ከቀናት በፊት መከላከያን የተቀላቀለችው አጥቂዋ ሥራ ይርዳው የዛሬው የሴቶች ገፅ ዕንግዳችን ናት።
ትውልድ እና ዕድገቷ በባህር ዳር ከተማ ነው። እግርኳስን ከወንዶች ጋር በትውልድ መንደሯ በመጫወት ጀምራ በኃላም በፕሮጀክት ታቅፋ የልጅነት ህልሟን የማሳካት ጉዞ እንደጀመረች የምትናገረው አጥቂዋ ሥራ ይርዳው ከመንደሯ የጀመረው ህልሟ እያደገ መጥቶ ባህር ዳር ከተማን እንዲሁም አማራ ክልልን በመወከል መጫወት ችላለች፡፡ አማራ ክልልን ወክላ አዳማ ላይ በነበረ ሀገር ዓቀፍ ውድድር ላይ ጥሩ አቅም ማሳየት በመቻሏም ለኢትዮጵያ ቡና ተመርጣ የክለብ ሕይወትን ጀምራለች።
ከትምህርቷ ጎን ለጎን ትልቅ ተስፋን ሰንቃ የተነሳችው አጥቂዋ ከቤተሰቦቿ የሚደረግላት ጠንካራ ድጋፍ ያልተቋረጠ በመሆኑ እና ከጊዜ ወደ መሻሻልን በማሳየት 2010 ላይ ወደ ድሬዳዋ አምርታለች። በድሬዳዋ ካሳየችው እንቅስቃሴ አንፃር የብዙሀኑን ስፖርት ቤተሰብ ትኩረት የሳበችው አጥቂዋ ውሏ በዎመጠናቀቁን ተከትሎ በበርካታ ክለቦች ብትፈለግም በስተመጨረሻ ከቀናቶች በፊት መከላከያን በይፋ መቀላቀል ችላለች። ተስፋ ከተጣለባት ከዚህች አጥቂ ጋር ቀጣዩን ቆያታ አድርገናል።
በርካታ ክለቦች ቢፈልጉሽም አንቺ ግን መከላከያን መርጠሻል። የተለየ ምክንያት ነበረሽ ?
በመጀመሪያም ከልጅነቴም ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡናም ከገባሁ ጀምሮ መከላከያን እወደው ነበር። የክለቡን መለያ ለመልበስ ፍላጎቱም ያደረብኝ ከድሮም ነው። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ጥያቄ ነበር፣ አዳማም ይፈልገኝ ነበር። በኃላ ግን ወደ መከላከያ መጣሁ። ሌሎች ተጨማሪ ክለቦች ቢኖሩም ስሙንም ሆነ ክለቡን ስለምወደው መከላከያን መርጫለሁ።
ዛሬ ላይ እግርኳስ ተጫዋች ለመሆንሽ አርዓያ የሆነሽ ማነው ?
ሲኒየር የሚባሉ ተጫዋቾችን አይቼ አላደግኩም። ሠፈር ላይም በምንጫወት ጊዜ ሴት ተጫዋቾች አልነበሩም ፤ ከወንዶች ጋር ነበር ስጫወት ያደግኩት። በውጪዎቹ ስለ እነሜሲ ሲወራ ከመስማት ውጪ በኢትዮጵያ አርዓያ የማደርገው ተጫዋች አልነበረም።
የእግርኳስ ውድድሮች በኮቪድ 19 ተቋርጠው ረጅም ወራት ተቆጥረው ነበር ፤ ጊዜውን እንዴት አሳለፍሽው ?
ከቤት አትውጡ በተባለበት ጊዜ ኳስ እና የልምምድ ማቴሪያሎችን በፕሮጀክት አሰልጣኛችን በኩል አገኘው እና ቤት መስራት ጀመርኩ። መውጣት ሲጀመርም ለቤተሰብ ከማሰብም የተነሳ የመውጣት ዕድሉ ቢኖረኝም አልወጣሁም። ቤት ውስጥ ነበር ስሰራ የነበረው። ቤተሰቦቼም ያበረታቱኝ ነበር፡፡ በብዛት ኢትዮጵያ ውስጥ ሴቶች ላይ ቤተሰብ ተፅዕኖ ይፈጥራል ይባላል። እኔ ላይ ደግሞ ምንም ነገሮች አልነበሩም። ከልጅነቴ ጀምሮም ተፅዕኖ በእኔ ቤተሰብ ዘንድ አላደረሰብኝም። ጊዜውንም በጥሩ አሳልፌዋለው።
ኮቪድ ከገባ በኃላ የለመድሽው አዲስ ነገር ይኖራል ?
አዎ ፤ ቤት ውስጥ ብዙ ማየት ያለብኝን ነገር የማይበት ጊዜ ነበር። በፊት ሜዳ ሜዳ ነበር የምለው ፤ ብዙ ቁጭም አልልም ነበር። አሁን ቤተሰቦቼ ሲሰሩ ሳይ ከምግብ አዘገጃጀት እና ከቤት ፅዳት ጀምሮ ብዙ ብዙ ነገሮችን ተምርያለው።
ሥራ በግሏ ጥሩ ዓመት ያሳለፈችው መች ነበር ?
ያው ኮሮና አቋረጠው እንጂ 2012 ጥሩ ነበርኩ። ፈጣሪ ይመስገን አሪፍ ዓመት ነበር፡፡ እኔ ግን ተከፍቼበታለሁ ብዬ የማስብበት ጊዜ የለም። በሁሉም አመታት የማሳልፋቸው ጊዜዎች በሙሉ ለእኔ የተሳኩ ናቸው፡፡ ይህን ስል ከዓመት ዓመት መሻሻልን የማይበት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን ዓመት ብዬ መለየት ይከብደኛል። ሁሉም ዓመት ለእኔ ደስ የሚል ነበር፡፡
ዛሬ ላይ እግርኳስ ተጫዋች ባትሆኚ ኖሮ በምን ሙያ ላይ እናገኝሽ ነበር ?
(እየሳቀች) ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ አስቤው አላውቅም። ከልጅነቴ ጀምሮ የመጣ ነገር ነውና ምንም አልሆንም ብዬ ነው የማስበው። ትምህርት እማራለሁ በዛው እዘልቃለሁ አልዘልቅም ፈጣሪ ነው የሚያውቀው። ምናልባት አይ ሲ ኤስ ነበር ስማር የነበረው እና በኤሌክትሮኒክ ኮንትሮል ሰርቪስ ምናልባት ጥገና ነገሮችን እሞክራለሁ። እና ምናልባት እሱን እሆን ነበር ግን ከባድ ነው፡፡
አብረሻት በጣምራ መጫወት የምትፈልጊያት ተጫዋች ?
ባንክ ቤት ካሉት ሽታዬን በጣም እወዳታለሁ። ከእርሷ ጋርም አብሬ የመጫወት ዕድሉ ቢኖረኝ ደስ ይለኛል። ብርቱካን ገብረክርስቶስንም እወዳታለሁ። ከሁለቱም ጋር ብጫወት እጅግ ደስ ይለኛል፡፡
ስትገጥሚያት የምትከብድሽ ተጫዋች አለች ?
የለችም ፤ ምንም የምትከብደኝ ተጫዋች የለችም።
በዚህ ሰዓት በሀገራችን ከሚገኙ ተጫዋቾች ያንቺ ምርጧ ተጫዋች ማነች ?
ውጤታማነቷ እና በራስ መተማመኗን የማደንቅላት ሎዛ አበራን ነው፡፡ አቅም ያላት ተጫዋች ነች። አቅሟን እንድታወጣ ያደረጋት ደግሞ ልቧ ላይ ያላት ጥንካሬ ነው። ወይንም ከሌሎቹ ተጫዋቾች ለየት የሚያደርጋት ነገር በቃ ይቻላል ካለች የማይቻል ነገር የለም ብላ ስለምታስብ ነው። ብዙ ተጫዋች አሉ። ለእኔ ግን እሷ አንበሳ ናት። በቃ ድፍረቷን የልብ ጥንካሬዋን እወደዋለው። በዚህ የተነሳ በጣም ምርጧ ናት ለእኔ፡፡
በእግርኳሱ በጣም የተደሰትሽበት ወቅት መቼ ነበር ?
ብዙ አጋጣሚዎች አሉ ውጤት ሲመጣ ከማሸነፍ እና ከመሸነፍ ጋር የምታያቸው ነገሮች አሉ። በጣም በጣም ተደሰትኩ የምልበት ነገር የለም። ግን ኖርማል ደስታ ሁሌም በውስጤ አለ፡፡
በእግርኳሱ ካሉ ግለሰቦች ለአንቺ ቅርብ የሆነችሽ ማናች ?
ሁሉም ጓደኞቼ ናቸው። በቡድን ውስጥ ለይቼ የማያቸው የሉም። ማለት አሁን ድሬዳዋ በነበርኩበት ሰዓት በጣም እንድሰራ የምትመክረኝ ብዙሀን እንዳለ ነበረች። በእርግጥ ሌሎቹ ግን በጓደኝነት ደረጃ ነው እንጂ ሚስጥር በማወቅም ሆነ በሌላ ነገር የማማክረው የለም። ቡድኑ ውስጥ ያሉ ግን ሁሉም ጓደኞቼ ናቸው፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ስለ ግል ባህሪሽ አጫውቺኝ ምን የተለየ ባህሪ አለሽ ?
የተለየ ባህሪ የለኝም። ሁሉም በሚያውቀኝ ባህሪ ልክ ነው ያለውት። ጓደኞቼ የሆኑ ሰዎች እኔን ያውቁኛል። ከዛ ውጪ ግን ለይቼ የምጠራው ባህሪ የለኝም፡፡
የግል ህይወትሽ ምን ይመስላል ?
ከቤተሰቦቼ ጋር ነው የምኖረው።
በመጨረሻም ከእግርኳሱ ውጪ ባሉት ቀናት ጊዜሽን በምን ታሳልፊያለሽ ?
ፕሌይ ስቴሽን መጫወት እወዳለው ፤ ያዝናናኛል። የውጪ ኳሶችንም አያለሁ። እነኚህን አዘወትራለው፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!