በሁለቱም እግሩ ይጫወታል፤ በተጫወተባቸው ክለቦች ሁሉ ምርጡን አቋሙን አሳይቷል። የሜዳውን መስመር አልፎ ከገባ መሸነፍ የማይወድ ጀግና ተጫዋች እንደነበር ይነገርለታል። በዘጠናዎቹ ከታዩ ኮከቦች መካከል ጌታቸው ካሣ (ቡቡ) ማነው ?
ቄራ ቀበሌ ዘጠኝ አልማዝዬ ሜዳ ከፈጠረቻቸው ድንቅ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በልጅነቱ ትልቅ ተጫዋች እሆናለው ብሎ ሳያስብ ከሠፈሩ ልጆች ጋር እግርኳስን መጫወት ጀምሯል። ታዲያ በሚጫወትባቸው ሜዳዎች ሁሉ በሚያደርገው እንቅስቃሴ አብረውት ከሚጫወቱ ልጆች ሁሉ እርሱ የተለየ ክህሎት ስለነበረው ይህን ያዩ የአካባቢው ሰዎች “ይሄ ልጅ ክለብ አግኝቶ መጫወት ከቻለ ነገ ትልቅ ተጫዋች ይሆናል” በማለት ያወሩለት ነበር። በመብራት ኃይል መስሪያ ቤት በመካኒክነት ተቀጥሮ ይሰራ ነበረው የአክስቱ ልጅ ሰይፈም ሲጫወት አይቶት በጣም ከመገረሙ የተነሳ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ለመብራት ኃይል ‘ሲ’ ቡድን ሙከራ እንዲያደርግ አሰልጣኝ ቢረዳ (ነፍስ ሄር) ጋር ይዞት ይሄዳል።
የሙከራው ቦታ አሁን ደብዛው የጠፋው እና አስቀድሞ ብዙ ክለቦች የታዳጊ ተጫዋቾች ምርጫ (ምልመላ) የሚያደርጉበት ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው ሜዳ ነበር። በዚህ ሜዳ እጅግ ብዙ ታዳጊዎች ተሰብስበዋል። ከዚህ ሁሉ መሀል አልፎ ወደ ‘ሲ’ ቡድኑ ለመግባት ምልመላው በጣም ፈታኝ ነበር። ምልመላውን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ከኳስሜዳ (መሳለሚያ) ፣ ከአውቶቢስ ተራ ፣ ከመርካቶ ፣ ከተክለኃይማኖት እና ከአብነት አካባቢ የሚመጡ ተመልማዮች ከየሠፈሮቻቸው በጋራ በመምጣት አንድ ቡድን ይሞሉና ወደ ሜዳ በመግባት ተናበው በመጫወት ከአንድ ቡድን በርከት ያሉ ልጆችን በማስመረጥ የሚታወቁ መሆኑ ነበር። በአጋጣሚ ከቄራ አካባቢ ለመጣው ብቸኛው ታዳጊ ግን ይህ ሁኔታ አሳሳቢ ሆነ። በምን ዓይነት መንገድ ከማን ሠፈር ልጆች ጋር ተጫውቶ ኳሱን እያቀበሉት ራሱን እያሳየ በመጫወት መልመላውን ማለፍ እንደሚችል ያስባል። በአጋጣሚ ከአብነት ሠፈር ልጆች ጋር ይደርሰውና ለሙከራ ወደ ሜዳ ይገባል። የፈራውም አልቀረም ኳስ የሚያቀብለው በማጣት ለደቂቃዎች ሜዳ ውስጥ ቢንከራተትም በአንድ አጋጣሚ እግሩ የገባችውን ኳስ ተቆጣጥሮ ሁለት ተጫዋቾችን በማለፍ ወደ ጎል ሲመታት የግቡን አግዳሚ ለትማ ትመለሳለች። ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ በተመሳሳይ መንገድ ተጫዋቾችን በማለፍ ጎል ያስቆጥራል። ይህን ያየው አሰልጣኝ ቢረዳ ገና ጨዋታው ሳይጠናቀቅ በልጁ ሁኔታ በጣም ተገርሞ ብዙም ተጨማሪ ሙከራ ሳያደርግ ገና በ17 ዓመቱ በ1982 የዛሬ ዕንግዳችን ጌታቸው ካሣ (ቡቡ) መብራት ኃይል ‘ሲ’ ቡድንን ተቀላቅሎ የእግርኳስ ሕይወቱን እንዲጀምር ዕድሉን ሰጠው።
በመብራት ኃይል ‘ሲ’ ቡድን ሁለት ዓመት ከቆየ በኃላ ወደ ‘ቢ’ ቡድን የተሻገረው ጌታቸው በአሰልጣኝ ሠውነት ቢሻው ምርጫ በ1984 ዋናው ቡድን እና ‘ቢ’ ቡድን እየተመላለሰ እንዲጫወት ተደርጎ በ1985 ወደ ዋናው ቡድን አደገ። ብዙ የመጫወት ዕድል ባያገኝም ተቀይሮ በሚገባበት አጋጣሚ ጥሩ በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያ ሻምፒዮ እና የአሸነፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከኤልፓ ጋር ማሳካት ችሏል። ለአራት ዓመታት በጥሩ ብቃት በኤልፓ በነበረው ቆይታም ሁሌ በታሪክ አጋጣሚ የሚነገረላቸውን ሁለት ክስተቶች አስመልክቶናል። አንደኛው የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ድንቅ አማካይ የተስፋዬ ኡርጌቾን የፊት ጥርስ አውልቆ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣበት ሲሆን በተመሳሳይ በሌላ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ እጅግ የሚገርም ጎል አስቆጥሮ ደስታውን ለመግለፅ እንደ አንበሳ አፉን ከፍቶ የስታድየሙ የአጥር ሽቦ ላይ በመውጣት አጥሩን ሲነቀንቅ የውቅቱ የፈረሰኞቹ አለቃ አስራት ኃይሌ “እዩት ! ተመልከቱት !” በማለት ተጫዋቾቹን ያነሳሳበት አጋጣሚ ይታወሳል።
በመብራት ኃይል አብሮት ከታችኛው ቡድን ጀምሮ ያደገው እና በተለያዩ ክለቦች እንዲሁም በብሔራዊ ቡድን አብሮት የተጫወተው ዘላዓለም ምስክር (ማንዴላ) ስለ ጌታቸው ሲናገር “ቡቡ ከመብራት ኃይል ጀምሮ አብሮኝ የተጫወተ እንደጓደኛ ሳይሆን እንደቤተሰብ የማየው ሰው ነው። ብዙ ነገሮችን አብረን ያሳለፍን አሁንም የምንገናኝ ወንድሜ ነው። በተጫዋችነት ዘመኑ በጣም ጎበዝ ፣ ሜዳ ውስጥ እልኸኛ ፣ ድል አድርጎ የሚወጣ ተጫዋች ነው። በጣም ጠንካራ ፣ ጎል የሚያገባ ፣ የሚከላከል ፣ የሚነጥቅ በዛ ላይ ከመሳቅ ከመጫወት ውጪ ምንም የማያውቅ በጣም ሰላማዊ እና የዋህ ሰው ነው።” በማለት ይገልፀዋል።
የሚሰማውን ስሜት ሳይደብቅ ፊት-ለፊት በመናገር የሚታወቀው ቡቡ ከመብራት ኃይል አመራሮች ጋር አለመስማማቱን ተከትሎ ከእናት ክለቡ ጋር በመለያየት በ1988 ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርቷል። በኢትዮጵያ ቡና ጋር ጣፋጭ ሦስት ዓመታትን ያሳለፈው ቡቡ በተለይ በ1989 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና የአሸነፊዎች አሸናፊ ዋንጫዎችን በማንሳት ስሙን ተክሏል። በዚሁ ዓመት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ወደ ሞሮኮ በሄደበት ወቅትም ለትራንዚት ጣልያን ላይ ከጠፉት እና ከቀናት ቆይታ በኃላ ከተመለሱት ስድስት ተጫዋቾች መሀከልም አንዱ እንደበር ይታወቃል። ከቡና ጋር ከሦስት ዓመት በላይ መዝለቅ ሳይችል በደጋፊዎቹ እየተወደደ ከክለቡ አለቆች ጋር ውዝግብ ውስጥ በመግባቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ እርሱን ለመውሰድ ፍላጎት ቢኖረውም ምርጫውን ኒያላ በማድረግ ከ1991 ጀምሮ ለተከታታይ አራት ዓመታት በኒያላ ተጫውቷል። በኒያላ ቆይታው ከአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ጋር በመሆን ቡድኑን ከብሔራዊ ሊግ አርባምንጭ ከተማን ተከትሎ ፕሪምየር ሊጉን እንዲቀላቀል ማድረግ ችሏል።
በቡና አብሮት የተጫወተው ካሊድ መሐመድ ስለቡቡ ሲናገር “ቡቡ በፈለግከው ሰዓት ተጫዋች አልፎልህ የሚሄድ ፣ ወደፊት ኳሶችን ይዞ ለመሄድ ደፋር የነበረ ፣ ጎል አካባቢ ደርሶ ጎል አስቆጥሮ የሚመለስ ፣ በሁለቱም እግሮቹ መጫወት የሚችል በጣም የተሟላ ተጫዋች ነበር። በዚህም ለአንድ ቡድን ውጤታማነት ከሚያስፈልጉ ወሳኝ ተጫዋቾች መሀከል ይመደባል። ቡድንህ ሲቸገር ሰው ቀንሶልህ በማለፍ የቡድኑን ባላንስ በመጠበቅ የሚታወቅ ልዩ ችሎታ የነበረው ተጫዋች ነው።” በማለት ይገልፀዋል።
ከኒያላ በኃላ በመድን ፣ በወንጂ ስኳር ፣ በአዳማ ከተማ እና በመተሐራ ስኳር ቆይቶ ወደ የመን በመሄድ ከተጫወተ በኃላ 2003 ላይ ጫማውን ሰቅሏል። በወኔ የሚጫወት በመሆኑ ሁሌም ውዝግብ የማያጣው ቡቡ እንደነበረው ችሎታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብዙም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። እግርኳስ ካቆመ በኃላ ታዳጊዎችን በማሰልጠን ሲሰራ የቆየው ጌታቸው በቄራና አካባቢው የጤና ቡድን ውስጥ ተካቶ አሁንም የትናንቱ ልዩ ችሎታው አብሮት ያለ መሆኑን በዓመታዊው ውድድር ላይ እያስመሰከረ ይገኛል። በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ድንቅ አማካይዮች መካከል የሚመደበው ጌታቸው ካሣ (ቡቡ) የዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከብ እንግዳችን ሆኖ ቀጣዮቹን ሀሳቦች አጋርቶናል።
“በእግርኳስ ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። በተለይ ከመብራት ኃይል ጋር የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫዎችን ያነሳሁበት እንዲሁም እጄ ተሰብሮ በፋሻ ታስሬ ከነጉዳቴ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር እየተጫወትኩ የኢትዮጵያ ቻምፒዮን የሆንኩባቸው ቀናት ለእኔ ትልልቅ ስኬቶቼ ናቸው። በአጠቃላይ በሄድኩባቸው ክለቦች ሁሉ ጥሩ የእግርኳስ ዘመናትን አሳልፊያለሁ። በዚህም ደስተኛ ነኝ።
“በታሪካዊው የ1990 የአል አህሊው ጨዋታ ያልተሳተፍኩበት ምክንያት ነፍሱን ይማረውና ከሥዩም አባተ ጋር አንዳንድ አለመግባባቶች ስለነበሩ በዚህ ጨዋታ ላይ ሳይጠቀመኝ በመቅረቱ ነው። በባህሪዬ የተሰማኝን ማንኛውንም ነገር በግልፅ ነው የምናገረው ፤ መደበቅ እና መሸፋፈን አልወድም። የአኛ ሀገር አሰልጣኞች ደግሞ እንዲህ ያለ እውነተኛ ነገር አይወዱም። ፊትለፊት የሚናገራቸውን በሆነ መንገድ ማጥፋት ይፈልጋሉ። እነርሱ የሚፈልጉት ተገዝተህላቸው ሲሰድቡህ አንገትህን ደፍተህ እንድትኖር ነው። እኔ ደግሞ እንዲህ ያለ ነገር አልቀበልም። ስራዬን በጣም አከብራለው ፣ በአግባቡ እሰራለው ፣ በጣም ዲሲፒሊድ ነኝ። ግን ከስራዬ በላይ አልፎ የሚመጣ ነገር አልቀበልም። ይህ ባህሪዬ አሁንም አብሮኝ ያለ ነገር ነው። ለሰው ሁሉ ከበሬታ አለኝ ፤ መብቴ እንዲነካ ግን አልፈልግም። እኔ በወቅቱ ጥሩ አቋም ላይ ነበርኩ። ሆኖም የተሰማኝን ፊትለፊት በመናገሬ ብዙ ችግሮች ተፈጥረውብኛል። በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሞኝ ከቡድኑ ውጪ የሆንኩበት ሁኔታ አለ።
“በመጀመርያ ነፍሱን ይማረውና ተስፋዬ ኡርጌቾ በጣም የማከብረው ትልቅ ተጫዋች የሆነ ጓደኛዬ ነው። በ1987 መብራት ኃይል እያለው የመጨረሻ ጨዋታዬ ነበር ፤ የአሸነፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ይመሰልኛል። በጣም አሪፍ እና ድባቡም ደስ የሚል ጨዋታ ነበር። በጨዋታውም ጎልም አግብቼ ነበር። ያው እንደሚታወቀው ተስፋዬ ኡርጌቾ ሰውነቱ በጣም የተጠቀጠቀ ጠንካራ ጉልበት ያለው ተጫዋች ነው ፤ በእርሱ ከተመታህ ዋጋም አይኖርህም። በጨዋታው አንድ ለአንድ ሆነን ከፍተኛ ፉክክር በነበረበት ጊዜ ወደ ጥላፎቅ አካባቢ ኳስ ሸፍኜ ሳለ እግሬን መታኝ። ‘ምንድን ነው ? ቀስ ብለህ አትጫወትም ?’ ብዬ ቃላት ስንመላለስ በትንሹ በቦክስ ስመታው ጥርሱ አርቴፊሻል ነበረች ወለቀች ፤ ግርግር ተፈጠረ። ወዲያውኑ ሜዳው ጭቃ ስለነበር ጥርሱን ከመሬት ጋር ረግጬ አጠፋኋት። የዕለቱ ዳኛ እየሮጠ መጥቶ የተስፋዬ ኡርጌቾ ጥርስ ወልቆ ሲመለከት በቀይ ካርድ አስወጣኝ። ተመልካቹ በጣም ይጮሀል ፤ ከአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ጋርም ውዝግብ ተፈጠረ። በመጨረሻም አስታውሳለው ገነነ መኩርያ ይመስለኛል ቀስ ብሎ ይዞኝ ወደ መልበሻ ክፍል ወጣሁ።
“በሌላ የዙር ውድድር ወቅት ደግሞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረ ጨዋታ ምርጥ ጎል አስቆጥሬ ወደ ስታድየሙ አጥር በመሄድ አጥሩን እየነቀነቅኩኝ ስጨፍር አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ‘ወንድ ልጅ ሜዳ ላይ ሥራውን ጨርሶ ከብረት ጋር ይታገላል ፤ ተመልከቱ ወኔ ! እንዲህ እንድትሆኑ ነው የምፈልገው !’ በማለት በተጠባባቂ ወንበር ላይ ለተቀመጡት ሲናገር ፋሲል ተካልኝ ለአንድ የሠፈር ጓደኛዬ ነግሮት ጓደኛዬ መጥቶ ነገረኝ። በነገራችን ላይ ብዙ ጊዜ ጎል ሳስቆጥር የምሄድበትን አላውቅም። ግን ወደ ደጋፊዎች በመሄድ አጥር ላይ ወጥቼ መጨፈር ይቀናኝ ነበር።
“አንዳንድ ጊዜ የተለያዩ ነገሮችን ወደ ኃላ መለስ ብለህ ስታስብ የምትቆጭበት ነገር ይኖራል። የእግርኳስ ህይወቴ እልህ የተሞላበት ነበር። መሸነፍ አልወድም ፤ ለለበስኩት መለያ ያለኝን ነገር ነው የምሰጠው። ይህ ደግሞ ትንሽ ጎድቶኛል። ሆን ብዬ ተጫዋቾችን መትቼ ወይም ተናግሬ አላውቅም። ግን ከዳኛች ጋር ብዙ አልግባባም ነበር። በዛን ጊዜ የነበረው ዳኝነት ደግሞ አድሎ ይበዛበታል። ያንን እያየው አለማለፌ ትንሽ የጎዳኝ ይመስለኛል። ቀይ ካርዶችን እመለከት ነበር። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው በብልጠት ማለፍ እየቻልኩኝ በመጋጨት ፣ በመከራከር እና ከአሰልጣኞች ጋር ፊት ፊት በመከራከር ማሳለፌን ሳስብ ‘ይሄን ባላደርግ ኖሮ’ እያልኩ እቆጫለው። ማንም አያግዝህም ፤ አንዳንዱ ተጫዋች ዝም ይላል። እኔ ደግሞ ትንሽ ነገር ይገንብኛል። ያም ቢሆን በእግርኳስ ህይወቴ ደስተኛ ነበርኩ። ስራዬን በጣም ነበር የማከብረው ፤ ልምምዴን ሰራለሁ ፣ በጣም ዲሲፒሊንድ ነኝ ፣በጣም ሠራተኛ ነኝ ፣ ቀልድ አላውቅም። የተለየ ወጣ ያለ ባህሪ የሌለኝ ሰው ነበርኩ።
“እልኸኝነቱ የመጣው ከልጅነቴ ጀምሮ ነው። የማልዋሽህ ነገር ሠፈር ውስጥም እንደዚሁ ዋንጫ ተበልቼ ዋንጫ ነጥቄ ሄጃለሁ። እነዛ ልጆች እየጨፈሩ በአጠገቤ ሲያልፉ ስለምናደድ ነጥቄያቸው ወስጄ ማታ እመልስላቸው ነበር። ቅድም እንዳልኩት በህይወቴ መሸነፍ አልወድም። ከተሸነፍን እንኳን እራቴን ሳልበላ ነበር የማድረው ፣ ከቤቴም ሳልወጣ የምውልበት ቀን ነበር። ለዚህም ነው ሜዳ ውስጥ እልኸኛ የሆንኩት።
” በኒያላ በጣም ደስ የሚል ሰላማዊ የሆነ ቆይታ ነበረኝ። በዚህ ቡድን ውስጥ ኤልያስ ጁሀር ፣ ወደ መጨረሻ አካባቢ ለአንድ ዓመት ሙሉጌታ ከበደ ፣ ዘላለም ምስክር (ማንዴላ)፣ ሀይደር መንሱር ፣ ቶፊቅ መሐመድ ፣ መስፍን ላንባሮ እና ሌሎች ልጆች ነበርን። ቡድኑን ለተወሰነ ዓመት አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ያሰለጥነው ነበር። ቡድኑን ከታችኛው ዲቪዚዮን ወደ ብሔራዊ ሊግ አውጥተነው እንደገና ወደ ፕሪምየር ሊግ ያስገባነው እኛ ነን። በኒያላ በጣም ደስተኛ ነበርኩ ፤ ደጋፊውም ይወደኝ ነበር። ብዙ ቆይቼ እንድጫወት ይፈልጉ ነበር። በስንት ጭቅጭቅ ነው ከኒያላ የወጣሁት። ሆኖም ግን በኒያላ ቆይታዬ በጣም ደስተኛ ነበርኩ።
“በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ቆይታ ነበረኝ። በወጣት እና በታዳጊ ቡድን አልተጫወትኩም ፤ ቀጥታ ነው ወደ ዋናው ቡድን ያደግኩት። በ1989 ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ወደ ሞሮኮ ሄደን ጨዋታውን ሳናደርግ ጣልያን ላይ አስራ ስድስት ተጫዋቾች ጠፍተን ነበር። ይህ በታሪክ ብዙ ተጫዋቾች የጠፉበት ቁጥር ሳይሆን አይቀርም። ስድስታችን ፋሲል ተካልኝ ፣ አንተነህ አላምረው ፣ አሸናፊ ሲሳይ እና ሌሎችም ነበርን። በኋላ ግን ከቀናት በኋላ ተመልሰናል። እንደማንኛውም ሰው የተሻለ ነገር እንዲኖረን ህይወታችንን ለመቀየር በማሰብ ነበር የጠፋነው። በወቅቱም ጣልያን መግባታችን ትልቅ አጋጣሚ ነበር። መንግስትን የሚቃወም የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ የሚባል ድርጅት ውስጥ ቆይተን ነበር። ሆኖም አንዳንድ ነገሮችን ስንሰማ እንዲሁም ተዘጋጅተንበት ስላልሆነ (እንደ ድንገት ፓስፖርት እንኳን ሳንይዝ ስለጠፋን) ከአራት ቀን በኃላ ተመልሰን መጣን። እዚህ ስንደርስ ደህንነቶች ያዙን። ሊያጉላሉንም ፣ ሊያስሩንም ፈልገው ነበር። በኃላ አንድ ጀማል የሚባል የቡና የልብ ደጋፊ ፤ ለእኔ ባለ ውለታዬ ነው ማለት እችላለው። እሱ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ተነጋግሮ ወድያው ‘ይለቀቁ ሲፈለጉ ይመጣሉ’ ተብሎ ወጣን። ፌዴሬሽኑም ለምን ጠፋችሁ ብሎ ለስድስት ወር አገደን። በግላችን ልምምድ እየሰራን ከስድስት ወር በኃላ መጫወት ትችላላችሁ ተብለን ወደ ሜዳ መመለስ ችለናል።
” ከየመን እንደመጣሁ የመጫወት አቅሙ እያለኝ በእኛ ሀገር አሰልጣኞች የአረዳድ ችግር የተነሳ ኳስ እንዳቆም ሆኛለው። እግርኳስ ዕድሜ ሳይሆን አዕምሮ ነው። መጫወት የምችልበት ጊዜ ገና ቢሆንም ኳስን አቁሜ ወደ አሰልጣኝነቱ በመግባት የተለያዩ ኮርሶችን በመውሰድ የ ‘ቢ’ ላይሰንስ አለኝ። በታዳጊ ፕሮጀክት ላይ ያለፉትን አራት ዓመታት ስርቼ ነበር። ያው በግለሰቦች ደረጃ የሚሰራ ስለነበር ጠንካራ አልነበረም። እየተሸራረፈ መጥቶ አቆምነው። አሁን በድጋሚ ለመስራት እየተንቀሳቀስኩኝ ነው።
“ቡቡ የሚለው ቅፅል ስም የወጣልኝ ኤልፓ ‘ሲ’ ቡድን እያለው ነው። ግብጠባቂው አንድዓለም ፍስሀ ነው ያወጣልኝ። መብራት ኃይል ‘ሲ’ ቡድን ስጫወት አጥቂ ሆኜ ነበር። በኃላ ነው ወንድምአገኝ ከበደ ወደ አማካይ ያወጣኝ። እና በ’ሲ’ ቡድን ስንጫወት ግብጠባቂው ዓለምፍስሀ ላይ በተደጋጋሚ ጎል ሳገባበት እንደመናደድም እንደስድብም ሆኖ ‘ምን ዓይነት ቡቡ ልጅ ነው !’ ብሎ ሲናገር በዛው ስም ሆኖ በቅፅል ስምነት እጠራበት ጀመር።
“ሙሉጌታ ከበደ ሲጫወት አይተነው ያደግን በጣም የምናከብረው ትልቅ ተጫዋች ነው። ሙሉጌታ ገና ስትገባ ጥሩ ሆነህ ካየህ የሆነ ነገር ይሰራብሀል። ወይም የሆነ ነገር አድርጎህ ያበሳጫሀል ወይም ይሰድብሀል ፤ በዚህ ባህሪው ይታወቃል። የዛን ጊዜ እኛ ቡድን ውስጥ ኃይሌ ካሴ ነበር። በዚህ አጋጣሚ በጣም የምወደው ኳስ የሚችል ትልቅ ተጫዋች ነበር። ኃይሌ ካሴ ‘ዲዲ’ እያለ ይጠራኝ ነበር። እርሱ ያወጣልኝ ስም ነው። ‘ዲዲ አንተ ብቻ ኳሱን ነጥቀህ ስጠኝ ፤ እኔ ስራዬን እሰራለሁ እንዳትፈራ !’ ይለኛል። ተስፊቲ የሚባል ተከላካይም ጊዮርጊስ ሲጫወት ሙሉጌታን ስለሚያውቀው ‘እንዳትፈራ ነግሬሀለው’ ይለኛል። እኔም በቃ ሙሉጌታን እንዳይጫወት አደረግኩት። የሆነ ደቂቃ ላይ ካታንጋ አካባቢ ከኳስ ጋር አብረን ወደቅን። የዚህ ሰዓት በክርኑ ፊቴን ይመታኛል። እኔም ዞር አልኩና በጫማዬ አፉን ስመተው ለካ ጫማዬ አፉ ውስጥ ገብቷል። እዛው እግሬን ይዞኝ ነከሰኝ። ጮኸኩኝ። ጋሽ ዓለም ነበር ዳኛው። እየሮጠ ሲመጣ ሙሉጌታ ምንም እንዳላደረገ ‘ይህው ጋሽ ዓለም ራሱ ነው እንዲህ ያደረገኝ’ በማለት ሲናገር ጋሽ ዓለም ‘አንተነህ ጥፋተኛው ፤ ነገሬሀለው አስወጣሀለው’ ያለበትን ጊዜ አስታውሳለው።
“ፊት ለፊት ስለምናገር ብዙ ጊዜ ብሔራዊ ቡድን አልመረጥም ፤ አሰልጣኞቹ ‘ይናገራል’ እያሉ ስለሚፈሩ። ኒያላ እያለው በጣም ጥሩ ስለነበርኩኝ ደጋፊዎች ‘ለምን እርሱ አይመረጥም ?’ እያሉ ጥያቄ ያቀርቡ ነበር። እኔም ጋዜጣ ላይ ‘ለምንድን ነው ብሔራዊ ቡድን የማትመረጠው ?’ ሲሉኝ ‘ደሜ አሜሪካዊ ስለሆነ አይመርጡኝም ፤ ኢትዮጵያዊ መሆኔ ተረስቷል’ ብዬ ተናግሬ ነበር። ይህን በተናገርኩ በሦተኛው ቀን ለ1994 የሴካፋ ዋንጫ ዝግጅት ተጠራሁ። የሚገርምህ ተከላካይ ፣ አጥቂ ፣ አማካይ አድርገው አጫውተውኛል። ግን ሁሉም ላይ ጥሩ ሆንኩባቸው። ይህም ቢሆን እኔ አላመንኩበትም። እንዲያውም ከጋና ጋር አንድ ጨዋታ ስንጫወት በመስመር አውጥተው አጫወቱኝ። በወቅቱ ትዝ ይለኛል በጥላ ፎቅ ያሉ ደጋፊዎች ‘ያለቦታው ለምንድን ነው የምታጫውቱት ?’ ብለው ሲቃወሟቸው ወደ መሀል መልሰው አጫውተውኛል። በኃላ ቡድኑ ውስጥ ትንሽ ብጥብጥ ተፈጥሮ ስለነበር በሰርቪስ እየሄድን አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ‘እዚህ ቡድን ውስጥ ችግር ያለበት ሰው ካለ ይናገር’ ሲል እኔ እጄን አውጥቼ ‘ቤተሰቤ ውስጥ ችግር ስላለ እኔ ራሴን ከብሔራዊ ቡድን ማግለል እፈልጋለሁ።’ አልኩት። ‘ለምን ?’ አለኝ ‘በቃ ስለማልፈልግ !’ ብዬ ከአስራት ጋር ተከራከርን። ሠውነት ቢሻውም ‘ግዴ የለህም ተረጋጋ እናጫውትሀለን’ ቢለኝም አይሆንም አልኩ። ያለቦታዬ እያጫወቱ የማይሆን ነገር ማድረጋቸው አልተመቸኝም። በቃ ከዛ በኃላ ብሔራዊ ቡድን ተመልሼ አልመጣሁም። የሴካፋ ዋንጫ ካነሳው ቡድን ውጪም ሆንኩ።
“ሁለት ልጆች አሉኝ ፤ ወንድ እና ሴት። ወንዱ አስራ ስምንት ዓመቱ ነው። እግርኳስ ቢወድም ብዙ የሚያዘነበለው ወደ ትምህርቱ ነው። ግን ኳስ ያያል ፤ የሚደግፈውም ክለብ አለው። እኔ በግሌ የተለያዩ ሥራዎችን ከወንድሜ ጋር እስራለሁ። ከዚህ በተረፈ ‘ቄራ እና አካባቢው’ የሚባል የጤና ቡድን አለ። እዚያ እስካሁን ድረስ እጫወታለሁ። እኔም የማሰለጥናቸው የጤና ቡድኖች አሉ ፤ በእርሱም እሳተፋለሁ።
“የአሁን ዘመን እግርኳስን ይቅርታ አድርግልኝ እና ብዙም አልከታተልም። አንድ ዓይነት ነገር ነው ፤ የተለየ ነገር ብዙ አታይበትም። አዲስ ፊትም የለም። በእኛ ጊዜ በዓመት ውስጥ በአንድ ክለብ አራት ፣ አምስት ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን ታያለህ። አሁን በዓመት አንድ ተጫዋች ታያለህ። እርሱም አንድ ዓመት ከተጫወተ በኃላ ሲጠፋ ትመለከታለህ ፤ ተከታታይነት የለውም። ሁሉም ነባር ነው። አዲስ ነገር ስታይ ነው ጨዋታዎችን የማየት ፍላጎት የሚኖርህ። ምንም በሌለበት እንዴት ልከታተል ? አንዳንዴ እገባለው ግን ተደስቼ የወጣሁበት ጨዋታ የለም።
“አንዳንድ ሰዎች ሲያዩኝ በጣም እለኸኛ እና ተደባዳቢ አድርገው ያዩኛል። እኔ ግን በጣም ሰላማዊ ሰው ነኝ። ትንሹንም ትልቁንም አክባሪ ነኝ ፤ ለሰው ፍቅር እሰጣለሁ። ህይወቴ መልካም ነው። እግርኳስን ካቆምኩ በኃላ ሲያዩኝ እየተረዱኝ መጥተዋል። እኔ ሜዳውን ስረግጥ ፣ መስመሩን አልፌ ስገባ ነው የኔ ነገር የሚቀየረው። እንጂ ፀሎት አድርጌ ነው ወደ ሜዳ የምገባው። ከገባው በኃላ ምን እንደሆነ አላውቅም ሌላ ሰው ነው የምሆነው። ከሜዳ ውጪ ግን በጣም ሰላማዊ ሰው ነኝ። ስለራሴ ብዙ መናገር ባልፈልግም በአዕምሮ መጫወት እፈልጋለሁ። ብዙ ንክኪ አልወድም። ኳስ ስነጥቅም በብልጠት ነው። በአጠቃላይ ሰዎች በዚህ መልኩ ቢረዱልኝ ደስ ይለኛል።
“በመጨረሻም አልማዝዬ ሜዳ ለእኔ በእግርኳስ ህይወቴ ትልቅ ቦታ የምሰጣት መሆኗን መናገር እፈልጋለው። እዚህ ሜዳ ላይ ትልልቅ ውድድሮች ይካሄዱ ነበር። ‘አልምዬ’ የሚባል ቡድንም ነበረን። ይህ ሜዳ እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙ ትውልድ ያፈራ ትልቅ ሜዳ ነው።”
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!