀድሞ የስልጤ ወራቤ፣ መከላከያ ፣ ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ተጫዋች የነበረው ባዬ ገዛኸኝ ነሃሴ 14 ቀን 2012 ላይ ከቀድሞ ክለቡ ጋር ለመቆየት የሚያስችለውን ውል ለመፈረም ተስማምቶ ነበር። ከዛም በኋላ ተጫዋቹ ሃሳቡን በመቀየር መስከረም 13 2013 ላይ ለወልቂጤ ከተማ ለመጫወት ተስማምቶ ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ ነበር። ሶከር ኢትዮጵያም ዜናውን ከምስል ጋር በማስደገፍ ለአምባቢያኖቿ አቅርባ ነበር።

ይሁንና ይህ ፈጣን የአጥቂ መስመር ተጫዋች ዳግም ሃሳቡን በመለወጥ በትናንትናው ዕለት ህጋዊ ፊርማውን ለባህር ዳር ከተማ ማኖሩ ታውቋል። ሶከር ኢትዮጵያም የዝውውር መስኮቱ ከመከፈቱ በፊት የነበረውን ነገር እና ትናንት ህጋዊ ፊርማውን ለጣና ሞገዶቹ ካኖረ በኋላ እየተሰነዘሩበት ያለውን ሃሳብ አንስታለት ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

“ልክ ነው ከወላይታ ድቻ እና ወልቂጤ ከተማ ጋር ተስማምተን ነበር። ግን ስምምነቱ በፌዴሬሽን ዘንድ ህጋዊነት ያለው አልነበረም። በመጀመሪያ ለቀድሞ ክለቤ ውሌን ለማራዘም ነበር የተስማማሁት። ግን ክለቡ ቃል የገባልኝን ነገር ሊፈፅምልኝ አልቻለም። በተደጋጋሚ ቃል የገቡልኝን ነገር እንዲፈፅሙልኝ ብጠይቅም እነሱ ፍቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም። ከዛ እኔ አማራጮችን ለማየት ተገደድኩኝ። በዚህም ወልቂጤ ለመፈረም ተስማማሁ። እረግጥ ወልቂጤዎች ቼክ ሰጥተውኝ ነበር። ግን ቼኩ ገንዘብ የለውም። እኔም ቃላቸውን እንዲጠብቁ በተደጋጋሚ እነሱ ጋር ስልክ ደውዬ ነበር። ስልክ ግን አያነሱም። አጭር የፅሁፍ መልዕክትም ልኬ ነበር። መልዕክቱንም አይተው አልመለሱልኝም። ከዛ መጨረሻ ላይ የሰጡኝን ቼክ እንደምመልስላቸው አሳውቄያቸው የመጨረሻ ውሳኔ ወሰንኩ። ከዛ ቃላቸውን ለጠበቁት ባህር ዳር ከተማዎች በፌዴሬሽን ተገኝቼ ህጋዊ ፊርማዬን አኑሬያለሁ።

“ትናንት በአንዳንድ ሰዎች ስሜ የጠፋበት መንገድ አግባብ ያለው አይደለም። እኔ ህመም ላይ ነበርኩ። ብሔራዊ ቡድን ብጠራም ህመም ላይ ስለነበርኩ ቡድኑን አልተቀላቀልኩም። ግን ከአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በገጠመኝ ጉዳት ዙሪያ አውርተን ነበር። ወንድሜ ሀብታሙም ስብስቡ ውስጥ ስለሚገኝ ያለውን ነገር በሚገባ አስረድቶት ነበር። አሠልጣኙም ‘በደንብ ያገግም እና ይቀላቀለናል’ ብሎ ነግሮታል። እስከ ትናንት ድረስ ሀዋሳ ነበርኩ። ትላንት አዲስ አበባ የመጣሁት ለተሻለ ህክምና ነው። የእኔ ሃሳብ እዚሁ ታይቼ ቡድኑን ለመቀላቀል ነው። በዛውም ከባህር ዳር ጋር ህጋዊ ፊርማዬን በፌዴሬሽን አኖርኩ።”

በመጨረሻም ተጫዋቹ ባህር ዳር ከተማ በመፈረሙ የተሰማውን ስሜት አጋርቶን ሃሳቡን አገባዷል።

“ባህር ዳር ጥሩ ቡድን ነው። ጥሩ ደጋፊዎችም አሉት። በተጨማሪም ለተጫዋች ምቹ የሆነ ግዙፍ የመጫወቻ ሜዳ አለው። ብቻ በብዙ ነገር ባህር ዳር ደስ የሚል ከተማ እና ክለብ ነው። እዚህ ክለብ ውስጥ ለመጫወት በመፈረሜ ደግሞ ደስተኛ ነኝ።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!