ዋሊያዎቹ ልምምዳቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ15ኛ ቀን የልምምድ መርሐ-ግብሩን ዛሬ አከናውኗል።

ካሜሩን ለምታስተናግደው የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከኮትዲቯር፣ ኒጀር እና ማዳጋስካር ጋር ተደልድሎ የማጣሪያ ጨዋታዎቸን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድቡ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታዎችን ለመከወን ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ለ41 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ መስከረም 25 ዝግጅቱን በካፍ የልህዕቀት ማኅከል የጀመረው ቡድኑ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን እየከወነ ይገኛል። በዛሬው ዕለት በነበረው የጠዋት የልምምድ መርሐ-ግብር ላይም ስብስቡ ለ1 ሰዓት ከ40 ደቂቃዎች የቆየ ልምምዱን በተገቢው ሁኔታ አከናውኗል።

በቅድሚያ ጥሪ ከቀረበላቸው 41 ተጫዋቾች መካከል ሽመልስ በቀለ እና መስፍን ታፈሰ ከሃገር ውጪ በመሆናቸው ስብስቡን ያልተቀላቀሉ ሲሆን ዳዊት እስቲፋኖስ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና አህመድ ረሺድ ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ መሆናቸው ተነግሯል። በኮቪድ-19 ቫይረስ እንደተያዙ የተነገረው እና ከቫይረሱ ነፃ እስኪሆኑ ድረስ ራሳቸውን አግልለው የነበሩት አምስቱ የቡድኑ ተጫዋቾች ከትላንት ጀምሮ ከልዑካኑ ጋር መደበኛ ልምምዳቸውን በጋራ መስራት ጀምረዋል።

በዛሬው የልምምድ መርሐ-ግብር ላይም 6 ግብ ጠባቂዎቸን ጨምሮ አጠቃላይ 36 የቡድኑ አባላት ልምምዳቸውን በጥሩ ሁኔታ ሲከውኑ አስተውለናል። በልምምዱም ተጫዋቾቹ ሰውነታቸውን ካፍታቱ በኋላ ከኳስ ጋር ቀላል የቅብብል ሥራዎችን ሰርተዋል። በመቀጠልም መዝናኛ የተቀላቀለበት የህብረት ጨዋታ አባላቶቹ ሲሰሩ ተመልክተናል። ከዛም ቡድኑ ለሁለት ተከፍሎ የግማሽ ሜዳ ጨዋታ ከከወነ በኋላ የዛሬውን የጠዋት የልምምድ መርሐ-ግብር አገባዷል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከረዳቶቻቸው አስራት አባተ፣ አንዋር ያሲን እና ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ እንዲሁም ከስነ-ምግብ ባለሙያው ከሚያገኙት እርዳታ በተጨማሪ ከስፖርት ሳይንስ መምህሮቹ ዶክተር ዘሩ በቀለ እና ሳሙኤል ስለሺ ድጋፎችን ሲያገኙ አስተውለናል። ከሁለቱ ባለሙያዎች በተጨማሪም ኢትዮ ፉትቦል ሶሉሽን የብሔራዊ ቡድኑን ልምምድ በመተንተን ድጋፎችን ሲያደርግ አይተናል።

ቡድኑ ነገም በተመሳሳይ ልምምዱን ከከወነ በኋላ ሐሙስ ከዛምቢያ አቻው ጋር የመጀመሪያ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከውናል። ከዛም አርብ እና ቅዳሜ ልምምዱን ቀጥሎ እሁድ በድጋሜ ከዛምቢያ ጋር ሁለተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ያደርጋል። ከአቋም መለኪያ ጨዋታዎቹ በኋላም የመጨረሻዎቹ 23 ተጫዋቾች እንደሚታወቁ ሰምተናል። ከቡድኑ ጋር በተያያዘም ነገ ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ለማወቅ ችለናል።



© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!