አዳማ ከተማ በርካታ ተጫዋቾችን በሙከራ ተመልክቶ ሊያስፈርም ነው

የፋይናንስ ችግሮቹን ለመቅረፍ ከሰሞኑ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው አዳማ ከተማ ለማስፈረም የተስማማቸው ተጫዋቾችን ጨምሮ በቅርቡ በሙከራ ጨዋታ መልምሎ ለማስፈረም ተዘጋጅቷል፡፡

ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ብርቱ ተፎካካሪ ተብሎ ስማቸው ከፊት ከሚጠሩ ክለቦች መካከል የሆነው አዳማ ከተማ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በተጫዋቾቹ በተደጋጋሚ የደመወዝ አለመከፈል ጋር ተያይዞ ጥያቄ እየተነሳበት የቆየ ሲሆን በዚህ ችግር ውስጥም ሆኖ ሲጓዝ ቆይቶ የእግድ ውሳኔ እንደተላለፈበትም ይታወሳል። ከእግድ ውሳኔዎቹ ባሻገር ዕዳዎች የነበሩበት አዳማ ከተማ በጥንካሬው የመቀጠሉ ነገር አጠያያቂ የነበረ ቢሆንም በተሠሩ ሥራዎች ለ2013 የውድድር ዓመት በተለየ አቀራረብ ለመቅረብ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ የነበረበትን ቅሬታ ለመፍታት እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ሲሆን የተከሰሰባቸውን የተጫዋቾቹን ጥያቄ ለመፍታት እና ክፍያ ለመፈፀም በጀት መድቦ ጨደ ተግባር ስለመግባቱ ሰምተናል፡፡

ክለቡ ችግሮቹን ከፈታ በኃላ ለ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአነስተኛ የክፍያ ስርዓት ለመቅረብ ያሰበ ሲሆን በክረምቱ ከሀያ በላይ ተጫዋቾች በመልቀቃቸው ከከፍተኛ ሊጉ እና ከአንዳንድ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ከአርባ በላይ ተጫዋቾችን አምጥቷል፡፡ በርካታ የስፖርት ቤተሰብ ክለብ ቁጥራቸው ላቅ ያሉ ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ግርታን የፈጠረበት የነበረ ቢሆንም ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ከጥቂት ተጫዋቾች ውጪ በርካቶቹን የሙከራ ዕድል ሰጥቶ ለማስፈረም ማሰቡን ሰምተናል፡፡ ከአዲስ ፈራሚዎች አክሊሉ ተፈራ እና ታፈሰ ሰርካ፤ ከነባሮቹ ደግሞ ሚካኤል ጆርጅ፣ ዱላ ሙላቱ፣ ሱሌይማን መሐመድ እና በላይ ዓባይነህ የፈረሙ መሆናቸው ታውቋል።

ክለቡ በሙከራው ጥሩ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ከመለመለ በኃላ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት ለመግባት መሰናዳቱን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!