አሰልጣኝ ብርሃኔ ገብረእግዚአብሔር የት ይገኛሉ?

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለረጅም ዓመታት ካሰለጠኑ አንጋፋ አሰልጣኞች መካከል ስማቸው ይጠራል። በአሰልጣኝነት ጊዜያቸው ኪራይ ቤቶች፣ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ ኢትዮጵያ መድን፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ እና ወሎ ኮምቦልቻን አሰልጥነዋል። በ2009 ወልዋሎን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳለፉበት ድላቸው ትልቁ ነው። በ2010 ከወሎ ኮምቦልቻ ጋር ከተለያዩ በኃላ ከአሰልጣኝነት ርቀው የሚገኙት አሰልጣኙ ከሞያው ስለራቁበት ምክንያት እና አሁን ስለሚገኙበት ሁኔታ አጭር ቆይታ አድርገዋል።

በምን ሁኔታ ይገኛሉ ?

በአሁን ሰዓት የግል ሥራ በመስራት ላይ ነኝ። ወሎ ኮምቦልቻን ካሰለጠንኩ በኃላ ላለፉት ዓመታት ከአሰልጣኝነት ርቅያለው። ከዛ በኃላም ትኩረቴን በግል ሥራዎች በማድረግ ጊዜዬን እያሳለፍኩ ነው። በአሁን ሰዓት በግል ሥራ ላይ ነኝ።

ከአሰልጣኝነት የራቁበት ምክንያት

ምክንያቱ ብዙ ነው፤ በሀገራችን ያለው ወቅታዊ ሁኔታም አንዱ ምክንያት ነው። ከዛ ውጭ እንቅስቃሴ ከማድረግ አልተቆጠብኩም። ግን እኔ በቤተሰብ ምክንያት ከአዲስ አበባ ርቄ ማሰልጠን አልፈለግኩም ነበር። አንዳንድ አጋጣሚዎችም ነበሩ። ግን መጀመርያ ሥራውን ፣ የክለቡን ሁኔታ መውደድ አለብኝ። ዝም ብዬ አጋጣሚውን ስላገኘሁ እሺ ማለት አልችልም። መጨረሻ ላይም አጋጣሚዎች ነበሩ። በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት አልተሳኩም እንጂ።

ቀጣይ እቅድ

በቀጣይ ወደ አሰልጣኝነት ለመመለስ አስብያለው። ከኢትዮጵያ መድን፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ወልዲያ እና ዲላ ከተማ ጋር በንግግር ነኝ። በቅርቡም ከአንዱ ክለብ ጋር ወደ አሰልጣኝነቱ እመለሳለው።

ስለ መጨረሻ ያሰለጠናቸው ክለቦች አጭር ቆይታ

ለበርካታ ዓመታት ነው ያሰለጠንኩት። በእግር ኳስ የረጅም ዓመት ልምድ ነው ያለኝ። በመጨረሻዎቹ ክለቦቼም ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። መቐለ 70 እንደርታን የዞኑ ቻምፒዮን አድርጌ ጥሩ ቡድን ሰርቼ ነበር፤ ማጠቃለያ ውድድር ላይ ባይሳካልንም። ከዛ በኃላ ደግሞ በወልዋሎ ድንቅ ዓመት አሳልፈን ቡድኑን ወደ ፕሪምየር ሊጉ አሳልፈናል። በመጀመርያው ዓመት የሊጉ ቆይታችንም እስከ አምስተኛው ሳምንት ሊጉም መምራት ችለን ነበር። ሆኖም ብዙ መሰናክሎች ነበሩ። አንዳንድ ግለሰቦች እንቅፋት ሆነው ነበር። በዛ ምክንያት ከክለቡ ጋር ብለያይም ለክለቡ እና ለደጋፊው ልዩ ፍቅር አለኝ። በወሎ ኮምቦልቻም ጥሩ ቡድን ገንብቼ ነበር። በወጣቶች የተገነባ ቡድን ነበር። ክለቡም ደጋፊውም ከጎኔ ነበር። ከዛ በኃላ ግን በአንዳንድ ምክንያቶች ለመለያየት ችያለው።

በመጨረሻ ..

መጨረሻ ላይ ማለት የምፈልገው ሃገራችን ሰላም ይሁንልን። ወረርሺኙ ጠፍቶ ወደምንወደው እግርኳስ ለመመለስ ይብቃን።

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!