የባርሴሎናው ከፍተኛ የግብ ጠባቂ ባለሙያ ለሀገራችን የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል

የባርሴሎናው ላሜሲያ ወጣቶች አካዳሚ የግብ ጠባቂ ዋና አሰልጣኝ የሆነው ሪቻርድ አርጋይ በሀገራችን ኢትዮጵያ ላሉ የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ትናንት ምሽት ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ እና የአሜሪካው ሳክሪሜንቶ የእግር ኳስ አካዳሚ አሰልጣኝ አምሳሉ ፋንታሁን በጋራ ሆነው ከተለያዩ አለማት ካሉ የእግርኳስ ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጠው የኦንላይን ስልጠና ቀጥሎ ትናንት ምሽት 4፡00 ጀምሮ ከሁለት ሰአታት በላይ የቆየ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በስፔኑ ሀያል ክለብ ባርሴሎና ውስጥ በሚገኘው የላሜሲያ ወጣት ቡድን የግብ ጠባቂ ዋና አሰልጣኝ በመሆን እየሰራ የሚገኘው ሪቻርድ አርጋይ በዋናነት ይህን ስልጠና የሰጠ ሲሆን በስፔን ከፍተኛ የስፖርት ኤክስፐርት ዴቪድ ሮበርትሰን በጋራ በመሆን አቅርበዋል፡፡

ሪቻርድ በተለይ ስለ ባርሴሎና አካዳሚ የግብ ጠባቂዎች የስልጠና መንገድ እና ሒደት በአሜሪካ እና ካናዳ ሰጥተውት የነበረውን ስልጠና ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ በማምጣት ነው በZOOM ታግዘው ለሀገራችን ግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ያጋሩት። በስልጠናው በተለየ መልኩ ባርሴሎና ከ13 ዓመት ጀምሮ ከላሜሲያ አካዳሚ እስከ ዋናው ቡድን የሚከተላቸውን የተግባር፣ የክፍል እንዲሁም መሰል የስልጠና ሒደቶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ግብ ጠባቂዎች ሊተገብሯቸው የሚገቡ መሠረታዊ የቴክኒክ ጉዳዮችን በማንሳትም ገለፃ አድርገዋል። ከዚህም ባለፈ የባርሴሎናው ላሜሲያ አካዳሚ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የመጡበት መንገድ እና ጀርመናዊው የአሁኑ የባርሴሎና ቋሚ ግብ ጠባቂ አንድሬ ቴር ስቴገን የሚከተላቸው የጨዋታ መንገዶች በምሳሌነት ቀርቦ በትምህርት መልክ ተሰጥቷቸዋል፡፡

በሌላ በኩልም የጋራ፣ የግል እና ብዛት ባላቸው ግብ ጠባቂዎች መካከል የሚሰጡ ስልጠናዎች ምን አይነት እንደሆኑ እና ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች ከታዳጊ፣ ወጣት እስከ አዋቂ ድረስ መከተል ስላለባቸው የስልጠና አማራጮች ገለፃ የተደረገ ሲሆን አንድን ግብ ጠባቂ ለማፍራት ተንከባክቦ ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ተገልጿል።

በመጨረሻም ሰልጣኞቹ በስልጠናው ዙርያ ጥያቄዎች አንስተው በባለሙያዎቹ ምላሽ ከተሰጠ በኋላ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!