የሴቶች ገፅ | ባለ ክህሎቷ አማካይ ቅድስት ቦጋለ

በኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ውስጥ ድንቅ ክህሎት አላቸው ከሚባሉት መካከል ነች። ብዙሀኑ የስፖርት ቤተሰቦች በደደቢት ስትጫወት አውቀዋታል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማም ተጫውታ አልፋለች፡፡ ከ2012 ጀምሮ ደግሞ ለመቐለ 70 እንደርታ በመጫወት ላይ ትገኛለች፡፡በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በተደጋጋሚ ተጠርታ ሀገሯን አገልግላለች። ውብ እግር ኳስን የምትጫወተው አማካይዋ ቅድስት ቦጋለ የዛሬው የሴቶች ገፅ ዕነግዳችን ናት፡፡

ትውልድ እና ዕድገቷ እዚሁ አዲስ አበባ አባኮራን ተብሎ በሚጠራው ሠፈር ነው፡፡ በልጅነት ዕድሜዋ የደረጃ ተማሪ የነበረች በመሆኑ ቤተሰቦቿ ትምህርቷ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግን ፍላጎት ቢኖራቸውም እሷ ግን በምትማርበት ትምህርት ቤት መማር ብቻ ሳይሆን ከጓደኞቿ ጋር ሆና ኳስን መጫወት ጀመረች፡፡ ደበቅ እያለች በትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ እግር ኳስን መጫወት የጀመረችው እንስቷ ቀስ በቀስ በውስጧ የመጫወት ፍላጓቷ እያየለ ሲመጣ ሠፈር ውስጥም ይስሀቅ ወደሚባል ወንድም ሆኑ ሴት የመጫወት አቅሙ ያላቸውን ታዳጊዎች በፕሮጀክት ደረጃ በግሉ ሲያሰለጥን ወደነበረ አሰልጣኝ ጎራ እያለች መጫወቷን ቀጠለች፡፡

በትምህርት ቤት ሳለች የእግርኳሱ ጥልቅ ፍቅር ያየለባት የዛሬዋ ባለታሪካችን ቅድስት ቦጋለ በአሰልጣኝ ይስሀቅ ይመራ በነበረው አዲስ ፍሬ ፕሮጀክት ውስጥ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ለአንድ ዓመት ያህል ቆይታ አድርጋለች። ቅድስት ላቅ ያለ የመጫወት አቅምን ታሳይ ስለነበር የፕሮጀክት አሰልጣኟ ይህ አቅሟ መክኖ ከሚቀር በርካታ የሴት ቡድኖች ልምምድ እና ውድድር ወደሚከውኑበት ጃን ሜዳ ሄዳ አቅሟን እንድታሳይ መንገዱን ያመቻችላታል፡፡ እሷም መጫወት ከውስጥ የመነጨ ህልሟ ስለነበር ያለማመንታት ወደ ቦታው በመሄድ ዕድሜዋ ገና የነበረ በመሆኑ የአራዳ ጊዮርጊስ ዋናውን ቡድን ከመቀላቀሏ በፊት የሁለተኛ ቡድኑ አባል በመሆን ወዳሰብችበት ሐሕይወት መንደርደሯን ቀጠለች።

“በአራዳ ጊዮርጊስ የተወሰኑ ዓመታትን እዛው እየሰራሁ ነበር ግን በመሀል በቤተሰቦቼ እንዳልጫወት እከለከል ነበር፡፡ በትምህርቴ አሪፍ ስለነበርኩኝ እንዳልጫወት ፍላጓት ነበራቸው ፤ የእነሱን ቃል ለማክበር ብዬ በመሀል አቋረጥኩኝ ለሦስት ወር አካባቢ፡፡ እዛው አራዳ ጊዮርጊስ እያለሁ አብረሀም ተክለማርያም የሚባል አሰልጣኝ ነበር ፤ አሁን ጋዜጠኛ ነው። አራዳ ጊዮርጊስን ከነዓለማየሁ ጋር ሆኖ ያሰለጥን ስለነበር ቤት መከልከሌን ሰምቶ እንድጫወት ኃላፊነቱን በመውሰድ ወረቀት ፅፎ ፈርሞ ለቤተሰቦቼ ሰጣቸው። ምንም ችግር እንዳያጋጥመኝ በሚል ማህተም ያለው ወረቀት ተፅፎ ለቤተሰብ ተሰጠ። በዚህም እንደገና ተመልሼ እዛው ቡድን መጫወት ጀመርኩ” ስትል ስለገጠማት ፈተና እና በድጋሚ ተመልሳ የጨዋታውን ዓለም መቀላቀሏን አስታውሳናለች፡፡

ከዚህ በኋላ በአራዳ ጊዮርጊስ በአሰልጣኝ አስራት አባተ እና አብርሀም ተክለማርያም ስር ሥልጠናዋን ቀጠለች፡፡እግር ኳስን ከመጫወት በዘለለ እግር ኳስ ምን ማለት እንደሆነ በአራዳ ጊዮርጊስ ቆይታዋ በሚገባ ተምራ ማለፏን የምትገልፀው አማካዩዋ አሰልጣኝ አስራት አባተ ‘አይዞሽ በርቺ !’ በማለት ደካማ እና ጠንካራ ጎኗን እየነገራት የተሻለ ቦታ መድረስ እንደምትችልም እያሳመናት በእሷ አገላለፅ እግርኳስ ስራም ህይወትም መሆን እንደሚችል ተረዳች። በአራዳ ጊዮርጊስ አራት ዓመታትን ያሳለፈችው ተጫዋቿ 2004 ላይ ደደቢት ተመስርቶ አሰልጣኝ አስራት አባተም ቡድኑን በመረከቡ እና ጥቂት ተጫዋቾችን ይዞ ወደ ሰማያዊ ለባሾቹ ቤት ሲያመራ እሷም የዚህ አጋጣሚ ተጠቃሚ ሆነች።

ቅድስት ደደቢት ከገባች በኃላ ቤተሰቦቿም ፍላጎቷን በሚገባ በመረዳታቸው እሷን ወደማዳመጡ እና ሀሳቧን ወደማክበሩ ተሸጋገሩ፡፡ በደደቢት ቆይታዋ ለክለቧ ከምታደርገው እንቅስቃሴ ባሻገር ሜዳ ላይ ያላት የተለየ አቅም እና የምታሳየው ልዩ ክህሎት ይበልጥ እየጎላ መጥቶ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሲጀመር ከደደቢት ጋር ዋንጫውን በማንሳት ባለታሪክ ተጫዋች ለመሆን በቃች፡፡ “ትክክለኛ የእግርኳስ ህይወቴ የጀመረውም ብዙዎችም ያወቁኝ በደደቢት ቤት ነው፡፡ ወደ ክለቡ ስገባ በጣም ከእኔ የተሻሉ ሲኒየር ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ በደደቢት ገብቼ ስሰራ እግርኳስ በቃ ህይወት መሆኑን ያወኩበት በደመወዝም በምንም ነገር ያደግኩበት ቻምፒዮን እስከመሆንም የደርስንበት ነበር። እኔም በደንብ የታወኩበትም ጊዜ ነበር፡፡ ደደቢት ለእኔ ቤቴ ማለት ነው። ብሔራዊ ቡድንም ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠራሁበት ወቅት ነበር። ረጅም ጊዜን ለብሔራዊ ቡድን ስጠራ ደደቢት ውስጥ ሆኜ ነበር።”

በደደቢት ጊዜዋ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ተጠርታ ለተከታታይ ዓመታት መጫወት የቻለችው ቅድስት ሀገርን ወክሎ መጫወት የሚሰጠውን ስሜት እንዲህ ትገልፀዋለች። “ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ቡድን ስትጠራ ደስ ይልሀል። ሀገርህን ከመወከል አንፃር ማለት ነው፡፡ እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ስጠራ ደደቢት ውስጥ ሆኜ ነው። በተጠራሁበት ወቅት በጣም ሲኒየር የሚባሉ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ እኔ ስሄድ ልምዱን እንዳገኝ ነበር። በወቅቱ በእኔ ቦታ እነሠሚራ ከማል ፣ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ፣ ብርክታዊት ግርማ የመሳሰሉ ብዙ ጠንካራ ልጆች ነበሩ፡፡ ሆኖም ግን ለተከታታይ ጊዜ ብሔራዊ ቡድን ተጠርቻለው። ሠላም ዘርዓይ በቅርቡ ይዛው በነበረበት ወቅት ብቻ ነው ያልተጠራሁት እንጂ ለረጅም ጊዜ ተጠርቻለው። ግን ዕድሉን መስጠት አለመስጠት የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው፡፡እኔ በነበርኩበት ሰዓት ጠንካራ ስብስብ ነበር የነበረው ማለት እችላለው።” ትላለች።

በደደቢት አንድ ዓመት እየቀራት በ2008 ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያቀናችው ቅድስት በደደቢት ካሳለፈቻቸው ድንቅ ዓመታት በበለጠ መልኩ በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ስብስብ ውስጥ ታብባለች ተብሎ ቢጠበቅም የታሰበው ሳይሆን ቀርቷል። “ቀጥታ ከትልቅ ክለብ ወደ ትልቅ ክለብ ነው የሄድኩት። ተጫዋቾቹም አሰልጣኞችም ያው በብሔራዊ ቡድን ደረጃ አውቃቸው ነበር። ከደደቢት ትልቅ ስኬትን ይዤ ነበር የገባሁት። ግን የደደቢትን ያህል ጊዜ አልነበረኝም። ከራሴ ምጠብቀውን ነገር ለቡድኑ ማድረግ አልቻልኩም። የመጀመሪያ ተሰላፊ ነበርኩ። ግን እኔ ራሴን ከምጠብቀው አንፃር እንቅስቃሴዬ ልክ አልነበረም። የቡድኑ አጨዋወት መንገድ እና የእኔ የጨዋታ ባህሪ አንድ አልነበረም። አንዳንዴ የቡድኑ ስታይል እና የተጫዋቹ ስታይል ልዩነት ካለው ተፅዕኖ ይኖረዋል። ያም ሆኖ ግን መጥፎ ጊዜ አሳልፊያለው ብዬ አላስብም። እንደውም በተገላቢጦሽ ከደደቢት በተሻለ እግር ኳስ ትልቅ ስራ መሆኑን ፣ ትልቅ ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻልበትም ያወኩት ንግድ ባንክ ቤት ውስጥ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛውን ላመሰግን እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ከደደቢት ስወጣ ብዙ ነገር ነግሮኝ ንግድ ባንክ ቤቴ እንደሆነ አሳምኖኝ ነው ወደ ክለቡ የሄድኩት። በአጠቃላይ በሥልጠናውም ሆነ በፋይናንስ ረገድ ከባንክ ስትወጣ ራሱ ተለውጠህ ትወጣለህ። ብርሀኑም ተጫዋቾች እንዲለወጡ ይፈልጋል። ከዚህ ከዚህ አንፃር መጥፎ ጊዜ አሳልፌያለሁ ብዬ አላስብም። “በማለት ስለ ንግድባንክ ቆይታዋ ያላትን እይታ ታስቀምጣለች።

2009 ላይ ባንክን የለቀቀችው ቅድስት አዲስ አበባ ከተማን ተቀላቅላ በዛም የአንድ ዓመት ቆይታ አድርጋለች። 2010 ላይ በነበራት ድንቅ የውድድር ዓመት መነሻነትም በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ስር ዳግም ወደ ንግድ ባንክ ተመልሳ ለሁለተኛ ጊዜ ከተጫወተች በኃላ ለሁለተኛ ጊዜ ለአዲስ አበባ ከተማ ፈርማ በመጫወት ጥሩ ጊዜን አሳልፋ ከ2012 ጀምሮ ደግሞ ወደ መቐለ ተጉዛ የአሰልጣኝ ህይወት ዓረፋዓይኔውን ክለብ በማገልገል ላይ ትገኛለች። ለሁለተኛ ጊዜ በመቐለ ቆይታን ለማድረግ ውሏን ያደሰችው ቅድስት እግር ኳስን ለመጫወት አንድ ሴት ልጅ ነፃነት ያስፈልጋታል እኔም ነፃነትን ቀዳሚ ምርጫዬ አድርጌ ነው የምወስደው ትላለች። “እኔ እግርኳስን ስጫወት ጥቅማጥቅሞች እንዳሉ ሆነው ግን ለእኔ ትልቁ መስፈርቴ ነፃነት ነው፡፡ ነፃነት ስልህ እኔ አሁን ባለኝ ነገር የተሻለ ቡድን መጫወት እችላለው፡፡ ስጫወት ግን ነፃነትን እፈልጋለሁ። ሀሳብ ሼር እየተደራረክ እየተግባባህ መጫወትን እፈልጋለሁ። ያን ያህል ጥቅም ብዬ አስቤ አላውቅም። አዕምሮዬ ነፃ ሆኖ እንደ ሁለተኛ ሥራ ነው የማስበው። እንደ ሁለተኛ ሥራ ስል ሴት ልጅ ስትሆን እግርኳስን ሁሌ አትጫወትም እና ግን አዕምሮህ ፍሬሽ መሆን አለበት። ከስፖርቱ ላለመራቅ በአቅም ደረጃ በጣም አቅም አለኝ ብዬ ነው የማስበው፤ ገና ምንም ያልተነካ። ከብሔራዊ ቡድን ከራኩም የተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ደግሞ ተመልሼ እመጣለው። ምክንያቱም ሀገር ውስጥ ክህሎት አላቸው ከሚባሉ ጥቂት ተጫዋቾች አንዷ ነኝ። ይሄን የምልህ እናንተም የምታዩት ነገር ስለሆነም ማለቴ ነው፡፡ እና ወደፊት ተመልሼ ሀገሬን በደንብ አገለግላለው።”

በመቐለ 70 እንደርታ ለመቀጠል የተስማማችው ቅድስት በተሻለ አቅም የተሻለው ቦታ ላይ ለመድረስ ታትራ እንደምትሠራ ገልፃ ቀጣይ ዕቅዷን እንዲህ ታስረዳለች። “እኔ እግር ኳስን በጣም እወዳለሁ። አሁንም ስጫወትም ትርጉም አልባ ለሆነ ነገር አይደለም። አሁን እየተጫወትኩኝ ዋነኛው ዓለማዬ ወደ ብሔራዊ ቡድን መመለስ ነው፡፡ከዛ በኃላ ደግሞ ከሀገር ወጥቼ ብጫወት ደስ ይለኛል፤ ለዚህም ብዙ ሕልም አለኝ። ዋናው ነገር ጠንክሮ መስራት ነው፡፡ የመጀመሪያው ዓላማዬ ግን ወደ ብሔራዊ ቡድን መመለስ ነው። በምፈልገው ደረጃ ሀገሬን አገልግያለው ብዬ ባላስብም በቀጣይ የተሻለ ነገር እሰራለው የሚል ዕምነት አለኝ።”

“የክለብ አመራሮች አሰልጣኞችን ሲቀጥሩ ዕውቀት ላይ ቢያተኩሩ የሴቶች እግርኳስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማደግ ይችላል ብዬ አስባለው። እዚህ ሀገር ላይ ጥሩ ጥሩ አሰልጣኞች አሉ። ግን ክለቦች ሲቀጥሩ ዝም ብለው ባይቀጥሩ በዕውቀት የጎለበቱ ፣ ለሴቶች ትኩረት የሚሰጡ ፣ በእግርኳሱ ልምድ ያላቸው ቢሆኑ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ። በጣም የለፉ እና የተረሱ አሰልጣኞች አሉ። ብቻ ሴቶችን በደንብ የሚያውቁ ከሆኑ የሴቶች እግር ኳስ በአጭር ጊዜ ያድጋል።” የምትለው ቅድስት እዚህ ለመድረሷ ምክንያት የሆኗትን ሰዎች በማመስገን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የነበራትን ቆይታ አጠቃላለች።

” እዚህ ላለሁበት ደረጃ እንድደርስ ያደረገኝ አሰልጣኝ አስራት አባተ ነው፡፡ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ተጫዋቾች ተምሳሌት ነው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ እሱን ነው ማመስገን የምፈልገው፡፡ በመቀጠል ደግሞ አሁን ያለሁበት ክለብ አሰልጣኝ ህይወት ዓረፋዓይኔ በጣም አመሰግናታለው። ከምነግርህ በላይ የወደፊቱ ጎበዝ አሰልጣኝ ትሆናለች ብዬ ከማስባቸው አንዷ ናት። እኔ አሁን አንድ ዓመት ብቻ ነው ከእርሷ ጋር የሰራሁት። በክለቡ ልቆይም የቻልኩት አሰልጣኟ በጣም ጠንካራ ስለሆነች ነው። ሦስተኛ ደግሞ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛውን በጣም አመሰግነዋለው። ከደደቢት ስወጣ የተወሰኑ ቻሌንጆች ነበሩ፡፡ ወደ ንግድ ባንክ ስሄድ ውሌን ጨርሼ አልነበረም የሄድኩት። ከኃላፊዎቹ ጋር ትንሽ ያለመስማማት ነገሮች ነበሩ። ያንን ተቀብሎ ምንም ችግር እንደሌለ አድርጎ በሀሳብም በምክርም አግዞኝ በጥሩ ሞራል የመራኝ እሱ ነው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!