በወልዋሎ ከሚገኙ ወጣቶች አንዱ የሆነው እና ዘንድሮ የተሻለ የመሰለፍ ዕድል እንደሚያገኝ የሚጠበቀው ግብ ጠባቂው ሽሻይ መዝገቦ የዛሬው የተስፈኞች አምድ እንግዳችን ነው።
በትግራይ ክልል በሁሉም የሊግ እርከን በሚገኙ ክለቦች ወጣት ታዳጊ ተጫዋቾች በብዛት ማግኘት አዳጋች ነው። ወልዋሎች ግን ከሌሎች ክለቦች በተሻለ ታዳጊዎችን ከስር በማሳደግ የተሻለ ተስፋዎች እያሳዩ ይገኛሉ። ቡድኑን ለረጅም ጊዜ ያገለገለው በረከት አማረን ጨምሮ ሰመረ ሃፍተይ፣ ስምዖን ማሩ እንዲሁም ብዙ ተስፋ ተጥሎለት እንደታሰበው ያልሆነው ኤፍሬም ኃይለማርያም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከቢጫ ለባሾቹ ቤት የወጡ ተጫዋቾች ናቸው። የዛሬው የተስፈኞች ዓምድ እንግዳችንም በወልዋሎ ተስፋ ከሚጣልባቸው ተጫዋቾች የሆነው እና በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ትግራይ ክልልን ወክሎ የተጫወተው ሽሻይ መዝገቦ ነው። በ2011 ግማሽ ወደ ዋናው ቡድን አድጎ ለበርካታ ጊዜያት በተጠባባቂ ወንበር ላይ የተቀመጠው ይህ ወጣት ግብ ጠባቂ በእግር ኳስ ሕይወቱ ዙርያ በ”ተስፈኞች” አምድ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረግነው ቆይታን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
“የእግር ኳስ አጀማመሬ በተወለድኩበት ከተማ ዓድግራት በሚገኝ አቢሲኒያ ፕሮጀክት ነው። እግርኳስ ስጀምር አጥቂ ነበርኩ። ከዛ በኃላ ግን ቡድናችን የግብ ጠባቂዎች እጥረት አጋጥሞት ለጥቂት ጊዜ ግብጠባቂ ሆንኩ፤ ቦታው ስለተመቸኝ በዛው ፀናው። የግብጠባቂትነት ፍቅሩ ያደረብኝ ወልዋሎ ዋናው ቡድን ልምምድ እየሰሩ ሳያቸው ነው። ቀስ በቀስም ግብ ጠባቂዎች ልምምድ እየሰሩ ከነሱ ጋር የመቀራረቡ ዕድል አጋጠመኝ። አንድ ቀን በግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ይድነቃቸው አማካኝነት አንድ ቀን ልምምድ የመሥራት ዕድሉን አግኝቼ ጥሩ ብቃት አሳየሁና አንዳንዴ እየመጣሁ ልምምድ እንድሰራ ፈቀዱልኝ። ጥሩ መሻሻል ስላሳየሁም በትግራይ የጥሎ ማለፍ ውድድር ወደሚወዳደረው ኬይ ኤም ኤስ የሚባል የታዳጊዎች ቡድን ገባሁ። ተስፋአለም ይባል ነበር አሰልጣኛችን። ጥሩ ቡድንም ነበረን፤ በግሌም ብዙ ትምህርት የወሰድኩበት ጊዜ ነበር። በዚህ ሁሉ ወቅት ግን አልፎ አልፎ ከወልዋሎ ዋናው ቡድን ልምምድ የመስራት ዕድል አገኝ ነበር። በዛ ምክንያትም ወልዋሎዎች ወደ ሁለተኛ ቡድናቸው አስገቡኝ። ለሁለት ዓመት ያህል ከወልዋሎ ቢ ቡድን ጋር እጅግ የተሳካ ጊዜ አሳለፍኩ።
“በኬይ ኤም ኤስ ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። ከዛ በተጨማሪም በይድነቃቸው እምሽ አማካኝነት በተሰጠኝ ጥቂት ዕድል ከወልዋሎ ዋናው ቡድን ጋር ልምምድ ስስራ ጥሩ ነገር አሳይቻለው ብዬ ነው የማስበው። ከወልዋሎ ሁለተኛ ቡድን ጋር ሁለት ዓመታት ነው የቆየሁት። ጊዜውም በጣም ጥሩ ነበር። ሃገራዊ ውድድሮች ላይ እስከመሳተፍ ደርሰን ነበር። እሱ እንደ ቡድንም ትልቅ ስኬት ነው። ከዛ ውጭ በአስራ ሰባት ዓመት በታች ሀገሮ አቀፍ ውድድር ትግራይን ወክዬ ተጫውቻለው። በአሸናፊ አማረ ስር የሚሰለጥን ጥሩ ስብስብ ነበር። በክልል ደረጃም ዋንጫዎች አንስተናል።
“ወደ ወልዋሎ ዋናው ቡድን በ2011 ግማሽ ላይ ነው በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አማካኝነት ወደ ዋናው ቡድን ያደግኩት። በቆይታዬም ብዙ ትምህርት ወስጃለው። ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ ለዋናው ቡድን ጨዋታ ማድረግ ባልችልም ብዙ ልምዶች ወስጃለው። ከብዙ አንጋፋና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ጎን ልምምድ መሥራት ራሱ ትልቅ ነገር ነው። ሁሉም ተጫዋቾች ያበረታቱኛል አሰልጣኞችም እንደዛው በግሌም ካለማጋነን ብዙ ነው የለፋሁት። በዛ ምክንያት አንድ ቀን የወልዋሎን ማልያ አርጌ እንደምጫወት ለውስጤ እነግረው ነበር። እንደውም ወደ ዋናው ቡድን እንዳድግ የተነገረኝን ቅፅበት በደምብ አስታውሰዋለው። ዋናው ቡድን መቐለ ነበር። እኔ ከሁለተኛው ቡድን ጋር ዓድግራት ነበርኩ። ጠዋት ረጅም ልምምድ ሰርተን ልክ ስንጨርስ ገና ከማረፌ ዮሐንስ ሳህሌ እንደሚፈልገኝ ተነግሮኝ ሳላርፍ ወደ መቐለ ነው የሄድኩት። መቐለ ገብቼም ድጋሜ ለአስር ሰዓት ልምምድ እንድዘጋጅ ተነግሮኝ በነጋታው ወደ ዋናው ቡድን ማደጌን አበሰሩኝ። በዋናው ቡድን ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነኝ። ያሳደገኝን ክለብ ማልያ ለብሼ መጫወትም የሁልግዜ ህልሜ ነው።
“ከግብ ጠባቂዎች በረከት አማረ እና ዴቪድ ዴሂያን አደንቃለው። በረከት ማለት አርዓያዬ ነው። እሱን በቅርበት እያየሁ ነው ያደግኩት። ብዙ ግብ ጠባቂዎች አይቻለው፤ እንደ በረከት ጠንክሮ የሚሠራ፣ ለታዳጊ ትልቅ አክብሮት ያለው፣ ያለውን ነገር የሚያካፍል ግን አላየሁም።
“በቀጣይ የመጀመርያው እቅዴ ከወልዋሎ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ነው። ከዛ ቀጥሎ ደግሞ የሃገሬን ማልያ ለብሼ የመጫወት እቅድ አለኝ።
” በመጨረሻም ብዙ ማመስገን የምፈልጋቸው ሰዎች አሉ። ግን አሁን እዚ ላይ ብዘረዝራቸው ጊዜ ራሱ አይበቃንም። በአጠቃላይ ግን በእግርኳስ ሕይወቴ ትልቅ ድጋፍ ያደረጉልኝን ሁሉ ማመስገን እልፈጋለሁ። ከዛ ውጭ ለቤተሰቦቼ፣ ለወልዋሎ እና ለክለባችን ደጋፊዎች ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!