ሶከር ታክቲክ | በጥልቀት መከላከል (Low Block)

አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ከተለያዩ ድረ-ገጾች ያገኛቸውን የእግርኳስ ታክቲክ ንድፈ-ሐሳቦችን የተመለከቱ ጥልቅ ትንተናዎች፣ የሥልጠና መመሪያዎች እና መጻህፍትን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም ሌሎች አሰልጣኞችና አንባቢን ይጠቅም ዘንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ይሞክራል፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው ፅሁፍም አንዱ አካል ነው፡፡
ጸሃፊ- ጄክ አስካም
ትርጉም- ደስታ ታደሰ

በጥልቀት መከላከል (Low block) ማለት  አንድ ቡድን በሜዳው ቁመት እጅጉን ወደ ኋላ በማፈግፈግ ተጋጣሚ ቡድን ከተከላካዮች ጀርባ ሊጠቀም የሚችለውን ክፍተት ለመሸፈን የሚያስችል የመከላከል ታክቲካዊ መርህ ነው፡፡ ጆዜ ሞውሪንሆ ይህንን የሜዳ ክልል “አውቶብስ ማቆምያ” ብለው ይገልፁታል፡፡ በመሃል ሜዳ አካባቢ ክፍት ቦታ ስለማይገኝ በዚህ የመከላከል ዘዴ የሚጠቀም ቡድን ላይ ግብ ማስቆጠር አስቸጋሪ ነው፡፡ 

ከላይ በምስሉ የሚታየው በሰማያዊ ቀለም የተቀለመው ክልል ወደኋላ አፈግፍጎ ለመጫወት የሚያቅድ ቡድን የሚከላከልበትን ከባቢ ያሳያል፡፡

በእግርኳስ በጥልቀት መከላከል እንደ አሉታዊ ታክቲክ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን የመከላከል ዘዴ በሜዳ ላይ በአግባቡ ለመተግበርም ክህሎት እና እውቀት ይጠይቃል፡፡ ፔፕ ጓርዲዮላ፣ አርሰን ቬንገር እና ቪሴንቴ ዴልቦስኬን የመሳሰሉ አሰልጣኞች ተጋጣሚዎቻቸውን በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለመብለጥ ሲጥሩ ሌሎች በጥልቀት የመከላከል ዘዴን የሚተገብሩት ደግሞ በሜዳው ላይ ያሉ ክፍት ቦታዎችን በመቆጣጠር ከተጋጣሚዎቻቸውን የበላይ ለመሆን ይታትራሉ፡፡

በጨዋታ 75% የሚሆኑ ግቦች የሚቆጠሩት በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ከሚመቱ ኳሶች ነው፡፡ ስለዚህም የመከላከል ዋነኛ ትኩረት የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳስ እንዳያገኙ ማድረግ ላይ እንዲሆን ግድ ይላል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ <low block> የሚተገብሩ ቡድኖች የሜዳውን ስፋት ለተጋጣሚ ቡድን በመተው ሳጥኑ አካባቢ ያለውን መሃለኛ ክፍል በጥብቅ ለመከላከል ከፍተኛ ዝግጅት ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡

የርገን ክሎፕና ፔፕ ጓርዲዮላን በመሰሉ ታላላቅ አሰልጣኞች የሚመሩ ቡድኖች በላይኛው የሜዳ ክፍል ወይም በተጋጣሚ ቡድን የሜዳ ክልል ከባላንጦቻቸው ኳስ መንጠቅ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ውጥናቸው ከተሳካ የተጋጣሚያቸው ተጫዋቾች ወደ ግብ ክልላቸው ሳይጠጉ በቀላሉ ሊከላከሏቸው ስለሚያስችላቸው ነው፡፡ በአንጻሩ ወደኋላ በማፈግፈግ በጥልቀት የመከላከል ዘዴን የሚጠቀሙ አስልጣኞች ቁልፍ በሆኑ የሜዳው ክፍሎች የተሻለ ለመከላከል የተጫዋቾች ቁጥር ማብዛታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡

በጥልቀት የመከላከል ዘዴን የሚጠቀሙት ቡድኖች የትኞቹ ናቸው?

ማንኛውም ቡድን በጥልቀት የመከላከል ዘዴን በውድድር ዘመኑ አንድ ወቅት ላይ ለተወሰኑ ጨዋታዎችም ቢሆን መጠቀሙ አይቀርም፡፡አንዳንድ ቡድኖች ተጋጣሚ ቡድን በጨዋታ መጠናቀቂያ ሰዓት ላይ ነጥብ ለመጋራት በሚል ወደ ማጥቃት ሲሶው በርካታ ተጫዋቾችን ሲያዘምት ይህንን የመከላከልሥልት እንደ መጨረሻ አማራጭ ይጠቀማሉ፡፡ ሌሎች ቡድኖች ደግሞ ከሜዳቸው ውጪ በሚያደርጉት ጨዋታ ተጋጣሚያቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እንደሚወስድባቸው ሲገምቱ ገና ከጅምሩ በጥልቀት የመከላከል አጨዋወትን ሲመርጡ ይታያሉ፡፡

በዲዬጎ ሲሞኔ ሲመሩ የነበሩትት አትሌቲኮ ማድሪዶች በጥልቀት የመከላከል ጨዋታን በውጤታማነት በመተግበር የላቁ ናቸው፡፡ አትሌቲኮዎች በገንዘብ አቅማቸው ሪያል ማድሪድና ባርሴሎናን መገዳደር ተራራን የመግፋት ያህል ቢሆንባቸውም ይህኛው የእግርኳስ ታክቲካዊ መዋቅር ግን ሜዳ ላይ የሁለቱ ቡድኖች ተፎካካሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ክለቡ በዚሁ አርጀንቲናዊ አሰልጣኝ  ሥር የላሊጋ፣ የስፔን ንጉስ ዋንጫ እና የዩሮፓ ሊግ ክብሮችን ተቀዳጅቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአምስት ዓመታትም ውስጥም ሁለት ጊዜያት ያህል በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ ሊሆን ችሏል፡፡

ሲሞኒ ውጤታማ በነበረባቸው እነዚያ ዓመታት ዝርጉንና ጠባቡን 4-4-2 ፎርሜሽን ሲጠቀም አንቷን ግሬዝማንን ከብቸኛ አጥቂው ጀርባ ያሰለፈው ነበር፡፡ በሜዳው ስፋት በሚዘረጉ ተቀራራቢ የሆኑ ትይዩ መስመሮች የሚሰለፉትና አራት-አራት ተጫዋቾችን የሚያካትቱት  የተከላካይና አማካይ ክፍሎች (Two-banks of-4) ለመከላከሉ የጨዋታ ሒደት ጥሩ መሰረት ይጥላሉ፡፡ እነዚህ ተከላካዮች እና አማካዮች ተጋጣሚያቸው መሃለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ብልጫ ወስዶ እንዳሻው እንዳይጫወት እንደሚሹ በእንቅስቃሴያቸው እንዲሁም በሚዋልል የቦታ አያያዛቸው ይታወቃል፡፡ ከላይ ባለው ምስል የክብ ምልክት የተደረገባቸው ሁለቱ ተጫዋቾች እና መስመሩን ተክኮ ያለውን የባየርን ሙኒክ ተጫዋች ስናስተውል የባየርኑ ተጫዋች ክፍት ቦታ ያገኘው በጎንዮሽ መስመሩ ላይ መሆኑን እንረዳለን፡፡

በተጨመሪም ፊሊፕ ላኻም ወደ መሃለኛው ክፍል ኳስ ለማቀበል የሚያስችለው ክፍት ቦታ እንደሌለው እንመለከታለን፡፡ የአትሌቲኮው የግራ መስመር ተከላካይ ፊሊፔ ሉዊስ ከባድ አደጋ ሊያስከትል የሚችለው ጫና የሚያርፍበት በቀኝ ትከሻው አቅጣጫ ባለው ባላጋራው እንደሆነ ተገንዝቧል፡፡ ይህንንም እንቅስቃሴያዊ በሆነው ቦታ አጠባበቁ ማየት ይቻላል፡፡  ባላጋራውን “ፕረስ” ማድረግ የግድ ከሆነበት ለተልዕኮው ዝግጁ መሆኑን ከአቋቋሙ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ  የሉዊስ እንቅስቃሴ ላኻም ከመስመሩ አጠገብ በክብ ለተመለከተው ዳግላስ ኮስታ ብቻ የማቀበል ንጥል አማራጭ ይተውለታል፡፡

ከዚያም ላኻም ኳሱን ለዳግላስ ኮስታ ይለቅለታል፡፡ ኮስታ በተፈጥሮው የግራ እግር ተጫዋች በመሆኑ ወደ ውስጥ ሰብሮ ለመግባትና በተጋጣሚ ቡድን ክልል ውስጥ ኳስን እየገፋ መዝለቅ ይፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ የኮኬ አቋቋም ኮስታ ሐሳቡን እንዲቀይር የሚያስገድድ ይመስላል፡፡ ስለዚህም ወደ መሃል ሜዳው ጥሶ ከመግባት ይልቅ ቀኝ እግሩን የመጠቀም አማራጭ ብቻ እንዲኖረው ይገደዳል፡፡ ስለዚህ የመከላከል ታክቲኩ ለአትሌቲኮ በጀ፤ ባየርንን ግን  ወደ ተጋጣሚው አደገኛ ዞን አገደው፡፡

የአትሌቲኮ ማድሪዶቹ የመከላከል መስመር ምንያህል በጥልቀት ወደኋላ እንዳፈገፈገ እንመልከት፡፡ በሁለቱ የመሃል ተከላካዮችና በግብ ጠባቂው መካከል ያለው ርቀት በጣም ጠቧል፡፡  በዚህ ምክንያት የተሻጋሪ ቅብብሎች መዳረሻ ሊሆን የሚችለውና ከግቡ ቋሚዎች ፊትለፊት 5.5 ሜትር ያህል የሚሆነው ክልል ላይ እንዲሊኖር የሚጠበቀው ክፍተት እጅግ አንሷል፡፡ በብዛት የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች በግንባር የሚገጩ ኳሶች የሚያገኙት ይህኛው ቦታ ላይ በመሆኑ በጥልቀት በመከላከል ዘዴ አደጋውን መቀነስ ተችሏል፡፡ 

በዚሁ በጥልቀት የመከላከል ሒደት መጨረሻ ላይ አትሌቲኮ ማድሪዶች 4-ለ-3 የሆነ የተጫዋቾች ቁጥር ብልጫ ሲያገኙ የሚፈጥሩት ጫና ጠቅሟቸዋል፡፡ የቁጥር ብልጫው ባየርን ሙኒኮች የአትሌቲኮ ተከላካዮችን አልፈው መሄድ እንዳይችሉ ከማስገደዱም በላይ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ከተከላካዮች ጀርባ መገኘትን አዳጋች ያደርግባቸዋል፡፡

ከላይ በምስሉ እንደሚታየው ዳግላስ ኮስታ ከላኻም ኳስ ከተቀበለ በኋላ የነበሩት አማራጮች ሁለት ብቻ ሆነዋል፡፡ ወደ ራሱ የግብ ክልል ኳስን መልሶ መጫወት አልያም ፊሊፕ ላኻም ለመሮጥ ሙከራ እያደረገ ወዳለበት ቦታ ለማቀበል መሞከር፡፡ ባየርን ሙኒክ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አስደናቂ ጎል በማስቆጠር የአትሌቲኮን የመከላከል አደረጃጀት መስበር ካልቻለ በቀር የአትሌቲኮ ተጫዋቾች የቦታ አሸፋፈናቸው ባየርን ግብ ማስቆጠር የሚያስችለው ቀላል መንገድ እንደሌለው ያመላክታል፡፡

የአትሌቲኮ ተከላካዮች የላኻምን የማፈትለክ ሐሳብ እና የኮስታን ኳስ የማቀበል ዕቅድ እንዳስተዋሉ የላኻምን እንቅስቃሴ ለመግታት፣ ምናልባት ላኻም ኳሷን ካገኘ ደግሞ አደገኛውን የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ለመከላከል በተጠንቀቅ ተንቀሳቀሱ፡፡

ኮስታ ኳሷን ለላኻም አቀበለው፡፡ ይኽን ጊዜ የአትሌቲኮ ጥብቁ የተከላካይ መስመር ይበልጡኑ ወደኋላ በጥልቀት በመመለስ ወደ ሳጥኑ ሊላክ የሚችል ተሻጋሪ ኳስን በንቃት ይጠብቅ ጀመር፡፡ የአትሌቲኮ ማድሪዱ የግራ-መሃል ተከላካይ በአቋቋሙ ላኻም ኳስን እንዳያገኝ በማድረግ ኳስ በመልስ ምት እንዲጀመር አስቻለ፡፡

እዚህ ላይ ሌላኛው ሊነሳ የሚገባው ነጥብ በጥቁር የተከበበው የግሬዝማን የቦታ አያያዝ ነው፡፡ ግሪዝማን የአትሌቲኮዎች ዋነኛው ግብ አስቆጣሪ ቢሆንም በራሱ ቡድን የፍፁም ቅጣት ምት ክልል እየተከላከለ ይገኛል፡፡ ይህ አስደናቂ ጠንካራ የመከላከል ስራ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት አትሌቲኮን ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡


የጽሁፉ ተርጓሚ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፂዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


ያጋሩ