የኢትዮጵያ ቀጣይ ተጋጣሚ አሰልጣኟን ይፋ አድርጋለች

በኢትዮጵያ ምድብ የምትገኘው ኒጀር አስቀድመው ሥራ ጀምረው የነበሩትን አዲስ አሰልጣኝ በይፋ አስተዋውቃለች።

በኮቪድ -19 ምክንያት ለተዘዋወረው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከኢትዮጵያ፣ ማዳጋስካር እና ኮትዲቯር ጋር የተደለደለችው ኒጀር በትላንትናው ዕለት አዲሱን የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዣን ሚሸል ካቫሊን በይፋ የቡድኗ ዋና አሠልጣኝ አድርጋ መሾሟን አስታውቃለች። የ62 ዓመቱ ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ካቫሊ ከ13 ቀናት በፊት የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ለመሆን ኒያሚ ደርሰው ድርድሮችን ሲያደርጉ እንደነበረ ይታወሳል። ድርድሮቹም በተሳካ ሁኔታ ተገባደው ግለሰቡ አሠልጣኝነታቸው ይፋ ሳይሆን ከቡድኑ ጋር የተገናኙ ስራዎችን ሲከውኑ ቆይተዋል። በትላንትናው ዕለትም የኒጀር እግርኳስ ፌዴሬሽን ካቫሊን ዋና አሠልጣኝ አድርጎ መሾሙን በይፋ አስታውቋል።

በተያያዘ ዜና ኒጀሮች ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርጉት የደርሶ መልስ ጨዋታ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርጉ ቀደም ብለው ማስታወቃቸው ይታወሳል። በዚህም ነገ እና የፊታችን ማክሰኞ ከቻድ አቻቸው ጋር የአቋም መለኪያ የደርሶ መልስ ግጥሚያ ያደርጋሉ። በተጨማሪም ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2020 የቻን ውድድር ያለፈው የኒጀር ብሔራዊ ቡድኑ ሁለተኛ ስብስቡን (የሃገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበትን) ይዞ በተመሳሳይ ማክሰኞ ከሴራሊዮን ጋር ጨዋታ ያደርጋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!