የዳኞች ገፅ | ዶክተሩ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው

በዛሬው የዳኞች ገፅ አምዳችን ላይ በደፋርነቱ የሚታወቀውን ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘውን እንግዳ አድርገነዋል።

ከአዲስ አበባ 580 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ በምትገኘው ባህር ዳር ከተማ ተወልዶ ያደገው ኃይለየሱስ አሁንም በዚህች ውብ ከተማ ኑሮውን እየቀጠለ እንደሆነ ይናገራል። እድገቱን ባደረገበት ቀበሌ 3 (ጊንጦ ሰፈር) አካባቢ በሚገኘው ዐፄ ቴዎድሮስ ስታዲየምም ኳስን ከለጋ እድሜው ጀምሮ ሲከታተል እንደነበር ያስታውሳል። ከመከታተልም አልፎ በ1990’ዎቹ መጀመሪያ በነበረው የከተማው ፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ታቅፎ እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን ጥሯል። ነገርግን ቤተሰቦቹ በቀለም ትምህርቱ እንዲገፋ ተግፃስ የተቀላቀለበት ምክር ሰጥተውት እግርኳሱን እርግፍ አድርጎ ትቶ ወደ ትምህርቱ ትኩረቱን አደረገ። ኃይለየሱስ ምንም እንኳን ፍላጎቱ በሆነው ኳስ ተጫዋችነት ባይቀጥልም የቀለም ትምህርቱን እየገፋ ጎን ለጎን የዳኝነት ሙያ ውስጥ እንደገባ ያወሳል። ከ1993 ጀምሮም የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ኮርሶችን በመውሰድ ጨዋታዎችን መምራት መጀመሩን ይናገራል። በዚህም ለስድስት ዓመታት በክልል እና ዞን ደረጃ ጨዋታዎችን ከመራ በኋላ 1998 ላይ የፌዴራል የዳኝነት ደረጃ ትምህርቱን አገባዶ ከ2000 ጀምሮ የኢትዮጵያ አንደኛ የሊግ እርከን የሆነውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መዳኘት ጀመረ።
ራሱን በየጊዜው እያሻሻለ የሚመጣው የዛሬው የዳኞች ገፅ አምድ እንግዳችን 2004 ላይ የኢንተርናሽናል ባጁን በመውሰድ ከሃገራችን ከሚገኙ ጥቂት ታላላቅ የመሃል ዳኞች መካከል ተሰለፈ። ይህንን ኢንተርናሽናል ባጅ ይዞ ለ6 ዓመታት ግልጋሎት ከሰጠ በኋላ ለሁለት ዓመታት ያክል ፍቃዱ ተነጥቆ ከኢንተርናሽናል ዳኝነት ተገለለ። ከሁለት ዓመታት በፊት ግን “አሳማኝ ባልሆነ መንገድ የተነጠቀውን” ኢንተርናሽናል ባጅ ዳግም አስመልሷል። ከእግርኳስ ዳኝነት በተጨማሪ የቀለም ትምህርቱ ላይ ብርቱ የሆነው ኃይለየሱስ ፒ ኤች ዲ’ውን ይዞ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር ሆኖ እየሰራ ይገኛል። ከ1993 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በዳኝነቱ ዓለም ውስጥ የሚገኘው እና ተስፋ ያለመቁረጥ ተምሳሌት የሆነው ኃይለየሱስ ባዘዘው ዕለተ አርብ በምናቀውበው የዳኞች ገፅ አምድ ላይ እንግዳ አድርገነው ከዳኝነት ህይወቱ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አቅርበንለታል።

ወደ ዳኝነት ሙያ እንዴት ልትገባ ቻልክ?

ታዳጊ እያለሁ እግርኳስ ነበር የምጫወተው። እንደውም ተወልጄ ባደኩበት ባህር ዳር ከተማ በነበረው የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ተይዤ ነበር። ግን ቤተሰቦቼ በእግርኳሱ እንድዘልቅ አይፈልጉም ነበር። እኔ ግን ለስፖርቱ ትልቅ ስሜት ስለነበረኝ መጫወትን ቀጠልኩ። ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ ዶክመንቶችን እና ፎቶ ግራፍ አምጡ ሲባል ግን ከየት ላምጣ። ምክንያቱም ቤተሰቦቼ አይሰጡኝም። ከዛ በፕሮጀክቱ ሳልቀጥል ቀርቼ እግርኳስን አቆምኩ። እርግጥ እግርኳስ ብቻ አልነበረም የምጫወተው። ቅርጫት እና መረብ ኳስም እየተጫወትኩ ነው ያደኩት። ግን በጠቀስኩት ምክንያት በተጫዋችነት ሳልገፋ ቀረሁ። አንድ ቀን ግን እኛ ቅርጫት ኳስ የምንጫወትበት ሜዳ ላይ እግርኳስ የሚጫወቱ ሁለት ቡድኖች መጡ። ከዛ እነሱን የሚያጫውቱት ዳኞች ደግሞ ቀሩ። ከዛ በሰዓቱ እዛው የነበርነው እኔ እና ጓደኞቼ ጨዋታውን እንድንመራላቸው ሲጠይቁን እሺ ብለን በልምድ አጫወትናቸው። ከዛም ሌሎች ቡድኖችም ሲመጡ እኛ እንድናጫውታቸው እየጠየቁን ማጫወት ቀጠልን። በዚህ ሂደት ውስጥ እያለሁ ግርማ ተወልደ የሚባለው የፕሮጀክት አሠልጣኛችን ትክክለኛ የጨዋታ ዳኛ እንድሆን መክሮኝ 1993 ላይ ሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ትምህርት ወስጄ መደበኛ ዳኛ ሆንኩኝ።

1993 ሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ኮርስ እንደወሰድክ እየነገርከኝ ነው። ከዛስ በኋላ ራስህን እያሻሻልክ የመጣህበትን የዳኝነት ህይወትህን አጫውተኝ?

የሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ኮርሱን 1993 መጨረሻ ላይ ከወሰድኩ በኋላ እስከ 1998 ድረስ በዚህ ደረጃ እያገለገልኩ ነበር። 1998 ላይ ደግሞ በሃገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን እና ከየክልሉ አንድ አንድ ሰው ተመርጦ የሚሰጠውን የፌዴራል ኮርስ ወሰድኩ። ይህንን ኮርስ ካጠናቀኩ ከአንድ ዓመት በኋላ (1999) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሊግ ውድድርን በዋና ዳኝነት ማጫወት ጀመርኩ። ከዛም ሚሌኒየሙ ላይ ዋናውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መምራት ጀመርኩ። በሊጉ ላይም ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ ባለሁበት ሰዓት 2004 ላይ ኢንተርናሽናል የዳኝነት ባጄን አገኘሁኝ። እስከ 2009 ድረስም ይህንን ኢንተርናሽናል የዳኝነት ባጅ ይዤ ጨዋታዎች ከመራሁ በኋላ እስካሁን ባላሳመነኝ ምክንያት ባጄን ተነጠኩ። ከሁለት ዓመታት በኋላ ግን የተነጠኩትን ባጅ አስመልሼ እስከ አሁን በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛነት እያገለገልኩ እገኛለሁ።

በትልቅ ደረጃ እግርኳስን መቼ መምራት ጀመርክ?

በሃገራችን የሚገኘው ትልቁ ሊግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነው። ይህንንም ሊግ ማጫወት የጀመርኩት 2000 ላይ ነው። ከዚህ በፊት ግን ከክልል እና ከዞን ውድድሮች ውጪ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አወዳዳሪነት የሚዘጋጀውን የብሔራዊ ሊግ ውድድር 1999 ላይ አጫውቻለሁ።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያጫወትከውን የመጀመሪያ ጨዋታ ታስታውሳለህ?

በደንብ። ኢትዮጵያ መድን እና ኦሜድላ ያደረጉት ግጥሚያ ነበር። እንደውም በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታዬ ቀይ ካርድ ሰጥቼ ነበር። በወቅቱ ስሙን የማልጠቅስልህ አንድ የመድን ተጫዋች ጥፋት ሰርቶ ቀይ ካርድ ሰጠሁት። ተጫዋቹ ግን ‘እንዴት ቀይ ካርድ ትሰጠኛለህ’ ብሎ ሜዳ ላይ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ። በዛ ቅፅበት የጥፊ ድምፅ ሰማሁ። ፊቴን ሳዞር በጊዜው የመድን አሠልጣኝ የነበሩት ጋሽ አስራት ነበሩ ተጫዋቹን በጥፊ መትተው ከሜዳ እንዲወጣ ያደረጉት። እሳቸው በፀባይ የሚደራደሩ ስላልሆነ። ተጫዋቻቸውን በጥፊ መትተው ከሜዳ አስወጡት። በዚህ አጋጣሚ መነሻነት የመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታዬን አልዘነጋም።

እንደነገርከኝ ከሆነ ከ1993 ጀምሮ መደበኛ ዳኛ ነበርክ። በእነዚህ 19 ዓመታት ከመራሃቸው ጨዋታዎች የከበደህ ወይንም የፈተነህ ጨዋታ ይኖር ይሆን?

እውነት ለመናገር የከበደኝ ጨዋታ አልነበረም። ምክንያቱም ጨዋታውን እንድመራ ስመደብ በአካልም ሆነ በአምሮ በደንብ ተዘጋጅቼ ስለምሄድ። ነገርግን በደጋፊ እና በሚዲያ ከባባድ ግምት የተሰጣቸውን ጨዋታዎችን መርቻለሁ። በዳኝነት ህይወቴ ከበድ ያለ ግምት በፌዴሬሽኑ፣ በደጋፊው እና በሚዲያው የተሰጠውን ጨዋታ የመራሁት 2003 ላይ የተደረገውን የኢትዮጵያ ቡና እና የሙገር ሲሚንቶን ነው። በጊዜው ለእኔ እንደዚህ አይነት ጨዋታዎችን ስመራ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ቡና እና ጊዮርጊስ ተናንቀው ለዋንጫ የደረሱበት የሊጉ የመጨረሻ መርሐ-ግብር ነበር። ግን እኔ ለድባቡ አዲስ ብሆንም ከተመደብኩበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ዝግጅት በማድረግ ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ መራሁ። ከዚህ ጨዋታ በተጨማሪ የሸገር ደርቢን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳጫውት ድባቡ እና ጉጉቱ ጨዋታውን ከባድ አድርጎት ነበር። እኔም ገና ወጣት የነበርኩበት ሰዓት ላይ ስለነበረ ጨዋታውን እንድመራ የተመደብኩት የተለያዩ አካላት ‘እንዴት ወጣት ዳኛ ይህንን ከባድ ጨዋታ ይመራል’ ይሉ ነበር። እንደተባለው ጨዋታው ከባድ ግምት የተሰጠው ቢሆንም እኔ ግን ያን ያህል አልከበደኝም። እንደውም ራሴን ያሳየሁባቸው ናቸው።

በዳኝነት ውስጥ እየሰራህ ያገኘኃቸውን የኮከብነት ሽልማቶች ንገረኝ?

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደረጃ 2004 ላይ ምስጉን ዳኛ ተብዬ ተሸልሜያለሁ። በተጨማሪም 2007 ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ምስጉን ዳኛ ተብዬ ተሸልሜያለሁ። በአጠቃላይ በእነዚህ ሁለት ጊዜያት የዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶልኛል።

እኔ እንዲህ አይነት ዳኛ ነኝ ብለህ ራስህን ግለፅልኝ እስኪ?

እኔ ጨዋታ ልመራ ሜዳ ውስጥ ስገባ መንገስ የማልወድ፣ የማልበሳጭ፣ የማልቆጣ፣ የማልናደድ እንዲሁም ሜዳ ላይ የሚፈጠሩ ነገሮችን ሳልጨነቅ ማሳላሰል የምፈልግ ዳኛ ነኝ። በተጨማሪም ውሳኔዎቼን በደጋፊ እና በክለብ ጫና የማልቀይር ነኝ። በአጠቃላይ ትክክል ነው ብዬ ላመንኩት ነገር የምሞት እንዲሁም ያለየሁትን ነገር አላየሁም ብዬ በድፍረት የምናገር ዳኛ ነኝ።

ኢንተርናሽናል ባጅህን እንዴት አገኘህ?

ቀድሜ እንደገለፅኩልህ 2003 ላይ የተደረገውን የሊጉን የመጨረሻ ወሳኝ መርሐ-ግብር አጫውቻለሁ። ይህ ጨዋታ ራሴን በደንብ እንዳሳይ እና የስፖርት ቤተሰቡን እንድተዋወቅ አድርጎኛል። በወቅቱ ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ወጣት ዳኞች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ የነበረበት ሰዓት ነበር። እኔም ቀድሜም 2004 ላይ ኢንተርናሽናል ዳኛ ልሆን እቻላለሁ ብዬ ስዘጋጅ ነበር። በጊዜውም እኔ እና ጓደኞቼ ኤሊት ዳኖች ከተባሉት የሃገራችን ዳኞች ስም ዝርዝር ውስጥ ነበርን። ከዛ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመሆን የመጣውን የቋንቋ፣ የአካል ብቃት እና የዳኝነት ብቃትን የሚለካውን ፈተና ወስደን ባጁን እንድናገኝ ሆነ። ይህንንም ባጅ ይዤ ለስድስት ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ 2009 ላይ ባጁን ተነጠኩ።

የኢንተርናሽናል ባጅህን ለምን እና እንዴት ነበር የተነጠከው?

ይህ ጉዳይ ውጣ ውረዶች ነበሩበት። በወቅቱም ብዙ ነገሮች ተብለውበታል። በጊዜው ከነበሩ የፌዴሬሽን ሰዎች ጋርም ተገቢ ነው ተገቢ አደለም በሚል ስንጨቃጨቅበት ነበር። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አመራሮችም የሰጡት ምክንያት ምንም አሳማኝ አደለም። ጉዳዩ ስላለፈ አሁን ላይ ምንም ባልልበት ደስ ይለኛል። በአጠቃላይ ግን የተሰራው ስራ ክፍተቶች ነበሩበት።

እንዴትስ ነው ባጅህን ያስመለስከው ታዲያ?

2009 ላይ ለእኔ አሳማኝ ባልሆነ መንገድ ባጁን ከተቀማሁ በኋላ ለሁለት ዓመታት በኢንተርናሽናል ዳኛነት አላገለገልኩም። 2011 ላይ ግን ፌዴሬሽኑ ያለው መዋቅርም ሲለወጥ፣ ሌሎች አመራሮቹ ሲተኩ እና የዳኞች ኮሚቴው ሲቀያየር ብቃቴን ታሳቢ በማድረግ ባጄን አስመለስኩ።

ወደፊት ዳኛ መሆን ለሚፈልግ ሰው ምን ብለህ ምክር ትለግሳለህ?

መጀመሪያ ዳኛ መሆን የሚፈልግ ሰው ስፖርተኛ ማሟላት ያለበትን ነገር መያዝ ይጠበቅበታል። በዋናነት ደግሞ ስፖርታዊ ዲሲፕሊን ሊላበስ ይገበል። ስፖርት ዲሲፕሊን በጣም ሰፊ ነው። ልምምዶችን ሰያጓድል ከመስራት ጀምሮ ራስን በአካል እና በአምሮ እስከማዘጋጀት ድረስ ይደርሳል። ሁለተኛ ሙያውን ከገንዘብ ጋር ለይቶ ማየት ይኖርበታል። አንድ ዳኛ ጨዋታ ሲመራ ገንዘብ ያገኛል ፣ ገንዘብ ለማግኘት ግን ዳኝነት ሙያ ውስጥ ከገባ ችግር ነው። ስለዚህ ዳኝነትን ሊወደው እና ሊያከብረው ይገባል። ከዚህ ባሻገር በየጊዜው የሚወጡትን የጨዋታ ደንቦች እየተከታተለ ራሱን የሚያበቃ መሆን ይጠበቅበታል። በአጠቃላይ ከላይ የጠቀስኳቸውን እና እየተለዋወጠ እንዲሁም እየፈጠነ የመጣውን እግርኳስ ለመልመድ የማይቸገር ሰው ጥሩ ዳኛ መሆን ይችላል።

ዶክተር እንደሆንክ አቃለሁ። እስቲ የትምህርት ህይወትህን በአጭሩ ንገረኝ? በተጨማሪም የት ነው የምታስተምረው?

ልክ ነው ዶክተር ነኝ። በእግርኳስ አሠልጣኝነት (Football Coaching) ነው ፒ ኤች ዲ’ዬን የሰራሁት። አሁን ላይ ከዳኝነቱ ጎን ለጎን በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር ነኝ። በነገራችን ላይ ከእኔ ውጪ በሃገራችን ፒ ኤች ዲ ያለው የእግርኳስ ዳኛ የለም። በሃገራችን ብቻ ሳይሆን በአህጉራችንም ያለ አይመስለኝም።

አስበልጠህ ማጫወት የምትፈልገው የሊጉ መርሐ-ግብር አለ?

ይህኛውን ጨዋታ አልልህም ግን ከበድ ያለ ግምት የሚሰጣቸውን ጨዋታዎች ብመራ ደስ ይለኛል።

የወደፊት እቅድህ ምንድን ነው? ምን ማሳካት አለብኝ ብለህ ታስባለህ?

ብዙ እቅዶች አሉኝ። በመጀመሪያ ግን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ጨዋታን መምራት እፈልጋለሁ። በቀጣይም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎቸን ማጫወት እፈልጋለሁ። በተለይ እነ ባምላን የደረሱበትን ደረጃ መመልከት እሻለሁ። እዚህ ደረጃ ላይ ደግሞ እንደምደርስ እርግጠኛ ነኝ። ለዚህም ደግሞ ራሴን በብዙ ነገር እያበቃሁ ነው።

በመጨረሻ የቤተሰብ ህይወትህ ምን ይመስላል?

ባለትዳር ነኝ። ሁለት የምወዳቸው ሴት ልጆችም አሉኝ። በአሁኑ ሰዓት ተወልጄ ባደኩበት ባህር ዳር ከተማ እየኖርኩኝ እገኛለሁ።





© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!