የሰማንያዎቹ …| ለጎል የተፈጠረው በላቸው አበራ (ትንሼ) የእግርኳስ ሕይወት

👉”የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ሆኜ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ የመቀየሬ ምክንያት ምን እንደሆነ አላቀውም”

👉”በ1987 ሙሉጌታ ከበደ እኔ ተቀይሬ ስወጣ ወደ ደጋፊዎች በመሄድ ያሳየው ደስታ አስገራሚ ነበር”

👉”ንግድ ባንክ በሃያ ዓመት የሚጠቀምበትን ገንዘብ በአራት ዓመት ውስጥ ሁሉን ነገር ሙልጭ፣ ቅርጥፍጥፍ አድርገው ጨረሱት”

👉”በዓለም እግርኳስ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ጎሎቼን ፌዴሬሽኑ ነጥቆኛል”

ቴክኒካል ተጫዋች ባይሆንም አስቦ ቦታ አይቶ እርግጠኛ ሆኖ ጎል የሚያገባ፣ ለጎል የተፈጠረ አጥቂ ነው። ጎል ከሳተ የሚናደድ ግልፅ ፣ እልኸኛ አልሸነፍ ባይ ነው ይሉታል። በሰማንያዎቹ ከታዩ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው በላቸው አበራ (ትንሼ) ማነው ?

በምድር ጦር ታዳጊ ቡድን ውስጥ የነበረውን አቅም በሚገባ ያወቁት የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለውለታ የሆኑት ነፍሳቸውን ይማር እና ከበደ መታፈርያ ናቸው። በ1940ዎቹ እና ሀምሳዎቹ መካከል ከነበሩ ተጫዋቾች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና ኢትዮጵያ ዋንጫ በርካታ ዋንጫዎችን አንስተዋል። ወቅቱ ከፍተኛ ተወዳጅነት የነበረው የጦር ሠራዊት (ኋላ ላይ መቻል) ወሳኝ የአጥቂ ስፍራ ተሰላፊ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበል በመሆንም አገልግለዋል። ለመጀመርያ ጊዜ የተከናወነው የ1957ቱ (በኢትዮጵያ 1949) አፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ታሪካዊ ተጫዋቾች፣ ለብሔራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታ እንዳደረጉ የሚነገርላቸው ከበደ መታፈርያ በላቸው አበራ (ትንሼን) ይዘው በወቅቱ ለነበሩት የምድር ጦር ቡድን መሪ ኮነሬል ፈለቀ ያስረክቡታል ኮነሬሉም አይተው ‘አንተ ተጫዋች ነህ ?’ ብለው ሲጠይቁት ‘አዎ’ ይላል። ‘ለመሆኑ ምን ቦታ ነው የምትጫወተው ?’ ብለው መልሰው ጥያቄ ያቀርቡለታል። ልጅነቱም ትዕቢቱም ነበር እና ትንሼ በልቡ ሙሉነት ‘ከግብጠባቂ ውጪ የትም ቦታ መጫወት እችላለው’ ይላቸዋል። ኮነሬሉም ድፍረቱ አስገርሟቸው ‘በል እስቲ ና’ ብለው በከባድ የጦር መኪና (አይፋ) አስጭነው ለሊቱን ሙሉ ሲጓዝ አድሮ ጠዋት ሐረር ከተማ ይገባል። በዚህች ከተማ ደግሞ የምድር ጦር ቡድን የቅድመ ውድድር ዝግጅት እያደረገ ነበር። የምድር ጦር ተጫዋቾች በሙሉ ማለት ይቻላል ይህን ልጅ ሲመለከቱ ከዋናው ቡድን ጋር ተቀላቅሎ ዝግጅት ሊሰራ የመጣ ሳይሆን የአንድ የጦር መኮንን ልጅ ለእረፍት ሊዝናና የመጣ አልያም በወቅቱ ከነበረው ብሔራዊ ውትድርና ለመሸሽ የመጣም ነው የመሰላቸው ፤ ‘ይህችማ ኳስ ለማቀበል የመጣች ናት’ ያሉም አልጠፉም። አንዳቸውም ከሰውነቱ ቅጥነት ፣ ከቁመቱ ማጠር እግርኳስ ተጫዋች ነው ብለው የገመቱ አልነበሩም። ለአስራ አምስት ቀናት ከኳስ ጋር ትኩረቱን ያላደረገ የትንፋሽ (የሩጫ) ልምምድ ይስሩ ስለነበር የዚህን ትንሽ ልጅ የእግርኳስ ችሎታ ባለማወቅ የተለያዩ ነገሮችን በማንሳት ሲያወሩበት ከርመዋል። በኃላ ግን በሩቅ የተመለከቱት ያ ትንሽ ልጅ እግሩ ኳስ ገብቶ ሲመለከቱት ጎል የሚያገባበት መንገድ እና ብስለቱን ሲመለከቱ ብዙዎቹ ማመን አቃታቸው። ያን ትንሽ ልጅን በጣም ወደዱት። ባዩት ነገር በጣም ተገርመው ምድር ጦርን በፍጥነት ተላምዶ ክለቡን እንዲጠቅም ቢያስቡም የሰውነቱ ቀጭን መሆን እና ዕድሜው ገና መሆኑ አሳስቧቸው ምን መደረግ እንዳለበት በማለት የተለያዩ አማራጮች መጠቀም ጀመሩ። አንደኛ ዋና ቡድን መጫወት እስኪጀምር እዚሁ ካምፕ ይቀመጥ። ሁለተኛ ሰውነቱ እንዲጨምር የአሳማ ስጋ ይብላ የሚል ሀሳብ አስቀመጡ።

እንዲህ እንዲህ እያለ በአስገራሚ ፍጥነት ያደገው በላቸው በአዕምሮም ፣ በአካልም አድጎ በ1981 በታዳጊ ቡድን ውስጥ ቆይታ አድርጎ ከ1982 ጀምሮ እየተመላለሰ በዋናው ቡድን መጫወት ጀምሯል። ይልቁንም በ1982 ምድር ጦር የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን እንዲያነሳ ተቀይሮ በመግባት ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ቻምፒዮን በማድረጉ የእግርኳስ ህይወቱ እየተቀየረ እሱም እየታወቀ እንዲመጣ አድርጎታል። ሆኖም ከመንግስት ለውጥ በኃላ ምድር ጦር በመፍረሱ ምክንያት ተስፋው ቢጨልምም የወንድም ያህል ጓደኛው የሆነው ቦጋለ ዘውዴ (ኢንተሎ) ተስፋ ቆርጦ ቤቱ የተቀመጠውን ትንሼን እጁን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲቀላቀል አድርጎታል። እለኸኛ ፣ መሸነፍ የማይወድ ፣ ግልፅ ተጫዋች እንደሆነ የሚነገርለት ትንሼ ከ1984 እስከ 1993 ለአስራ አንድ ዓመት ክለቡ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ እና በብዙዎች ዘንድ እንዲታወቅ ካስቻሉ የቡድኑ የልብ ምት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር። እርሱ ሜዳ ውስጥ ካለ የቡድን አጋሮቹ ቅለት ሲሰማቸው በተቃራኒው ደግሞ ለሎች ብድኖች ይረበሻሉ ፤ ይደናገጣሉ።

በንግድ ባንክ አስራ አንድ ዓመታት ቆይታው የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊ አሸናፊዎች ዋንጫ ቢያነሳም በ1987 የኢትዮጵያ ቻምፒዮን ለመሆን ከጫፍ ደርሰው በመጨረሻው ደቂቃ በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች ዋንጫውን በአስደናቂ ሁኔታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 በማሸነፍ ሲወስድ የንግድ ባንክን የመጀመርያውን ጎል በሚገርም የአዕምሮ ውሰኔ አስቆጥሮ የቅዱስ ጊዮርጊስን ስራ ያበዛው እና ሲረብሻቸው ያረፈደው ትንሼ ነበር። ሆኖም በማይታመን እና ብዙዎችን ባላሳመነ ሁኔታ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ትንሼን ቀይረው ማስወጣታቸው ‘ለምን ?’ የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ከዚህ በኃላ ፈረሰኞቹ ተነቃቅተው ሁለት ጎሎችን አከታትለው በማስቆጠር ቻምፒዮን የሆኑት።

በንግድ ባንክ አስር ዓመት ከትንሼ ጋር አብሮት በመጫወት ያሳለፈው እና የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ተጫዋች የወቅቱ አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ(አግሮ) ስለበላቸው አበራ ትንሼ ሲናገር “እንግዲህ ትንሼ በሜዳም በካምፕም ውስጥ ያለውን ስሜት በጣም ግልፅ ሆኖ የሚናገር ልጅ ነበር። ለቡድኑ ያለው ፍቅር የተለየ የሆነ ፣ የዋህነት ያለው ፣ ሰው መርዳት የሚወድ ፣ ከ ‘ቢ’ ለሚያድጉ ተጫዋቾች ፍቅር የሚሰጥ ነው። ለብሔራዊ ቡድን ብዙ ጊዜ እይታ ውስጥ ገብቶ ተመርጦ አለመጫወቱ እንጂ ለቡድን ውጤት የተሻለ አቅም ያለው ጎበዝ አጥቂ ነበር።” በማለት ይገልፀዋል።

በ1992 ከንግድ ባንክ ጋር ከተለያየ በኃላ ለአንድ ዓመት የንግድ ባንክ ቅጥር ሠራተኛ በመሆን እየሰራ ለብርሀን እና ሠላም ከተጫወተ በኃላ ከ1994 ጀምሮ እስከ 2006 ድረስ የንግድ ባንክ ዋናው ቡድን የቡድን መሪ በመሆን አንዳንዴ ደግሞ አሰልጣኝ ሲሰናበት በጊዜዊነት እያሰለጠነ ለአስራ ሦስት ዓመታት የሚወደውን ክለቡን አገልግሏል። ብዙዎች እንደሚሉት ከሆነ ትንሼ ከንግድ ባንክ ለቆ ሲወጣ ነው ቡድኑ የተፍረከረከው። ከነበረው ችሎታ እና በየዓመቱ ለኮከብ ጎል አግቢነት የሚፎካከረው ሆኖ ሳለ ለብሔራዊ ቡድን አንድ ጊዜ ለዝግጅት ከመመረጥ ውጪ የብሔራዊ ቡድን መለያ ያልለበሰው ትንሼ በአሁን ወቅት የንግድ ባንክ ቋሚ ሠራተኛ በመሆን እየሰራ ይገኛል።

በምድር ጦር እና በንግድ ባንክ አብሮት በመጫወት የልብ ጓደኛውም እንደሆነ የሚነገርለት ቦጋለ ዘውዴ (ኢንተሎ) ስለ ትንሼ ይህን ምስክርነት ይሰጣል። “ትንሼ ለጎል የተፈጠረ ነው። እኔ የማውቀው ጦሩ ቤት ትንሽ ሆኖ እኔ ዋናው ቡድን ሆኜ እርሱ ከ’ቢ’ ቡድን ልምድ ከኔ እንዲያገኝ አቀርበው ስለነበር ነው። እርሱ ማለት ጎል ነው። እንደገና ጎል ሲስት እኮ የሚናደድ መሬት ተኝቶ የሚንፈራፈር ተጫዋች ነበር። ንግድ ባንክ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ብዙ የደከመ ተጫዋች ነው። ለኔም በጣም የምቀርበው የልብ ጓደኛዬ ወይም ወንድማማቾች ነን።” በማለት ይገልፀዋል።

ብዙዎች በነበረው ድንቅ ችሎታ የሚመሰክሩለት የዛሬው የሰማንያዎቹ ኮከብ ገፃችን እንግዳ በላቸው አበራ(ትንሼ) የእግርኳስ ዘመን እና ቀሪው ህይወቱን አስመልክቶ ሰፊ ቆይታ አድርገናል።

“የ1982 በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ጎል ለኔ ብዙ ትውስታ አላት። ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታድየም ከመተሐራ ጋር ነበር። በመተሐራ በኩል ሀሰን በሽር ከመሐል ሜዳ አለፍ ብሎ ባስቆጠረው ጎል መተሐራዎችን መሪ ማድረግ ጀመረ። አንድ እኩል ሆነን ሁለተኛ ጎል መተሐራዎች ደግመው አስቆጥረው ጨዋታው ሊጠናቀቅ ቡድኑ ዋንጫ ሊያጣ ሲደርስ መጨረሻ ላይ አሰልጣኙ ተቀይሬ እንድገባ አደረገ በነገራችን ላይ አሰልጣኙ ተቀይሬ እንድገባ ባያደርገኝም ከኃላ ሆነው ቡድኑን የሚደግፉ ደጋፊዎች ተነስቼ እንድገባ ጫና ያደርጉ ነበር ፤ በቃ ተነስቼ ገባው። ማትያስ ኃ/ማርያም የሚባል እኔ እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እንደርሱ ያለ ምርጥ ተጫዋች አልተመለከትኩም። በእጁ የሰጠኝ ነው የሚመስለው ቁጭ እንዳደረገልኝ አግብቼ አቻ ሆንን። ብዙም ሳንቆይ ራሴ ሦስተኛ የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሬ አሸነፍን የጥሎ ማለፍ ዋንጫን አነሳን። ማታ የራት ግብዣ ላይ አሰልጣኙ በእኔ ተደስቶ የእጅ ሰዓት እንደሸለመኝ አስታውሳለው።”

“መቻል ቤት በጨዋታ ስህተት ከሰራህ በኃላ የሚመጣብህ መከራ ከባድ ነው። አንዴ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነበረን። ጨዋታው ያለ ጎል በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርቶ ከአምስቱ መቺዎች አንዱ ሆንኩኝ። እንዳጋጣሚ ሆኖ በጊዮርጊስ በኩል ሦስተኛ መቺ አሰግድ ተስፋዬ ነፍሱን ይማረው እና ይስታል። እኔ ልመታ ስሄድ ሙሉጌታ ከበደ ‘አንተ ቀጫጫ ሳትከው ሳትከው !’ እያለ ያወራል። እኔም በውስጤ እስተዋለው ብዬ አላሰብኩም ነበር። ስታድየሙ በጣም ከሞምላቱ የተነሳ ትራኩ ላይ ሳይቀር ተመልካቹ ተቀምጦ ይመለከት ነበር። ኳሱን አስቀምጬ ስመታው አንግሉን መትቶ በግብጠባቂው ታደሰ ጀርባ አልፎ ኳሱ መሬት ለመሬት እየሄደ በካታንጋ በኩል የእጅ ፎሪ ወጣ። እኔ እስካሁን እንዲህ ያለ ሪጎሬ አይቼ አላውቅም። ሪጎሬ መትተህ የእጅ የሚወጣ (እየሳቀ)። በጣም ደነገጥኩ ፤ በቃ ራሴን አላውቅም አለቅስም ጀመርኩ። ምክንያቱም በእኔ መሳት ከተሸነፍን ወደ ውትድርና እላካለው ብዬ ፈራው። በመጨረሻም አንዳንድ ተመትቶ አምስቱ አለቀ። በጊዮርጊስ በኩል ስድስተኛ መቺ ከሪም የሚባል የድሬደዋ ልጅ ነበር እርሱ ይስታል። በኛ በኩል ሚኒሊክ ይመታና አግብቶ እናሸንፋለን። እኔ በዚህ ሰዓት ወደ ሚኒሊክ ሄጄ ደስታዬን ከመግለፅ ይልቅ የሳተው ከሪም ጋር ሄጄ አንገቱን እቅፍ አድርጌ ስስመው የጊዮርጊስ ደጋፊዎች አበዱ ፤ ሊገሉኝም ፈለጉ። እኔ እርሱ ባይስት እና ባናሸንፍ ኖሮ ወደ ውትድርና ስለምሄድ እርሱን ላመሰግን የሄድኩበት ይህ አጋጣሚ ይገርማል።”

“ራሴን ለመግለፅ በጣም ለጎል የተፈጠርኩ ፣ በግምት ጎል የማላገባ በተለይ ጎል ለማስቆጠር ከሆነ አሰቤ እግሬ እና አዕምሮዬን ተጠቅሜ የማገባ ነበርኩ። የእግሬም ትንሽ ሸፈፍ ማለትም ይረዳኛል መሰለኝ ጎል ለማስቆጠር የማልቸገር ፣ እለኸኛ ፣ መሸነፍን የማልወድ ፣ የሚሰማኝን ስሜት በግልፅ የምናገር ተጫዋች ነበርኩ። ቡድን መሪ ስሆንም በታዳጊ ምልመላ ላይ አስተዋፆኦ የነበረኝ እነ ዳዊት እስጢፋኖስ ወደዚህ ክለብ እንዲመጡ ያደረኩ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን ከአሰልጣኙ ባልተናነሰ ተጫዋቾችን እየተንከባከብኩኝ እጠብቅ የነበርኩኝ ሰው ነበርኩ።”

“በ1987 የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ሆኜ ጎልም አስቆጥሬ የተቀየርኩበት ምክንያት የብዙዎች ጥያቄ ቢሆንም ይህ ነው ብዬ ምክንያቱ መናገር አልችልም። ግን በወቅቱ አንድ ልምድ መውሰድ ነበረባቸው በምንም መንገድ እኔ ተቀይሬ ስወጣ ንግድ ባንክ ላይ ጎል ይገባብ ነበር። እንደውም አንድ ከገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ጋር አብሮ የሚሰራ ፎቶ የሚያናሳ ልጅ ገነነ ልኮት ያረፍንበት ሆቴል አንድ ጥያቄ ይዞልኝ ይመጣል። ‘ምንድነው አንተ ልጅ ሁሌ ተቀይረህ ስትወጣ ንግድ ባንክ ላይ ጎል ይገባል ? ምክንያቱ ምንድን ነው ?’ ብሎ በላከው ወረቀት ላይ መልስ መልሼ እንድልክ ይጠይቀኛል። እኔ ደግሞ ይህ ቡድን ወደ ዋንጫ እየሄደ ያለ ቡድን ነው። እንዲህ ያለ ነገር ጋዜጣ ላይ ማውጣቱ አስፈላጊ አይደለም ብዬ አድበስብሼ አለፍኩት። ምን ለማለት ፈልጌ ነው። እስካሁን ድረስ ያቺ ተቀይሬ የወጣሁባትን ሳስብ ሁልግዜ የገነነ ነገር በጭንቅላቴ ይመጣል። ሁለት ዕድል ይዘን ወደ ሜዳ ገባን እና ገና ጨዋታው በተጀመረ ሁለት ደቂቃ ውስጥ የደሳለኝን አቋቋም አይቼ ጭንቅላቴን እና እግሬን አገናኝቼ ቆንጆ ጎል አስቆጥሬ መምራት ጀምረን ነበር። የሚገርምህ የማዕዘን ምት የቅጣት ምት በተገኘ ቁጥር ሙሉጌታ ከበደ እኔን ነበር መጥቶ የሚዘው። ተቀይሬ ስወጣ እንኳን ወደ ደጋፊዎቹ በመሄድ በምልክት ቪ እያለ ያሳያል። ሜዳ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾችን ‘በቃ አሁን ነው መጫወት ያለብን ትንሼ ወጥቷል !’ ይል ነበር። ለምንድድ ነው እፎይ ያሉት ? እኔ የጎል ሰው በመሆኔ ነው። እኔ በምንቀሳቀስ ሰዓት ሁሉንም ይዤ እቆማለው። ሆኖም ግን ለምን እንደተቀየርኩ አላውቅም። ህልም ሁሉ ነው የሚመስለኝ። ተቀየርኩ ብዬ ተናድጄ ነው የወጣሁት በዕለቱ ካፊያ ነገር ስለነበር ተጫዋቾችን እንዳላቆሽሻቸው ትራኩ ላይ ተቀምጬ እያለ የገነነ ጥያቄ ወደ ውስጤ ሲመጣ ፈርቼ ተነስቼ ወደ መልበሻ ክፍል እንደገባው ፀጋዬ ተንበርክኮ ይፀልያል። ታዲያ ለመታጠብ ማልያዬን ሳወልቅ ስታድየሙ የፈረሰ እስኪመስል ተንቀጠቀጠ። በቃ ሁለተኛ ጎል አስቆጠሩ ገላዬን አልታጠብም ብዬ ፊቴ ላይ የነበረውን ጭቃ አስለቅቄ ወደ ሜዳ እንደተመለስኩ ፋሲል አብርሀ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው አለቀ። ከልጆቹ አልቀላቀልም ብዬ ትሪቡን ትራክ ላይ ቆሜ እያለቀስኩ ሙሉጌታ ከበደ ዋንጫውን ተቀብሎ በእኔ በኩል ሲመጣ እውነት ነው የምለው ዋንጫውን ንጠቀው ንጠቀው ነው ያለኝ። በጣም ተናደድኩ አለቀስኩ ተንፈራፍሬ የተቀየርኩበት ሁኔታ አበሳጭቶኝ ወደ ማረፊያችን ሄደናል።”

“በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በወቅቱ በእኛ ላይ የተሰሩ ብዙ አሻጥሮች ነበሩ። የሚገርምህ በጣም እርቀነው እንመራ ነበር። አጠጋግተው አጠጋግተው እኛ ላይ እንዲደርስ አመጡት። ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ፀጋዬ ወንድሙ (አግሮ) በሳቦታጅ ቢጫ አይቶ እንዳይገባ ተደረገ። እኔ ከመድን ጋር ስንጫወት በቀጣይ ለጊዮርጊስ ጨዋታ እንዳልሰለፍ እና ጎል አግቢነቱን እየመራው ያለሁት እኔ በመሆኑ እርሱንም እንዳጣ ተፈልጎ በተቀያሪ ወንበር ላይ ተቀምጬ መሐል ሜዳ ላይ በተፈጠረ ግርግር ለማብረድ ገብቼ ሆን ተብሎ ባላጠፋሁት ቀይ እንደይ ተደርጎ ነበር። በኃላ ዳኞቹ መጥተው ‘ይቅርታ ተሳስቼ ነው ቀይ የሰጠሁህ’ ብሎ ተነስቶልኝ ነው ለጊዮርጊስ ጨዋታ የደረስኩት። መድን ከጊዮርጊስ ጋር የነበረው አሻጥር አንድ ቀን ጊዜ ሳገኝ የምናገረው ነገር ነው። ብቻ በሰባት ነጥብ የምንመራውን ቡድን አጠጋግተው አምጥተው በጊዜው የእኔም መቀየር አስተዋፆኦ አድርጎ ዋንጫውን ልናጣ ችለናል። ብቻ የኢትዮጵያ እግርኳስ በዛን ጊዜ የነበረው መድሎ ይገርመኛል።”

” ከፍተኛ ጎል አግቢነቴን ያጣሁበት መንገድ በጣም ይገርማል። የአዲስ አበባን ዋንጫ ከብዙ በደል እና ግፍ በኃላ እንደገና አገግመን ለኢትዮጵያ ሻምፒዮን እየተጫወትን ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በብዙ ጎል እየመራው አራት ውስጥ ገብተን ነበር። በዓለም እግርኳስ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ፌዴሬሽኑ የኔን ጎሎች ለመንጠቅ እና ለጊዮርጊሶች ለመስጠት ‘ጎል የሚቆጠረው ከአሁን በኃላ ነው’ በማለት የለፋሁበትን ጎሎቼን ነጠቁኝ። (በአግርሞት እየሳቀ) በኃላ አሸናፊ ሲሳይ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ሁለት ሺህ ብር ተሸለመ። በኃላ አሸነፊ ፈጣሪ ይስጠው በሰዓቱ “ጎል ለማግባት የሚከፈለው መሰዋዕትነት ቀላል ስላልሆነ የትንሼን ላብ እኔ በላሁት’ አለ። በወቅቱ ይህ መሆን የለበትም በማለት እስከ ካፍ ድረስ እንደርሳለን ተገቢ አይደለም በማለት ብቻውን ሲታገል የነበረው ገነነ መኩሪያ ብቻ ነበር። ‘የልጁ ላብ ተበላ’ በማለት ሲጮህልኝ የነበረው ሌላው በዝምታ ነበር ያለፈው።”

“ትንሼ የሚለውን ቅፅል ስም ማን እንዳወጣው አላውቅም። ሠፈሬ በአራት ኪሎ እና በሥላሴ መሐል ስለነበረ ጃንሜዳ የታዳጊ ቡድኖች ጨዋታ ይደረጋል። አጋጣሚ ሆኖ እናቴ ማሙሽ እያለች ነበር የምትጠራኝ። ምድር ጦር ታዳጊ ቡድን ውስጥ ደግሞ ማሙሽ የሚባል ሌላ ልጅ ነበር። ስለዚህ ከእርሱ ለመለየት ትንሹ ማሙሽ ፣ ትልቁ ማሙሽ በማለት ለመለየት ይጠሩን ነበር። በኃላ ‘አንተ ትንሹ አቀብለው’ እንዲህ አድርግ እያሉ ሲጣሩ አብረውኝ የሚጫወቱት በላቸው ከሚሉኝ ትንሼ እያሉ መጥራት ቢጀምሩም ትንሼ የሚለው ስም ዋናው መነሻ ግን ዋናው ቡድን ዝግጅት ሐረር እያደረግን ‘ይህች ትንሽ ልጅ ምን ልትሰራ መጣች ?’ በማለት ትንሼ እያሉ ይጠሩኝ የነበረ በመሆኑ ቅፅል ስሜ ሆኖ ቀርቷል።”

“ቡድን መሪ ሆኜ በተለያዩ ጊዜያት አሰልጣኝ የመሆን ዕድል አግኝቼ ነበር። በተለይ ግን በ1996 ወርቁ ደርገባ ባንክን ለማሰልጠን ይመጣል። ከእኔ ጋር ተስማምቶ እንደ ም/አሰልጣኝ እና ቡድን መሪ ሆኜ እንድሰራ ተደረጎ ቡድኑን ለውድድር አዘጋጅተን ሳለ ወርቁ ከሥዩም አባተ ጋር ለብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ለጨዋታ የሆነ ሀገር ይሄዳል። የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከጊዮርጊስ ከተሸነፍንበት ጨዋታ ውጪ ሁሉንም ጨዋታ አሸንፈን የሲቲ ካፑን ሁለተኛ ሆንን ጨረስን። አስበው ገና እግርኳሱን ካቆምኩ አጭር ጊዜ ነው። ብዙ የአሰልጣኝነት ልምድ የለኝም። ሆኖም የቡደኑን ተጫዋቾች አበረታትቼ ፣ በሚገባ እንደ እንቁላል ተንከባክቤ ፣ ልምዴን ተጠቅሜ ውጤታማ አደረኩት። ወርቁ ተመልሶ መጥቶ ብዙ መቆየት ሳይችል ሲለቅ በድጋሚ ቡድኑን በጊዛዊ አሰልጣኝነት ተረክቤ ትልልቅ ጨዋታዎችን በድል በማጠናቀቅ ቡድኑን የተሻለ ደረጃ ማድረስ ቻልኩ። ነገ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለነበረ ጨዋታ ቡድኑን እያዘጋጀው ሳለ ተጫዋቾቹ ‘ካሶተኒ የለንም’ ሲሉ ቢሮ ሄጄ ላስገዛ ስል ነፍሱን ይማረው እና ሥዩም አባተን ቢሮ አገኘዋለው። እንዴ ሥዩም ባንክ ምን ይሰራል ? ብዬ ሳየው አንድ ሰው አትተዋወቁም እንዴ ሲል ሥዩም ‘ኧረ ልጄ ነው አሰልጥኜዋለው’ ይላል። በኃላ ባንክ አሰልጣኝ እንደሚሆን አወኩኝ። እኔ ቡድን መሪ እንጂ አሰልጣኝ አይደለሁም ፤ በመምጣቱ ደስ ይለኛል። ነገር ግን ነገ ከጊዮርጊስ ጋር ጨዋታ አለ። ‘በዚህ ሰዓት ሥዩም መጣ የሚለውን ነገር ልጆቼ ባይሰሙ ደስ ይለኛል። እኔም የመጣሁት በአጋጣሚ ለሌላ ጉዳይ ነው።’ አልኩኝ። በዚህ ተስማምተን ቡድኑን ይዤ በንጋታው ጊዮርጊስን አንድ ለዜሮ አሸነፍን። በቃ የምሆነውን አላውቅም ልጆቹ ያቅፉኛል ይስሙኛል። ደስታችን ወደር አልነበረውም። በነጋታው በጋዜጣ ላይ በዓርስት ‘ሥዩም አባተ ባንክ ገባ ፤ ትንሼን በስልክ እየመራው ውድድሩ ተካሄደ።’ የሚል ተፅፏል። የሚገርምህ በአንድ አጋጣሚ ሜዳ ሆኜ ቦጋለ ዘውዴ (ኢንተሎ) ደውሎልኝ። ‘እስራኤል እየደከመ ነው። እስራኤልን ቀይሪው ተከላካዩን አጠናክር’ እያለ በስልክ አውርቶኛል። እኔም ኢንተሎን የማምነው ሰው ስለነበር ተቀብዬ ይሄን አደረኩኝ። በቃ ይሄን ነው ያወራሁት። ሌላ ያናገርኩት ስልክ የለም። እንዴት እንዲህ ይፃፋል ብዬ አበድኩኝ። ሥዩም ጋር ደወልኩኝ። ‘እንዴት እንደዚህ ታፅፈለህ ?’ አልኩት ‘እኔ አይደለሁም’ አለኝ። እንደ አጋጣሚ የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ስለነበር እረፍት ተሰጥቶ ነበር። ‘ከዚህ በኃላ የራስህን ቡድን ማዘጋጀት ትችላለህ ይህ የኔን ዋጋ ለማሳጣት ሆን ተብሎ የተሰራ ነው’ ብዬ ተከፋው። ቅዱስ ጊዮርጊስንም የኢትዮጵያ ቡና ጨምሮ ያሸነፍኩት በኃላ ሥዩም ቡድኑን ተረክቦ የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን አነሳን። ኢትዮጵያ ውስጥ ቲፎዞ ያስፈልጋል። በጊዜው ያገኘሁትን ዕድል ተጠቅሜ ያስመዘገብኩትን ውጤት አይተው ቢታስቀጥሉኝ ኖሮ ራሴን አሻሽዬ ትልቅ አሰልጣኝ እሆን ነበር ፤ ይህ ሳይሳካ ቀርቷል።”

” ንግድ ባንክ መፍረሱን የሰማውበትን ዕለት መግለፅ ስሜቱ ከባድ ነው። ምን አለ መሰለህ ባንክ ሁሉ ነገር ያገኘሁበት ከአጥንቴ እና ከስጋዬ ጋር የተጣበቀ ስጫወትበት ያደኩበት ቡድን ነው። ችግሩ ምን እንደሆነ ጉድለቱ በደንብ የምረዳ ሰው ነኝ። ምንም ነገር ሲፈጠር ለማስተካከል ወደሚመለከተው አካል የምሮጠው እኔ ነኝ ፤ ይህንንም ብዙ ሰው ያውቃል። በግልፅ ነው ክለቡን የሚጎዳ ነገር እንዳይደረግ ስታገል የቆየሁት። ይህ ክለብ ኖሮ ልጆቻችን የሚረከቡት እንዲሆን ነበር ምኞቴ። ሆኖም ከአቅም በላይ በሆነ ነገር በቦታው እንድቆይ ስላልተፈለገ 13 ዓመት በቡድን መሪነት ከቆየሁበት ቦታ እንድነሳ ተድገ። መጨረሻውም ቡድኑ ሃያ ዓመት ኖሮ የሚያገኙትን ጥቅም በአንዴ እናግኘው ብለው በሃያ ዓመት ክለቡ የሚጠቀምበትን ገንዘብ በአራት ዓመት ውስጥ ሁሉን ነገር ሙልጭልጭ ፣ ቅርጥፍጥፍ አድርገው ጨረሱት። ቡድኑም እስከ መፍረስ ደረሰ። እኔ የህሊና ሠላሜን ይዤ ደረቴን ነፍቼ ነው የምንቀሳቀሰው። እኔን ሲያዩ የሚገቡበት ነው የሚያጡት። ባንክ መኖር እየቻለ ለልጆቻችን እዚህ ክለብ ነው የተጫወትነው እንዳንል ክለቡ የለም ፤ በጣም ነው የሚያሳዝነው። ምንም ሳያጣ የገንዘብ አቅም ኖሮት አይደለም እግርኳስን ሌላም ነገር ማስተዳደር የሚችል አውራ የሆነ ባንክ እንዲሁ የኔነት የሚሰማው ሰው ባለቤት በማጣት ይህን ትልቅ ክለብ ማጣት ከባድ ነው። አንድ ቀን ተስፋ አደርጋለው ይመለስ ይሆናል።”

“በብሔራዊ ቡድን አለመጫወቴ ይገርመኛል። በአሰልጣኝ ደረጃ ያላሰለጠነኝ ሰውነት ቢሻው ብቻ ነው። ከመንግስቱ ወርቁ አንስቶ የተለያዩ ትልልቅ አሰልጣኞች አሰልጠነውኛል። ለብሔራዊ ቡድን በ1986 ተጠርቼ ለሁለት ወር ዝግጅት ገብቼ ነበር። በኃላ ውድድሩ ይቀራል። ጉዳትም አጋጠመኝ በዛው ዳግመኛ ብሔራዊ ቡድን ሳልጠራ ቀረው። በብሔራዊ ቡድን ያለኝ ትውስታ መቶ ሃምሳ ብር መብላት እና ሁለት ወር ብቻ መቆየት ነው። ከዚህ ውጪ አንድም ቀን የብሔራዊ ቡድን መለያ ለብሼ አልተጫወትኩም። ከሙሉጌታ ከበደ ፣ አሰግድ ተስፋዬ ፣ ሚሊዮን በጋሻው ጋር ጥሩ የዝግጅት ጊዜ በማሳለፌ ብቻ ደስተኛ ነበርኩ። ያው ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ቲፎዞ ያስፈልጋል። በጣም ልቀህ መገኘት አለብህ ፤ በጣም ከባድ ነው። አሁን እኮ አንድ ጎል ስታገባ የምትመረጥበት ጊዜ ነው። ያኔ ኮከብ ጎል አግቢ እየተፎካከርኩ አለመመረጤ የሚገርም ነው።”

” አሰልጣኝነት በተመለከተ “ቢ” ላይሰንስ ወስጃለው። ወደአሰልጣኝነቱ የመምጣት ሀሳብ አለኝ። ግን ሥራው በጣም አንቆ ይዞኛል። ጥሩ የአሰልጣኝነት እይታ እንዳለኝ አምናለው። ይሄን ደግሞ አብረውኝ ሲሰሩ የነበሩ ተጫዋቾች ይመሰክራሉ። በጣም ምኞታቸው ነበር። አሰልጣኝ በሌለበት ጊዜ ሁሌም ሲያዩኝ በእኔ አሰልጣኝ አለመሆን ይናደዱ ነበር። ያው ማሰልጠን ከቻልኩ ንግድ ባንክ ብቻ ነበር ዕድሌ። ወደ ሌላ ልሂድ ካልኩ የመንግስት ስራውን ማቆም አለብኝ። በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያን እግርኳስን ተማምነህ ቤተሰብህን ጥለህ የሌላ ክለብ አሰልጠኝ መሆን በጣም የማይታሰብ፣ ከባድ ነገር ነው።”

“የ1987 ዋንጫ ያጣንበት ሁኔታ ሁሌም በእግርኳስ ህይወቴ የምቆጭበት አጋጣሚ ነው። ያው ለብሔራዊ ቡድን አለመመረጤ ሌላው የሚቆጨኝ ነገር ነው። ከዚህ ውጪ ምንም የምቆጭበት ነገር የለም። ።”

“የቤተሰብ ህይወቴ ፈጣሪ ይመስገን ፈጣሪ ክሶኛል። ከሁለት ሴት ልጆቼ እና ከባለቤቴ ጋር በመሆን በሠላም ደስ የሚል ኑሮ እየኖርኩኝ ነው። የንግድ ባንክ ቋሚ ሠራተኛ በመሆን እስካሁን ሀያ ሰባት ዓመት እያገለገልኩኝ እገኛለው።”

“በመጨረሻም እናንተ አስታውሳችሁ የሚሰማኝን ስሜት የእግርኳስ ህይወቴን ስለጠየቃችሁኝ በጣም አመሰግናለው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!