ከፍተኛ ሊግ | መከላከያ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈረመ

ዮሐንስ ሳህሌን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠሩት መከላከያዎች ሦስት ተጫዋቾች አስፈርመዋል፡፡

በከፍተኛ ሊጉ ተወዳዳሪ የሆኑት መከላከያዎች ከወራት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን በዋና አሰልጣኝነት፣ የቀድሞው ተጫዋች ዮርዳኖስ ዓባይን ረዳት አሰልጣኝ በማድረግ የቀጠረ ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚመልሰውን ጠንካራ ቡድን ለመገኖባት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህም መሠረት ጃፋር ደሊል፣ ገናናው ረጋሳ እና ልደቱ ለማን አስፈርሟል፡፡

ግብ ጠባቂው ጃፋር ደሊል የመጀመሪያው የመከላከያ ፈራሚ ነው፡፡ የአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ለወልዋሎ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በድጋሚ ከአሰልጣኙ ጋር በመከላከያ ተገናኝቷል፡፡

ሌላኛው ፈራሚ ገናናው ረጋሳ ነው፡፡ በአጥቂነት፣ አማካይነት እና ተከላካይነት የሚጫወተው ሁለገቡ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋች በድሬዳዋ ከተማ እና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ አብሮ ከሰራው አሰልጣኝ ጋር በድጋሚ የሚገናኝ ሁለተኛው ተጫዋች ሆኗል፡፡

የጦሩ ሦስተኛ ፈራሚ አጥቂው ልደቱ ለማ ነው፡፡ይህ የቀድሞው የባህር ዳር ከተማ እና ስሑል ሽረ አጥቂ በተሰረዘው የውድድር አመት በከፍተኛ ሊጉ በለገጣፎ ለገዳዲ መልካም ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስም የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን ሲመራ ቆይቷል።

ክለቡ በቀጣዮቹ ቀናትም ተጨማሪ ዝውውሮችን ለመፈጸም በሒደት ላይ ሲሆን በጊዜ ወደ ልምምድ ለመግባት ለተጫዋቾቹ ጥሪን አቅርቦ ወደ ካምፕ መግባት መጀመራቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!