በዛሬው ይህን ያውቁ ኖሯል? አምዳችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እና የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎን የተመለከቱ ተከታይ ክፍል ዕውነታዎችን ይዘን ቀርበናል።
ማስታወሻ: የተጠቀሱት ሁሉም ዓመታት በኢትዮጵያ የዘመን ቀመር የተቀመጡ ናቸው።
– ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመርያ ጨዋታዋን የካቲት 8 ቀን በ1949 ከግብፅ ጋር ስታከናውን በመጀመርያ አሰላለፍ ተካተው የተጫወቱ ተጫዋቾች ጊላ-ሚካኤል ተክለማርያም፣ አዳል ተክለሥላሴ፣ ግርማዬ ፍቅረማርያም፣ መሐመድ ኢብራሂም፣ አየለ ተሰማ፣ አዳሙ ዓለሙ፣ ነፀረ ወልደሥላሴ፣ ዘውዴ ሳሙኤል፣ ከበደ መታፈርያ፣ አስፋው ብርሀኔ፣ ተከስተ ጎይቶም ናቸው።
– ኢትዮጵያ ከ32 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች መካከል በመጀመርያዎቹ ሰባት ተከታታይ ውድድሮች (ሱዳን-49፣ ግብፅ-51፣ ኢትዮጵያ-54፣ ጋና-55፣ ቱኒዚያ-57፣ ኢትዮጵያ-60፣ ሱዳን-62) የተሳተፈች ሲሆን ከዛ በኋላ ከተደረጉ 25 ውድድሮች መካከል የተሳተፈችው በሦስቱ (ኢትዮጵያ-68፣ ሊቢያ-74 እና ደቡብ አፍሪካ-2005) ውድድር ብቻ ነው።
– ኢትዮጵያ የመጀመርያ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዋን ያሸነፈችው ከሦስት ሙከራዎች በኋላ በአራተኛው ጨዋታ ሲሆን ራሷ ባዘጋጀችው የ1954 ውድድር ቱኒዚያን 4-2 በመርታት ነው።
– በተቃራኒው በውድድሩ ለመጨረሻ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ያሸነፈችው ከዛሬ 44 ዓመታት በፊት ሲሆን ራሷ ባስተናገደችው የ1968 ውድድር መክፈቻ ላይ ዩጋንዳን በሽፈራው ሰለሞን እና ተስፋዬ ጎሎች 2-0 አሸንፋለች። ከዛ ድል ወዲህም ስምንት ጨዋታዎች አድርጋ ድል አልቀናትም።
– ኢትዮጵያ ካደረገቻቸው 27 ጨዋታዎች መካከል 10 ጨዋታዎችን ያከናወነችው ራሷ ባስተናገደቻቸው ሦስት ውድድሮች ላይ ነው። በዚህም ስድስት አሸንፋ አንድ አቻ ስትለያይ በቀሪዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ተረታለች።
– በተጠቀሱት የሜዳዋ ጨዋታዎች 20 ጎሎችን አስቆጥራለች። (ከአጠቃላዩ ጎል 69%) በአንፃሩ 13 ጎሎችን አስተናግዳለች።
– በሌሎች ሀገራት በተስተናገዱ ሰባት ውድድሮች ላይ የተካፈለው ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ ሱዳን (2)፣ ግብፅ፣ ቱኒዚያ፣ ጋና፣ ሊቢያ እና ደቡብ አፍሪካ ላይ 17 ጨዋታዎችን አከናውኖ 1 ጨዋታ ብቻ ሲያሸንፍ 14 ጨዋታ ተሸንፏል። በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
– ቡድኑ በተጠቀሱት 17 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች 48 ጎሎችን ሲያስተናግድ 9 ጎሎችን ብቻ አስቆጥሯል። በተጨማሪም 12 ጨዋታዎች ላይ ጎል ሳያስቆጥር ወጥቷል።
– ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በ27 ጨዋታዎች 29 ጎሎችን ስታስቆጥር 13 የተለያዩ ተጫዋቾች ጎሎቹን አስቆጥረዋል። መንግሥቱ ወርቁ፣ ሉቻኖ ቫሳሎ፣ ጌታቸው ወልዴ፣ ግርማ ዘለቀ፣ ተክሌ ኪዳኔ፣ ኢታሎ ቫሳሎ፣ ግርማ አስመሮም፣ በኩረፅዮን ገብረሕይወት፣ ሸዋንግዛው አጎናፍር፣ ሽፈራው ሰሎሞን፣ ተስፋዬ ሥዩም፣ መሐመድ ዓሊ እና አዳነ ግርማ ጎሎች ማስቆጠር የቻሉ ተጫዋቾች ናቸው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!