ጅማ አባጅፋር በዚህ ሳምንት አዲስ አሰልጣኝ በመሾም የ2013 ዝግጅቱን ይጀምራል፡፡
በተደጋጋሚ ከተጫዋቾች ደመወዝ ካለ መከፈል ጋር በተያያዘ ጥያቄዎች እየተሰነዘሩበት ያሳለፈው የ2010 የፕሪምየር ሊጉ ቻምፒዮን ጅማ አባጅፋር ለ2013 የውድድር ዘመን ከሌሎች ክለቦች ዘግይቶም ቢሆን ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት ቅድመ ሥራዎችን መከወን ጀምሯል፡፡ በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው መሪነት 2012ን ውድድሩ እስተቋረጠበት ጊዜ ድረስ የዘለቀው ክለቡ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱበትን የደመወዝ ጥያቄ ለመፍታት እና በተሻለ አቅም ፕሪምየር ሊግ ላይ ጠንክሮ ለመቅረብ ክለቡ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጀምር የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አጃይብ አባሜጫ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ አቶ አጃይብ በቅድሚያ ክለቡን በገንዘብ ለማጠናከር እየሰሩ እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን በመቀጠልም በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወደ ሥራ እንደሚገቡም በተከታዩ ሀሳባቸው ገልፀዋል፡፡
“እንቅስቃሴ ጀምረናል በዚህ ሳምንት መጨረሻ አሰልጣኝ እናሳውቃለን። አንዳንድ ተጫዋቾችንም ለማስፈረም እያናገርን ነው፡፡ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለሁሉም ነገር ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን የሚል እምነት አለን፡፡ ለክለቡ አዲስ የበላይ ጠባቂ ተሹሟል። የእነሱም ተነሳሽነት በጣም ጥሩ ነው፡፡ የበፊቱ ችግር የፋይናንስ ስለሆነ ይሄን ለመቅረፍ ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ኮሚቴ ተዋቅሯል፤ ባለሀብቶቹንም እናወያያለን። የተለያዩ ስፖንሰሮችንም በማፈላለግ ወደ ስራ የገባንበት ወቅት ነው። ክለቡን የመታደግ ስራዎችን ጀምረናል። ያሉብን ዕዳዎችንም በአጭር ጊዜ ለመፈፀም ተዘጋጅተናል።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!