ዋልያዎቹ በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ አዲስ አበባ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአዲሱ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቹ እየተመራ በአዲስ አበባ በሚገኘው የካፍ አካዳሚ መስራት ከጀመረ አስራ ሦስት ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ቡድኑ ያለፉትን ቀናት አብዛኛዎቹን የልምምድ መርሀ ግብሮች የተጫዋቾቹን የአቅም ደረጃ ለመመለስ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ የነበረ ሲሆን በዚህ ሳምንት ደግሞ ቴክኒካዊ ስራዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከተጠሩት አርባ አንድ ተጫዋቾች መካከል አምስቱ በኮቪድ 19 መያዛቸው ባዬ ገዛኸኝ በህመም አስቀድሞ ስብስቡን ያልተቀላቀለ ሲሆን ከሀገር ውጪ ያሉት ሽመልስ በቀለ እና መስፍን ታፈሰም እስከ አሁን ቡድኑን መቀላቀል አልቻሉም፡፡
ቡድኑ በያዝነው ጥቅምት ወር መጨረሻ የኒጀር አቻውን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሦስተኛ መርሀግብሩን ከመከወኑ በፊት የወዳጅነት ጨዋታን በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ ለማድረግ መዘጋጀቱን አቶ ባህሩ ጥላሁን የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በአቶ ኢሳይያስ ጅራ ጥረት የተገኘው ይህ ጨዋታ ከዛምቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚደረግም ጨምረው ነግረውናል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ቀናት ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅትን በተመለከተ በስፍራው በመገኘት አዳዲስ እና ሰፋ ያሉ መረጃዎችን ወደናንተ የምታቀርብ ይሆናል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!