የዋልያዎቹን ዝግጅት በተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የዝግጅት ጊዜ እና ከዛምቢያ ጋር የሚደረገውን የወዳጅነት ጨዋታ በተመለከተ ዛሬ ከሰዓት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎቹን እያደረገ ይገኛል። ብሔራዊ ቡድኑ የምድቡ 1ኛ እና 2ኛ ጨዋታውንም አከናውኖ ሦስት ነጥቦችን በመያዝ የምድቡ 2ኛ ደረጃን ይዟል። በህዳር ወር የመጀመሪያ ቀናትም የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታውን ከኒጀር አቻው ጋር ኒያሚ እና ባህር ዳር ላይ ለመጫወት ዝግጅቱን በካፍ የልህዕቀት ማኅከል እያከናወነ ይገኛል።

ለ41 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ መስከረም 25 የዝግጅት ጊዜውን የጀመረው ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ከሰዓት በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ አማካኝነት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። አሰልጣኙም የዝግጅት ጊዜያቸውን በተመለከተ አጠር ያለ ገለፃ በስፍራው ለተገኙ ብዙሃን መገናኛ አባላት በማድረግ መግለጫቸውን ጀምረዋል።

“ለ41 ተጫዋቾች ጥሪ ብናደርግም ልምምዳችንን የጀመርነው 38 ተጫዋቾችን በመያዝ ነው። ከእነዚህ ተጫዋቾች ውስጥ ደግሞ የተወሰኑትን በኮቪድ-19 ምክንያት አጥተን ነበር። በዚህም በቅድሚያ ባቀድነው መንገድ አልነበረም ስንዘጋጅ የነበረው። ዛሬን ጨምሮ ባለፉት አራት ቀናት ግን በቫይረሱ ያጣናቸው ተጫዋቾች ተቀላቅለውን ልምምዳችንን በጋራ እየሰራን እንገኛለን። ከተጠሩት ተጫዋቾች ውስጥ ደግሞ ሽመልስ በቀለ እና መስፍን ታፈሰ ከሃገር ውጪ በመሆናቸው ስብስቡን አልተቀላቀሉም። ባዬ ገዛኸኝ ደግሞ ጉዳት ላይ ስለነበር አልተቀላቀለንም። ከእነሱ ውጪ ልምምዳቸውን ሲከውኑ የነበሩት አህመድ ረሺድ እና ዳዊት እስቲፋኖስ ጉዳት በማስተናገዳቸው ከእኛ ተለይተዋል።

“እውነት ለመናገር እንደተፈራው እና እንደተገመተው የተጫዋቾቻችን አቋም ወርዶ አላገኘሁትም። ያለ እንቅስቃሴ 7 ወር ቢቀመጡም በተናጥል ራሳቸውን ሲጠብቁ እንደነበር ያስታውቃል። በጣም ከተጫዋች አቋም የወጣ አልነበረም። ለዚህም ደግሞ ተጫዋቾቹን ማመስገን ያስፈልጋል። እንደመጡም የተለያዩ መስፈርቶችን ተከትለን ያሉበተን ነገር ለመለካት ሞክረናል። የአካል ብቃት ባለሙያችንም በቴክኖሎጂ የታገዙ ልኬቶችን ሲያደርጉ ነበር። ግን በአጠቃላይ እንደተፈራው ተጫዋቾቻችን ከአቋም ወጥተው አልመጡም።

“አሁን የገጠመን አዲስ ነገር ነው። ያለ እንቅስቃሴ እንደዚህ ቆይተን አናቅም። ለዚህም ደግሞ ስብስባችንን ሰፋ አድርገን 41 ተጫዋቾችን ጠርተናል። በየመጫወቻ ቦታው በርከት ያሉ ተጫዋቾችን መርጠናል። ምክንያቱም ተጫዋቾቹ ያሉበትን ነገር ስለማናውቅ እና በየቦታው ጥሩ አማራጭ ለማግኘት ነው በርከት ያለ ስብስብ የጠራነው።”

መሰከረም 18 የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ሆነው በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ የተሾሙት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የዝግጅት ጊዜያቸውን በተመለከተ ገለፃ ካደረጉ በኋላ ነገ እና እሁድ ስለሚደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ተከታዩን ሃሳብ ሰጥተዋል።

“የተጫዋቾችን አቋም ለመለካት የአቋም መለኪያ ጨዋታ አዘጋጅተናል። በነገው እና በእሁዱ የዛምቢያ የወዳጅነት ጨዋታ ሁሉም ተጫዋቾች ተሳታፊ ይሆናሉ። የመጨረሻ ተጫዋቾችንም የምንለየው ከእነዚህ የወዳጅነት ጨዋታዎች በኋላ ነው። በልምምድ ብቻ ተጫዋቾችን ከመቀነስ በአቋም መለኪያ ጨዋታ ተጫዋቾቸን አይቶ መቀነስ ጥሩ ነው። ስለዚህ በልምምድ ካየነው የተጫዋቾቹ አቋም በተጨማሪ ቡድኑን ለሁለት ከፍለን በጨዋታዎቹ የሚታየውን ነገር እንመለከታለን።”

ለአስር ቀናት በካፍ የልህዕቀት ማኅከል ልምምዱን ከከወነ በኋላ ወደ ባህር ዳር ተጉዞ ልምምዱን ይቀጥላል ተብሎ ሲነገር የነበረው ብሔራዊ ቡድኑ ከወቅታዊው የኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ስጋቶች እንዳይኖሩ ጉዞውን እንደተሰረዘ እና ከኒያሚ መልስ ብቻ ጨዋታውን ለመከወን ወደ ባህር ዳር ጉ እንደሚጓዝ ተጠቁሟል። መግለጫውን የሰጡት አሠልጣኙ ጨምረውም ስለ ቀጣይ ተጋጣሚያቸው ኒጀር ተከታዩን ብለዋል።

“ኒጀር ያደረገውን ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ሙሉ ምስል አልተመለከትንም። ምስሉን ስላላገኘን ነው እንጂ ሳንፈልግ ቀርቶ አደለም። ግን በቪዲዮ ትንተና ከሚያግዘን ኤልሻዳይ ጋር በመተባበር ምስሉን ለማግኘት እየጣርን ነው። ኒጀር ከወዳጅነት ጨዋታዎቹ በፊት በምድብ ጨዋታ ያደረገውን እንቅስቃሴ ግን ተመልክተናል። ያንን ጨዋታ ከአሁኑ የወዳጅነት ጨዋታ ጋር ስናነፃፅረው ግን ብዙ ልዩነቶች አሉት። ቡድኑም ከ40 በመቶ በላይ የተጫዋቾች ለውጥ አድርጓል። እንደምታቁትም የአሰልጣኝ ለውጥ አድርገዋል። ስለዚህ በእነዛ የምድብ ጨዋታ ብቻ የእነሱን ብቃት አንገመግምም።”

አሠልጣኙ በመጨረሻም ከወንድማቸው እና ከብሔራዊ ቡድኑ ማኔጀር አቶ እንዳለየሱስ አባተ ጋር የተፈጠረውን ነገር በአጭሩ አስረድተዋል።

“ስለዚህ ጉዳይ ምንም ባልል ደስ ይለኛል። ግን ጉዳዩ የእንዳለየሱስ እና የፌዴሬሽኑ ነው። ወንድሜ ስለሆነ አደለም። እኔንም የሚመለከተው በደብዳቤው ላይ ስሜ መጠቀሱ ነው። በዚህም ደግሞ ደስተኛ አደለሁም። ስሜም በደብዳቤው መገለፁ ትክክል እንዳልሆነ ለፌዴሬሽኑ ገልጬላቸዋለሁ።”

በስተመጨረሻም ቡድኑ እስካሁን አምበል እንዳልመረጠ እና በቀጣይ የመጨረሻ ተጫዋቾቹ ለተይተው ሲታወቁ ልምድ ያለውና ተጨዋቾችን በማነሳሳት የሚታወቅ ተጫዋች ከተጫዋቾቹ ጋር በመነጋገር እንደሚመረጥ ተጠቁሟል።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!