ወልዋሎዎች አራት ተጫዋቾች አስፈረሙ

እስካሁን ድረስ የዝውውር እንቅስቃሴ ካልጀመሩ ክለቦች ውስጥ የነበሩት ቢጫ ለባሾቹ ወደ ዝውውር ገብተዋል።

አማካዩ ዳንኤል ደምሴ፣ የግራ መስመር ተከላካዩ አስናቀ ሞገስ፣ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዓወት ገብረሚካኤል እና ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ የቢጫ ለባሾቹ የመጀመርያ ፈራሚዎች በመሆን ቡድኑን በሁለት ዓመት ውል የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ባለፈው የውድድር ዓመት ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር ጥሩ ዓመት በማሳለፍ በጉዳት ካመለጡት ጨዋታዎች ውጭ የአሰልጣኙ ቀዳሚ ምርጫ የነበረው ዳንኤል ደምሴ ለክለቡ ጥሩ ፊርማ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ተጫዋቹ ከዚ በፊት በወልዲያ፣ አውሥኮድ እና ኢትዮጵያ ቡና መጫወቱ ይታወሳል።

ሁለተኛው ከመቐለ 70 እንደርታ ወደ ወልዋሎ ያመራው የግራ መስመር ተከላካዩ አስናቀ ሞገስ ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት ከሄኖክ ኢሳይያስ እና አንተነህ ገብረክርስቶስ ጋር በመፈራረቅ በቦታው የተሰለፈው አስናቀ ባፈለው ዓመት የቡድኑ ኮከብ የነበረው ሳሙኤል ዮሐንስ ትቶት የሄደውን ቦታ ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል።

ሦስተኛው ቡድኑን የተቀላቀለው ዐወት ገብረሚካኤል ነው። የቀድሞው የጅማ አባጅፋር እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመስመር ተከላካይ በስሑል ሽረ የተሰረዘውን የውድድር ዓመት ማሳለፉ ይታወሳል።

በተመሳሳይ በተሰረዘው የውድድር ዓመት በስሑል ሽረ ጥሩ ቆይታ የነበረው ወንድወሰን አሸናፊ ቢጫለባሾቹን የተቀላቀለ አራተኛው ተጫዋች ነው። የቀድሞው የወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ ዓምና በቦታው የነበረውን ክፍተት እንደሚደፍን ይጠበቃል።

ቀደም ብለው አዲስ ሥራ አስከያጅ የቀጠሩት እና በቅርቡም የቴክኒካል ዳይሬክተር እና ቡድን መሪ ይቀጥራሉ ተብለው የሚጠበቁት ወልዋሎዎች በቀጣይ ቀናትም በርከት ያሉ ተጫዋቾች ያስፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!