Soccer Ethiopia

የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ቆይታ ከአብዱልከሪም መሐመድ ጋር…

Share

“ተርምኔተር” በሚል ቅፅል ስም የሚጠራው ታታሪው የመስመር ተከላካይ አብዱልከሪም መሐመድ በዘመናችን ከዋክብት ገፅ ላይ ቆይታ አድርጓል።

የዛሬው እንግዳችን አብዱልከሪም በወንዶ ገነት ከተማ ነው ተወልዶ ያደገው። ተጫዋቹ ዕድገቱን እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እስኪደርስ ድረስ በወንዶ ገነት ካደረገ በኋላ 21 ኪሎ ሜትሮችን ከተወለደበት ከተማ በመጓዝ ሀዋሳ ከተማ ደረሰ። ሀዋሳም እንደገባ ትምህርቱን ጎን ለጎን እያስኬደ ከልጅነቱ ጀምሮ የተለከፈበትን የእግርኳስ ተጫዋችነት ፍቅርን ማስቀጠል ያዘ። እርግጥ ተጫዋቹ በወንዶ ገነት እያለም እግርኳስን ይጫወት የነበረ ቢሆንም በተሻለ ደረጃ ከኳስ ጋር የተገናኘው ሀዋሳ ሲገባ እንደሆነ ይናገራል። በከተማዋ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ታቅፎ ራሱን ማብቃት ከጀመረ በኋላም በሲዳማ ዞን ልዩ ልዩ ሻምፒዮና ውድድር ላይ የሚካፈልበትን ዕድል አገኝቶ ብቃቱን ለብዙዎች አሳየ። በይርጋለም በተደረገው በዚህ ውድድር ላይ ሲጫወት የበርካታ ክለቦች ዕይታ ውስጥ የገባው ተጫዋቹ ለመጀመሪያ ጊዜ ለትልቅ ክለብ እንዲጫወት ሆኖ ለሲዳማ ቡና ፈረመ።

2002 መጨረሻ አካባቢ ሲዳማ ቡና ቤት በቢጫ ቴሴራ ከተያዘ በኋላም ከሁለት ወራት ያልዘለለ ጊዜን በክለቡ ቆይቶ የተሻለ የመጫወት እድል የሚያገኝበትን ክለብ ፍለጋ ወደ ደቡብ ፖሊስ አመራ። በዚህም ክለብ በፕሮጀክት ሲያሰራው የነበረውን አሠልጣኝ ያሬድ ገመቹን አግኝቶ ራሱን በተሻለ ደረጃ መጫወት የሚያስችለው ብቃት ላይ እንዲደርስ ማዘጋጀት ቀጠለ። አንድ ዓመት በፖሊስ ቤት ካገለገለ በኋላም 2004 ላይ ለሀዋሳ ከተማ ፊርማውን አኖረ። በሀዋሳም ለሁለት ዓመታት ከተጫወተ በኋላ በቢጫ ቴሴራ ለሁለት ወር ተይዞ የቆየበትን ክለብ ሲዳማ ቡናን ዳግም ተቀላቀለ። በዚህ ክለብም ጋሮእጅግ ድንቅ ሁለት ዓመታትን ከተጫወተ በኋላ 2008 ላይ ወደ መዲናችን አዲስ አበባ በመምጣት ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ወሰነ። በተመሳሳይ በቡናማዎቹ ቤት ለሁለት ዓመታት የአቅሙን ከቸረ በኋላ 2010 ላይ ለሌላኛው የመዲናችን ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፊርማውን አኑሮ የእግርኳስ ህይወቱን ቀጥሏል።

እግርኳስን በክለብ ደረጃ ሲጀምር በአማካይ መስመር ተጫዋችነት የጀመረው አብዱልከሪም በተጫዋች ጉዳት እና ቅጣት ምክንያት ወደ መሐል ተከላካይነት ቦታ ተስቦ ተጫውቷል። ከዛም በሀዋሳ ከተማ በተለይ ደግሞ በሲዳማ ቡና ቤት አሁን የሚጫወትበትን የመስመር ተከላካይነት ቦታ በመያዝ ግልጋሎት መስጠት ጀምሯል። 2008 ላይ በማሪያኖ ባሬቶ አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ጥሪ የቀረበለት ተጫዋቹ በዛው ጥሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሩን ወክሎ ከማላዊ ጋር በመጫወት የብሔራዊ ቡድን ህይወቱን ጀምሯል። በመዲናችንን ሁለት ሃያል ክለቦች የተጫወተው ፣ በታታሪነቱ የሚታወቀው እንዲሁም የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠውን ይህን ተጫዋች በዛሬው የዘመናችን ከዋክብት ገፅ እንግዳ አድርገነው ተከታዮቹን ጥያቄዎች አቅርበንለታል።

የእግርኳስ አርዓያህ ማነው ?

እውነት ለመናገር በልጅነቴ እንደ አርዓያ የምመለከተው እግርኳስ ተጫዋች አልነበረም። ግን ካደግኩ እና እግርኳስን በደንብ መጫወት ከጀመርኩ በኋላ ሀዋሳ ከተማ ሲጫወቱ የነበሩትን ሙሉጌታ ምህረት እና ዳንኤል ደርቤን ሳደንቅ ነበር። ከውጪ ደግሞ በቴሌቪዥን የምመለከተውን ዳኒ አልቬስ በደንብ እከታተል ነበር።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተቋረጠ በኋላ ጊዜህን በምን እያሳለፍክ ነው ?

ኮቪድ ሊጉን ለረጅም ጊዜ አቋርጦታል። በሽታው ሊጉን ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችንም ገትቷል። እኔም በሽታው እንደመጣ በቀጥታ ቤተሰብ ጋር ነው የሄድኩት። እዛም ከቤት ብዙ አልወጣም ነበር። የስፖርት መስሪያ መሳሪያዎቼን ይዤ ስለነበር የሄድኩት ግቢያችን ውስጥ እንቅስቃሴዎችን ከታናሽ ወንድሜ ጋር እሰራ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ግቢያችን ፊት ለፊት የትምህርት ቤት ግቢ ነበር። ግቢውን አስፈቅጄ ሜዳውን ካስተካከልኩ በኋላም ከመኖሪያ ቤት ግቢዬ በተጨማሪ እዛ ልምምዶችን ስሰራ ነበር። በአጠቃላይ በሽታው የሚያስከፋ ቢሆንም እኔ ራሴን እየጠበኩ ጊዜውን በጥሩ ሁኔታ አሳልፌያለሁ።

ኮሮና ከመጣ በኋላ የለመድከው ምን አዲስ ልማድ አለ ?

መጥፎ ቢሆንም ከሰው ጋር አለመገናኘት አዲሱ ልማድ ይመስለኛል። እንደበፊቱ ጓደኞቼን አላገኝም። ይህ አዲስ ልማድ ነው።

ኮሮና አሁን ጠፋቷል ብትባል መጀመሪያ የምታደርገው ነገር ምንድን ነው ?

ማድረግ የምፈልገው የመጀመሪያ ነገር በደጋፊዎች ታጅቦ እግርኳስን መጫወት ነው። ይህ በጣም ናፍቆኛል። እርግጥ ከጓደኞቼ ጋር እንደበፊቱ ተሰብስቦ ማውራት እና መጫወትም ቢናፍቀኝም እሁን ላይ በርቀትም ቢሆን እያደረግነው ነው። ግን ከምንም በላይ ደጋፊዎች እየዘመሩ ሜዳ ላይ መጫወት ናፍቆኛል።

በግልህ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍክበት ዓመት መቼ ነበር ?

በአንፃራዊነት 2008 እና 2010 በኢትዮጵያ ቡና እና በቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታዬ ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። እርግጥ ሌሎችም ነበሩ። ነገር ግን በጣም ምርጥ ጊዜን ያሳለፍኩት በእነዚህ ዓመታት ቆይታዬ ነው።

ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችህ ምንድን ናቸው ?

እነዚህን ነገሮች እኔ መናገር ይከብደኛል። ከውጪ ሆኖ የሚያየኝ ሰው ነው ስለእኔ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች መመስከር የሚችለው። እኔም ሰዎች የሚነግሩኝን ደካማ ጎኖች ለማስተካከል እሞክራለሁ። ግን አሁን ላይ ይህ ነው ጠንካራ እና ደካማ ጎኔ ብዬ መናገር አልችልም።

አብዱልከሪም እግርኳስ ተጫዋች ባይሆን ምን ይሆን ነበር ?

በቀለም ትምህርቴ ጥሩ ነበርኩ። ከዚህ መነሻነት ትምህርቴን ገፍቼ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ እሞክር የሆናል። ይህ ካልሆነ ደግሞ ቤተሰቦቼ የሚገኙበትን የንግድ ዓለም እቀላቀል ነበር።

አብሬው ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለሁ የምትለው ተጫዋች አለ ?

እውነት ለመናገር የለም። ምክንያቱም ከአብዛኞቹ የሀገራችን ተጫዋቾች ጋር በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ስለተጫወትኩ።

ልምምድ ላይ ጠንካራ ነህ ? ብዙዎች ልምምድ የምትሰራበትን ትጋት ሲያደንቁ ይሰማል ፤ ስለዚህ ጉዳይ አጫውተኝ እስኪ ?

ልክ ነው ፤ ልምምድ ላይ ኮስታራ ነኝ። አሠልጣኞች የሚሰጡኝን ልምምድ በደንብ ነው የምሰራው። በተጨማሪም ዕረፍቴን በደንብ ከወሰድኩ በኋላ በግሌ ጂም ሄጄ ሌሎች ስራዎችን እሰራለው። ስፖርተኛ ልምምዱን በደንብ መስራት አለበት። የተሻለ ደረጃ ለመድረስም ጠንክረህ መስራት አለብህ። ይህንን ተከትሎ አሠልጣኙ ከሰጠኝ ነገር የበለጠ የሚጎድሉ ነገሮችን እየሞላሁ ጥሩ ብቃት ላይ ለመድረስ እሞንራለሁ። እንደውም እኛ ሀገር የግል አሠልጣኞች ብዙም የሉም እንጂ ቢኖሩ እና ቢረዱን ደስ ይለኝ ነበር። ግን ይህ የለም ብዬ መቀመጥ ስለሌለብኝ ከኢንተርኔት ላይ የሚጠቅሙኝን ነገሮች እያየሁ እሰራለሁ። በዚህ አጋጣሚ እንደውም ተጫዋቾቸ ይህንን ዓይነት ልምድ እንዲከተሉ እመክራለው።በተቃራኒ ስትገጥመው የሚከበደህ ተጫዋች ይኖር ይሆን ?

እውነት ለመናገር ፈትኖኛል የምለው አጥቂ ገጥሞኝ አያውቅም።

በዚህ ሰዓት በሀገራችን ከሚገኙ ተጫዋቾች ያንተ ምርጡ ተጫዋች ማነው?

ሊጉ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ያለውን ወቅታዊ የተጫዋቾቻችን ብቃት ታሳቢ ካደረግን ሱራፌል ዳኛቸው ምርጡ ተጫዋች ነው። አምናም ብቻ ሳይሆን ከዛም በፊት ሱራፌል ጥሩ ዓመታትን ሲያሳልፍ ነበር። ስለዚህ ሱራፌልን መርጫለሁ።

በእግርኳስ በጣም የተደሰትክበትን አጋጣሚ አውጋኝ እስኪ ?

በሁለት አጋጣሚዎች በጣም ተደስቻለው። አንደኛው 2008 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሬን እንዳገለግል ጥሪ ሲቀርብልኝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 2010 ላይ የሊጉ እንዲሁም የኢቢሲ ኮከብ ተጫዋች ተብዬ የተመረጥኩበት ጊዜ ነው።

በተቃራኒው የተከፋህበትን እና ጥሩ ስሜት የማይሰጥህስ አጋጣሚስ ?

ቀድሜ እንዳልኩት 2010 ላይ ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። በግልም ሽልማቶችን አግኝቻለሁ። ግን በዚሁ ዓመት ክለቤ ጊዮርጊስ ጅማ ላይ በተፈጠረ ነገር ዋንጫ ሳናነሳ መቅረቱ ያንገበግበኛል ፤ እስካሁንም ይቆጨኛል። በተለይ ደጋፊው የሆነው ነገር እና እኛ ውጤት ያጣንበትን መንገድ መቼም የምረሳው አይመስለኝም።

እግርኳስ ካቆምክ በኋላ ምን ለመሆን ታስባለህ ?

ፈጣሪ ያውቃል። አሁን ላይ ምን እንደምሆን አላሰብኩም። ይህንን ጉዳይ አቅሜ እስከፈቀደው ድረስ ተጫውቼ ኳሱን ሳቆም የማስብበት ይሆናል።

ቅፅል ስምህ ‘ተርምኔተር’ ነው ? ለምን ተባልክ ? ማንስ ነው ያወጣልህ ?

ልክ ነው ‘ተርምኔተር’ ይሉኛል። ይህ ቅፅል ስም የወጣልኝ ኢትዮጵያ ቡና እያለሁ ነው። ጥላሁን ወልዴ ነው ልምምድ ላይ ያለኝን ነገር አይቶ ይህንን ስም ያወጣልኝ።

የግል ህይወትህ ምን ይመስላል ?

ወደ ትዳሩ ዓለም አልገባሁም ፤ ከቤተሰቦቼ ጋር ነው የምኖረው። እርግጥ ቤተሰቦቼ ያሉት ወንዶ ገነት ቢሆንም ሀዋሳም ቤት ስላለን እየሄድኩ አብዛኛውን ጊዜዬን አሳልፋለው።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!

ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ በ ‘አብርሀም ገ/ማርያም የማስታወቂያ ድርጅት’ ስር የሚሰራ ድረገፅ ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በሚያተኩሩ ዜናዎች፣ ቁጥራዊ መረጃዎች፣ ታሪኮች፣ ጥልቅ ዘገባዎች፣ አስተያየቶች እና ትንታኔዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

ዘርፍ

ማኅደር

top