ከፋሲል ከነማው ፊዚዮቴራፒስት ሽመልስ ደሳለኝ ጋር ከክፍል አንድ የቀጠለ በኢትዮጵያ እግርኳስ ስለሚያጋጥሙ ጉዳቶች እና በህክምና ወቅት ስለሚያጋጥሙ ችግሮች ባለፈው ሳምንት በክፍል አንድ ቆይታ ማድረጋችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ በክፍል ሁለት ተከታዩን መሰናዶ ይዘን ቀርበናል።
ማሳጅ ሳይንስ ነው ማለት እንችላለን ?
ማሳጅ ጥበብ እና ሳይንስ ነው። ማሳጅ ለመሥራት ሳይንስ አናቶሚ እና ፊዚዮሎጂ በጣም አስፈላጊ ነው። የጡንቻዎችን መነሻ እና መድረሻ (ኢንሰርሽን አና ኦሪጅን) ማወቅ አለብኝ። ሳይንሱን ካላወቅን የሰውን ህይወት ልንጎዳ እንችላለን። ለዚህ ነው ሳይንስ ነው የምንለው። ለምሳሌ የደም መርጋት ያለበትን ሰው በምታሸው ጊዜ ያ የረጋው ደም ወደ ሳንባው ሄዶ የሳንባን ትቦ ሊዘጋው እና ሊሞት ይችላል። በአዋቂ የሚሠራ እንጂ በየጉራንጉሩ የሚሠራ አይደለም፤ እውቀት ይጠይቃል። አርት ነው ስንልም የተለያዩ ቴክኒኮችን ተምረህ እንጂ እንዲሁ ቤት ማንም እንደሚያሸው አይደለም። የተለያዩ ቴክኒኮችን እንደየ ጉዳቱ እና እንደየአስፈላጊነቱ መጠቀም ይጠይቃል።
ተጫዋቾች ለምንድነው በተደጋጋሚ የሚጎዱት ?
ተጫዋቾች በብዙ መንገድ ሊጎዱ ይችላሉ። ለምሳሌ ስፖርተኛ ስትሆን ጡንቻ ለማሞቅ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ሰውነቱ በአግባቡ መሞቅ አለበት። ይህን ከልምምድ ወይም ከጨዋታ በፊት አሰልጣኙ በተገቢ ሁኔታ መስጠት ይጠበቅበታል። ይህ ካልሆነ ግን ጉዳት ቶሎ ቶሎ የማጋጠም ዕድሉ ሰፊ ነው። የጡንቻ ወይም የጅማት ከተገቢው በላይ መለጠጥ እና የጭን ጉዳት በቀላሉ ሊያጋጥም ይችላል። አሰልጣኝ እና ቴክኒካል ስታፎች በመናበብ ተገቢ የሆነ ልምምድ፣ እረፍት እና ምግብ (TRF method ) መስጠት ይኖርባቸዋል። ከልምምድ በኋላ አልጋ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ በመቀመጥ ሳይሆን ስልክ አጥፍቶ በመተኛት ራሳቸውን በሚገባ ካሳረፉ እና በቂ የሆነ ምግብ እንዲመገቡ ከተደረጉ ጉዳትን መቀነስ ይቻላል። አንድ አዋቂ ሰው ከትሪሊየን ሴሎች የተገነባ ስለሆነ በደንብ በማረፍ የሚወገዱትን መተካት አለበት። ይህ ከአላስፈላጊ ጉዳት ይጠቦቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተመጣጣኝ ምግብ የሚመገብ ከሆነ እስከ 30% አላስፈላጊ ጉዳትን መቀነስ ይቻላል። አብዛኛውን ጊዜ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች የማይተገብሩ ተጫዋቾች ለአላስፈላጊ ጉዳት ይጋለጣሉ።
በእንቅስቃሴ መሐል ውሀ የመውሰድ ጠቀሜታ እስከምን ድረስ ነው?
ውሃ ጤና ነው! አንድ አዋቂ ሰው በሰውነቱ ውስጥ 60-70 % በአማካይ ውሃ በሰውነቱ ወይም በጡንቻው ውስጥ ይኖራል። በምሳሌ ማስረዳት ካለብኝ ቤታችን በግ አርደን ሥጋው ተዘልዝሎ ገመድ ላይ ይሰቀላል። ከቀን ወደ ቀን የሚያምር የነበረው ሥጋ እየጠወለገ እየጠቆረ ቋንጣ የሚሆነው ሥጋው ላይ የነበረው ውሃ ሙሉ ለሙሉ ስለሚተን ነው። የኛም ጡንቻ አምሮ እና ተመችቶት የሚታየው ውስጡ ላይ ባለ ውሃ ነው። በመጠጣታችን ብቻ ቆሻሻ ከሰውነታችን በላብ እና በሽንት እንዲወገድ ያደርጋል። ኦክስጅን በደም አማካኝነት ይዞ ለሴሎቻችን እንዲደርስ ያደርጋል። በላብ መልክ ከሰውነታችን የሚወገደውን ፈሳሽ ይተካልናል። በተለይ ስፖርተኛ በቀን ከሌላው ሰው የተለየ መጠጣት ይኖርባቸዋል። እኛም 3-4 ሊትር በቀን እንሰጣቸዋለን።
በአንድ ክለብ የተጨዋቾች መኖርያ ላይ ቢኖር ይጠቅማል የምትላቸው ነገሮች ካሉ?
አንድ ክለብ ካምፕ ላይ በጣም ብዙ ነገሮች ያስፈልጋሉ። ከነዚህም ውስጥ ለምሳሌ አይስ ባዝ (የበረዶ ገንዳ) ቢኖር ከልምምድ ወይም ከጨዋታ መልስ ከዛ ውስጥ በመግባት ትንንሽ የህመም ስሜቶችን ማስወገድ ያስችላል። ሌላው ጂም ቢኖር አለበለዚያም የፑሽ አፕ፣ የፑል አፕ፣ የዲግ አፕ እና የተለያዩ የብረት መስሪያ ብሎኬት ወይም ብረት ቢኖር መልካም ነው።
በክለቦች በኩል የህክምና መሳሪያ አቅርቦት የተሟላ ነው ማለት ይቻላል ?
በጣም በሚገርምህ በአብዛኛው ክለብ ለህክምና የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው። ነገር ግን የህክምና ማዕከል ከነ ሙሉ መሳሪያው አስፈላጊ ነው። በአብዛኛው ወጌሻው በጨበጣ ነው የሚሰራው። ወሳኝ የሆኑ ስፖርቱ ላይ የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎች አሉ። ለምሳሌ infrared (ማሞቂያ )፣ Massager ማሳጅ ማድረጊያ መሳሪያ Tens, electro therapy እና massage teble በጣም ወሳኝ ናቸው። እኛም ጋር ከሚዋጥ ክኒን ውጭ ሌላ ምንም አይነት አቅርቦት የለም። ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ፋሲል ከነማ ቤት እየተደረገ ያለውን ለውጥ ሳለመሰግን አላልፍም።
በአሰልጣኞች እና ተጫዋቾች መካከል እንደ ድልድይ ሆነህ ስትሠራ ትታያለህ። ያ እንዴት ሊሆን ቻለ?
በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። እኛ ከሁሉም በተለየ የንክኪ ባለሙያዎች ነን። Physio massage therapist እንደመሆኔ ተጫዋቾ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለኝ። ደስ ሲላቸውም ሲከፋቸውም የመጫወት ፍላጎታቸው ሲጨምር ሲቀንስ በግልፅ ያናግሩኛል። ይህ ደግሞ ያለባቸውን ችግር ይዘው ከሚቀመጡ ከአሰልጣኞቹ ጋር የሚያወሩበትን መንገድ እንከፍትላቸዋለን። ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ጋር ደግሞ ይበልጥ በመቀራረብ ለተጫዋቾች የታክቲክ እና ቴክኒክ መልክቶችን ሜዳ ውስጥ በምገባ ሰዓት አደርሳለሁ።
ለተጫዋቾች ህክምና የምታደርገው በምን ሰዓት ነው ?
የቡድን ወጌሻ ወይም የህክምና ባለሙያ ስትሆን ሙሉ ጊዜህ የተጫዋቾች ነው የሚሆነው። ለሊት ተጫዋች ሊታመም ይችላል። ያኔ የግዴታ ለተጫዋቾች መድረስ አለብህ። በአጠቃላይ ከተጫዋቾች አትርቅም።
የምታደንቀው ተጫዋች ማን ነው? ራሱን በመጠበቅ ደረጃ?
ሁሉንም ተጫዋቾች አደንቃለሁ፤ አከብራለሁ። አብዛኞቹም ራሳቸውን ይጠብቃሉ። የግድ አንድ ተጫዋች ጥራ ካልከኝ ለተምሳሌት ማቅረብ ካለብኝ ከዳሽን ቢራ ጀምሮ ለበርካታ ዓመታት በፋሲል ከነማ ጨምሮ አብሬው በመስራት ላይ የምገኘው ያሬድ ባየ ነው። እሱ አርዓያ መሆን የሚችል ተጫዋች ነው። ስርዓቱ፣ ከሜዳ ውጭ ራሱን የሚጠብቅበት መንገድ፣ ሜዳ ላይ ራሱን የሚጠብቅበት እና ስለ ጤናው አንባቢነቱ እንዲሁም ጠያቂነቱ በጣም ያስደንቀኛል። የያሬድ ባየ አድናቂ ነኝ።
በሥራህ በተለየ መንገድ ድጋፍ የሚያደርግልህ ሰው አለ ?
አዎ! ምንም ጥርጥር የለውም። ፋሲል ከነማ ክለብ ውስጥ በጣም ድጋፍ የሚያደርግልኝ ሀብታሙ ዘዋለ ነው። ከዚህ በፊት ነግሬህ ነበር ሀብታሙ የመረዳት እና የማስረዳት ችሎታው ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ክለቡ ላይ በጣም ድጋፍ የሚያደርግልን እሱ ነው። ለምሳሌ የተጎዳ ተጫዋች ተጎድቷል ያልተጎዳ ተጫዋች አልተጎዳም ብለህ የሙያ ግዴታህን ብትወጣም አንድ አንድ ሰው አይረዳህም። ይህንን ጉዳይ ግን በተገቢው መንገድ ተረድቶ ድጋፍ የሚያደርግልኝ ሀብታሙ ዘዋለ ነው። ከዚህ በላይ ስልጣን ቢሰጠው በአግባቡ መወጣት የሚችል የቡድን መሪ ነው። ከእንደሱ አይነት ሰው ጋር በመስራቴ ደስተኛ ነኝ። ላመሰግነውም እፈልጋለሁ ።
በመጨረሻ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ?
ለተጫዋቾች እንዲሁም ለሌሎች ባለሙያዎች ይጠቅማሉ ያልኳቸውን ልምዶቸን አካፍያለሁ። በመጨረሻ ማመስገን የምፈልጋቸው ሰዎችን ብጠቅስ ደስ ይለኛል። በመጀመሪያ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይገባል። በሥራዬ ጠንክሬ እንድገኝ ብርታት ለሆኑኝ ለፋሲል ከነማ ደጋፊዎች፣ ለቤተሰቦቼ፣ ከዚህ በፊትም አሁንም አብረውኝ ለሚሰሩ ኮቺንግ ስታፍ እና ደግሞ የተደበቁ ባለሙያዎችን እየፈለጋችሁ ለምታቀርቡት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ድምፅ ለሆናችሁ ለሶከር ኢትዮጵያዎችም ምስጋናዬን ማብቅብ እፈልጋለሁ።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!